ሴቶች ተፈጥሮ የቸረቻቸውን ዕድል ተጠቅመው ጀግና በመውለድ ለአገር አስረክበዋል። ከዚህም በላይ በነፍሰ ጡርነታቸው ወቅት በአውደ ውጊያዎች ተሰልፈዋል። ግዳይ በመጣልም ድልን ተቀዳጅተዋል።
ለአገራቸው በመውደቅ ብዙ መስዋዕዋትነቶችን እየከፈሉ አልፈዋል። ሴቶች በፖለቲካው ተሳትፎም በኩል ቀደም ባሉት ጊዜያት የላቀ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። በዚህ በጥንቱ የአገራችን ወግና ልማድ መሰረት በተለይም ከቤት እስከ አደባባይ የዘለቀው የአስተዳደሩ መስክ ለወንዶች (ለአባ ወራው) ብቻ የተተወ ነበር። በአክሱም ገናና ከነበረችው ከንግስተ ሣባ ወዲህ ከልጇ ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ የሠሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ንግስና በወንዶች በኩል እንዲቀጥል ሲደረግ የነበረ መሆኑ በማሳያነት ይጠቀሳል።
በኢ.ዜ.ማ ሕዝብ ግንኙነት በኩል በ2012 ዓ.ም ተዘጋጅቶ የወጣ አንድ ጽሑፍ፣ የታሪክ መዛግብቶችን ዋቢ አድርጎ እንዳተተው፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የነገሠው የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ሴትን በመንግሥትነት አስተዳደር ቦታ አላስቀመጠም።
ከዛጉዌ ስርወ መንግሥት ፍጻሜ በኋላ በአፄ ይኩኖ አምላክ እንደገና ያንሰራራው ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥትም ወራሾቹ ወንዶች እንዲሆኑ ክብረ ነገሥት ላይ በተደነገገው አሠራር እንዲተገበር ሲያደርግ የቆየበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም በዚህ ዘመንም ቢሆን ሴቶች የመንበረ ሥልጣኑን ዙፋን በይፋ አይቆናጠጡ እንጂ በመንግሥት አስተዳደሩ ውስጥ የአንበሳውን ሚና ሲጫወቱ የቆዩበት ሁኔታ ነበር። ከዚህ አኳያ፣ እንደ ኢ.ዜ.ማ ጽሑፍ ከሆነ፣ ከዚህ ዘመን ሴቶች የአፄ በካፋ ሚስት፣ እቴጌ ምንትዋብን አብነት ማድረግ ይቻላል። እቴጌ ምንትዋብ አፄ በካፋ ከሞተ በኋላ በዙፋኑ ላይ ለአቅመ አስተዳደር ያልደረሰውን ብላቴና ልጇን ዙፋኑን እንዲወርስ አድርጋለች።
የወረሰው ወንድ በመሆኑ ነው። ሆኖም ልጇ አቤቶ እያሡ ሕፃን በመሆኑ ከበስተጀርባ ሆና የመንግሥት አስተዳደር ሚናውን በሙሉ የምትጫወተው እሷ ራሷ ነበረች። በልጇ ሥም የብዙ ሥራዎች አድራጊ ፈጣሪ ሆና ቆይታለች። ይቺ ሴት በልጇ ስም ብልሀት በተሞላበት መንገድ በመንግሥት አስተዳደሩ መስክ ውጤታማ ስኬቶችን መጎናፀፍ ችላለች። ከውስጥም ከውጭም የገጠሟትን በርካታ የሥልጣን ተቀናቃኞች በመጋፈጥ በመንግሥት አስተዳደር ብቃቷ ገናናነትን አትርፋበታለች።
ባቲ ድል ወንበራ በበኩሏ ከኢማም አሕመድ ሞት በኋላ የተበታተነ ሠራዊቱን አሰባስባና አስተባብራ በአዋጊነት ከፊት የመራች ነች። ታዋቂዎቹ የወሎ ሴት ባላባቶች እነ ወይዘሮ ወርቄና እነ ወይዘሮ መስተዋትም በአገር አስተዳደር መሪነት ባላቸው ጉልህ ሥፍራ በታሪክ መጠቀስ ችለዋል። ከአጼ ቴዎድሮስ ጀርባ የነበሩት እቴጌ ተዋበች እንዲሁም ከአፄ ምኒልክ ጀርባ የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ብጡል በውጤታማው የባሎቻቸው መንግሥት አስተዳደር የነበራቸው ተሳትፎ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። እነዚህ ሴቶች በተለይም በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበሩትና ያለፉት እቴጌ ጣይቱ የጦር መሪና የጦር ዘዴ ቀያሽ መሪም እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ።
ኢትዮጵያውያን ሴቶች በዓድዋ ጦርነት በተዋጊነት፣ በጦርነቱ የተጎዱትን ወታደሮች በማከም እንዲሁም ያላሰለሰ የስንቅ ዝግጅት እያዘጋጁ በማቅረብ ጭምር ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አስችለዋል። የአባታቸውን የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ዘውድ በመጫን ንግስተ ነገሥታት ለመሆን የበቁት ዘውዲቱም ለወንዶች ብቻ የተተወውን የመንግሥት አስተዳደር ለመጀመርያ ጊዜ የሰበሩና የመሪነት በትረ ሥልጣን ለመጨበጥ የቻሉ ለመሆን በቅተዋል።
