ሕወሓት ወደ አማራ ክልል ከመግባቱ ቀደም ብለው ነው ዘመቻውን በድጋፍ የተቀላቀሉት፡፡ መከላከያ ሲገባ ደግሞ የበለጠ ግንባር ላይ ሆነው ማገዙን ተያያዙት፡፡ በተለያየ ቦታ ላይ ሲወጣም ቢሆን አወዳድሞ በመሄዱ የአካባቢው ሕዝብ እንዳይጎዳ ብዙ ድጋፎችን አድርገዋል፡፡ በተለይ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ብዙ ችግር መፍታት የቻሉ ናቸው፡፡ መከላከያን የሚቀላቀሉ ሰልጣኞችን ወደ ግንባር በመውሰድም የድርሻቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ አሁንም በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
በማህበረሰቡ የሚሰበሰቡ አልባሳትና ምግቦችንም በቻሉት ልክ ጭነው ግንባር ድረስ በማድረስ እያገለገሉ ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆንም አግዘዋል፡፡ በተለይ አሁን ድል በተደረገው በጋሸና ግንባር የእርሳቸው ሚና ከመጀመሪያው እስካሁን ድረስ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ይህና መሰል አገራዊ አገልግሎቶችን እንዴት ማድረግ ጀመሩ፤ ምን አይነትስ ልምድ ቢኖራቸው ነውና መሰል ነገሮችን በማንሳት የሕይወት ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩን ጠየቅናቸው፡፡ እርሳቸው ግን «አገሬ አደረገችልኝ እንጂ እኔ ምን አድርጌላት ተሞክሮ ይኖረኛል ብላችሁ ጠየቃችሁኝ» ሲሉ ነበር የመለሱልን፡፡ እኛ ግን አቶ ሰፊው ኃይሌን ከሠሩት ተግባር አንጻር ብዙ ለሌሎች አርያነት የሚሆን ልምድ ስላላቸው ትማሩበት ዘንድ ለዛሬ «የሕይወት ገጽታ» አምድ እንግዳችን እንዲሆኑ ጋብዘናችኋል፡፡
ልጅነት
አቶ ሰፊው በቅጽል ስማቸው ማሙሽ ትውልዳቸው በአማራ ክልል መቄት ወረዳ ገረገራ በምትባል ቦታ ውስጥ ነው፡፡ በእናታቸው ጥሩ እንክብካቤ የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል፡፡ ለቤተሰቡ የበኩርና ለእናት ብቸኛ ልጅ ሲሆኑ፤ ከአባታቸው ጋር ብዙ ቀረቤታ አልነበራቸውም። በዚህም የእናታቸው ልጅ ሆነው አድገዋል፡፡ የእናት ልጅነታቸው የእናትን ባህሪና ሥራ እንዲለምዱና እንዲኖሩበት አድርጓቸዋል፡፡ እናታቸው ለእርሳቸው ሕይወት መለወጥና የኑሮ መሻሻል መሪያቸው ስለነበሩም የልጅነት ሕልማቸው በእናታቸው ሥራ ላይ ማለትም ንግድ ላይ እንዲያርፍ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የዛሬ አቅጣጫ ቀያሻቸው እናታቸው እንደሆኑ ያጫወቱን ባለታሪካችን፤ ብዙ መሥራት፤ አልችለውም አለማለትና ወደፊት መጓዝንም በሕይወት የተማሩት ከእርሳቸው እንደነበርም ያስረዳሉ፡፡ ገና ልጅ እያሉ የሱቅ ሥራውን ቀጥ አድርገው የያዙት እርሳቸው እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡
እንግዳችን ሰፊው የሚል ስምን ከእናታቸው ቢቸራቸውም ስሙን ብዙም አይወዱትም፡፡ ከዚያ ይልቅ የአካባቢው ሰውና ራሳቸው እናታቸው ዘወትር የሚጠሩትን ማሙሽ የሚለውን ቅጽል ስም ነው የሚወዱት፡፡ ስለዚህም ሁሉም ሰው ማሙሽ ቢላቸው ይመርጣሉ፡፡ ብዙዎች የሚያውቋቸውም በዚህ ስማቸው ነው፡፡ በባህሪያቸው ዝምተኛ ግን ታዛዥ ናቸው፡፡ የጀመሩትን መጨረስ የሚወዱ አይነት ልጅ እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡ በተለይም ነገሮችን በሰከነ መንገድ ማየት ላይ የተለየ ችሎታ እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡
ፈጠራ የሚመቻቸው፤ አዲስ ነገርን የሚመርጡና ተደጋግሞ በሚደረግ ነገር የሚሰለቹም ናቸው፡፡ ከዚያ ባሻገር እኔ ከተሻልኩ ከእኔ የደከሙትን ማገዝና ካሉበት ችግር ማውጣት አለብኝ የሚል አቋምም አላቸው፡፡ ዛሬም የሚያደርጉት ይህንኑ ነው፡፡ ገንዘባቸውን ለመልካም ነገር ማዋልም አላማቸው ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ እድሜም በረከትም እንደሰጣቸውና በትንሹ እንዳበዛቸው ያስባሉ። መልካም ህልም ነገሮችን ያስተካክላል፤ መንገድን ቀና ያደርጋል፤ እድገትን ያፋጥናል የሚል እምነትም ያላቸው ለዚህ ነው፡፡
እንግዳችን ቤተሰባቸውን በማገዙ ዙሪያም ልጅነት ጭምር የማያግዳቸው ናቸው፡፡ የማይሰሩት ሥራ አልነበረም፡፡ በተለይም ሁለት ወንድ ልጆች ቤቱ ውስጥ በመኖራቸው የሴት ሥራ ተብሎ የሚታሰበውን እናት ብቻ እንዲሰሩ ይገደዳሉ፡፡ እናም ሆዳቸው የማይችለው ባለታሪካችን የእናታቸውን ጫና ለመቀነስ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ከእነዚህ መካከል ምግብ መሥራትና ቡና ማፍላት የመጀመሪያውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ እንጀራ መጋገርም ቢሆን ይሞክሩ ነበር፡፡ እንዲያውም አንድ ቀን መሶቡ ባዶ ሲሆንባቸው እናታቸው ከድካም ወደ ድካም እንዳይገቡ በማሰብ ምጣድ አስምተው ሲጋግሩ እንደዋሉ አይረሱትም፡፡ ይሁን እንጂ ሊጡን ጨረሱት እንጂ በጥራት ያወጡት እንጀራ ሦስት ብቻ ነበር፡፡ ብዙው ሊጥ የተነኳኮተ እንጀራ ነው የወጣው፡፡ ስለዚህም በዚያ እንዳይናደዱባቸው ብለው እንጀራውን ለከብቶች እንደሰጡት ያስታውሳሉ፡፡ እናት ሲመጡ ግን የጠበቁትን ነገር አልነበረም የተናገሯቸው፡፡ እንባቸው ቀድሞ ሀሳባቸው ምን ያህል እንደነበር ሲመለከቱ አቅፈው ሳሙዋቸው፡፡ በሥራቸው ተገርመውም አመሰገኗቸው። መረቋቸውም፡፡ ይህ ያስደሰታቸው አቶ ሰፊውም ከዚያን ቀን በኋላ ትቆጣኛለች በሚል የማያደርጉት ነገር እንዳልነበረ አጫውተውናል፡፡
ትምህርት
ከትምህርት ጋር የተተዋወቁት በቄስ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ፊደላትን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ሆነውበታል፡፡ ከዚያ ዘመናዊ ትምህርትን በዚያው በትውልድ ቀያቸው ገረገራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጀምረዋል፡፡ እስከ ስምንተኛ ክፍልም ተከታትለውበታል፡፡ ቀጣዩ ክፍልም ቢሆን በዚያው ነው የሆነው፡፡ በእርግጥ እርሳቸው ስምንትን እስኪያጠናቅቁ ድረስ አልተጀመረም፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሲዛወሩ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚሄዱ እያሰቡ ሳለ እድል ቀናቸውና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከፈተ፡፡ በዚህም በገረገራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ አስረኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ሆነዋል፡፡
እንግዳችን በትምህርታቸው ጎበዝና ውጤታማ ናቸው፡፡ ሆኖም የ10ኛ ክፍል ውጤት ግን አልቀናቸውም። የጠበቁትን ያህል አልሆነላቸውምም፡፡ ስለዚህም ፕሪፓራቶሪን ለመቀላቀል አላስቻላቸውም፡፡ እናም ትምህርቱን ትተው ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቀሉ።
በእርግጥ ይህንን ማድረግ አልፈለጉም ነበር፡፡ መማራቸውንም መቀጠል ያስባሉ፡፡ ነገር ግን የንግዱ ሁኔታ በአንድ ቦታ ተወስነው የሚያደርጉት ስላልነበረ ተመቻችተው ለመማማር አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ሥራቸው ሹፍርናውን እያደረጉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ መነገድ ነው፡፡ ስለዚህም ሳይወዱ በግዳቸው ሁለት ነገሮችን በውስጣቸው እያሰላሰሉ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡
የመጀመሪያው ባላቋርጥ ኖሮ የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ከንግዱ ውጤታማነት በኋላ መማር እችላለሁና እንኳንም አደረኩት የሚል ነው፡፡ እናም ሁለቱም ልባቸው ውስጥ ስለነበሩና ቁጭታቸውን ስላፋፋሙት የዛን ጊዜ መማርና መቀጠል ባይችሉም አሁን ግን መማር እንዳለባቸው እንዲወስኑ አድርጓቸዋል፡፡ የመማር ፍላጎታቸውንም አነሳስቶታል፡፡ በዚህም አሁን አገር ሲረጋጋ ብዙ ነገሮች በቅርባቸው ስለሚሆኑላቸው መማር የውዴታ ግዴታቸው እንደሆነ እንዲቆርጡ ሆነዋል፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ መማር ራስን ብቻ ሳይሆን አገርንም እንደሚለውጥ ያምናሉና ነው፡፡
ወሰን አልባው ሥራ
እንግዳችን መጀመሪያ ከሥራ ጋር የተዋወቁት በቤተሰብ ሥር ሆነው የሱቅ ውስጥ ንግድን በጀመሩበት ወቅት ነው፡፡ ከዚያ ከአስረኛ ክፍል በኋላ ውጤት ሳይመጣላቸው ሲቀር ቀጥታ ራሳቸውን ወደ መምራቱና በራሳቸው ወደ መሥራቱ ገቡ፡፡ የመጀመሪያ ሥራቸውንም ያደረጉት ሥራ ሳይንቁና በአንድ ሥራ ላይ ሳይወሰኑ የሰሩት ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች በወቅቱ አካባቢው ላይ የሌሉ ናቸው፡፡ አዳዲስ ፈጠራም የሚታከልባቸውና እርሳቸውን የሚያስደስቷቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡
የፈጠራ ሥራዎችን ማከናወን ምርጫቸው የሆነው ባለታሪካችን፤ ሰው የሚሠራው ሥራና ተመሳሳይነት ያለው ሥራ ምንም አያስደስታቸውም፡፡ ስለዚህም ፈጥረውም ቢሆን አዲስ የሚሉትን ሥራ መርጠው ያከናውናሉ፡፡ ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ ከሱቅ ንግዱ በኋላ የተሰማሩበት ሥራ ጆተኒ ማጫወትና ብስክሌት ማከራየትና መጠገን ነበር፡፡ ተግባሩን ሲከውኑ ደግሞ ፈተናዎችንና መሰናክሎችን በመፍታት ነው፡፡ ለአብነት ጆተኒ ሲያጫውቱ በአካባቢያቸው መብራት አልነበረም። እናም በፋኖስ ጭምር እስከምሽት ድረስ ይሠራሉ፡፡
ጆተኒው ላይ መሥራት ሲሰለቻቸውና ሌሎች ሲጀምሩት ደግሞ ሥራቸውን ወደ ሞተር ሳይክል ማለማመድና ማከራየቱ አዞሩት፡፡ በሥራው ብዙም ሳይቆዩ ደግሞ ሥራውን ከፍ አድርገው ባጃጅ በመግዛት መሥራቱን ተያያዙት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአማራ ቁጠባና ብድር ተቋም (አብቁተ) ተበድረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በራሳቸው የሚተማመኑና በሚሠሩት ሥራ ልግም የማያውቁ በመሆናቸው ባጃጁን በገዙ በአራተኛ ወሩ እዳቸውን መልሰዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም መበደራቸውን አላቆሙም፡፡ ምክንያቱም ከአንድ ሁለት ይሻላል በሚል ሁለተኛ ባጃጅ ገዝተው ለመሥራት ብድሩ ያስፈልጋቸዋል። አድርገውትም ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡
በሥራቸው ጠንካራ የሆኑት እንግዳችን፤ ሁለተኛ ባጃጃቸውን የገዙበትንም ቢሆን ቀን ከሌት ስለሚሠሩ በአጭር ጊዜ ነው የመለሱት፡፡ በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ሥራ በኋላ የጀመሩት ሌላኛው ሥራቸው ከአንድ ወዳጄ ከሚሉት ሰው ጋር በመሆን አይሱዚ ገዝተው በአሽከርካሪነት እየሠሩ የሚነግዱበትን ተግባር ነው፡፡ ከስድስት ዓመት በላይ አገልግለውበታል። ይህም የሆነው በነበራቸው ገንዘብ ሳይሆን በአብቁተ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ የአብቁተን ውለታም እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ‹‹አንድን ሥራ ለመሥራት ብዙ ውጣ ውረዶች አሉበት፡፡ አንድም ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንም። ስለዚህም በዚህ ሁሉ ጉዞዬ ውስጥ ብድር ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተለይም የአማራ ቁጠባና ብድር ለእኔ መለወጥና እዚህ ላይ መድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በመበደሬ ሠርቼ እንድለወጥ ሆኜበታለሁና››
ሰው በብዛት የሚሠራቸው ሥራዎች የማይመቻቸው ባለታሪካችን፤ ሁለቱን ባጃጃቸውን ለመሸጥና የጋራ አይሱዙ ለመግዛት ያስገደዳቸው አካባቢው ላይ የባጃጅ ሠራተኞች መብዛታቸው ነው፡፡ እናም ራሳቸውን ሹፌር አድርገው የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመሄድ ንግዱን ያፋፍሙት የነበረውም በዚህ የተነሳ ነው። ስድስት ዓመታትን በሥራው ላይ ሲቆዩም ብዙ ሰው የተሰማራበትና ተደጋግሞ የሚሰራ ሥራ እንዳልነበራቸው ያነሳሉ፡፡ እንደ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያና ደቡብ እንዲሁም አማራና ሌሎች ክልሎች የሚገኙ ምርቶችን በተለያዩ ክልሎች በማዘዋወር ሲነግዱም ብዙዎች ደስተኛ ሆነውም ነው የሚገዟቸው፡፡ ይህ ደግሞ አዋጭነቱ በጣም ከፍ ያለ እንዲሆንላቸው አስችሏቸዋል፡፡ አባዱላ ጨምረው የመግዛታቸው ምስጢርም ይህ እንደነበር እንግዳችን አጫውተውናል፡፡
ከአይሱዙ ሹፌርነት ወደ አባዱላው ራሳቸውን ያዛወሩ ሲሆን፤ ምክንያታቸውም የአይሱዙው ሹፌር ሆነው ሳለ በምሽት ሥራውን ስለሚያከናውኑ በተደጋጋሚ ሽፍታ ያስቸግራቸው ነበር፡፡ አደጋው ከባድም ሆኖባቸዋል፡፡ እንዲያውም ከአምስት ጊዜ በላይ ከአደጋ መትረፋቸውንም አውግተውናል፡፡ ስለዚህም አንድም ሥራ ማቆም አለያም ሥራ መቀየር ግዴታ መሆኑን ስላመኑበት አባዱላው ላይ እንዲሰሩ ሆነዋል። ይህም ቢሆን ብዙ ምቾት እንዳልሰጣቸው ይናገራሉ። የመነኸሪያው ባህሪ እርሳቸው በሚፈልጉት መንገድ አልሄደላቸውም፤ መልመድም አልቻሉም፡፡ እናም ይህንን ሸጠው ኤፍ.ኤስ.አር ገዝተው መሥራት ጀመሩ፡፡ ኤፍ.ኤስ.አሩን ይዘውም ለሁለት ዓመት ያህል ሠሩ፡፡
አጋራቸው አበባው ተስፋዬ ከአጋርነት በላይም የሚረዷቸው ናቸው፡፡ ወንድምም አባታቸውም ጭምር ሆነውም ነበር የሚያግዟቸው፡፡ ይህ መተሳሰባቸው ደግሞ ሥራው ታስቦበት እንዲሠራና በእድገት ላይ እድገት እንዲጨምሩ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ በተለይም የንብረቱ ተቆጣጣሪና ፈላጭ ቆራጭ እርሳቸው መሆናቸው ብዙ ለውጦችን በጋራ ሥራቸው ላይ እንዲያመጡ እንዳስቻላቸውና ለሦስተኛ ጊዜ በአጋርነት እንዲሠሩ እንዳደረጋቸው አውግተውናል፡፡ ዛሬ ድረስ አብረው የመቆየታቸውና የመሥራታቸው ምስጢርም ይህ እንደነበር አጫውተውናል፡፡
የአቶ ሰፊውና የአጋራቸው ወዳጅነት ከሥራ ጋር በተያያዘ ጥብቅ በመሆኑ የእርሳቸውን ውሳኔ የሚቃወማቸው የለም፡፡ በዚህም በአይሱዙ እየተዘዋወሩ የሚሰሩትን ሥራ በአዲስ መልክ ለመቀየር ሲያስቡ ማንንም ሳያማክሩ ነው፡፡ ሥራው ኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ ወደ ተግባሩ ለመግባት አሁንም በጋራ ሲኖ ትራኮችን ገዝተው ነበር፡፡ በእርግጥ መጀመሪያ በአንድ ሲኖ ትራክ ነበር ሥራው የተጀመረው። ሁኔታው አዋጪ መሆኑን ሲረዱ ወደ ሁለት አሳደጉት፡፡ ይህ መሆኑ ግን ሁለት ነገሮች እንዲከሰቱ አደረጋቸው፡፡ የመጀመሪያው አቶ ማሙሽ ሁለቱንም ሲኖዎች መሾፈር አይችሉምና አንዱን የአጋራቸው ሰው እንዲይዝ ሀሳብ አቀረቡ፡፡ ነገር ግን የሚሆን አይነት አልሆነላቸውም፡፡ ስለዚህም ወደ ሁለተኛው አማራጭ ገቡ፡፡ ይህም ለየብቻ መሥራት ሲሆን፤ ሁለቱንም ስምምነት ላይ ያደረሳቸው ነው፡፡
የየራሳቸውን ቢሰሩ አዋጪነቱ የበለጠ እንደሆነ በመተማመንም ያሉትን መኪኖችና ንብረቶች ተከፋፍለው በየግላቸው ወደ መሥራቱ ገቡ፡፡ እንግዳችንም ያንኑ ሥራ አጠናክረውበት ቀጠሉ፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ እንደ ሎደርና ኤክስካቫተር የመሳሰሉ መኪኖችን ገዝተው በስፋት እንዲሰሩ አግዟቸዋል፡፡ ከኮንስትራክሽን ሥራው ጎን ለጎን የማሽነሪ ኪራይ ላይም ሥራዎችን እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል፡፡
ሥራ መፍጠር የሁልጊዜ ተግባራቸው የሆነው ባለታሪካችን፤ በጥቃቅን ኢንተርፕራይዝነት ቦታ ጠይቀው ስለተፈቀደላቸው የቤቶች ግንባታ ሥራን ለማከናወን የሚያስችል ግብዓት በአካባቢው የሚያቀርቡ ናቸው። ይሁን እንጂ በወቅታዊ ጉዳይ ይህ ሁሉ በመቆሙ ሥራዎችን እያከናወኑ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከድል በኋላ እንደሚመለሱበት ያምናሉና በዚህ ብቻ ሳይሆን በሌላም ሥራ አገሬንና ወገኔን እጠቅማለሁ ራሴም እለወጣለሁ የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡ ምክንያቱም ጁንታው ሲመጣ የእርሳቸውን ንብረት ምንም ሳይነካው የአካባቢው ሰው አድኖታል፡፡ ይህንን ያደረገላቸውን የአገራቸውን ሰው አለማገልገል ደግሞ ባለእዳ እንደሚያደርጋቸው ያውቃሉና ከድል በኋላ እንገናኝም ይላሉ፡፡ በእርግጥ አሁንም ቢሆን ወቅታዊ አስተዋጽኦአቸውን አላቋረጡም። ከማንም በላይ ለአካባቢውም ሆነ ከዚያ ውጪ ላለው የአገራቸው ዜጋ እየደረሱ ይገኛሉ፡፡ የህልውና ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ድረስም በዚህ ተግባራቸው እንደሚቀጥሉ አውግተውናል፡፡
ጊዜና የአገር ባለውለታነት
በአቶ ማሙሽ እምነት ቀድሞ መደገፉ አንዱ ሆኖ ድጋፍን አለማቋረጡ ሌላው ነው፡፡ በዚህም ሕወሓት የአማራ ክልልን ጠላት አድርጎ ከዘመተበት እለት ጀምሮ ባለታሪካችን አንድም ቀን ተኝተው አያውቁም። 11 ሰዓት ላይ ተነስተው እንደግል ሥራቸው በቋሚነት አገራቸውን የመደገፉን ተግባር ያከናውናሉ፡፡ መጀመሪያ ላይ ከሠሯቸው ተግባራት መካከል የመጀመሪያ ቦታውን የሚይዘው ለሚሊሻውና ልዩ ኃይሉ እንዲሁም ለፋኖው ምግብ ማቀበልና የተለያዩ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ነው፡፡ ምንም አይነት ገንዘብ ከማንም አይቀበሉም። እያንዳንዱ ተግባር በራሳቸው ወጪ ይከናወናል፡፡ በተለይም የመኪና አገልግሎቱ ራሳቸው ሹፌር፣ ራሳቸው ነዳጅ ቻይ ሆነው ነው ግልጋሎቱን ሲሰጡ የቆዩት፤ አሁንም እየሰጡ ያሉት፡፡
