ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ነው:: የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ነው:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን የመቀላቀል እድል አገኙ:: ወዲያውኑ ለስልጠና ወደ ሶቭየት ኅብረት ተላኩ:: በሶቭየት ኅብረትም በራዲዮ ኤሌክትሮኒክስ ኢንጂሪንግ ዘርፍ ሰልጥነው ወደ አገራቸው ተመለሱ::
አገራቸው ከገቡ በኋላ ድሬዳዋ በሚገኘው የአየር ኃይል ማሰልጠኛ ገብተው የመኮንነት ስልጠና ወሰዱ:: በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ አስመራ፣ መቀሌ፣ ባህርዳር ፣ ኦጋዴን እና በሌሎቹም የአገሪቱ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ አገለገሉ:: ብዙም ሳይቆዩ ለተጨማሪ ስልጠና እስራኤል ተላኩ:: ለትምህርት እንደሄዱ ግን በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ::
እናም ከእስራኤል ወደ ጣሊያን በመሄድ በስደት ለአንድ ዓመት ቆዩ:: በኋላም አሜሪካ የመሄድ እድሉን አገኙ:: በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ቦስተን ከተማ ሁለት የትራንስፖርት ድርጅት አቋቁመው በመስራት ላይ የሚገኙት እኚሁ ሰው፤ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለማገዝ በተቋቋመው የቦስተን ግብረኃይል ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው የራሳቸውን አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛሉ::
ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ወደ አገራቸው የመግባት እድሉን ያላገኙት እንግዳችን የለውጡ መንግሥት መምጣቱን ተከትሎ ዳግም ከሚወዱት ሕዝብ ጋር መቀላቀል ችለዋል:: ከሰሞኑ ደግሞ በአየር ኃይሉ ሲያገለግሉ ከነበሩ የሠራዊቱ አባላት ጋር በመሆን በጦርነቱ የተጎዱትን ወገኖች ለማገዝ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል:: መቶ አለቃ እዮብ ሽባባው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል::
አዲስ ዘመን፡- ከአገር ከወጡ በኋላ ለረጅም ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ያልደፈሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ ያንሱልንና ውይይታችንን እንጀምር?
መቶ አለቃ እዮብ፡- ወደ አገሬ መመለስ ያልቻልኩበት ዋነኛው ምክንያት የቀድሞው ሠራዊት ሲፈርስና በርካታ አባላት ላይ ይደርስባቸው የነበረውን ግፍ ስለማውቅ ወደ አገሬ ለመመለስ አልፈለኩም ነበር:: ደግሞም ወያኔዎቹ የእነሱን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሚያቀነቅን ብቻ ስለሆነ የቀጠሩት እኔ ወደ አገሬ ብመጣም ትርጉም አልነበረውም::
በተለይ በአየር ኃይሉ አብራሪ የነበሩት አብዛኞቹ ጓደኞቼ ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል:: እንደ ኮሎኔል ብርሃነ መስቀል አይነት ጀግና የሠራዊቱ አባላት በግፍ እንዲበተኑ፣ እንዲሰቃዩ ፣ እንዲሁም እስከ 20 ዓመት ድረስ እንዲታሰሩ ተደርገዋል:: በደረሰባቸው ግፍ እና በደል ወህኒ ቤት እያሉም የሞቱ አሉ:: ወታደር አገርና ሕዝብ ያገለግላል እንጂ የአንድ ፖለቲካ ድርጅት ቅጥረኛ አይደለም:: እኛ ሠራዊቱን የተቀላቀልነው ብሔራችን ወይም ማንነታችን ተጠይቆ አይደለም:: ስናገለግል የቆየነውም በእውቀታችንና በክህሎታችን እንጂ በማንነታችን ሳንመዘን ነው:: እንደሚታወቀው ደግሞ አየር ኃይል የትምህርት ተቋም ጭምር እንደመሆኑ የሰለጠነው ከፍተኛ አቅም እንዲኖረን ተደርገን ነው:: እናም ያንን የመሰለ የካበተ ልምድና አቅም የነበረውን የሠራዊቱን አባላት የወያኔ ባለስልጣናት ከበተኑት በኋላ ዳግም የእዚህ አይነት ተቋም ለመገንባት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል:: በጣም ከፍተኛ ወጪ ወጥቶብን የተማርን እንደመሆኑ ሠራዊቱን በዚህ መልክ መበተናቸው ለአገሪቱ ትልቅ ጉዳት ነው:: ለምሳሌ አንድ አውሮፕላን አብራሪ ለማሰልጠን እስከ 25 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል:: እናም ወያኔ የበተነው ሠራዊቱን ብቻ ሳይሆን እውቀታቸውንና የአገሪቱን ሀብትም ጭምር ነው:: እኛ እንዳጋጣሚ ውጭ በመሆናችን ብንተርፍም አሁንም ድረስ እየተንገላቱ ያሉ ወገኖቻችን አሉ::
አዲስ ዘመን፡- ለአገሩ የደም ዋጋ የከፈለው ይህ የቀድሞ ሠራዊት ምንም እንኳን ያለአግባብ ሜዳ ላይ በትነውት እያሰቃዩት ቢኖርም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዳግም ሲጠሩት አሻፈረኝ አላለም:: ለመሆኑ የዚህ ምስጢር ምንድን ነው?
