ኢትዮጵያ ከናዚስት ትህነግና ከሚመራው የሲዖል ሠራዊት ጋር የህልውና ጦርነት ውስጥ ከገባች አንድ ዓመት ሆናት። ናዚስት ትህነግ የሲዖል ሠራዊቱን በአፋር፣ በጎንደርና በወሎ አሰማርቶ ሳጥናኤላዊ ግፍና ዕልቂት ሲፈፅም ቆይታል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ሕዝባዊ ሠራዊቱ (ልዩ ሀይላት፣ ፋኖ፣ ሚሊሺያ) ኢትዮጵያን ወደ ሲዖል አወርዳታለሁ ብሎ የዛተውንና የሚዳክረውን የናዚስት የሲዖል ሠራዊት ወረራ እየመከቱና ትህነግን ወደ ግብዐተ መሬቱ እየወሰዱት ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ሲመጡበት የሚያቃጥል እሳት ነው።
ኢትዮጵያ በታሪክ የተከበረች፣ በበረከት የተሞላች፣ ለአሸናፊነት የተመረጠች፣ ለምስክርነት የተቀመጠች፣ ጀግና የምትወልድ፣ ወልዳ የምታሳድግ ነች። ኢትዮጵያዊነትም ክብር፣ አንድነት፣ ትዕግስት፣ አሸናፊነት፣ ዘለዓለማዊነት፣ ፅናት እና ድል ነው። ኢትዮጵያን ጠላቶች ብዙ ጊዜ ፈትነዋታል።
ይሁንና የኢትዮጵያን ስም ጠርቶ፣ ስለ ኢትዮጵያ ሰይፍ አንስቶ የተሸነፈ የለም። በኢትዮጵያ ሰይፍ እልፍ ጠላቶች ተሸልተዋል፤ ተወግተዋል። አያሌ ጠላቶች ተመክተዋል። ብዙዎች ደንግጠው ወድቀዋል፤ አፈር ሆነዋል። ላይመለሱ ትቢያ ገብተዋል። የነኳትን እየሰበረች፣ የደፈሯትን እያሳፈረች ከታሪክ ላይ ታሪክ እየጨመረች፣ ታሪኳን እያደመቀች፣ ስሟን እያገነነች የመጣች ሀገር ናት።
እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም አያሌ ጠላቶች ተነስተውበታል። የውጭ ጠላቶች የውስጥ ጠላቶችን እንደ ፈረስ ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለማሳነስ፣ ታሪኳንም ለማርከስ ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። በተለይ አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በውጭ ጠላቶች እየታገዘ፣ ከውስጥ ባንዳዎች ጋር እየተባበረ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት ከከፈተ አንድ ዓመት አስቆጥራል። በእነዚህ ጊዜያትም፣ የክፋት በትሩን አንስቶ ኢትዮጵያን አሰቃይቷል። ኢትዮጵያዊያንን በግፍ ገድሏል፤ አፈናቅሏል።
ሃብትና ንብረታቸውን ዘርፏል፤ አውድሟል። ችግር የሚያጠነክራቸው፣ ክፉ ቀን የሚያስተሳስራቸው፣ ኢትዮጵያዊያን በአንጻሩ በቁጣ ተነስተውና በአንድነት ቆመው፣ የሽብር ቡድኑን በሚገባው ቋንቋ እያናገሩት ይገኛሉ። የወገን ጦርም ወራሪውን፣ አሸባሪውንና የውጭ ጠላቶች አሽከር የሆነውን ሽብርተኛ ቡድን እየለበለበ እያቃጠለ፣ አመድ እያደረገው ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ የተነቃቃው የግንባርና የደጀኑ ሃይል፣ በአጭር ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ድል እያስመዘገበ ይገኛል። ወራሪውና ተስፋፊው ቡድን በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ማለትም በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም በአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በሁሉም ግንባሮች እየተሸነፈና ወደ ኋላ እየሸሸ ይገኛል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እየተመራ በሁሉም ግንባሮች ወደ ከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የገባው ጦር አስደናቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑንና የተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎች በወገን ጦር ነጻ መውጣታቸውን ከቀናት በፊት ይፋ አድርገዋል።
ጠላት ለበርካታ ወራት የዘረፈውን ሀብት በመጠቀም በወረራ የያዘውን አካባቢ ህዝብ በማስገደድ ያሰራውን ባለብዙ እርከን ኮንክሪት ምሽግ በተቀናጀ እቅድ፣ አመራርና ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአነስተኛ መስዋዕትነት መሰባበራቸውም ታውቃል።
በምስራቅ ግንባር በጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ባደረጉት ተጋድሎ የካሳጊታና ጭፍራን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በወገን ጦር ተይዘዋል። አሸባሪው ቡድን አይደፈርም ብሎ ሕወሓት ሲሸልልና ሲፎክር የነበረውና
የጋሸና ምሽግ በጀግኖቹ ተደምስሶ በወገን ጦር እጅ ገብቷል። ለመሆኑ የእነዚህ ስትራቴጂክ ቦታዎች በኢትዮጵያ ሃይሎች መያዝ በጦርነቱ ላይ የሚኖረው ትርጉም ምን ይሆን? ሲልም አዲስ ዘመን ከወታደራዊ አመራሮች ጋር ቆይታ አድርጓል።
አስተያየታቸውን ካጋሩን መካከል ደግሞ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ አንዱ ናቸው። ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ እንደሚገልጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከቤተ መንግስት ወንበር ላይ ተነስቶ አገሬ ከእኔ ስልጣን፣ ክብር፣ እውቀት እና ከነፍሴ በላይ ነች በሚል ወደ ግንባር ካቀኑ በኋላ የጦር አውዱ በእጅጉ ተለውጣል።
በየአቅጣጫውም የድል ዜማዎች መዘመር ጀምረዋል፡ ‹‹ጋሸና፣ ጭፋራ፣ ካሳጊታ ሌሎችም ወታደራዊ እስትራቴጂ ቦታዎች በወገን ጦር መያዝም የኢትዮጵያ ሰንደቅ በአሸናፊነት መሰረት ላይ የሚያቆም የድል መሰረት ነው›› የሚሉት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፤ ውጤቱም ቀሪ አካባቢዎችን ለመያዝና ውጊያውን በበላይነት ለማጠናቀቅ ከፍተኛና ሁለንተናዊ አቅምን እንደሚፈጥር ያስረዳሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባራ መገኘት ለተገኘው ድል ሁነኛ መሰረት ስለመሆኑ አፅእኖት የሚሰጡት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ ‹‹ክብርና ዝናውን ትቶ ከቤተ መንግስት ወጥቶ በግንባር አመራር መስጠትም እጅግ በጣም ታላቅነት ነው›› ይላሉ።
የአገርን መሪ አጠገብ አድርጎ መዋጋት ለሰራዊቱ የሚሰጠው ሁለንተናዊ የሞራል ከፍታ በቃላት መግለፅ እንደማይቻልና በተለይ ለአገር ለመስዋት ይበልጥ መነሳሳት የሚፈጥር ስለመሆኑም የሚገልፁት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ፕሬዚዳንት፤ ‹‹በጥቂት ቀናት የተመዘገቡ ድሎችም የሽብር ቡድኑን የሕወሓትን ቀን ያጨልሙታል።
አከርካሪውን ይሰብሩታል። ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለልዩ ሃይሎችና ለሚሊሻዎች ደግሞ ከፍተኛ የአሸናፊነት ሞራልን ይሰጡታል›› ነው ያሉት። የአንዳንዶቹ ቦታዎች በወገን ጦር ስር መግባት ትርጉሙ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚያስረዱት ሃምሳ አለቃው፣ በተለይም የአሸባሪ ቡድን ከፍተኛ አመራሮችም ሆኑ ጦር የሚመሩና በህግ የሚፈልጉ ግለሰቦች መውጪያ መግቢያ ቀዳዳ እንዲያጡ፣ እንደራደር የሚለውን ሃሳባቸውንም ከንቱ እንዲሆን እንደሚያደርግ ነው ያመላከቱት። ከሽብር ቡድኑ ባሻገር ሌሎችም ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች እጃቸውን እንዳያስገቡ ሁሉን ዝግ ያደርጋል ነው ያሉት። እንደ ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ገለፃ፤ በአሁን ወቅት ጀግኖች በደም ቀለም ታሪካቸውን እየፃፉ ነው። ጠላትን እየደመሰሱ ወደፊት እየገሰገሱ ነው።
የመጨረሻው የድል ቀን ተቃርቧል። የጠላት መዳፈኛ መቃብሩ ተቆፍሯል። አፈር የሚመልሱበት ኢትዮጵያዊያንም ዙሪያ ገባውን ተዘጋጅተዋል። የሚያቆማቸው ማሸነፍ ብቻ ነው። የጠላት የማምለጫ ተስፋው አልቋል። በሮች በሁሉም በኩል ዝግ ናቸው። ጠላት ዙሪያ ገባውን እሳት በሚተፋ፣ ለብልቦ
በሚያጠፋ ጦር ተወጥሮ መውጫ መግቢያው ጠፍቶበታል። ወደ ፊት እንዳይገሰገሰ፣ ወደ ኋላም እንዳይመለስ ሆኖ ተሰቅዞ ተይዟል። ወደፊት መገስገስ አልቻለም። ወደኋላ እንዳይመለስ የሚረግጠው ሁሉ ረመጥ እሳት ሆኖበታል። ይሕ እንደመሆኑም የሽፍታው ቡድን ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊትም ሆነ ህዝብ ተፋልሞ ማሸነፍ ቅዠት እንደሆነ መረዳት ይኖርበታል የሚሉት ሃምሳ አለቃው፤ አላስፈላጊ መስዋዕትነትን በመክፈል ጀሌዎቹን ከማስጨረስ ይልቅ ብረቱን ማውረድ ብቻ አንድ እና እንድ አማራጭ መሆኑን መገንዘብ እንዳለበትም ሳይገልጹ አላለፉም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ለተሰለፉ ሃይሎች እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። ሃምሳ አለቃ ብርሃኑም ጥሪውን፤ ‹‹ የጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ መንግስታቸው ያለውን የሞራል ልዕልና የሚያሳይ ነው›› ሲሉ ይገልፁታል። ጥሪው የመንግስትን ሰላም ወዳድነት ከማረጋገጥ ባሻገር ከሁሉም በላይ ከአንድ ስለአገርና ህዝብ ከሚያስብና ከሚጨነቅ መሪ የሚጠበቅና ተምሳሌታዊ ስለመሆኑም ያስገነዝባሉ።
የጥሪው አንድምታም የሽፍታው ቡድን አባላት አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከመክፈል እንዲድኑ፣ እጃቸውን በሰላም ሰጥተው ከኢትዮጵያ ቀሪው ህዝብ ጋር እንደ ትላንቱ በጋራ የሚኖሩበት እድል የሚፈጥር ስለመሆኑ የሚጠቁሙት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ከዚህ ባሻገር ጥሪው ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንደሚደመደም ግልፅ ማረጋገጫን እንደሚሰጥ አፅእኖት ይሰጡታል። በዕድሉ መጠቀም የፈለገ ሳይረፍድ እጅን መስጠት እንዳለበትና ከዚህ ምንም ምርጫ እንደሌለው ያስገነዝባሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር መገኘት በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያን ይበልጥ የማነሳሳትና በአንድነት እንዲቆሙ ከማድረግ ባሻገር ውሳኔውን ተከትሎ የተገኙ ድሎች በአለም አቀፍ ደረጃም የመሪውን የአገር ፍቅር፣ ስነልቦናና ጀግንነት በማስተጋባት ረገድ ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑን ሳይጠቁሙም አላለፉም።፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በቀጣይ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ተግባራት ሲጠቁሙም፣ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ በድል እንዲቋጭ በማድረግ ረገድ የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና አንድነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ነው አፅእኖት የሰጡት።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱም፣ መንግስት በአሁን ወቅት እስካዛሬ ከነበረው መከላከል ወጥቶ ወደ ማጥቃት መግባቱንና አስደናቂ ድሎች እየተመዘገቡ፣ አሸባሪው ሕወሓት እየተወሰደበት ባለው እርምጃ እየተሽመደመደ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። ‹‹በውጊያ ጊዜ ለግዳጅ መሳካት ጠቃሚ የሆነ ቦታ መያዝ የግድ እንደሚያስፈልግና ጠላት ጋሸናን የመሳሰሉ ቦታዎች ለመያዝ የፈለገበት ዋና ምክንያትም ወታደራዊ መሬት በመሆናቸው እንደሆነ የሚያስረዱት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ ሰሞኑን የተለቀቁት ቦታዎች እንደ ሀገር መከላከያ ትልቅ ጥቅምና አቅም የሚፈጥሩ፣ በጣም ወሳኝና ወታደራዊ ጠቃሜታቸውም የላቀ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
‹‹በተለይ የጭፍራ፤ ጋሸናና ሌሎች ስትራቴጂክ ቦታዎች መያዝ ትርጉሙ ድል ነው የሚሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ። እነዚህን ቦታዎች ማስለቀቁ ለወገን ጦር በጣም ጠቃሚ ስለመሆኑ አፅእኖት ይሰጡታል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የእነዚህን ቦታዎች ማስለቀቁ ቀሪ አካባቢዎችንም ለመያዝና ውጊያውን በበላይነት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ አቅምን ይፈጥራል። ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለልዩ ሃይሎችና ለሚሊሻዎች ይበልጥ የመዋጋት ሞራልን ይሰጣል፣ የድል ልዕልናን ያጎናጽፋል።
ለሽፍታው፣ ለአመጸኛውና ለወንበዴው የሕወሓት ቡድን በአንፃሩ፣ በተለይ ጋሸናን መልቀቁ ከፍተኛ ኪሳራ ነው። በአሁን ወቅት ጦርነቱ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነትን መቋቋም እንደማይችል በግልጽ እየታየበት ስለመሆኑ አፅእኖት የሚሰጡት ብርጋዴር ጄኔራሉ፤ በዚህ ፍጥነት እነዚህን ቦታዎች ማስለቀቅ መቻሉንም፣ ያልተጠበቀ፣ አስገራሚና የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድል ነው ሲል ይገልጹታል። ቡድኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈፀመው ግፍም ለዚህ አሳፋሪ ውርደት እንደዳረገው ያነሳሉ። ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሰጡ ለሚገኘው አመራርና ለተገኘው ድል የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ትልቅ ማዕረግና እውቅና የክብር አምስት ኮኮብ ጀነራል ማዕረግ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ›› የሚሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ ድሉ በቀላል የተገኘ እንዳልሆነና ኢትዮጵያን መታደግ የተቻለበት አመራርና ጥበብ የተስተዋለበት መሆኑን ነው የገለጹት።
የሽብር ቡድኑ አሁን ላይ ሌላው ቀርቶ ለድርድር እድል ማጣቱን የሚያስረዱት ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፤ የሽብር ቡድኑ አባላት ከሥምንት ወር በላይ ዕድሉ ነበራቸው። በጣም በተደጋጋሚ ቢለመኑም የሰላም ድርድሩን አልፈለጉትም፤ ንቀውታል። አሁን ላይ ደግሞ ለድርድር በጣም ረፍዷል ይላሉ። ከዚህ በኋላ አሸባሪው ቡድን ጊዜ እና አጋጣሚ ቢያገኙ ስራው ክፋት እንደሆነ የሚያስገነዝቡት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ ለሰላም ሲባል ትላንት ሴቶች ተንበርክከውና አልቅሰው ቢማጸኑትም አሻፈረኝ በማለት ዕድሉን መጠቀም ያልፈለገውን ቡድን ዛሬ ላይ እስከ መጨረሻው ማፅዳት አስፈላጊ ስለመሆኑም አፅዕኖት ሰጥተውታል። በቀጣይ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ተግባራት ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ እንዳመላከቱትም፣ የአገር መከላከያም በቁጥጥር ስራ ያዋላቸው ቦታዎች ይዞ መቆየት ብቻ ሳይሆን ተከታታይ የሆነና የማያቋርጥ በአየር፣ መድፍ፣ ታንክና እግረኛ እየተከታተለ ማጥፋትና ማጥቃት ይጠበቅበታል።
እግር በእግር እስከ መጨረሻው ተከታትሎም መቀሌን ይዞ ወንበዴዎቹን ማደን አለበት። ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ጠንካራ ኢኮኖሚና ጠንካራ የአገር ሰራዊት መገንባት ግድ ይላል። ከዚህ ከቀድሞ ሁሉ በተለየ ጠንካራ መከላከያ ያስፈልጋል። ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚሰነዘሩ ፉከራና ቀረርቶዎች መመከት የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው። የአገር መከላከያ ሰራዊት ሲገነባ በሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂም እጅግ የተጠናከረ፣ የረቀቀና የተገነባ መሆን አለበት።
ይህም ኢትዮጵያ ማንም ብድግ ብሎም የማይደፍራት፣ ጠንካራና የምትፈራ ሀገር ያደርጋታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሦስተኛው ቁልፍ ግንባር ተገኝተው ከሠራዊቱ ጋር በመከሩ ወቅት ወታደሩ በከፍተኛ ሞራል ላይ ነው”ጠላት ፈርሷል፤ ተበትኗል፣” አሁን ጠላት ያለው አማራጭ የሰረቀውን አስረክቦ እጁን መስጠት ነው። ምርኮኞችን ተንከባክቦ መያዝ የጀግና ባህላችን ነው›› ማለታቸው ይታወሳል::
ታምራት ተስፋዬ እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ኀዳር 27 / 2014