የመኪና አገልግሎታቸው ቁስለኛ ከማመላለስ እስከ ምግብ ማድረስ ድረስ ይሰፋል፡፡ ስለዚህም ችግሩ ሲፈጠር ማለትም ቀበሮ ሜዳ ላይ ሚኒሻና ልዩ ኃይሉ ብቻ በሚጠብቅበት ጊዜ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ከብርድ ልብስ ጀምሮ ያሉ አልባሳትን እንዲሁም እርጎ ማህበረሰቡ አሰባስቦ ስለነበር ያንን የሚያደርስለት አጥቶ ሲንከራተት እርሳቸው የቁርጥ ቀን ልጅ ሆነው ተግባሩን ፈጽመዋል፡፡ የመጀመሪያ ሥራቸውም ይህ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ከመሆኑም በፊት የራሳቸውን ድጋፍ ያደርጉ ነበር፡፡ ሕብረተሰቡ ሲያሰባስብም ቢሆን በግላቸው የሚያደርጉትን ሳይጨምሩ አንድም ቀን አድርሰው አያውቁም፡፡ እናም ይህ ተግባራቸው የሁልጊዜ የደስታ ምንጫቸው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
መከላከያ ከገባና ጦርነቱ ጠንከር ካለ በኋላም ቢሆን ያንኑ ተግባራቸውን ከመሥራት አልተቆጠቡም፡፡ ብቻቸውን የሚያደርጉት ነገር ችግሩን በፍጥነት የሚፈታ ባለመሆኑም ሌሎችም እንደእርሳቸው እንዲያደርጉ በመገፋፋት ከአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰበሰበውን ምግብም ሆነ አልባሳት ወደ ግንባር ያደርሳሉ፡፡ ጎን ለጎንም የቅስቀሳ ሥራ ያከናውናሉ፡፡ ምክንያቱም አገር ተወሮ ቁጭ ማለት፤ መጨረሻው መኖሪያን ማጣት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እናም በራሳቸው መኪናና ሞንታርቦ ወጣቱን የማነሳሳት ተግባር ሰዎችን ጭምር እየቀጠሩ ይሠራሉ፡፡ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም በብዙ መንገድም እንደተሳካላቸው ይናገራሉ፡፡
መቄትና ገረገራ ያለው ሕዝብም በዚህ መልኩ መጓዛቸውን ሲመለከቱ የእርሳቸውን ተግባር በመደገፍ ብዙዎች እንደወጡና አገራቸውን ወደማስከበር እንደገቡ ያስረዳሉ፡፡ በተለይም ወጣቱ አንድም በመከላከያ አለያም በልዩ ኃይል ውስጥ በመግባት ሰልጥኖ ወደ ግንባር መግባታቸው የተደሰቱበት ተግባር እንደነበር አጫውተውናል፡፡
ግንባር ድረስ እየሄዱ ይህንን ማድረጋቸው ብዙ ነገር እንዲያደርጉ እንዳገዛቸው የሚናገሩት እንግዳችን፤ የመጀመሪያው መከላከያ ሰራዊቱ ምን እንደሚያስፈልገው በቀላሉ አይቶ መረዳት ነው፡፡ ሌላው የማያስፈልገውን ከሚያስፈልገው ለይተው እንዲንቀሳቀሱም ማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ ትይዩ ለሌሎች ሲናገሩና ሲሰበስቡ በቀላሉ የሚናገሩበትን እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ በእርሳቸውና መሰል ሰዎች ድጋፍ ኃይሉ እንዲጠናከርና ጠላትን እንዲመክት እንዳስቻሉ ሲሰማቸው ደግሞ የውስጥ ሰላም እንዲያገኙ እንዳደረጋቸውም ይገልጻሉ፡፡
በጋሸና ግንባር በኩል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው ጀምሮ ብዙ የሠሩበት እንደነበር የሚያስረዱት ባለታሪካችን፤ መከላከያና ልዩ ኃይሉ በአረፈበት ሁሉ ተግባራቸውን ያከናውናሉ፡፡ የማበረታታት ሥራም ይሠራሉ፡፡ ሕብረተሰቡ ያለበት ሁኔታ ከባድ በመሆኑም ከዚያ ችግር ለመታደግም የቻሉትን ያክል ያደርጋሉ፡፡ በተለይም ሕወሓት ሀብት ንብረቱን ከማውደሙና ከመዝረፉ ባሻገር ነገ እንዳይሰራም አድርጎ የደበደባቸው ክፍሎችን እየለዩ ከቻሉ ራሳቸው ካልቻሉ ሕዝብ በሚያደርገው እገዛ ድጋፉ እንዲደርሳቸው ይታትራሉ፡፡
ሕወሓት የአሰቃየውን ሕዝብ የማንሳትና የማገዝ ኃላፊነት የእንደእኛ አይነት ሰው ነው የሚል እምነት ያላቸው እንግዳችን፤ ድጋፍ ከአደረጉት ተግባራት መካከል አንዱ ሕክምና ወስዶ እገዛን እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ መሰረተ ልማት በወደመባቸው አካባቢዎች ላይ ደግሞ ማህበረሰቡ እንዳይሰቃይ ለማድረግ የምንጭ ውሃን የራሳቸው ጄኔሬተርን በመጠቀም በፓምፕ በፍጥነት በሳምንት ሦስት ቀን እንዲያገኙ በማድረግ አግዘዋል፡፡ ዛሬም እያደረጉት ይገኛሉ፡፡
ሌላው የሠሩት ተግባር በላሊበላ በኩል ተፈናቅለው ያሉ ነፍሰጡር እናቶችን በርሃብና በጥም እንዳይሰቃዩ እንዲሁም ሕክምና እንዳያጡ ለማድረግም በተቻለው ሁሉ መደገፋቸው ነው፡፡ የስኳርና መሰል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ጠላትን ለማምለጥ በሚያደርጉት ጉዞ ማምለጥ አይችሉምና እነርሱን መጠለያ ጣቢያ ድረስ በማድረስ ያግዟቸዋልም፡፡ በፍጥነት ድጋፍ እንዲያገኙም እድሉን ያመቻቻሉ፡፡
‹‹አሁን እየሆነ ያለው ነገር የስልጣንና የገንዘብ ማግኘትና ማጣት ጉዳይ አይደለም፡፡ የመኖርና አለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ለመኖር ደግሞ ክብርን ማስመለስና አገርን ማቆየት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህም ላንድክሩዘር መኪናዬን ይዤ ዘወትር በህልውና ዘመቻው ላይ መቆየቴ ለማንም ስል የማደርገው ሳይሆን ለራሴ ነው፡፡ እናም ሌላውም ይህንን እያሰበ በቻለው ሁሉ አገሩን ማገልገል አለበት፡፡ የተሰጠው ጊዜም ይህ ብቻ እንደሆነ ይሰማኛል። ሳያልፍበት መጠቀም ደግሞ ታሪካዊ ሰው መሆን ነውና ሁላችንም አይለፈን፤ አንድ ጠጠር እንወርውር›› ይላሉ፡፡
ከመስከረም ሦስት ጀምሮ ምሳ ቁርስ እራትን አስበው እንደማያውቁ የሚናገሩት እንግዳችን፤ ግንባር ድረስ በሚሄዱበት ወቅት ሰራዊቱ አስገድዷቸው እነርሱ የበሉትን እየበሉ እንደሚውሉና ያም ደስተኛ እያደረጋቸው ዛሬ ድረስ እንዳቆያቸው ያስረዳሉ፡፡ በዚህ መካከል ብዙ ፈተናዎች እንደገጠሟቸውም ያነሳሉ። በተለይም ከቤተሰብ በኩል መንገድ ላይ ይቀርብናል በሚል ስስት ዛሬ ይለፍህ የሁልጊዜ ጉትጓቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለአገር የሚከፈል መስዋዕትነት በቤት ውስጥ ሆኖ ሳይሆን ጠላትን ተጋፍጦ የሚመጣ ነው፡፡ እናም ቤተ ተቀምጬ አልሞትም በሚል ቤተሰቦቻቸው የሚሏቸውን አንድም ቀን ሰምተዋቸው አያውቁም፤ ጉዟቸውንም እንዲሁ አላቋረጡም።በእርግጥ ይላሉ እንግዳችን እናታችን ጀግና ናት፡፡ በተለይም አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስታይ የምትሰስተው ነገር የላትም። ስለዚህም ሁለት ልጆቿንም ህልውና ዘመቻው ውስጥ እንዲሳተፉ አድርጋለች፡፡ ታናሽ ወንድሜ ግንባር ላይ ጀብድ የፈጸመውም በዚህ ወኔ ስለተሸኘ ነው፡፡ እናም ዛሬ ላለንበት ሁኔታ ባለቤቶቻችንና ቤተሰቦቻችን መፍትሄም ድልም ናቸው፡፡ ስለሆነም ዝመት እንጂ ቁጭ በል ሊሉን አይገባም፡፡ እነርሱም ቢሆኑ በአካባቢያቸው ዘማችና ታጋይ መሆን ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡
መከላከያን አለማገዝ ማንም አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከሁሉም በፊት ለመሞት ቤተሰቡንና ሀብት ንብረቱን በትኖ ዘምቷል፡፡ እናም በተለይም አገሬን እወዳለሁ የሚል ሰው በቤቱ ከሞተ ውርደት ብቻ ሳይሆን የሞት ሞት እንደሞተ ሊቆጥረው ይገባል፡፡ በዛሬው ጊዜ ደግሞ ሞት ቤት ድረስ መምጣቱ አይቀሬ እንደሆነ በቅርብ ዘመዶቻችን እያየነው ነው፡፡ እናም እኛ ኢትዮጵያውያን የምንሞተው ሞት የድል፤ የታሪክ ፤ የጀግንነት ሞት እንጂ የፈሪ ሞት አይደለም ባይ ናቸው፡፡
የሕይወት ፍልስፍና
ማንኛውም ሰው ሥራን ባህሪውና ሕይወቱ ካደረገ አሸናፊነት ከስሩ አይለይም፡፡ ከሩቅ ሆኖ ስኬትንም አያይም የሚለው የመጀመሪያው አቋማቸው ነው፡፡
ሮጦ ከመሞት ታስሮ መዳን ይበልጣል መርሐቸው ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ብዙዎች ቀያቸውን ትተው እየሄዱ ለሌሎች ፈተና ለራሳቸውም ችግር ሆነዋል፡፡ ሞታቸው ቅርብ የሆነባቸውም ጥቂት አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም በሩጫቸው ውስጥ የሕወሓት የሳት ራት ሆነዋልና፡፡ ቀዬአቸውን ለማስጠበቅ የከረሙት ግን አትራፊ ሲሆኑ በብዙ መንገድ አይተናል፡፡ እናም የትም መሸሽ ሳይሆን በአለንበት ቆመን መፋለም የጀግንነትም የታሪክም ባለቤት መሆን የሚለው ሌላው ፍልስፍናቸው ነው፡፡
መልእክት
ወጣቱ ለአገሩ መከታ የሚሆነው ሥራ ወዳድና ከምንም አይነት ሱስ ነጻ ሲሆን ነው፡፡ በሱስ የተጠመደ ሰው ለራሱም ለአገሩም ሸክም ነው፡፡ እናም አሁን ከእንደዚህ አይነት ድርጊቶች እራሱን ቢያጸዳና ራሱን መሆን ቢችል ሥራ አጥ አይኖርም፡፡ አገርም በእድገት ማማ ላይ መቀመጧ አይቀርም፡፡ አሸባሪውም ቢሆን ይህንን እድል ተጠቅሞ የሚሠራው ሥራን አይፈጥርም። ምክንያቱም የሚሠራ እንጂ የሚያወራ አይኖርም፤ የሚሠራ እንጂ ሥራ ፈትቶና ጊዜ ኖሮት ሌላ እቅድ የሚተገበር አይፈጠርም፡፡ ስለሆነም አገር የሚያስፈልጋት ሠሪ እንጂ አውሪ እንዳልሆነ በማመን ወጣቱ ከሱስ በመውጣት ሥራ በመፍጠር ራሱን አድኖ ለሌሎች ተስፋ መሆን ይገባዋል የመጀመሪያ ምክራቸው ነው፡፡
ሌላው ያነሱት ነገር አሁን የሚደረገው ዘመቻ የነገውን ልጅ ቀና አድርጎ ማስኬድ እንደሆነ ነው። በዚህም እኔ ሞቼ ትውልዱ ቀና ይበል የሚል ዜጋ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ መሸሹ የጁንታው እንጂ የማንም ተራ አይደለም፡፡ ስለሆነም በትግሉ አሮጊቷ ሳትቀር ካራ ይዛ መሳተፍ አለባት፡፡ እየተፋለመችም እንደሆነ በእያንዳንዱ ዘመቻ እያየነው ነው፡፡ ስለዚህም በአገር ቁርጠኛ የሆነ ዜጋ ስለተፈጠረ ይህንን ባለን ላይ መጨመር ይገባል፡፡ እስከመጨረሻው መቀጠልም እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡
የሕወሓት ሴራ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ አቅምና የተጋድሎ ሰብዕና የጠየቀበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ምክንያቱም በልዩነት የእርስ በርስ መከፋፈልን አምጥቷል፡፡ እናም ታሪክ ሰሪውን ሕዝብ ለአዲስ ታሪክ ራሱን እንዲያዘጋጅ አስገድዶታል። ስለዚህም ዳግማዊ አደዋን በታሪካችን ካላስከበርን በስተቀር ጠላትን ድል ማድረግ አንችልም፡፡ እናም አሁን ያለውን የአንድነት ሥራ ማጠናከርና ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በሕብረት የዳግማዊ አደዋ ጀግኖች መሆን ይኖርብናል ሲሉ ይመክራሉ፡፡
አገር የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኗ ዋጋዋ እጅግ ውድ ነው። የአገርን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ፣ የህዝቦችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በዘላቂ መልኩ ለማስቀጠል ብዙ መስዋዕቶችን መክፈል የግድ ይላል። ኢትዮጵያውያንም እያደረጉ ያሉት ይህንን በመሆኑ ሁሉም መቀላቀልና በቻለው ሁሉ የድሉ አካል መሆን አለበትም መልእክታቸው ነው፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2014 ዓ.ም