የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ ጸንቶባቸው ውሳኔውን ተፈጻሚ ያላደረጉ አምስት ክለቦችን ከቀጣዩ የዝውውር መስኮት ማገዱን ከቀናት በፊት አሳውቋል። በፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ፊርማና ማህተም በወጣው ደብዳቤ መሰረት ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን ጨምሮ አራት ክለቦችን ማገዱን አሳውቋል።
በዚህም መሠረት የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ በይግረማቸው ተስፋዬ፣ ሀድያ ሆሳዕና በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ፣ ከፋ ቡና በዳግም እንዳልካቸው፣ በሙሉቀን አበበ፣ በአብይ ምንዋጋውና እንዳልካቸው ዘውዴ ፤ ቤንች ማጂ ቡና ደግሞ በሚካኤል እጅጉ በቀረበባቸው ክስ የፍትህ አካላቱ የሰጡትን ውሳኔ ባለመፈጸማቸው መታገዳቸውን የሕግ አማካሪ ጠበቃና የእግር ኳስ ስፖርተኞች ሕጋዊ ወኪል የሆኑት አቶ ብርሃኑ በጋሻው ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። በዚሁ ውዝግብ የተነሳ የሊጉ በጎ ገጽታ እንዳይጠለሽ ስጋት የፈጠረ ሲሆን ዘጠኝ ተጫዋቾች በዚሁ ችግር ልምምድ እስከማቆም መድረሳቸው ታውቋል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ዘጠኝ ተጨዋቾች የአምናው የፊርማ ክፍያ አልተከፈለንም በሚል ባለፈው ሳምንት ልምምድ ማቆማቸው ተነግሯል።
አንዳንድ የመረጃ ምንጮች እንደሚጠቁሙት እስራኤል፣ አቡበከር፣ ያሬድ፣ ሀብታሙ፣ ሙሉጌታ፣ ዳግም፣ ተስፋዬ፣ አህመድና በሀይሉ በ2013 ለክለቡ ሲፈርሙ በ50 ሺ ብር ተስማምተው የነበረ ሲሆን በወቅቱ ቃል የተገባላቸው ክፍያ ባለመፈጸሙ ልምምድ ማቆማቸው ታውቋል። ክለቡ ባለፈው አምስተኛ ሳምንት ጨዋታ በጌታነህ ከበደ ግብ ድሬዳዋ ከተማን 1ለ0 በረታበት ጨዋታ አስቀድሞ ተጫዋቾቹ ላለመጫወት ወስነው የነበረ ቢሆንም አሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸው ባደረገው የማግባባት ስራ መጫወታቸው ታውቋል። ዘጠኙ ተጫዋቾች ከ400 ሺ ብር እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ ከክለቡ ክፍያ የሚፈልጉ መሆናቸው ታውቋል።
ከተጫዋቾቹም ውጪ አሰልጣኙ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ተነግሯል። በርካታ ክለቦች የተጫ ዋቾቻቸውን ደመወዝ እየከ ፈሉ ባለመሆኑ ተጫዋቾች ችግር ውስጥ ገብተዋል፣ አሁንም ጉዳያቸው በፌዴ ሬሽኑ የፍትህ አካላት የተያዘላቸው እንዳለ ሆኖ ክለቦቹ በውላቸው መሠረት የተጫዋቾችን ደመወዝ እንዲከፍሉ የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበርም ጥሪ አቅርቧል።
በ1990 ዓ.ም. ጀምሮ መካሄድ የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንድ ክለብ ከ10 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ ማድረግ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ ክፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ክለቦች የተጫዋቾችን የወር ደመወዝ መክፈል ስለተሳናቸው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክስ ሲቀርብ ቆይቷል። በ2013 ዓ.ም. የቤትኪንግ ፕሪሚየርሊግ ውድድርከጀመረ በኋላ ጅማ አባ ጅፋር፣ አዳማ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እንዲሁም ሀዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ክፍተኛ የገንዘብ ቀውስ የገጠማቸው ክለቦች ናቸው፡፡ ክለቦቹም ጨዋታ እስከማቆም አድማ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከታችኛው ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድጉ ክለቦች፤ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች እንቅጠር በሚል የዳቦ ስም፤ ወደ ላኛው ሊግ ያሳደጓቸውን ተጫዋቾች ጥለው ሌሎችን ለማስፈረም በሚሊዮን ረብጣ ብሮችን ሲያወጡ ይስተዋላል፡፡
ይኼም ክለቦችን ለከፍተኛ ዕዳ ሲያጋልጣቸው ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ በአንጻሩ በክለቡ ወስጥ ታዳጊዎችን መያዝ፣ ለወጣቶች ዕድል መስጠትና የክለቦቻቸውን መዋቅር ማስተካከል ላይ እምብዛም በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የመፍረስ አደጋ ሲጋረጥባቸው ይስተዋላል። በሌላ በኩል አንድ አሠልጣኝ ወደ አንድ ክለብ ሲዘዋወር ተጫዋቾችን ቀድሞ ከነበረበት ክለብ ይዟቸው የሚያዞራቸው ተጫዋቾች መኖራቸው እየተለመደ የመጣ ነገር ነው፡፡
ይኼም የክለቦችን ካዝና ከማራቆት ባሻገር አሠልጣኝ ከተጫዋች ጋር የሚኖረውን የጥቅም ትስስር የሚያጎለብት እንደሆነ አስታየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡ በአውሮፓ የተለያዩ ሊጎች ላይ የሚሳተፉ ክለቦች በሚሳተፉበት ውድድር ላይ ተፎካካሪ ለመሆን ቡድኑን ምሉዕ ማድረግ ቀዳሚው ሥራ ነው፡፡
ለዚህም ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ማስፈረም የራሱ ሒደት አለው፡፡ በእግር ኳስ ገንዘብ ትልቅ አቅም ለመፍጠር ቁልፍ ጉዳይ ነው፡ ፡ በዓለም ላይ ትልልቅ ክለቦች ከእግር ኳስ በሚገኝ ገቢ አገራቸውን ሲጠቅሙ ይስተዋላል፡፡ በተለያዩ አገሮች ሊጎች የሚሳተፉ ክለቦች በውድድር ዘመን የሚያመጡት ውጤት በካዝናቸው ካላቸው ገንዘብ ጋር ገላጭ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኀዳር 27 / 2014