መቶ አለቃ እዮብ፡- ያነሳሽው በጣም ጥሩ ነው:: ምክንያቱም አገር ማለት እናት ነች:: አገር ማለት ሚስት ነች:: አገር ማለት እህትና ልጅ ነች:: እኛ ተቀርፀን ያደግነው በዚህ ስሜት ነው:: ብሔር የሚባል ነገር አናውቅም:: ለሠራዊትነት ከየአቅጣጫው ተመልምለን ስንመጣ መስፈርቱ እድሜያችንና የአካል ብቃታችን ብቻ ነው:: እናም በጣም ወጣቶች ብንሆንም ምንም አይነት ተጨማሪ ስነልቦና ይዘን አልመጣንም:: ሁሉም አባላት የሚፈልጉት አገራቸውን ማገልገል ብቻ ነበር::
ወያኔ ግን የፈፀመው ከዚህ በተቃራኒ ነው:: ወያኔ የሚፈልጋቸውንና የራሱ የሆኑትን አስቀርቶ ሌላውን ያለአግባብ አባሯል:: በዚህም ምክንያትም ብዙዎቹ የሠራዊቱ አባላት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው ነው የኖሩት:: ያ ሁሉ ከሆነ በኋላ ደግሞ ከሻዕቢያ ጋር ጦርነት ሲገጥም ያኔ የጣላቸውንና ለሰባት ዓመት ያህል ያለሥራ ተበትነው የነበሩ የእኛ ጓደኞች ዳግም ጥሪ ተደርጎላቸው እንዲመለሱ ተደርጓል:: እነዚያን የአገር ባለውለታዎች ለጦርነቱ ከተጠቀሙባቸው በኋላ ዳግመኛ እንዲበተኑ አድርገዋቸዋል:: የፈጠሩት ምክንያትም ‹‹ሠራዊቱ ውስጥ የትግራይ የበላይነት አለ ብላችኋል›› በሚል እና በደላቸውን ፊት ለፊት በመናገራቸው መርጠው አባረሯቸው:: ዞሮ ዞሮ ግን በአገር አይኮረፍም:: የወያኔን ጥሪ ተቀብለው ዳግም ሠራዊቱን ያገለገሉት እና አገርን ከጥፋት መታደግ የቻሉት የሻዕቢያ ወረራ የአገር ስጋት ነው ብለው ስለሚያስቡ ነበር:: እኛም ብንሆን በስደት በነበርንበት አገር ሆነን ጦርነቱ ሲካሄድ የነበረውን መንግሥት ባንደግፈውም አደጋው ለአገር ነው ብለን በማሰብ በምንችለው፤ በምናቀው መረጃ በመስጠት ለማገዝ ሞክረናል:: ይህንን ስናደርግ በእኛ እና በእነሱ መካከል የነበረውን የባላንጣነት ስሜት ከማለዘብ አልፎ ውስጣቸው አገራዊ ስሜት ይፈጥራሉ ከሚል እምነት ነበር::
በወቅቱ በአሜሪካን አገር የነበረው ብርሃነ ክርስቶስ ጠርቶ ሰብስቦን ሲያወያየን እኛ የቀደመውን በደላቸውን ትተን የሚፈልገውን መረጃ እንዲያገኝ አድርገናል:: ደግሞም እኛ የምናውቃቸው ብዙ ሚስጥሮች ስላሉ የነገርናቸው ምንም ሳንደብቅ ነበር:: ያንን ያደረግነው ጥያቄው አገራዊ ነው ብለን ስለምናስብ ነው:: ይሁንና ድል ካገኙ በኋላ ተመልሰው የገቡት ወደ ሚፈልጉት ሰይጣናዊ አስተሳሰባቸው ነው:: እስከመጨረሻው ድረስ የቀጠሉት ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ ጥቅማቸውን በማሳደድ ብቻ ነበር:: እውነቱን ለመናገር ግን ያ አጋጣሚ እነሱ ወደ ኢትዮጵያዊነት ሊመለሱ የሚችሉበት ጥሩ ዕድላቸው ነበር:: ምክንያቱም ያንን ወረራ የቀለበሰው ሕዝቡ በሙሉ በመረባረብ ነው:: ብዙ ሕይወት ተከፍሎበታል:: እነሱ ግን በዚያው በክፋታቸው በመቀጠል አሁን የደረስንበት ሁኔታ ላይ ጥለውናል::
አዲስ ዘመን፡- ይህ አሸባሪ ቡድን በሠራዊቱም ሆነ በአጠቃላይ ሕዝቡ ላይ ያደርገው የነበረው በብሔር የመከፋፋል ሴራ በውጭ በሚኖረው ዜጋ ላይም ተፅዕኖው ጎልቶ ይታይ እንደነበር ይነሳል:: ይህ ሁኔታ በአገር ገፅታ ላይ ምን አይነት አሉታዊ ሚና ተጫውቷል ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ እዮብ፡- ይገርምሻል! የምኖርበት አገር ላይ እኛ እንደአየር ኃይል ራሳችንን በዚህ ውስጥ አሳትፈን አናውቅም:: ከዚህ ቀደም እንዳልኩሽ ሠራዊቱን ስንቀላቀል ዋነኛ መስፈርቱ ብቃታችን እንጂ ብሔራችን አልነበረም፤ የታነፅነውም በዚያ መንፈስ ነው:: እናም ያ ስሜት በስደት በኖርባቸው ዓመታት በእኛም ውስጥ የፈጠረው ወንድማማችነትን ነው:: ይሁንና በምንኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ክፍፍሉ በደንብ ይታይ እንደነበር አይደበቅም:: በቤተክርስቲያን ውስጥ ሳይቀር ልዩነት ለመፍጠር ይጥሩ ነበር::
ኤምባሲን በተመለከተ ከጠየቅሽኝ ደግሞ የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር:: እውነት ለመናገር እኔ ኤምባሲው መኖሩን ልብ ብሎ የሚያውቅ ሰው አለ ብዬ አላምንም:: ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት መሥራት የቻልነው ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ነው:: አሁን ላይ ከእነአምባሳደር ፍፁም ጋር የምሰራው የቤተሰብ ያህል ነው:: እናም ያለን ቅርበት በፊት ከነበረው ጋር ስታነፃፅሪው የሰማይና የምድር ያህል ነው:: ምናልባት ወደ ኤምባሲ ልንሄድ የምንችለው ልንጮህ ልንሳደብ ወይንም ተቃውሞ ለማድረግ ነው እንጂ በሩ ተከፍቶልን አያውቅም ነበር:: ዛሬ ግን ለሁሉም ክፍት ሆኖ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውን ጉዳይ ያስፈፅማል፤ በቅርበት አብረን እየሠራን ነው::
ይሄ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው:: ከሦስት ዓመታት በፊት አብረን እየሠራን እንኳን የነበረን ማኅበራዊ ግንኙነት ጥሩ አይደለም:: እነሱ ይንቀሳቀሱ የነበሩት የራሳቸውን የልዩነት መስመር አስምረውና መንገዳቸውን መርጠው ነበር :: በመካከላችን ከሚገባው በላይ መገለል ነበር:: እነሱ ራሳቸውን ብቸኛ የአገር ባለቤት፤ እኛን ደግሞ የሚቆጥሩት ባይተዋር እና ሁለተኛ ዜጋ አድርገው ነበር:: ያም ጥሩ ያልሆነ ስሜት ፈጥሯል:: እኛ ላይም ከሚገባው በላይ ተፅዕኖ ለማድረግ ጥረት ያደርጉ ነበር:: ይህም ደግሞ በማኅበራዊ ሕይወታችንም ሆነ በአገር ገፅታ ላይ አሉታዊ ሚና ነበረው::
አዲስ ዘመን፡- አሁንም ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ እርስዎና ሌሎች የቀድሞው የአየር ኃይል አባላት ደግሞ አገራቸውን ለማገልገል ወደ አገራችሁ ገብታችኋል:: ይህንን አይነት ውሳኔ ለመወሰን ምክንያት የሆናችሁን ነገር ያንሱልን?
መቶ አለቃ እዮብ፡- እኔ በመሠረቱ ዶክተር ዐቢይ በምክር ቤት ያደረጉት ከመጀመሪያው ንግግር በኋላ በግሌ ያየሁት ነገር አለ:: እኔ በጣም የእርሳቸው ሃሳብ ይገዛኛል:: ከምንም በላይ አገራቸውን እንደሚያስቀድሙ ከዚያ በላይ እናታቸውን እና ሚስታቸውን እንደሚወዱ በአደባባይ ሲመሰክሩ እንደዚህ አይነት አቅም ያለው ሰው መሆናቸውን እንድረዳ አድርጎኛል::
ምክንያቱም ለእንደዚህ አይነት ነገር ቅድሚያ መስጠታቸው እውነተኛነታቸውን ያረጋገጠልኝ በመሆኑ ነው:: ከሁሉ በላይ ደግሞ እውነተኛ እና ኢትዮጵያዊ የሆነ መሪ መሆናቸውን ለመረዳት ችያለሁ:: እርሳቸው ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የወያኔ
ሰዎች በአገሪቱ ላይ የፈጠሩት ከፍተኛ ችግር እያለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገቡት ልማትና ውጤት አለማድነቅም አይቻልም:: በመሆኑም እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ከዓመታት በኋላ ወደ እናት አገራችን ስንመጣም ሆነ ድጋፍ ስናደርግ ዋነኛ ምክንያታችን ይሄ ለውጥ መደናቀፍ የለበትም ከሚል ነው:: እንደእኔ እምነት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅት ሥርነቀል ለውጥ የምታደርግበት የሽግግር ጊዜ ነው:: እያንዳንዳችን በደንብ ማሰብ የሚኖርብን ይህንን ለውጥ የምናጣው ከሆነ አገር እንደማይኖረን ነው :: ምክንያቱም ወያኔ ይሰራ የነበረውን ነገር በደንብ እናውቀዋለን:: ደርግ ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ሲሰራ የነበረው አገር የማፍረስ ሥራ ነው:: እናም ያ ሥርዓት ወድቆ አዲስ ሥርዓት መተካቱ የሰጠኝ ትልቅ ተስፋ ነው:: በዚያ መሰረት በምችለው አቅም ሁሉ እየደገፍኩ ነው ::
የመጣሁበት ዓላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመቻ ክተት ብለው ተከተሉኝ ሲሉ እንዴት ዝም ብለን ቁጭ እንላለን ብለን በማኅበራችን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ግሎባል ኔትወርክ አማካኝነት ለሕዝባችን ያለንን አጋርነት በተግባር ለማሳየት ነው:: በዚያ ማኅበር አማካኝነት ብንሰባሰብም ሌሎች ማኅበራትን ጋብዘን ሁሉም የመለሱልን ቀና የሆነ መልስ ነው:: ይህንን ድጋፍ ስናገኝ ተነስተን መሄድ እንዳለብን ወሰንን:: እዛ ያለው መንግሥት ዜጎቹን ከኢትዮጵያ ውጡ ቢልም እኛ ግን እናት አገራችን ኢትዮጵያ ታማለች መጠየቅ አለብን ብለን ተነሳን:: ስንመጣ ደግሞ ባዶ እጅ መሄድ የለብንም ብለን ሰውን አሰባሰብን:: የሚገርምሽ ነገር 40 ሺ ዶላር የሰበሰብነው በአንድና በሁለት ቀን ነው:: እያንዳንዱ ሰው በበይነ መረብ ባደረግነው ስብሰባ የእኛን መነሳሳት አይቶ ‹‹ባዶ እጃችሁን አትሄዱም ›› ብሎ ያለውን ሰጠን:: በእኔ እምነት እንዳውም ጊዜ ብናገኝ ኖሮ የተሻለ ገንዘብ እናመጣ ነበር:: በአጠቃላይ ያዋጡት አሜሪካ የሚገኙ የአየር ኃይል አባላትና ቤተሰቦቻቸው ሳይቀሩ ነው::
ብዙዎቹ እንዳውም በደል ተሰርቶባቸው እስር ቤት የተንገላቱ ልጆቻቸው በስደት የሚኖሩ አሉ:: ያዋጡት እነሱ ሳይቀሩ ነው:: ወደዚህ የመጣነው እኛ ልንሠራ የምንችላቸው ሥራዎች ካሉ በሙያችን አገራችንን ለመደገፍ መነሳሳቱ ስላለን በሩቅ ሆኖ ከመነጋገር በአካል ፊት ለፊት መነጋገር ያሻል በሚል ነው:: እናም በጣም ድንገተኛ ጉዞ ነው:: ብዙ አልተዘጋጀንም ግን ሁሉም ተሳክቷል:: ጥሩ አስተዋፅዖ እናበረክታለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ::
ይህ ገንዘብ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲደርስ የፈለግንበት ዋነኛ ዓላማም እናት ታማ እንዴት ባዶ እጅ ይኬዳል በሚል የሰበሰብነው እንጂ ብዙ የተዘጋጀንበት አይደለም:: በቀጣይ ግን አገራችን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያለች እንደመሆኑ ብዙ ሥራ መሥራት እንዳለብን እንገነዘባለን:: ደግሞም በዚህ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባት በመሆኑ በቋሚነት ልናግዝ የምንችልበትን ስትራቴጂ እንነድፋለን የሚል እምነት አለኝ:: አንዳንድ ከተሞች ላይ የደረሰውን ጉዳት መመለስ የሚያስችል ሥራ እንሠራለን ብዬም አምናለሁ:: ዋናው አመጣጣችንም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በዓይናችን አይተን ከዚያ እርዳታውን በቀጣይነት የምናካሄደው ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- ይህ የትግራይ ወራሪ ኃይል የፈፀማቸው ወንጀሎች፤ በተለይም ሕፃናትን ኣዛውንቶችን መድፈርና መግደልን ያካተተ ግፍ እንዳው ከዓለም አቀፍ የጦርነት ታሪክ አንፃር እንዴት ይታያል?
መቶ አለቃ እዮብ፡- ልክ ነው፤ ይህ እርኩስ የሆነ ቡድን እና ጨካኝ የሆነ ስብስብ የሚፈፅመው በደልና ግፍ በእርግጥ ከጤነኛ ሰው ይመጣል ብዬ አላስብም:: እየተደፈሩ ያሉት ሕፃናቶች እና መነኩሴዎች ሳይቀሩ ናቸው:: እንደዚህ አይነት የበቀል ስሜት የያዘ ኃይል ኢትዮጵያዊ ነው ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ:: በጣም የሚረብሽ፤ ለአዕምሮ ሁሌም ዕረፍት የሚነሳ ነው:: እኛ ወደዚህ ከመምጣታችን በፊት እንቅልፍ አልነበረንም:: ከአንድ ዓመት ጀምሮ ወያኔዎች ያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ፣ የሚሰሩት ግፍና በደልን እንከታተል ነበር:: ሕዝባችን ላይ የደረሰው ነገር ሲታሰብ ይቅር የምንለው እንዴት አድርገን ነው? እንዴት ነው ተመልሰን እንደዜጋ አብረን የምንኖረው የሚለው ሁልጊዜ ያቃጭልብኛል:: የሚበድሉት፤ የሚቀሙት ፤ የሚያራቁቱት ገበሬ ድሃ ነው::
በተለይ የሰሜኑ ገበሬ ይሄ ነው የሚባል ምንም ቅርስ የለውም :: እያንገላቱ እየገደሉ ልጁን እየፈጁ እያዋረዱት ያለው ያንን ሕዝብ ነው :: ወያኔዎች ደሀውን ገበሬ በዚህ መልኩ ግፍ የፈፀሙበት አንገት ለማስደፋት አስበው ነው:: ግን ደግሞ ይህ በተቃራኒው ከፍተኛ የሆነ ጥንካሬን ፈጥሯል:: ሕዝቡ ከዳር እስከዳር በቁጣ ተነስቶ ይህንን አረመኔያዊና ግፈኛ ስብስብ ዋጋውን እየሰጠ መሆኑን እያየን ነው:: እናም በእውነት እንደወታደር ከጠየቅሽኝ ወታደር ከጀርባ እንኳን አይመታም:: እናም እንደአንድ ኦፊሰር ጠላት ሊያጠቃ ሲመጣ መግደል ሥራችን ነው፤ ነገር ግን በተቻለ መጠን ሊገድል ከመጣው ወታደር ጋር እንጂ የምንፋለመው ሰላማዊ ሰው ጋራ እንዲህ ዓይነት በደል መፈፀም ትልቅ ወንጀል ነው::
ይህ ድርጊታቸው ከየት የመጣ የጦር ስልት እንደሆነም አላውቅም:: ሠራዊት እያለ ሕዝብን ማሰቃየት በሰውም በፈጣሪም ዘንድ የሚያስጠይቅ ነው:: ዓላማቸው ያንን የጦር አካሄድ ስልት ቀይረው ሕዝባዊ ማዕበል በመጠቀም ሰውን በማንገላታት፤ በማሸማቀቅና ከፍተኛ የስነልቦና ተፅዕኖ በመፍጠር ይህንን ጦርነት ለማሸነፍ ነበር:: እውነት ነው ፤ ንብረት አውድመዋል፤ ሕዝባችን ተንገላቷል፤ ከፍተኛ የሆነ በደል ፈፅመውበታል፡ ነገር ግን ይህንን በደል መመለሳችን አይቀርም::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በገፍ በምርኮ የሚያዙ የሕወሓት ተላላኪዎችን ጉዳይ በሕዝቡ ከፍተኛ ጥያቄ እያስነሳ ነው:: በተለይ በጦርነቱ የተማረኩት ሰዎች ‹‹ተገደን ነው›› የሚሉት ነገር ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ይገለፃል:: ከዚህ አንፃር የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
መቶ አለቃ እዮብ፡- ያነሳሽው በጣም ትክክለኛ ጉዳይ ነው:: ምክንያቱም እኔ ራሴ የሚረብሸኝ እና ልቤን የሚሰብረው ትልቁ ነገር እነዚህ ወራሪ ኃይሎች ሲያዙ የሚናገሩት ነገር ነው :: እያንዳንዱን እርምጃቸውን ወንጀል በመፈፀም የመጡ ሰዎች እንደመሆናቸው ተገደን ነው ስላሉ ብቻ ዝም ሊባሉ አይገባም:: እኔ መንግሥት ሆደ ሰፊ መሆኑን አደንቃለሁኝ:: መንግሥት አባት ነው፤ እናት ነው:: ነገር ግን ሕግም አለ:: በመሆኑም ወያኔ የላካቸው ወሮበላዎች የጦር ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች በመሆናቸው እንደተራ ምርኮኛ ልንቀበላቸው አይገባም:: በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ሰዎች እድሜያቸውም ጨቅላ፤ በአስተሳሰባቸውም ጨቅላ፤ የስነ ልቦና ችግር ያለባቸው ሰዎች ናቸው:: በመሆኑም ጊዜ ተሰጥቶ የሆነ የስነ ልቦና ትምህርት ሊሰጣቸውና ከባድ ቅጣት ሊተላለፍባቸው ይገባል:: ዳግም እንደዚህ አይነት ስህተት ውስጥ ተመልሰው እንዳይገቡ፤ እንዲህ አይነት እብሪት፤ ጥጋብ እኛ ነን ተዋጊ ጦረኛ የሚለውን ትዕቢታቸውን ከልቦናቸው እስከሚያጠፉ ድረስ ትክክለኛ የቅጣትና የትምህርት እርምጃ መንግሥት መውሰድ አለበት:: ነገር ግን ዝም ብሎ ገረፍ ገረፍ አድርጎ ተሐድሶ ብሎ ቢተዋቸው ተመልሶ የእሳት ቦምብ ማስቀመጥ ነው:: እነዚህ ሰዎች ጠላት ናቸው:: በደል ፈፅመዋል:: ደግሞም ተገደው ሊዋጉ ቢችሉም እንኳን አስገድዶ ‹‹ድፈሩ›› የሚላቸው ያለ አይመስለኝም:: የሰው ንብረት መስረቅ እና የሰው ዱቄት መዝረፍ የሚመስለኝ በራሳቸው ፍላጎት ያደረጉት ነው:: ይህ ድርጊት በራሱ ከባድ ቅጣት የሚያከትል መሆን ያለበት:: በአጠቃላይ ትክክለኛ እና ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ መንግሥትን አሳስባለሁኝ::
