አዲስ አበባ ፡- በዓሉን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በማሰብ ማክበር እንደሚገባ መጋቢ ሀዲስ ናሁሰናይ አሸናፊ ገለጹ። ለበዓሉ ማድመቂያዎች የምናደርጋቸው ተግባራት በልኩ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳሰቡ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ መጋቢ ሀዲስ ናሁሰናይ አሸናፊ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የልደት በዓሉን ስናከብር ደስ እያለንም፤ እያዘንም ነው።
ደስ የምንሰኘው እለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተወለደበት በመሆኑ ነው ያሉት መጋቢ ሀዲስ፤ የምናዝነው ደግሞ በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያለው አለመረጋጋት የብዙ ንጹሀን ዜጎችን ህይወት ፈተና ውስጥ በመክተቱ ነው ብለዋል።
የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድን ከፍታቸው ታላቅ የሆኑ መላዕክት፣ የተማሩ የጥበብ ሰዎች ሰብዓ ሰገል እና ምንም የማያውቁ ትሁት እረኞች በአንድነት በምስጋና የተቀበሉት እንደሆነም ጠቁመዋል። እኛም በዓሉን በመካከላችን ምንም ልዩነት ሳይኖር፣ እንደምንፈልገው ሳይሆን ፈጣሪ እንደሚፈቅደው ልናከብረው ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።
በዓሉን ስናከብር በአንድነት ፣ በመከባበር መሆን አለበት፤ በዓሉ የባለጸጎች ወይም የድሆች ተብሎ የሚከፈል አይደለም። የሁሉም በዓል በመሆኑ በእለቱ የተቸገሩ ወገኖችን ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደትን በማሰብ ከህዳር 15 ጀምሮ በጾም እና በጸሎት ሆነው የጌታችንን መወለድ ይጠብቃሉ፤ በበዓሉ እለት የሚደረጉ የተለያዩ ዝግጅቶች የበዓሉ ማድመቂያዎች እንጂ በዓሉ የሚከበርባቸው ዋነኛ መንገዶች እንዳልሆነም አስታውቀዋል።
ከሁሉም በላይ በዓሉን በምስጋና እና በዝማሬ ማክበር ይገባል ያሉት መጋቢ ሀዲስ፤ በእለቱ የምናደርጋቸው ማድመቂያዎች በልኩ የሚደረጉ እና ከእግዚአብሔር ትእዛዝ የወጡ መሆን እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።
እንደ መጋቢ ሀዲስ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ የምስጋና እና የዝማሬ አገልግሎት ይከበራል። በእለቱም የሃይማኖት አባቶች እና ምዕመኑ በጋራ በመሆን ነዳያንን ይመግባሉ።
የእምነቱ ተከታዮች ይህን የደስታ ቀን ከተቸገሩ እና አቅም ከሌላቸው ጋር በመሆን እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም