ህይወት ገጸ ብዙ ናት…ለአንዱ አዳፋ ለአንዱ ደግሞ ጸአዳ።መኖር ሁለት አይነት መልክ ነው… በአንዱ ውስጥ እውነት እና ፍትህ ስፍራቸው አይታወቅም በአንዱ ውስጥ ደግሞ የሌለ የለም።በህይወት ውስጥ የታጡ ጸጋዎች በጉድለት የተፈጠሩ ሳይሆን በተትረፈረፈ ራስ ወዳድነት የተፈጠሩ ይመስለዋል፡፡
የአለም ትንሳኤ ፍቅር ነው መጥፊያዋ ደግሞ ራስ ወዳድነት።ፍቅር የሰውነት ቀዳማይ ጸጋ ነው፤ ጥላቻ ደግሞ በተቃራኒው ቀዳማይ መርገምት።በዚህ ጥንድ እውነት ውስጥ እንደተፈጠረና እንደቆመ ሲያስብ መጨረሻው ያስጨንቀዋል።በራስ ወዳዶች አለም ላይ የመፈጠር ዋጋው ዛሬም ድረስ አልገባውም…ግን ይኖራል በፍቅር ጸጋ፣ በተስፋ ኩራዝ፡፡ ሰይፈ ይባላል ጎዳና አዳሪ ነው።
ጎዳና እንዴት እንደወጣ ከእሱና ከመላኩ ገብርኤል በቀር የሚያውቅ የለም።እሱ ካለበት አስፓልቱን ተሻግሮ የነሙዳይ ሰፊ ግቢ አለ።ከነሙዳይ ቤት አጠገብ ግሮሰሪውን አለፍ ብሎ ደግሞ የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አለ።
የመላኩ በዛ መገኘት የሙዳይን ባለቤት ካሳን ለመቅጣት ይመስለዋል።እንዴትም ቢያስብ ከዛ ሌላ ትርጉም ሊያገኝለት አይችልም።እሱ ይቅር ካላለው በስተቀር በፈጣሪ ምህረት ብቻ ካሳ መንግስተ ሰማያት እንደማይገባ ያውቀዋል።በህይወቱ ሁለት ሰዎችን አይረሳም።አንዷ ሙዳይ ናት አንዱ ደግሞ ባለቤቷ ካሳ።ህይወቱ በነዚህ ሁለት ነፍሶች መሀል የተቀመረች ናት።በሙዳይ አብቦ በካሳ ጠውልጓል።በእሷ ለምልሞ በእሱ ደርቋል።ጎዳና የወጣው በእሷ ፍቅርና በእሱ ጥላቻ ነው፡፡
ጠዋት በቤተክርስቲያኑ የተንስኦ ድምጽ ከእንቅልፉ ይነቃል።ማታ በዚያው የቡራኬ ድምጽ ያንቀላፋል።በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ሙዳይን ማየት ይባርከው ነበር።በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ከሥራ ወደ ቤት ከቤት ወደ ሥራ ስትል በነፍሱ ውስጥ ይሄ ነው የማይለው መታደስ ይጎበኘው ነበር።ለምን ወደዚህ መጣህ ለሚለው የሚናገረው አንድ መልስ አለው።እንዲህ የሚል ‹በህይወቴ ሙሉ የምወዳት አንድ ሴት ነበረች ሙዳይ የምትባል።
በልጅነቷ ውስጥ በቅዬ፣ በልጅነቴ ውስጥ በቅላ ዋርካ ሆኜ ሳፈራ ዋርካ ሆና ስታፈራ ፍሬዋን ለሌላ ሰጠች።ካለኝ ሳልሰስታት እስከ ጥጉ የህልውናዬ ዳር ድረስ ያፈቀርኳት የነፍሴ አለላ ጌጥ ናት፣…ሳቋ የሚያኖረኝ፣ ባስጠለልኩት ልጅነቷ ውስጥ ጆሌ ገብቶ ለሌላ ብታፈራም ቅያሜ ያልገባኝ የነፍሷ ባሪያ ነኝ› እያለ የሚያወራው ታሪክ አለው፡፡ ሁሌ ጠዋትና ማታ ከባሏና ከሁለት ልጆቿ ጋር በአጠገቡ ስታልፍ ያያታል።
ሩህሩህ አይደለች ያኔ ያላትን ትጥልለታለች።ያኔ ጎንበስ ብላ ቀና ስትል በልጅነቱ ውስጥ የሚያውቀው ውብ ጠረኗ ውልብ ይልበታል።ከአይኑ እስክትርቅ ድረስ ያነፈንፋታል። በክፉ ባል ተይዛ ደግነቷ ዛሬም ድረስ አብሯት መኖሩ ይገርመዋል።ባሏ ግን ሁሌም እንዲህ ይላት ነበር ‹ድሀን ገንዘብ ማስለመድሥራ እንዳይሰሩ መንገድ መክፈት ነው›።በዚህ ሁሉ ውስጥ ነበር የምትሰጠው።
ሙዳይና ካሳ ጥቁርና ነጭ ናቸው።ሁለቱን በአንድ ላይ ሲያያቸው እርግብና እባብ ተጋብተው አንድ ላይ የሚኖሩ ነው የሚመስለው።እንደፈራው ካሳ ሙዳይን ቀየራት። በመርዙ ነድፎ እንደ እሱ እንድታስብ አደረጋት።ሳትሰጠው ብዙ ቀን አለፈችው፣ ይባስ ብሎ ‹ድሀን ገንዘብ ማስለመድ ..› ማለት ሁሉ ጀመረች።
እርግቧ እባብ ሆነች።ለካ መልካምነት ይደበዝዛል፣ ለካ ንጽህና ይቆሽሻል።ሲያውቃት እንዲህ አልነበረችም።ሲያውቃት ቤቷ፣ ልቧ ለድሆች ክፍት ነበር አሁን ሁሉ ነገሯ ዝግ ሆኗል።የክፉ ሰው ዋጋው ምን ያህል እንደሆነ በሙዳይ ላይ አየ፡፡ ማታ አመሻሹ ላይ ነጠላዋ በንፋሱ እየተላጋ በአጠገቡ አለፈች።እንደ እስከ ዛሬው አልጠረነችውም፤ እንደ እስከ ዛሬው አላጓጓችውም።ለካ እስከ ዛሬ ሲጠርነው የነበረው መልካም ተግባሯ ነበር።ለካ ዘመኑን ሙሉ ሲከተለው የኖረው መልካምነቷን ነበር።
ለካ ሰው መልካም ካልሆነ የሚወደድ አንድም ነገር የለውም።ለካ ሰው ልቡና ነፍሱ ንጹህ ካልሆኑ ሰው አይባልም።ለካ ፍቅር ያለው በበጎነት ውስጥ ነው። ከቤተክርስቲያኑ ጓሮ አንድ ድምጽ ተሰማው፤ ‹ክፉ ባልንጀራ መልካሙን አመል ያጠፋል› የሚል።ለእሷ የተነገረ መሰለው።ነገ በዚህ መንገድ ደግማ ስታልፍ እንዲህ ይላታል፤ ‹ሙዳይ..› ሲል ይጠራታል፡፡ በድንጋጤ ‹ስሜን ማን ነገረህ? ስትል በመገረም ትጠይቀዋለች፡፡ ‹ሰይፈ የሚባል ሰው ታውቂያለሽ? ሲል ይቀጥላል።
ያኔ ወይ ራሷን ትስታለች ፤ አሊያም ደግሞ አሁን ላይ ሊገልጸው የማይችለውን ስሜት ታሳየዋለች፡፡ አሁን እሷ ፍቅረኛው እንደነበረች ማን ያምናል? ከዛሬ ስምንት አመት በፊት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ፍቅረኛው ነበረች።በሰአቱ እሱ ድሀ ስለነበር በቤተሰቧ አይን የሚሞላ አቅም አልነበረውም።ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ ቤተሰቦቿ ለባለጸጋ ዳሯት።እሷ ከእሱ ሌላ ማንንም አላገባም ብላ ብታምጽም፣ ቤተሰቦቿ ግን በሀይል የባለጸጋው የካሳ ሚስት እንድትሆን አስገደዷት።
እሱም ከዛ አካባቢ እንዲጠፋ ካልሆነ ግን ባሏ እንደሚገድለው ይዝትበታል።ያለው አማራጭ ሁለት ነበር፤ አንድ እንደተባለው ከዛ ሰፈር መጥፋት ሁለተኛ ደግሞ እሷን እያየ ሞቱን በጸጋ መቀበል።ከእሷ የመራቅ ሙጣጭ አቅም ስላልነበረው ሁለተኛውን መርጦ እዛው ሰፈር ውስጥ መኖር ጀመረ፤ ግን ነገሮች እንዳሰበው ቀላል አልሆኑለትም፡፡
የካሳ የበቀል ማረፊያ ሆነ።ሁለት ጊዜ ተዐምር በሚባል ሁኔታ ከሞት ተረፈ።ከዚህ በኋላም በባለጸጋው ሴራ ባልሰራው ወንጀል ስድስት ወር ተፈርዶበት ታሰረ።ከእስር ቤት ሲወጣ የጠበቀው ሌላ ነገር ነበር በባለጸጋው ሰው በታዘዙ ማጅራት መቺዎች ተደብድቦ ክፉኛ ተጎዳ።ከህመሙ ለማገገም ብዙ ጊዜ ወሰደበት፤ አሁን የሆነ ነገር ማድረግ እንዳለበት ያስብ ጀመር።
ሙዳይን አለማፍቀር በህይወቱ የማይችለው ነገር ነው።እሷን አለማሰብ፣ እሷን አለማየት ከቁጥጥሩ ውጪ የሆነ ስሜቱ ነበር።የሌላም ሆና እያያት ሊኖር ለራሱ ቃል ገባ።ግን እንዴት አድርጎ? በመጨረሻም አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ።ከቤታቸው ፊት ለፊት አስፓልቱን ተሻግሮ የኔ ቢጤ መስሎ መኖርን መረጠ። እንዳሰበውም አደረገ፤ ያለማንም ከልካይ ሙዳይን ያያት ጀመር።ግን እንዳስቀመጣት አላገኛትም፤ እርግብነቷ ልቧ ላይ አልነበረም፤ ካሾረው ወርቃማ ላባዋ ላይ አንድ እንኳን አልነበረም፤ በጎደሎው ሰው ጎላ አገኛት።በመጨረሻም ራሱን እንዲህ ጠየቀ የፍቅር ዋጋው ስንት ነው?
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኅሳሣሥ 1/2014