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያኑ ከሚያደርጉት ጫና አንፃር በዲፕሎማሲው ረገድ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ እዮብ፡- በመሠረቱ እኛ ያለችን ድሃ አገር ናት:: ይህ የማንደብቀው ነገር ነው:: ደግሞም ባለን አቅም ልክ አልሰራንም:: አሁን እኔ በምኖርበት አገር ብዙ ልማቶችን ስመለከት ልቤ ውስጥ የሚፈጥረው ቁጭት አለ:: እንዳለመታደል ሆኖ እኛም ተወልደን እስከምናድግ ድረስ ያለፍነው በስደት፤ በመከራና በበደል ውስጥ ነው:: መሥራት በሚገባንና ባለን አቅም አልሰራንም:: ስለዚህ ሁልጊዜ የእነሱን እርዳታ ተጠባባቂ ሆነናል:: ያንን ደግሞ እነሱም ያውቃሉ:: በእርዳታ ግን እድሜ ልካችን ልንዘልቅ አንችልም:: የብልፅግና መንግሥት አሁን ያስቀመጠው አቋም አለ:: ሕዝብን ከተረጂነት ማውጣትና ራስን መቻል የሚለውን አቋሙን ምዕራባውያኑ ተረድተዋል:: አካሄዱም ከእኛ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ አገሮችን አጠቃሎ ወደ ልማት መሄድና ራስን የመቻል ሃሳብ መኖሩን ከእኛ ይልቅ አውቀዋል:: የመንግሥትን ፅናትና ጥንካሬ ተገንዝበውታል:: በአጭር ጊዜ የተሠሩ ልማቶች በጣም አመርቂ መሆናቸው ትኩረት ስበዋል:: ይህ መሆኑ ደግሞ የእነሱን ጥቅም የማያስጠብቅ መሆኑ ስለገባቸው ስጋት አድሮባቸዋል:: ስለዚህ ይህንን መንግሥት ማፍረስና መበተን አለብን ብለው ተነስተዋል:: ጥቅማቸውን አያስከብርም ብለው ያሰቡት መንግሥት ምን አይነት ጥቅም እንደሚፈልጉ ፤ ምን አይነት የጂኦ ፖለቲካ ችግር እንዳለ አይቷል:: በመሆኑም ለእኛ የሚያዋጣን ነገር አሁንም ጠንክረን ፤ በያዝነው አቋማችን ፀንተን ይህንን የመጣብንን ተግዳሮት እና የምዕራባውያኑን ጫና ተቋቁመን በአንድነት መቆም ነው:: ምክንያቱም በአንድነት ከቆምን እነሱ ከዚህ ያለፈ ነገር ሊያደርጉ አይችሉም የሚል እምነት አለኝ:: አሁን ባለው ደረጃ እንደማንበታተንና በአቋማችን ፀንተን እንደቆምን የተረዱ ይመስለኛል:: እና አሁንም ይህንን አጠንክሮ መሄድ ይገባናል:: ከሁሉ በላይ ደግሞ በልማት የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማሳደግ፤ ወጣቱ በተቻለ መጠን የአገሩ ባለቤት እንዲሆን፤ የአካባቢው ባለቤት እንዲሆን ስደት እንዲቆም የሚሠራ ከሆነና በተጀመረው መንፈስ የሚቀጥል ከሆነ እናሸንፈዋለን የሚል እምነት አለኝ:: ግን ተፅዕኖው ቀላል አይደለም:: ምክንያቱም አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ እኛ ደሃ ነን:: እያንዳንዱ የአገሪቱ እንቅስቃሴ በእርዳታ የተጠናከረ ነው:: ይህም የሆነው ባለን ሃብት መጠቀም ስላልቻልን ነው:: ነገ ከነገ ወዲያ ግን የምጠቀምበት ዕድል እንዲኖር ኅብረት ኢትዮጵያዊነት ሊኖር ይገባል:: ከምንም በላይ ሁላችንንም አንድ አድርጎ ሊያስኬደን ይችላል:: መፍትሔው ይህ ነው እንጂ ከእነሱ እርዳታ እየጠበቅን የምንለምን ከሆነ እነሱ ምንጊዜም አይለቁንም:: የምንሆነው ምንጊዜም ከእርዳታ የማትወጣ አገር ነው:: የማምነው ያንን ለማስቀረት መስራትና ራስን መቻል ይገባል ::
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያኑን በመቃወም ረገድ በዲያስፖራው የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል?
መቶ አለቃ እዮብ፡– እኔ የምኖረው አሜሪካ እንደመሆኑ እናንተም እንደምታውቁት እዛ ያለው ዲያስፖራ የሚያደርገው የ‹‹በቃ›› እንቅስቃሴ ምን ያህል ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ አይተናል:: እኔ በምኖርበት ከተማ ውስጥም ንቁ ተሳትፎ አለኝ:: ሴናተሮች ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ከፍተኛ ሥራ እየሠራን ነው:: ደስ የሚለው ነገር አሜሪካ የአንድ ሰው ድምፅ የሚከበር መሆኑ ነው:: እኛ በምናደርገው እንቅስቃሴ ብዙ ለውጦች እየመጡ ነው:: አሜሪካኖቹ በተቻለ መጠን ትክክለኛውን የኢትዮጵያን እውነታ እንዲገነዘቡ ጉልህ ሥራ እየሠራን ነው:: የሚገርምሽ ነገር አሜሪካ ተወልደው ያደጉ የእኛ ልጆች የእኛ መንፈስ ተጋብቶባቸው በሚገርም እውቀት ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ነው:: በዚህ አጋጣሚ የምነግርሽ ነገር ‹‹የበቃ›› እንቅስቃሴ በተጨማሪ ‹‹አይዞን›› የሚባል የገንዘብ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማሰባሰብ የቻሉት እነዚሁ ልጆች ናቸው:: አሁን ያለን ቁጥርና አቅምም ከፍ ያለ ስለሆነ ተደማጭነታችን ከፍ እያለ ነው:: ይህም ደግሞ በአሜሪካ ዴሞክራሲ የሰው ድምፅ የሚደመጥበት አገር ስለሆነ ወደፊትም ይህንን ድምፃችንን ተጠቅመን የአገራችንን ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገቡ ጫና መፍጠር እንችላለን:: ባለፈው እንዳያችሁት ቨርጂኒያ ውስጥ በኢትዮጵያውያኖች ድምፅ ምክንያት ዴሞክራቶች ተሸንፈዋል:: ከአስር ወር በኋላ ደግሞ በሚካሄደው የሴኔት ምርጫ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ለማድረግ አስበን እየሠራን ነው:: እነሱም ቢሆኑ የእኛ ግስጋሴ ስጋት ፈጥሮባቸዋል:: በመሠረቱ እነሱ ንቁ የሆነ ማኅበረሰብ ሲመለከቱ ደስተኞች ናቸው:: እኛ ደግሞ ርቀን ብንኖርም ሁላችንም አገራችንን ስለምንወድ ልባችን እዚህ ነው:: ስለዚህ ማድረግ በምንችለው መጠን በገንዘብም በእውቀትም እየረዳን ነው::
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የገና በዓልንና የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት በማስታከክ ዲያስፖራው ወደ አገሩ እንዲገባና ወገኖቹን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል:: በዚህ ረገድ በማመንታት ላይ ላሉ የዲያስፖራ አባላት የሚያስተላለፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎትና ውይይታችንን በዚሁ እናብቃ?
መቶ አለቃ እዮብ፡- እንዳልሽው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀረበው ጥሪ መሠረት አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ እንዲመጣ ሰው እንቅስቃሴ ጀምሯል:: ይህ ዲያስፖራውን በጣም የሚያስደስት ነው:: ሆኖም ያንን ቁጥር የሚያስተናግድ ምን ያህል አቅም አለ የሚለው ነገር ያሳስበኛል:: ግን ሰዎች በብዛት መምጣት አለባቸው:: ጥሩ አጋጣሚ ነው:: በመጀመሪያ ደረጃ ከወገኖቻቸው ጋር ይገናኛሉ:: በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ ለአገራቸው ድጋፍ ያደርጋሉ:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ እኔ በአዕምሮዬ የመጣልኝ ነገር አለ:: ከውጭ የሚገባው እያንዳንዱ ዲያስፖራ አስርም ሆነ ሃያ ዶላር የሚያስቀምጥበት ቅርጫት ቢዘጋጅና እየጣለ ቢገባ እሱ ራሱ ትልቅ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገድ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ:: ዲያስፖራው ለአውሮፕላን ትኬትና ለሆቴል ከሚያወጣው ወጪ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቀነስ ጥቅም አለው ብዬ አስባለሁ:: ይህንን የሚያነቡ የመንግሥት ሰዎች ይህንን ሃሳብ ወስደው ቢተገብሩት ጥሩ ነው:: በእርግጠኝነት ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይህንን ጥሪ ተከትለው ይመጣሉ የሚል እምነት አለኝ:: ምክንያቱም አሁን አገራችንን እየሄደች ያለችበት የልማት ጎዳና ላይ የየራሳቸውን አሻራ ያሳርፋሉ:: ኢትዮጵያ ዳግም የማልቀስ የመተከዝ ሁኔታ ውስጥ አትመለስም የሚል ተስፋ አለኝ:: ለዚህ ደግሞ ሁሉም የየራሱን ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
መቶ አለቃ እዮብ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014