ዜና ትንታኔ
ኢትዮጵያዊያን ከበዓል ጋር ተያይዞ ባላቸው የተዛባ የአመጋገብ ሥርዓት የተለያየ የጤና ጉዳትን ያስተናግዳሉ። የጤና ጉዳቶቹም ከአጭር ጊዜ እስከ ረጅም ጊዜ የሚዘልቁ እንደሆኑ በባለሙያዎች ይነገራል። የጤና ችግሮቹ መከሰቻ አጋጣሚዎች ምን ምን ናቸው? መፍትሄዎቹስ? ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረናል።
አቶ እንደሻው ሙላቴ የስነምግብ ባለሙያ ናቸው። በኢትዮጵያ በበዓላት ወቅት ያለው የአመጋገብ ስርዓት በተለያየ መልኩ የጤና ጉዳቶች እንዲከሰቱ የሚያደርግ እንደሆነ ያነሳሉ። በተለይም በበዓላት ወቅት የሚዘወተረው የእንስሳት ተዋጽኦ መሆኑ ሌሎችን የምግብ አይነቶች እንዳናገኛቸው የሚያደርግና በአንድ የምግብ ምድብ ውስጥ እንድንጠቀም የሚያደርግ በመሆኑ በርካታ የጤና ችግሮች እንዲገጥሙን ያደርጋል ይላሉ።
በዓላቱ ሲከበሩ የሚዘወተሩት ምግቦች ቅባት የበዛባቸው፤ጣፋጮችና በሰውነት ላይ ከባድ ጫና የሚፈጥሩ ምግቦች በመሆናቸው ድንገተኛ ሕመሞች እንዲያገኙን ያደርጋሉ። ለአብነት የሆድ ህመም፤ ማቅለሽለሽ፤ ወደላይና ወደታች ማለት፣ የምግብ ፍላጎት መዘጋት፣ የጨጓራ፣ የአንጀትና የመሳሰሉ የጤና ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት እንደሚሆንም ያብራራሉ።
አቶ እንዳሻው፤ በስርዓተ ምግብ ሕግ የአመጋገብ ስርዓት ተዛብቷል ሊባል የሚችለው በሦስት መንገድ እንደሆነ ጠቅሰው፤ እነዚህም አብዝቶ መመገብ ፤ የምግብ እጥረትና የማይታይ ረሃብ ወይም በማየት የማይታወቁ ነገር ግን በቂ ንጥረ ነገሮችን ሳናገኝ የምናልፍባቸው አጋጣሚዎች ናቸው ይላሉ። ተግባራቱ በተለይ በበዓላት ወቅት እንደሚታዩ ይገልጻሉ።
በብዛት መመገብ ድንገተኛ የጤና ችግሮችን ከሚፈጥሩ የተዛቡ አመጋገቦች መካከል ይመደባል። በዚህም በአንጀት፤ በጨጓራና በሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች ላይ ቀላልና ከባድ ለአጭር ጊዜና ለረጅም ጊዜ የጤና ጉዳቶችን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን፤ በተመሳሳይ ለረጅም ሰዓት ምግብ ሳይቀምሱ መቆየትም እንዲህ አይነት ችግሮችን ከሚፈጥሩት መካከል ይመደባል። ይህም በስፋት በበዓላት ወቅት በተለይ እናቶች ላይ የሚታይ ስለመሆኑም አመላክተዋል።
ለረጅም ሰዓት ምግብ አለማግኘት በርካታ የጤና ጉዳቶችን የሚያስከትል ሲሆን፤ አንዱና ዋነኛው ተብሎ የሚጠቀሰው በጊዜው በስፋት አሲድ የመመንጨት እድል ስለሚኖር ሰዎች ጨጓራና ለስኳር በሽታዎች የመጋለጥ እድል ይኖራቸዋል። በተመሳሳይ ቀደም ሲል እንደ ስኳርና ግፊት እንዲሁም የልብ ችግር ላለባቸው ሰዎችም በሽታውን የማባባሻ ምክንያት ተደርጎም እንደሚወሰድ አስረድተዋል።
አንድ ሰው ቢያንስ በቀን አመጋገቡ ውስጥ ስድስትና ከዚያ በላይ የሆኑ የተለያዩ ምግቦችን አመጣጥኖ መውሰድ እንዳለበት ጥናቶች ያመላክታሉ። ሆኖም በበዓላት ወቅት ይህ ሲሆን አይታይም። ይልቁንም ተከታታይነትን የማይጠብቁና ተመሳሳይነት ያላቸው በአንድ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ይህ ደግሞ በቀን ማግኘት ያለባቸውን የተመጣጠነ ምግብ እንዳያገኙ ያደርጋል። በተለይ ቅባት የበዛበት ምግብ በመዘውተሩ የልብ ህመም፤ ስትሮክና የደም ዝውውር መስተጓጎልን የመሳሰሉ የጤና ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ይገልጻሉ።
