ልጆች እንዴት ናችሁ? ትምህርት ጥሩ ነው? መቼም ጥሩ ነው እንደምትሉ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም እናንተ ጎበዝ አንባቢ እንደሆናችሁ አምዳችንን ስለምትከታተሉ ብቻ እናውቃለን፡፡ ማንበብ የማይወድ ሰው መቼም ጎበዝ አይሆንም፡፡ ስለዚህም ዛሬ የተማራችሁትን ዛሬ በማንበብ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን አለባችሁ፡፡ ልጆች ለዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? በጽሑፍ ለእናንተ ከመናገራችን በፊት ጥያቄ በመጠየቅ እንጀምረው …
ኢትዮጵያን ትወዷታላችሁ? መቼም መልሳችሁ ‹‹አዎ! በጣም እንወዳታለን!›› እንደሚሆን አንጠራ ጠርም፡፡ መልካም! እኛም ኢትዮጵያን እንደምትወዷት እርግጠኞች ነን፡፡ ይህን ጥያቄ የጠየቅናችሁ ዛሬ ስለ አገር ፍቅር፣ አገርን ስለመውደድ ልንነግራችሁ ስለፈለግን ነው።
የአገር ፍቅር ማለት አንድ ሰው ለአገሩ ያለው ክብርና ክብሩን የሚገልጽበት ተግባር ነው፡፡ ሰው እና አገር እስካሉ ድረስ የአገር ፍቅርም ይኖራል፡፡ የአገር ፍቅር በልብ ውስጥ ታትሞ የሚኖር ህያው ስሜት ነው፡፡ የአገር ፍቅር የተለየ ስሜት ያለውና በቃላት የማይገለጽ ነው፡፡ ሰዎች ሕይወታቸውን ጭምር አሳልፈው የሚሰጡበት ታላቅ ሃሳብ ነው፡፡ አገርን መውደድ ሁሉም ሊተገብረው የሚገባ ኃላፊነትም ነው፡፡
የአገር ፍቅር ሰው ለአገሩ ያለው ክብርና ክብሩን የሚገልጽበት ተግባር ነው ሲባል ምን ማለት እንደሆነታውቃላችሁ? የአገር ፍቅር ሲባል በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባርም መግለፅ አለበት ለማለት ተፈልጎ ነው፡፡ ‹‹አገሬን እወዳለሁ፣ የአገር ፍቅር አለኝ›› እያሉ መናገር ብቻ የአገር ፍቅርን አይገልፅም፡፡ ስለዚህ ‹‹አገሬን እወዳለሁ›› የሚል ሰው ለአገሩ ያለውን ፍቅርና አክብሮት በተግባር ማሳየት አለበት፡፡
የአገር ፍቅር በብዙ መልክ ሊገለፅ ይችላል፡፡ አገርን ከውጭ ወራሪ ለመከላከል የሚደረግ ተጋድሎና አርበኝነት የአገር ፍቅር ከሚገለፅባቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡ አገር በጠላት ስትወረር ‹‹አገሬን አላስደፍርም›› ብሎ ጠላትን ለማሸነፍ መዋጋት የአገር ፍቅርን ያሳያል፡፡ አገሩን የሚወድ ሰው ለአገሩ ክብር ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ በእርሱ መስዋዕትነት አገሩን ያስከብራል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በውጭ ጠላት ስትወረር ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በወራሪ ላለ ማስደፈርና ለቀጣዩ ትውልድ ነፃ አገርን ለማስረከብ ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው በመስጠት አገር ወዳድነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
ሌላው የአገር ፍቅር መገለጫ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ጠንክሮ መሥራትና ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ነው። የሕክምና ቃል ኪዳናቸውን ጠብቀው ሕመምተኞችን የሚያክሙ ሐኪሞች፣ ተማሪዎችን በመልካም ስነ ምግባር አንፀው ትምህርታቸውን በሚገባ የሚያስተምሩ መምህራን፣ እርሻቸውን ጠንክረው የሚያርሱ ገበሬዎች፣ ትምህርታቸውን በትጋት የሚከታተሉ ተማሪዎች ወዘተ
አገራቸውን የሚወዱ ናቸው፡፡ ስለዚህም እናንተም ትምህርታችሁን ጠንክራችሁ የምትማሩ፣ ወላጆቻችሁን፣ አስተማሪዎቻችሁንና ታላላቆቻችሁን የምታከብሩና ሰውን የምትወዱ ከሆነ አገራችሁን ትወዳላችሁ ማለት ነው፡፡
ትምህርቱን በስነ ስርዓት የማይከታተል፣ አስተ ማሪዎቹንና ወላጆቹን የማያከብር፣ በትምህርቱ ዝቅተኛ ውጤት የሚያስመዘግብ ተማሪ አገሩን የማይወድ ልጅ ነው፡፡ እናም ልጆች አገርን መውደድ ሰውን ከመውደድ ይጀምራል፡፡ አገር ማለት ተራራው፣ ሸለቆው፣ ዛፉ፣ ሕንፃው፣ መንገዱ … ብቻ አይደለም፡፡ አገር ሲባል ሰውንም ያካትታል፡፡ ለዚህ ነው ‹‹አገር ማለት ሰው ነው›› የሚባለው፡፡
ሰው ከሌለ አገር ብቻውን ባዶው መሬት ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህም አገር የምትከበረውና የምት ወደደው በልጆቿ እንደሆነ ማወቅ አለባችሁ። ሰውን ሳይወዱ አገር መውደድ አይቻልም፡፡ አገሩን የሚወድ ሰው፣ ሰውን ይወዳል፤ያከብራል፡፡ ሰውን ሳይወድና ሳያከብር ‹‹አገሬን እወዳለሁ›› የሚል ሰው አገሩን አይ ወድም፡፡
ታሪክን ማወቅም አገርን መውደድ ነው፡፡ አገራችንን ስናውቃት የበለጠ እንወዳታለን፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ብዙ የሚያኮሩና የሚያስደስቱ ታሪኮችና ባህሎች ባለቤት ናት፡፡ እነዚህን ታሪኮች ማወቅ የበለጠ እንድንወዳት፣ እንድናከብራትና እንድንጠብቃት ያደርገናል፡፡ መጻሕ ፍትን ማንበብ፣ ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት፣ የታላላቅ ሰዎችን ንግግሮች ማዳመጥ እንዲሁም በስነ ጽሑፍ፣ በኪነ
ጥበብና በሌሎች መስኮች የሚገለጡ ታሪኮችን ተከታትሎ ዕውቀት መቅሰም ተገቢ ነው፡፡
ልጆች እናንተም አገራቸውን በጠላት ላለማስደፈር ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ታሪክ መጽሐፍትን በማንበብና ታላላቅ ሰዎችንና መምህራንን በመጠየቅ የእነዚህን አገር ወዳድ ጀግኖች ታሪክ ማወቅ ይኖርባችኋል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬም ነገም የሁላችንንም ፍቅርና አክብሮት ትፈልጋለች፡፡ ሐኪሞች የህክምና ስነ ምግባራቸውን አክብረው የታመሙ ሰዎችን መንከባከብና ማከም አለ ባቸው፡፡ መምህራንም ተማሪዎቻቸውን በመልካም ስነ ምግባር አንጸው ማስተማር ይገባቸዋል፡፡ ተማሪዎች ደግሞ ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተልና ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌሎች የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ መሐንዲሶች፣ ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች፣ ጋዜጠኞች … ሕግንና የሙያ ስነ ምግባራቸውን አክብረው ሥራቸውን መከወን አለባቸው፡፡ እንዲህ ካደረጉ አገራቸውን ይወዳሉ ማለት ነው፤አገራቸውም በእነርሱ ትኮራለች፡፡ ይህን የማያደርጉ ሰዎች ግን አገራቸውን አይወዱም፡፡
ስለዚህ ልጆች፣ አገራችሁን ውደዱ! አገራችሁን እንደምትወዱ ደግሞ በተግባር አሳዩ። ወላጆቻችሁን፣ አስተማሪዎቻችሁንና ታላላቆቻችሁን አክብሩ፤ ትም ህርታችሁን በርትታችሁ ተማሩ፤ የአገራችሁን ታሪክና ባህል እወቁ! በቀጣይ ሳምንት በሌላ ጽሑፍ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ! መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 26/2014