ሥዕል የሚናገር ብቻ ሳይሆን የሚያናግር ጥበብ ነው። በተለምዶ ‹‹ይናገራል ፎቶ›› ሲባል እንሰማለን፤ አባባሉ የብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶችም ዓምድ ነው።
አዎ! ፎቶ ይናገራል፤ ሥዕል ግን ያናግራል። ያናግራል ማለት እንድንናገር ያደርጋል፤ ከሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ብቻችንን ያስወራናል ማለት ነው። እንደ አእምሮ ታማሚ ድምጽ አውጥተን ባናወራ እንኳን በውስጣችን ግን እናወራለን፤ እንደመማለን፣ እንመሰጣለን። የጥበብ እርሾ ያለው ሰው ከሆነ ደግሞ ለሌላ ፈጠራ ይነሳሳል። ሥዕል የሚያዩት ብቻ ሳይሆን የሚናገሩበትም ነው።
ያልኖሩበትን ዘመን የሚያኖር ነው። ‹‹ሥዕል ካለመኖር ወደ መኖር መምጣት ነው›› ይሉታል የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ፤ ሙታንን ሕያው ያደርጋል ማለት ነው። የተለያዩ ነገሥታትም ሆኖ ሌሎች የጥንት ሰዎች በሥዕል እነሆ ዛሬም ድረስ መኖራቸውን የሚያሳይ ነው። ሥዕል ታሪክን አስታዋሽ ነው፤ ታሪክን የሚሰንድ ነው።
ጥንት ምን እንደነበር የሚያሳየን ነው። ዛሬን ከትናንት ጋር ለማነጻጸር ሁነኛ መሳሪያ ነው። ትናንት ምን እንደነበርን ለዛሬ ወኔ ነው። ባለፈው ሳምንት በአለ ፈለገሰላም የሥዕል ትምህርት ቤት የሥዕል ዓውደ ርዕይ ተከፍቷል። ይህ ዓውደ ርዕይ ለአንድ ወር ያህል ይቆያል። ዓውደ ርዕዩ ከአሁኑ አገራዊ ሁኔታ ጋር ይገናኛል። በተለያየ ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያውያን አርበኝነት ምንነት የሚያሳይ ነው።
በዚህ ዓውደ ርዕይ ውስጥ መገኘት፤ የመቅደላን፣ የመተማን፣ የካራማራን፣ የዓድዋን፣ የማይጨውን የአርበኝነት ውሎዎች ማየት ማለት ነው። ወደ ዓውደ ርዕዩ አዳራሽ እንደገባን አጼ ቴዎድሮስ ጎራዴ ታጥቀው፤ ከኋላ ደግሞ ጋሻ እና ጦር የታጠቁ ሕዝቦች ተከትለዋቸው እናያለን።
ከፊታቸው በፈረስ ፊት አንዲት ሴት ትታያለች። በነገራችን ላይ ሥዕል እንዲህ ነው ተብሎ ለማብራራት አይመችም። የሥዕል ውበት በመታየት ነው። ሥዕሎቹን ራሳቸውን ማብራራት ስለማንችል፤ ስለሥዕል ታሪካዊነት፣ ሳይንሳዊነት እና ፍልስፍናዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ጋር ባደረግነው ቆይታ ያገኘናቸውን ሙያዊ አስተያየቶች ነው ዛሬ የምናስነብባችሁ። ሠዓሊና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ታሪክ ከሚሰነድባቸው መንገዶች አንዱ ሥዕል ነው። ታሪክ በድምጽና በምስል ይሰነዳል። በሥዕል ሲሰነድ ለየት የሚያደርገው ግን ይተረጎማል። ከያኒው በመረጠው አተያይ ነው የሚሰነደው። ለማሳየት በመረጠበት መንገድ ያሳያል።
ይሄውም በቀለም ቅብ፣ በህትመት ጥበባት፣ በሀውልት እና በሌሎች የቅርጻ ቅርጽ አይነቶች ሊሆን ይችላል። ይህ በመሆኑም ታሪክን ለመሰነድ ብቻ ሳይሆን ለመተርጎም እና ለመተንተንም ዕድል ይሰጣል። ‹‹ሥዕል ‹ከዚህ እስከ እዚህ› የሚባል የለውም›› የሚሉት ሠዓሊ አገኘሁ፤ ከሰው ልጅ መፈጠር ጋር አብሮ የዘለቀና በሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ውስጥ አብሮ ያደገ መሆኑን ይናገራሉ። የንግግርም ሆነ የጽሑፍ ቋንቋ ከመጀመሩ በፊት መግባቢያ ነበር። አሁን ላለው የቋንቋ ሥርዓትም ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ፊደላት ከመኖራቸው በፊት የነገሮች ወካይ ሆነው የሚያገለግሉ ምሥሎች ነበሩ። ወካይ የሆኑ ምሥሎች በሂደት ወደ ፊደላት አደጉ።
አሁን በየቋንቋው የምንጠቀምባቸው ፊደላት ከእነዚያ ሥዕላዊ አገላለጾች የፈለቁ ናቸው። ዕይታዊ ጥበብ እያደገ መጥቶ ፊደላት ተቀረጹ። ፊደላት ተቀርጸው የሰው ልጅ በጽሑፍ ቋንቋ መግባባት ሲጀምር ሥዕል ራሱን ችሎ እንደ አንድ የዕውቀት ዘርፍ ሆኖ ቀጠለ። ሥዕል ከፍተኛ ጉልበት ያገኘው ቤተ እምነቶች ውስጥ እንደሆነም ሠዓሊው ይናገራሉ። ቤተ እምነቶች ውስጥ ሃይማኖታዊ መልዕክቶችን ለታሪክ ያስቀምጣል።
ከሥርዓተ ጽሕፈት ሥልጣኔ በኋላም ሁሉም ሰዎች ማንበብ ይችላሉ ማለት አልነበረም፤ እናም መልዕክቶች የሚቀመጡትም ሆነ ለሰዎች የሚገለጹት በመጻሕፍት መልክ ብቻ ሳይሆን በሥዕል ነው። ይህም በባህል ጥናት ‹‹ቁሳዊ ባህል›› ይባላል። የተለያዩ ዓለም አገራት የሥልጣኔ መነሻዎች እና መገለጫዎች ሥዕልና ቅርጻቅርጾች መሆናቸውን የገለጹት ሠዓሊው፤ ኢትዮጵያም በእንዲህ አይነት የዕደ ጥበብ ሥራዎች ቀዳሚ መሆኗን ያብራራሉ። ከዚህ የተነሳው የሥዕል ጥበብ የሳይንስ ዕድገቶች መነሻ ሆኗል።
በሒሳብ፣ በፊዚክስና ኬሚስትሪ ውስጥ ያሉ የሳይንስ ቀመሮችና ቅርጾች ሥዕል ወደ ድበ አካላዊነት እያደገ ሲመጣ የተደረሰባቸው ናቸው። ሥዕል ከምናባዊ እሳቤ ይነሳል፤ አካላዊ ቅርጽ ይይዛል። ስለዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ስለቀጣይ መጻኢ ዕጣ ፋንታም የማሰብ ሚና ይጫወታል። በሰማይ የሚሄድ አውሮፕላን ከመፈጠሩ በፊት ክንፍ ያለው አንዳች ቁስ ነገር በሥዕል ተሰርቶ ነበር። በሰማይ መሄድ እንዳለበት በምናብ ይታሰባል፤ በኋላም ወደ ቁስ አካላዊነት የሚለወጥበት የሳይንስ ደረጃ ላይ ሲደረስ አሁን የምናየውን አይነት ረቂቅ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማየት ተቻለ። ‹‹ራይት›› የተባሉት ወንድማማቾች አውሮፕላንን ከመሥራታቸው በፊት ዳቬንቼ የአውሮፕላን ቅርጽ ያለው ባለክንፍ ሥዕሎች ስሏል።
ሠዓሊው እንደሚሉት፤ በቤተ እምነቶች ውስጥ ከፍተኛ ጉልበት ያገኘው ሥዕል፤ በሒደት ‹‹ለምን አንድ ቦታ ብቻ?›› የሚል ጥያቄ ይዞ ተነሳ። ከቤተ እምነትም ከቤተ መንግሥትም ወጣ በማለት ዓለማዊውን የሰው ልጅ እንቅስቃሴም መቃኘት ጀመረ። የሰዎችን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ማሳየት ተጀመረ። በዚያው ሂደት ነው የጦርነት ውሎዎችም መሳል የጀመሩት። የዘመን ጥያቄዎችን መመለስ ጀመረ።
የሥዕል ፍልስፍና እና የሳይንስ ጀማሪነትን ሠዓሊው ምሳሌ ሲሰጡ፤ በሰው ልጅ አፈጣጠር ይመስሉታል። በሥነ ፍጥረት ፈጣሪ ሰውን ከአፈር ሰራ፤ ሀውልት ሠራ ማለት ነው። ይህንን ሀውልት እስትንፋስ ሰጠውና ሕያው ሰው አደረገው። እስትንፋስ ባይሠጠው ኖሮ ሀውልት (ግዑዝ አካል) ሆኖ ይቀር ነበር። የሥዕልና የሳይንስ ግንኙነትም ይሄው ነው ሲሉ ያብራራሉ። በመሬት የሚሽከረከረውም ሆነ በሰማይ የሚበረው መጀመሪያ በምናብ ይታሰባል፤ የቅርጻቸው ንድፍ ይወጣል፣ ከዚያ በኋላ አስፈላጊ ማሽኖች ይገጠሙላቸውና ተንቀሳቃሽ ይሆናሉ።
የሰው ልጅ የሰውነት ክፍል ላይ (መተንፈስ፣ ምግብ መፍጨት፣ መናገር፣ መንቀሳቀስ) የምናያቸው ነገሮች የሳይንስ ውጤት የሆኑ ቁስ አካላት ላይ ይተገበራል፤ ሕያው እስትንፋስ ባይኖራቸውም መሥራት የሚያስችላቸውን ሥራ ይሰራሉ። እነዚህ ረቂቅ የሳይንስ ውጤቶች በመጀመሪያ በሥዕል ምናብ የሚታሰቡ ናቸው። እነዚህ ረቂቅ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከሰው ልጅ እንቅስቃሴና ተፈጥሮ የተቀዱ ናቸው። አንዱ አካላቸው ቢጎድል አይሰሩም። ሥዕል ከሰው ልጅ አፈጣጠር ጋር የሚገናኘውም በዚህ ነው። ጥበብ እና ሳይንስ የተለያዩ ተደርገው የሚገለጹት ልክ እንዳልሆነ ሠዓሊው ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ አንድን ነገር ለማብራራት፤ ይሄ ጥበብ ነው፣ ይሄ ሳይንስ ነው›› ሲባል እንሰማለን።
እንደ ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ሳይንስና ጥበብ የሚለያዩ አይደሉም። ሒሳብ ሳይንስም ነው፤ ጥበብም ነው። የማስተማር ዘዴው ጥበብ ነው፣ ሥዕል ነው። ሥዕልን በተመለከተ አንድ አከራካሪ ነገር አለ። ይሄውም ሥዕል ማብራሪያ ያስፈልገዋል አያስፈልገውም የሚለው ነው። ሠዓሊዎች አያስፈልገውም ነው የሚሉት፤ አንዳንድ ለሥዕል ቅርበት ያላቸው ተመልካቾችም አያስፈልገውም ነው የሚሉት። አንዳንዶች ደግሞ መልዕክቱን ለማወቅ፣ እንዲሁም ለሥዕል ሩቅ የሆኑ ሰዎችን ለማቅረብ ማብራሪያ ቢኖረው ይመረጣል የሚሉም አሉ።
ሠዓሊ አገኘሁ እንደሚሉት፤ ሥዕል ራሱን መግለፅ የሚችል ስለሆነ ማብራሪያ አያስፈልገውም። የሚታይ መልዕክት ነው። ሠዓሊው ያንን ሥዕል ሲያብራራ አይኖርም። እነ ዳቬንቼ ዛሬ የሉም፤ የሥዕል ሥራዎቻቸው ግን አሉ። በጥንት ዘመን የተሰሩ ሥዕሎችን ዛሬ የሳላቸው ሰው መጥቶ ሊያብራራልን አይችልም፤ ማብራሪያም አያስፈልጋቸውም፤ ራሳቸውን ችለው የቆሙ ናቸው። በሌላ በኩል የሥዕል ውበቱ ማንም በራሱ መረዳት የሚችለው መሆኑ ነው ይላሉ። የሰዎችን የዕይታ አድማስ ያሰፋል። ሰዎች በራሳቸው እንዲናገሩና ከራሳቸው ጋር እንዲከራከሩ ያደርጋል።
የትኛውም የኪነ ጥበብ ሥራ ደግሞ ለትርጉም የተጋለጠ ነው። ጥሩ ዕድሉም ይሄው ነው፤ ሰዎችን አይገድብም። ሥዕል የሚተረጎመው እንደተመልካቹ ነው። የአዕምሮ ማሰብና ማሰላሰልን ይፈጥራል። ያም ሆኖ ግን ኪነ ጥበብን የሚያጣጥም ቅርበት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በሥዕል ዓውደ ርዕዩ ላይ ያሉ አርበኝነትን የሚገልጹት ሥዕሎች በተለያየ ጊዜ የነበሩ መንግሥታትን ሁኔታ የሚወክሉ መሆናቸውንም ሠዓሊ አገኘሁ ተናግረዋል። በንጉሣዊው ዘመን ጊዜ የነበሩት ቀደም ሲል ለነበረው ሃይማኖታዊ አሳሳል የቀረቡ ናቸው። በይዘት ደግሞ፤ የአርበኝነት ተጋድሎ ብቻውን ድል አያስገኝም፤ የመላዕክት ተራዳኢነትም ያስፈልጋል የሚል መልዕክት አላቸው።
በአርበኞችና በመላዕክት መካከል ተዋረዳዊ ግንኙነትና ለድል የፈጣሪ እርዳታ እንደሚያስፈልግ የሚያመለክት ነው። በደርግ ዘመነ መንግሥት ያለው ደግሞ ያንኑ ርዕሰ ጉዳይ (ለምሳሌ ዓድዋ) ከመለኮታዊ ኃይል ያላቅቀዋል። የሰው ልጅ ራሱን የቻለ እና ሁሉን ማድረግ የሚችል እንጂ ሌላ ድጋፍ የሚያስፈልገው ደካማ አይደለም ይላል። ሙሉ በሙሉ ዓለማዊ ይዘት ይኖረዋል። በአሳሳል ረገድ ደግሞ በአውሮፓ አገራት ተምረው የነበሩ ሰዎች የነበሩበት ስለሆነ የውጭውን ዓለም የአሳሳል ስልት የተከተለ ነው።
በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ፤ ትልልቅ ሁነቶች እና ትልልቅ ታሪካዊ ትረካዎች ቀርተው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች እና የሰዎች ኑሮ ላይ ማተኮር ተጀመረ። ለምሳሌ፤ እንጨት የምትለቅም ሴት፣ አውቶቡስ የሚጠብቁ ሰዎች፣ የፋብሪካ ሰራተኞች የመሳሰሉ ዘወትራዊ ነገሮች ናቸው የሚታዩ። ቢሆንም ግን በዚህ ዘመንም አርበኞችን የተመለከቱ አልተሰሩም ማለት አይደለም።
በብሄር መደራጀትና መከፋፈል ለአገር አንድነት አደጋ እንደሚሆን የተረዱ ሠዓሊያን ወደኋላ ሄደው የጥንት አርበኞችን ያመጡ ነበር። የእነዚህ ልጆች ነን ለማለት ነው፤ ይቺን አገር ለመሥራት እነዚህ ሰዎች ዋጋ ከፍለዋል ለማለት ነው። ለሥዕል ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በሌላውም የጥበብ ዘርፍ ላይ ያለውን መቀዛቀዝ ለማነቃቃት በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ወቅት የባለሙያው ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚያስፈልግ ሠዓሊ አገኘሁ ያሳስባሉ፤ አለበለዚያ ግን የአገሪቱ የሥልጣኔ መገለጫዎችና ምስክሮች የሆኑ የጥበብ ሥራዎች እንደሚዳከሙ አስገንዝበዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 30/2014