ለወንዶች ብቻ ተትቶ የነበረውን አገር የመምራት ንግሥና ለመያዝ በዘመኑ በነበሩ መኳንንቶች ይሁንታ ማግኘት የቻሉም ነበሩ። አባታቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ምንም እንኳን የአልጋ ወራሽነቱን ሥልጣን ለልጅ ልጃቸው ለልጅ እያሱ የሰጡ ቢሆንምና ጥቂት ጊዜም ልጅ እያሱ ቢያስተዳድሩም በኢትዮጵያ ታሪክ የመንግሥት በትረ ሥልጣን ጨብጠው ለመጀመርያ ጊዜ አገር የመሩ ብቸኛዋ ንግስት መሆን ችለዋል።
ይሄን ማድረግ መቻል በራሱ አቅም የሚጠይቅ ነውና ይደነቁ ዘንድ የግድ ይላል። ንግስቷ፣ ምንም እንኳን የንግስና ዘመን ቆይታቸው አጭር ቢሆንም፣ በአመራር ስኬታማ የነበሩ መሆናቸው ይነገርላቸዋል። ከዚህ ከሴቶች ፖለቲካዊና አገራዊ የመንግሥት ግንባታ አስተዳደር ተሳትፎ ሳንወጣ የሴቶችን አስተዋጽኦስንቃኝ የአፄ ኃይለ ሥላሴን ዘውዳዊ ሥርዓትና የደርግን ሥርዓት ለመጣል በተደረጉት ትግሎች ውስጥ በርካታ ሴቶች ተሳትፈው እናገኛቸዋለን። ለምሳሌ፦ ማርታ መብራሃቱ ዘውዳዊውን ሥርዓትን በመቃወም አውሮፕላን እስከ መጥለፍ ከደረሱት ሴቶች አንዷ ነበረች። በወቅቱ በነበሩት ፓርቲዎችም ከተራ አባልነት እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነትም የደረሱ ሴቶች ነበሩ።
ነገር ግን አገራችን ሞልቶ ከተረፋት የሺህ ዓመታት ታሪክ ውስጥ በተሳትፏቸው የሚጠቀሱት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው ። የመረጃ ምንጫችን እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅትም አብዛኞቹ የዓለም አገራት መንግሥታዊ የሥልጣን እርከኖች፣ ሃላፊነቶች እና ውሳኔ ሰጪነት በአብዛኛው በወንዶች የተያዘ ነው። እንደውም በአንዳንዶቹ አገራት ጭራሹኑ ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ ነው፡፡ ይሄ ማለት በቀላል አነጋገር በመስኩ ሴቶች መሳተፍ አይችሉም። ወይም ሴቶች እንዳይሳተፉ በሕግ ተከልክሏል ማለት ነው። በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ፣ በዘመናዊ መንግሥት አስተዳደር ውስጥ፣ ይብዛም ይነስም ሴቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በፌዴራል ፓርላማም ሆነ በሌሎች ምክር ቤቶች ያለው የሴቶች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ቢሆንም ተሳትፏቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየተሻሻለ መምጣት ችሏል። በተለይ ከለውጡ ጀምሮ ባሉት ዓመታት በካቢኔ ደረጃ ሴቶች ከወንዶች ጋር የተመጣጠነ ቁጥር (50/50) እንዲኖራቸው መደረጉ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። የሴቶች በፖለቲካ የመሳተፍ ጉዳይ የፍትህ ጥያቄ ጉዳይ እነደሆነም ይጠቀሳል።
ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ በላዩን ቁጥር የያዙትን ሴቶች በራሳቸው ለመወከል ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑም ይጠቀሳል። ‹‹የሴቶች ውክልና በራሱ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው›› የሚሉት በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አድነው አበራ ናቸው። ሆኖም ሴቶች ከቁጥራቸው አንፃር ሳይወከሉና ድምፅ ሳይኖራቸው በራሳቸውም ሆነ በማሕበረሰቡና በአገር ግንባታ ጉዳይ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደማይችሉም ያብራራሉ። በተጨማሪም ሴቶችን ያገለለ የፖለቲካ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ሴቶች በሕግ አውጪው፣ በሕግ አስፈፃሚው እንዲሁም በሕግ ተርጓሚው አካላት በተመጣጣኝ ሁኔታ ካልተወከሉ እንደ አገር በየመስኩ የሚፈለገውን ዕድገት ማሳካት እንደማይቻልም ይገልፃሉ። በማሕበረሰብ ውስጥ በዋነኛነት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግቦችን ለማረጋገጥም ሆነ ለማሳካት “አይቻልም” ብቻም ሳይሆን አሳታፊ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሠፈነበት አሠራርንም ማምጣት አይታሰብም።
ይሄን በመንተራስ በየዘመናቱ ሴቶች በራሳቸውም እንደ አጠቃላይ በሕብረተሰቡም በተደረጉ ትግሎች አነሰም በዛም በየደረጃው ለውጦችና መሻሻሎች መምጣት መቻላቸው አለመካዱንም ጽሑፉ ያሰምርበታል። አቶ አድነው እንደሚናገሩትም አነሰም በዛም ሴቶች በየሥርዓቱና በየደረጃው የነበራቸው አስተዋጽኦ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ውክልና በማረጋገጥ በኩል አበርክቶ እያደረገ መጥቷል። በማሕበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ግን ደግሞ ከቁጥር ሳይገባ የኖረውንም ዕውቅና እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ለዚህ ሩቅ ሳይኬድ አሁን ላይ የአገር ውስጥ የሽብር ኃይሎች ከጥቂት ለአገራችን ዕድገት በጎ አመለካከት ከሌላቸው ከውጭ (ባእድ) ኃይሎች ጋር በመተባበር አገራችን ላይ ከከፈቱት የውክልና ጦርነት ጋር ተያይዞ፣ ሴቶች ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ ግንባር እስከ መሰለፍ እያደረጉት ያለው አበርክቶ ማሳያ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት እዚህም እዛም በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለመከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ያለው ድጋፍ በአብዛኛው በሴቶች አስተባባሪነትና አዘጋጅነት የተፈጸመ ነው። እንደ ተቋምም ቢሆን የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖችና ለመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለው ድጋፍ ሴቶች ለማሕበረሰቡና ለአገራቸው ግንባታ ለሚያደርጉት አስተዋጾ ጎልህ ማሳያ ነው።
የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራ ክልል በከፈተው ጦርነት ከክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች የ 73 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። በቅርቡ የተደረገውን ይህን ድጋፍ ተቋሙ ከስዊድን የልማት ተራድኦ ድርጅት በዩኒሴፍ በኩል ያገኘው እንደሆነም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። የሴቶች ሕፃናት እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከ73 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብሩ ድጋፍ በተጨማሪ ለተፈናቃዮቹ የዓይነት ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል። ‹‹በሕወሓት በተከፈተ ጦርነት ምክንያት ለከፋ ማሕበራዊ ቀውስ የተጋለጡ ተፈናቃይ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል›› ሲሉም አስረድተዋል።
ከላይኛው ድጋፍ በተጨማሪም 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣው የዓይነቱ ድጋፍ በተለይ የተፈናቃይ ዜጎችን ችግር በከፍተኛ ደረጃ የሚያቃልል መሆኑንም ገልጸዋል። ከሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት እንደተገኘው መረጃ ከሆነ፣ በድጋፉ ርክክብ ወቅት የዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የአማራ ክልል አስተባባሪ አቶ አዲሱ ጫኔ የገንዘብ ድጋፉ በክልሉ ከ45 ሺህ በላይ በችግር ለተጋለጡ ዜጎች (አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት) የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።
የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት የተፈጠሩ ማሕበራዊ ቀውሶች እና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ዙሪያ በቅርቡ የቀረበ ጥናት እንደሚያመለክተው ጦርነቱ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ብቻ 54 ሺህ 354 ሕጻናት፣ 15 ሺህ 251 ሴቶች፣ 7 ሺህ 393 አረጋውያን 2 ሺህ 23 አካል ጉዳተኞች ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ከመሆኑ አንፃር በተለይ ሴቶች ሊያደርጉት የሚችሉት አስተዋፅኦ በቀላሉ ሊታይ የሚችል አይደለም። እኛም በዚሁ ጥናት የተካተተውን ሃሳብ በመጋራት ጽሁፋችንን ደመደምን።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ኀዳር 28 / 2014