ታሪካዊውና አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በቅርቡ የቀጠራቸውን ሰርብያዊ አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፓቲችን ማሰናበቱ እርግጥ ሆኗል። ፈረሰኞቹ ለሚቀጥሉት ጥቂት ጨዋታዎችም በጊዜያዊው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እንደሚመሩ ታውቋል።
በቀጣይም ማን ታሪካዊውንና ታላቁን ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በአሰልጣኝነት ይረከባል የሚለው ተጠባቂ ሆኗል። በተለይም ላለፉት በርካታ ዓመታት ፈረሰኞቹ ሙሉ ትኩረታቸው በውጭ አሰልጣኞች ላይ መሆኑን ተከትሎ ወደ አገር ውስጥ አሰልጣኞች ፊታቸውን ይመልሳሉ ወይስ አሁንም ወደ ውጭ ያማትራሉ የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል። ፈረሰኞቹ አሁን ያሰናበቷቸው የ62 ዓመቱ ዝላትኮ ክራምፖቲች በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በማሰልጠን በደካማ ውጤትና እጅግ አሰልቺ በሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ የሚታወቁ በመሆናቸው ገና ከጅምሩ በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ አልተወደዱም ነበር።
በተለይም አሰልጣኙ በቅርብ ዓመታት የተለያዩ የአፍሪካ ክለቦችን ለማሰልጠን ከተረከቡ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ከወራት በኋላ በተደጋጋሚ በማሠናበት የታወቁ መሆናቸው ፈረሰኞቹ የተጠና ቅጥር አላደረጉም በሚል ትችቶች ሲሰነዘሩም ነበር። የተፈራውም አልቀረም አሰልጣኙ በተለያየ ሰበብ ከፈረሰኞቹ ጋር ብዙም ሳይቆዩ ወደ ውጭ አገር ሄደው ሲመለሱ ለመሰናበት ችለዋል።
ክራምፖቲች የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ከመሆናቸው በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያሰለጠኑት የታንዛኒያውን ያንግ አፍሪካ ሲሆን አሰልጣኙ በክለቡ የቆዩት ለ37 ቀናት ብቻ ሲሆን በሌሎች ክለቦችም በተመሳሳይ ጥሩ ስም የላቸውም። ፈረሰኞቹ ከክራምፖቲች በፊትም በሚቀጥሯቸው የውጭ አሰልጣኞች ዙሪያ ስፖርት በርካታ ትችቶች በስፖርት ቤተሰቡ ይቀርብባቸው ነበር። ፈረሰኞቹ በበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪካቸው በአገር ውስጥ ውጤት ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዙ የቻሉት በአገር ውስጥም በውጭም አሰልጣኝ ጭምር ነው። ይሁን እንጂ ከአገር ውስጥ ስኬት በዘለለ በአፍሪካ መድረኮች አንድም ጊዜ የሚጠቀስ ዋንጫ ማንሳት አልቻሉም።
ክለቡን ለመምራት የሚመደቡ ሰዎች ሁሉ ለዚህ መፍትሄ ብለው የሚያስቀምጡት አሰልጣኝ መቀየርን ነው። በአገር ውስጥ ውጤታማና ኮከብ የተባሉትን አሰልጣኞች ሞክረዋል፣ ከውጭ አገርም አጣርተው አብጠርጥረው የሚያመጡትን ምርጥ አሰልጣኝ በሃላፊነት አስቀምጠዋል። ሁሉም የአገር ውስጥ ዋንጫ ያነሳሉ፤ ነገር ግን ከአገር ውጪ ተመሳሳይ ውጤት ነው ያላቸው። ‹‹እንዲህ ከሆነ የውጭ አሰልጣኝ መቅጠር ለምን አስፈለገ?፣ ከውጭ አገር በመጡ አሰልጣኞች ምንም ነገር እንደማይገኝ እየታወቀ ፈረሰኞቹ ለምን የውጭ አሰልጣኞች ላይ የሙጥኝ አሉ?›› የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከ40 ያላነሱ የውጭ አሰልጣኞች መጥተው ምንም ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። በተመሳሳይ ክለቦቻችንም ከውጭ አሰልጣኝ አምጥተው መለወጥ አልቻሉም። የቀድሞው መብራት ሃይልና ኢትዮጵያ ቡናም የውጭ አሰልጣኝ አምጥተው ለውጥ አላሳዩም። ፈረሰኞቹ ከ1996 ጀምሮ ለአስራ አንድ ዓመትና ከዚያም በኋላ የአገር ውስጥ አሰልጣኞችን ትተው በውጭ አልጣኝ እየተመሩ በርካታ የአገር ውስጥ ዋንጫዎችን ማንሳታቸው ውጤቱ የተገኘው የውጭ አሰልጣኝ በመቅጠራቸው ሊመስል ይችላል።
እውነታው ግን ፈረሰኞቹ በውጭ አሰልጣኝ እንዳልተጠቀሙ ያሳያል። ለዚህም ፈረሰኞቹ ከውጭ አሰልጣኝ ከማምጣታቸው በፊት በተደጋጋሚ ዋንጫ ማንሳት መቻላቸው ማሳያ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ያስመጣቸውን በርካታ የውጭ አሰልጣኞች ያባረረው በአገር ውስጥ ዋንጫ እያመጡ ነው። ለምን ቢባል በውጭ ውጤት ስላላገኙ ነው። እናም የውጭ አሰልጣኞች ጊዮርጊስ በፊት የነበረውን ውጤት ነው የሚያሳዩት እንጂ የተለየ ነገር አላመጡም። ፈረሰኞቹ ሌላው ቢቀር የውጭ አሰልጣኞችን ባሰናበቱ ማግስት ምክትል አሰልጣኞች ሙሉ የውድድር ዓመት በሚባል ደረጃ እየተመሩ ዋንጫ አንስተዋል።
ለዚህም ከጥቂት ዓመታት በፊት የቀድሞው ኮከባቸው ፋሲል ተካልኝ ቡድኑን በምክትል አሰልጣኝነት እየመራ ያነሳውን የፕሪሚየርሊግ ዋንጫ ማስታወስ ይቻላል። ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ፋሲል ቡድኑን ቻምፒዮን ባደረገ ማግስት የተቀጠረው ሌላ የውጭ አሰልጣኝ ነው። የፈረሰኞቹን ቤትና ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ የአገር ውስጥ አሰልጣኞች ምክትል ሆነው በርካታ ዓመታት እያገለገሉ እንኳን ወደ ዋና አሰልጣኝነት ተሸጋግረው እድል አለማግኘታቸው ሁሌም ጥያቄ ያስነሳል።
ዘንድሮ ግን ፈረሰኞቹ ፊታቸውን ወደ አገር ውስጥ አሰልጣኞች መመለስ ካለባቸው ትክክለኛ ጊዜው መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። ይህም ቢያንስ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያጡትን የአገር ውስጥ ዋንጫ በማንሳት ወደ አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመመለስ እድል ሊፈጥርላቸው እንደሚችል ያታመናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 29/2014