በበዓላት ወቅት ሌላው የአመጋገብን ስርዓት የሚያዛባው ነገር በንጽህና ምግቦች አለመዘጋጀታቸው ነው። ዘመድ አዝማዱ ስለሚጠራ ሰፋ ያለ ምግብ ይዘጋጃል። ይህ ሲሆን ደግሞ በአግባቡና ንጽህናው በተጠበቀ መልኩ ላይዘጋጅ የሚችልበት አጋጣሚ ይሰፋል። በመሆኑም ድንገተኛ የሚባሉ የጤና እክሎች ሰዎች እንዲያጋጥማቸው ይሆናሉ የሚሉት ባለሙያው፤ እነዚህ ሁሉ ችግሮች መፍቻ መንገድ እንዳላቸው ይናገራሉ።
በበዓላት ወቅት ቅባትን መቀነስ፤ የተመጣጠኑ ምግቦችን ለመውሰድ መሞከርና በቂ እንቅስቃሴ ማድረግና ከአልኮል ይልቅ ውሃ በብዛት መጠጣት በዋናነት ጤናችንን የምንጠብቅባቸው የመፍትሄ አካል እንደሆኑም ያስረዳሉ።
ወይዘሪት ይርጋለም መንግስቱም እንደ አቶ እንዳሻው ሁሉ የስነምግብ ባለሙያ ሲሆኑ፤ በበዓላት ወቅት ስለምንመገባቸው ምግቦችና የአመጋገብ ስርዓታቸን ሰፋ አድርገው ያብራራሉ። በዓላትን ስናከብር የበዓላቱ ድምቀት ከሚባሉ ነገሮች መካከል ምግቦችና መጠጦች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንጻርም በአብዛኛው የሚዘጋጁት ምግቦች ከአንድ አይነት የምግብ ምድብና ቅባት የበዛባቸው ናቸው። አበሳሰላቸውም በጣም ረጅም ሰዓት የሚወስድና ንጥረ ነገሮችን የሚያጠፋ ነው። መጠጦቹም እንዲሁ በዘልማድ ‹‹ምግብን ይፈጫል›› በሚል አልኮሎች ይዘወተራሉ። በዚህም በርካታ የጤና ችግሮች በዓሉን ተከትለው እንዲከሰቱ ይሆናሉ።
በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ አልኮል መጠጦች ሙሉ ለሙሉ ጥቅም እንደሌላቸው ነው። ይሁን እንጂ በዓል ነውና አቁሙ ለማለት ስለሚያስቸግር የተቀመጠለትን መጠን ማለፍ እንደማይገባ የሚናገሩት ባለሙያዋ፤ ይህ መጠን በሳምንት ከሁለት ብርጭቆ ያነሰ መሆኑን ያስረዳሉ። የቅባት መጠንም እንዲሁ ከሁለት እስከ ሦስት የሾርባ ማንኪያ ብቻ መሆን እንደሚገባውም ያስገነዝባሉ።
ስጋና የስጋ ተዋጽኦችን በሚመለከት ደግሞ ስንጠቀም በቀን በአማካኝ መውሰድ ያለብን 60 ግራም ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሪት ይርጋለም፤ በበዓላት ወቅት የሚዘወተሩት ጣፋጭ ምግቦችም ከ30 ግራም መብለጥ እንደሌለባቸው ያስረዳሉ።
ወይዘሪት ይርጋለም፤ የበዓላት ወቅት ምግቦች ጤናማነትን ጠብቀው እንዲጓዙ ከተፈለገ ከአዘገጃጀታቸው ሊጀምር ይገባል ይላሉ። ሲዘጋጁ በተመጣጠነ መልኩ ቢሆን ጤናችንን በቀላሉ መጠበቅ እንደምንችልና ለአብነት ስጋን ከጎመን ጋር፤ ስጋን ከሩዝና መሰል ሌሎች ምግቦች ጋር አቀላቅለን ብናዘጋጃቸው የተመጣጠነ የሚለውን ምግብ ማግኘት እንደምንችል ያስረዳሉ። ከዚያ ባሻገር ሰውነታችንን ማለማመድ ብንችል ማለትም ቀጥታ ከተለመደው አመጋገባችን ወጥተን ወደ ቅባቱ ከመሻገር ይልቅ በተልባና መሰል ውስጣችንን ሊያለሰልሱ የሚችሉ ምግቦችን ቀድመን ብንጠቀም ጤንነታችንን በቀላሉ መጠበቅ እንችላለን ይላሉ።
አንድ ሰው በቀን መመገብ ያለበት የተመጣጠነ ምግብ ከእድሜ፤ ከሚያደርገው ስፖርታዊ እንቅስቃሴና መሰል ነገሮች አንጻር እንደሚታይ የሚገልጹት ባለሙያዎቹ የምግብ አለማግኘትና እውቀቱ አለመኖር የአመጋገብ ስርዓታችንን እያዛቡት እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ አንጻርም በቀጣይ መደረግ ያለበት የተቀመጠለትን መጠን ጠብቆ መመገብ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ይህ ሆነ ማለትም በቀጣይ ሕይወታችን ላይ ብዙ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣ ጠቅሰው፤ በዋናነት ተላላፊም ሆኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በቀላሉ ለመከላከል፤ ጤናችንን አሻሽለን ምርታማ ለመሆን ያስችለናል ይላሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም