ኢትዮጵያን በዘር ልጓም አስረው ላለፉት 30 ዓመታት ሲገዙ፣ ሲዘርፉና የጥላቻ መርዝ ሲረጩ የቆዩት ወያኔዎች ነበሩ። አገራችንን ለመውረርና ለመዝረፍ ለዘመናት ካሰፈሰፉት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አራማጆች ተለይተው የማይታዩት እነዚህ የጣት ቁስሎች ዘመናችንን ጨለማ፣ ሕይወታችንን መከራ የበዛበት፣ እጣፈንታችን ከትግልና ከድህነት ጋር የተቆራኘ እንዲሆን የጥላቻ ልጋጋቸውን ሳይታክቱ አላከውብናል።
ኢትዮጵያን ከውጭ ሊያጠቋት የሚፈልጉ አገራት ሁሌም ቢሆን ለዘመናት ባንዳነትን ውርሳቸው አድርገው የእናት አገራችንን ጡት በመንከስ በሚታወቁት አሸባሪው የወያኔ ቡድን አባላት መሪነትና ጥላቻ በመመራት ነው ዳር ድንበራችንን የሚደፍሩት። ዛሬም ድረስ የቆሰለ ጣታችንን አንቆርጥም በሚል ተሸክመናቸው በመቆየታችን መሰል ጥቃቶችንና የሞራል ስብራቶችን እያደረሱብን ይገኛሉ።
እኛ ኢትዮጵያውያን የብዙ ሺ ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክና የሉዓላዊነት፣ የአንድነትና ስልጣኔ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን ። ከሁሉም በላይ ድብልቅ ማንነት ያላቸው “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን” ይቀይር ዘንድ አይቻለውም እስከሚባል በጉልህ የምንታወቅ ነን።
ባህላችን የአኗኗር ዘይቤያችንን የሚያሳይ፤ ማህበራዊ ትስስራችን የፍቅርና የአብሮነት መገለጫችን የሆነ፣ መተሳሰብና መተባበራችን በተግባር የሚታይ የመቻቻል ምሳሌ የሆንን ብዙ ዘመናትን እንቅፋቶቻችንን እየተሻገርን እዚህ ላይ ደርሰናል ። በእርግጥ በየመሃሉ እሴቶቻችንን የሚንዱ፣ ህልውናችንን የሚፈታተኑ፣ አብሮነታችን የሚተናነቃቸው የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቻችን ጉዳት አላደረሱብንም ማለት አይቻልም። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ አሸባሪው ትህነግ ቀዳሚው ነው።
የአንድነት እሴታችን ጠላት
በኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያውያን ላይ ግልፅ የህልውና ጦርነት ያወጀው ትህነግ ለዘመናት የአገራችንን ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እሴቶችን በመናድ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ቀርፆ ሰርቷል። ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመንም አንድ ከሚያደርጉን ይልቅ ሽብልቅ ሆነው የሚሰነጥቁን የማንነት መጣረዞችን ሲያጦዝና መከፋፈልን ሲፈጥር፣ ጥላቻን እንደ እንክርዳድ ሲዘራ ከርሟል። ሞራል፣ ባህል፣ ሽምግልና፣ እርቅ፣ መተባበር፣ አብሮነት፣ አንድነት የሚባሉትን የአገር ካስማና ዋልታዎች በሙሉ በዝርፊያ፣ ጥላቻ፣ መከፋፈል፣ መገፋፋት፣ ራስ ወዳድነት በድንበር ልዩነት ፣ በኢትዮጵያዊነት ጥላቻ ተክቶ ለተፈፃሚነቱ የቻለውን ያህል እውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ መድቦ ሰርቷል ። ይሄ ፍፁም ከኢትዮጵያውያን ማንነት ጋር የሚጋጭ ለሽብርተኛው ቡድን እኩይ አላማ ግን የተመቸ ነበር።
የአገር ዋርካ የሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ለፖለቲካው አላማ በማዋል የማህበረሰቡን ሞራል ገድሏል። የጀግንነትና ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ በዓላትን እንዳይታወሱና እንዳይዘከሩ ተግቶ ሲሰራ ቆይቷል። በአፉ ብሄር ብሄረሰብ እያለ የሚጠራቸው በተግባር ግን በማንነታቸው እንዳይኮሩ፣ አንገታቸውን ደፍተው ሌረማታቸውን እየበዘበዘ ሁለተኛ ዜጋ ሆነው ቆይተዋል። በጥቅሉ ታሪክ፣ ባህል ማንነት እንዲሁም ተፈጥሯዊ ሃብቶችን ከማውደም ባለፈ የህዝቦችን ለዘመናት የዘለቀ በጋራ አብሮ የመኖር እሴት አደጋ ውስጥ ጥሎ ቆይቷል።
ኢትዮጵያውያን ግን ይሄን የውስጥ ጠላት (የእናት ጡት ነካሽ) ዳር ቆመው አላዩትም። ይልቁኑ የጠመንጃ አፈሙዝ ደቅኖባቸው እንኳን የቀደመው አንድነትን፣ መተባበርን ፣ በጋራ የአገርን ህልውና የመጠበቅ እሴትን ፣ ታሪክን ለቀጣይ ትውልድ የማውረስ አደራን ተገን በማድረግ ታግለው ዳግመኛ የኢትዮጵያ ቁስል እንዳይሆን ወደ ዳር ገፍተውታል ። አሁንም በተለመደው ኢትዮጵያዊ መንፈስ ዳግም ጥላቻው አገርሽቶበት “ከአፈርኩ አይመልሰኝ” የሚል ትንቅንቅ ውስጥ የገባውን ትህነግ በሌላው ዓለም በሌለ ጥንካሬና ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን እየመከቱት ይገኛሉ ። ለመሆኑ አገር የማዳን ኢትዮጵያዊ ጥበብ ስንል ምን ማለታችን ይሆን ? ቀጣዩ የታሪክ መረጃ እውነቱን ይገልጥልናል።
የአባቶቻችን የክተት ጥሪ
አብሮ ለመኖር ብቻ ሳይሆን በጋራ ዳር ድንበርን ለመጠበቅ የሚያስችል ባህላዊ እሴቶች ኢትዮጵያውያን አሏቸው ። ይሄ እሴት ደግሞ በኢትዮጵያ እንጂ በሌላው የዓለም ክፍል የሌለ ልዩ መገለጫችን ነው። ታሪክም የሚነግረን ይሄንኑ ነው ። በተለያየ ጊዜ የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላት በመጣ ቁጥር በጠንካራ ማንነታችንና ብልሃታችን ታግዘን ጠላትን ልክ አስገብተናል ። ለዚህ ደግሞ ከፋሽስት ጣሊያን የላቀ ማሳያ አይኖርም ። እኛ ኢትዮጵያውያን በጦርና ጋሻ ታግዘው ዘመናዊ ጦርና ላቅ ያለ የኢኮኖሚ አቅም ያለውን ፋሽስትን ድል አድርገናል። ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት ከታሪክ ቅምሻ በጥቂቱ እንቋደስ።
መላው ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩና የውስጥ ባንዳም ሆነ የውጭ ጠላት አገራቸውን ሊያጠቃ ቢሞክር ቀፎው እንደተነካ ንብ ተምመው ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስከብሩ ማድረግ ችለዋል ። ስለዚህ ጉዳይ ስናነሳ የንጉሱን የሚከተለውን ንግግር እናስታውሳለን።
«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ ፤ በምቀኝነት፣ እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያ አገራችንን ለሌላ ባእድ አትሰጧትም ፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም ። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ድንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ሁላችሁም ሄዳችሁ በአንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ፤ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ» የሚል ታሪካዊ መልእክት ከማስተላለፋቸውም ባሻገር፣ በዚህ መንገድ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ በመጠበቅ “አድዋ” ላይ ጣሊያንን ድል አድርገው ዓለም ሲዘክረው የሚኖረው ታሪክ ሰርተው አልፈዋል።
ይሄ ኢትዮጵያዊ ቤት ብቻ የሚገኝ “የሞራል፣ የጀግንነት፣ የአንድነትና ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ” እሴትና ባህላዊ ማንነት መሆኑን መታዘብ ይቻላል። የአገራችን ህዝቦች ከሊቅ እስከ ደቂቅ በህልውናው ላይ የተጋረጠ አደጋ ሲመጣ “ቀፎው እንደተነካ” ንብ ተምሞ ክብሩንና ዳር ድንበሩን ያስጠብቃል። አቅም ያለው ጦርና ጋሻውን፣ መውዜርና ጎራዴውን ይዞ ጠላት ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሲዋደቅ ገሚሱ ደግሞ ስንቅና ትጥቅ ተሸክሞ በማቀበል ያገለግላል። እናቶችና አባቶች ወጣቱን የጀግንነትና የአገር ህልውና ምንነትን ከልምዳቸው በማካፈል የሞራል ስንቅ በማስታጠቅ እንዲሁም የዘማች ቤተሰቦችን ህፃናትና ታዳጊዎችን በመንከባከብ ሌላ አስገራሚ ገድል ይፈፅማሉ። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ ድል ይሆናል። አዝማሪውና የጥበብ ባለሙያው ኢትዮጵያዊ ማንነትና ፍፁም ሞራል የሚገነቡ ፣ ጀግኖችን እያስታወሱ ዳግም ጀግና የሚያደርጉ ዜማዎችንና ቅኔዎችን እየተቀኘ ወጣቱ የጠላትን ግንባር እንዲነድልና ዳር ድንበሩን እንዲያስከብር የራሱን ድርሻ ይወጣል።
ዳግም ክተት ታሪክ ሲደግም
“በታሪክ የምናውቃቸው አባቶቻቸው በአስተዳደርና በርእዮተ ዓለም ይለያያሉ፤ ለመብት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት በነበራቸው አመለካከት ይለያያሉ። ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት ባላቸው ቦታ ግን ልዩነት አልነበራቸውም። በቋንቋ፣ በብሔርና በጎሳ ብዝኃነት ቢኖራቸውም የአልደፈርም-ባይ ቆራጥነታቸው አንድ ያደርጋቸዋል ። የግል ፍላጎታቸው የቱንም ያህል የተራራቀ ቢሆን ፣ የጋራ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነታቸው በላይ ይቀመጣል” ይሄን ንግግር ያሰሙት አፄ ምኒልክ ከፋሽስት ጋር ግብግብ ሲገጥሙ፣ አፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጋር ሲዋደቁ፣ አሊያም የውጭ ወራሪ ከዘመናት በፊት ኢትዮጵያን ሲወሩ አንደኛው ንጉስ የተናገሩት አይደለም።
ንግግሩን ያደረጉት በቀደመው የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ጀግንነት፣ ዳር ድንበርንና ሉአላዊነትን ማስከበር ላይ ልዩነት የሌላቸውና ዛሬ ከባንዳው ትህነግ (ወያኔ) የገጠመንን የህልውና ትግል ፊት መስመር (ግንባር) ላይ ሆነው እየመሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ናቸው። በዚህ ንግግራቸው ላይ ኢትዮጵያውያን ታሪክ እራሱን ይደግም ዘንድ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣውን ጠላት ለመደምሰስ “በባህሉ መሰረት” አገር አደጋ ላይ ሲወድቅ እንደሚደረገው ሁሉ “የቻለ በግንባር እንዲዋደቅ፣ የቻለ ስንቅ እንዲያዘጋጅ፣ ከኋላ ደጀን እንዲሆን፣ የሰራዊቱን ሞራል የሚያነቃቁ ሁነቶች ላይ እንዲያተኩር፣ ከሁሉም በላይ ግን ቀዬውን እንዲጠብቅ” በማለት ክተት አውጀዋል።
ኢትዮጵያውያን ጊዜ ሄዶ ጊዜ ሲመጣ ወግ ባህላቸውን የማይዘነጉ መሪያቸውን የሚያከብሩና የአገር ምንነትን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው። ለዚህ ነው በማንኛውም ጊዜ ለሚመጣ የአገር አድን ጥሪ በተጠንቀቅ የሚቆሙት። አርሶ አደሩ እርሻውን ጥሎ፣ ነጋዴው ሱቁን ዘግቶ፣ እናቶች ማዕድቤታቸውን ለጦሩ ፍላጎት አዘጋጅተው ሁሉም “ነጋሪቱ በተጎሰመ” ቅፅበት በተጠንቀቅ ይቆማሉ። ይሄ ባህላችን ነው። ይሄ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቤት ሥራ ነው።
ለዚህ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የክተት አዋጅ ተከትሎ ህዝቡ ደጀን ለመሆን ጨርቄን ማቄን ሳይል መሪውን የተከተለው። ባለሃብቱ አገር ከሌለ የእኔ ሃብት ማፍራት ትርጉም አልባ ነው በማለቱ፣ ታዋቂውና ተፅዕኖ ፈጣሪው “የኔ ዝናና ክብር የአገር ህልውና ነው” የሚል መረዳት ስላዳበረ፣ መምህሩ፣ ወጣቱ ሴት አዋቂው እውቀቱን ጉልበቱንና ጥሪቱን በዚህ ትግል ላይ እያዋለው ያለው ። ይህን ዓይነት የሞራል ልእልና፣ ባህልና ጠንካራ ማንነት ያለው ህዝብ ያላቸው ጥቂት አገራቶች ናቸው። ከጥቂቶቹ ደግሞ ቀዳሚዋ ጥንታዊ መሰረትና አገረ መንግሥት ያላት ኢትዮጵያ ነች።
እንደ ማጠቃለል
ህዝቡ ብቻ ሳይሆን በየግዛቱ ያሉ አመራሮች የክተት አዋጁን ተከትሎ ደጀንነታቸውን አሳይተዋል። ህዝባቸውን አንቅተዋል። አንድ ልብ፣ ሃሳብና ጉልበት እንዲሆን አሰልፈዋል። ይህን መሰል ጠንካራ የአመራር ስብእናን ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት ገንብታለች። ይሄ የእኛ ብቻ ጥበብ ነው። ሃሳባችንን ለማገባደድ እንዲረዳን አሁንም ወደ ታሪክ ድርሳናት እንመለስና የሚከተለውን ጉዳይ እናስታውስ።
አፄ ሚኒልክ የአድዋ ጦርነትን ለማካሄድ “በጥር ጦርነት አለብኝ ወረኢሉ ከተህ ጠብቀኝ” ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ ጦሩም ቀጠሮውን ጠብቆ ወረኢሉ ሲከት ንጉስ ሚካኤል ጦሩን መንገድ በመምራት፣ የከተተውን ሠራዊት እግር በማጠብና ቀለቡን አዘጋጅተው ሠራዊቱን በማስተናገድ ትልቁን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡ ዘማቹ ሠራዊት ወኔ እንዳይሸሸው ሞራል ለመገንባት የተገኙትን የጥበብ ሰዎች፣ ጦሩን በፀሎት ለማገዝ የተሳተፉትን ካህናት አባቶች በማስተናገድ በኩልም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን የነገስታት ዜና መዋዕል አትቶታል። የጣሊያን በአድዋ ዘመቻው ላይ ከንጉሰ ነገስቱ ከአፄ ምኒልክ ቀጥሎ በቁጥር በርካታ ቁጥር ያለው ጦር በማሰለፍ ውጊያው በድል እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በአካል በመገኘት በሦስት ግንባር ተዋግተዋል፡፡ ለዚህም በወቅቱ “ማን በነገረው ለጣሊያን ደርሶ፣ ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ፤” ተብሎ የተገጠመላቸው ናቸው፡፡ ዛሬም የትህነግን ሴራ ለማክሸፍ በየጦር ግንባሩ የሚዋደቁና ህዝባቸውን አስተባብረው እራሳቸውን ለመስዋእትነት በማቅረብ “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን” የሚጠብቁ አያሌ ንጉስ ሚካኤሎች ፈጥረናል!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 26/2014