ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦሩን በግንባር ተገኝተው ማዋጋት ከጀመሩበት ሰዓት አንስቶ አንጸባራቂ ድሎች መመዝገባቸውንና አሸባሪው አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ መሆኑን ተከትሎ የምዕራባውያን ሚዲያዎች እነ CNN BBC FRANCE 24 Washington Post The economist New York Times The Guardian Reuters AP AFP Aljazeera Telegraph WIONwes እና ሌሎቹ ከአሸባሪው ሕወሓት ከሱዳንና ከግብጽ ጋር በመቀናጀት “ከባዝማ እስከ ኢትዮጵያ” በሚለው ሰነድ በግልጽ ባስቀመጡት ኢትዮጵያንና መንግሥቷን ለማጠልሸት ባስቀመጡት ዝርዝር ዕቅድ መሠረት በትግራዋይ ላይ ሀሰተኛ የዘር ማጥፋት ተፈጸመ ለማለት ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል።
እንደ አክሱሙ ሁመራው ሀሰተኛ የዘር ማጥፋት፤ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገዱ ፣ እንደ አስገድዶ መድፈሩ ፣ እርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀሙ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመፈብረክ ሱዳን ዋድ ሙዘሚል ከከተቱ ሳምንታት ማለፋቸውን ኬኒያዊው የደህንነትና የመከላከያ ተንታኝ ካፒቴን ኮሊንስ ዋንዴሪ አበክሮ ሹክ ካለን እንኳ ሳምንታት አልፈዋል። የሲኤንኤኗ ኒማ ኤልባገር ሰሞኑን የሕወሓትን አርማ ከለበሰ ወጣት ጋር የተነሳቸው ፎቶ በፌስቡክ መለቀቁ የሀሰተኛ መረጃው ፍብሪካ በሂደት ላይ መሆኑን ፍንጭ ይሰጣል ።
ህልውናችንና ሉዓላዊነታችን ለማስከበር ከአሸ ባሪው ሕወሓት ጋር ተገደን የገባንበት ጦርነት በአውደ ግምባር ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን ከተረዳን ዓመት አለፈን። በፕሮፓጋንዳና በዲፕሎማሲ ጦር ግንባሮች ተሰልፈን ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረናል። #ይበቃል! #በቃ! #No more! ንቅናቄያችን ከኢት ዮጵያ አልፎ አፍሪካን ካሪቢያን ዓለምን እያዳረሰ ይገኛል። በዚህ ሰዓት ብቸኛው ዓለማአቀፍ ንቅናቄ ሆኗል። ሆኖም በጊዜያዊ ውጤት ሳንዘናጋ ሳንታክት በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው በተቃውሞ ሰልፎች የኢትዮጵያን ሀቅ ማሳወቅ አለብን። ለዚህ ይረዳን ዘንድ የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱን የምር መረዳት አለብን።
ተገደን የገባንበት ጦርነት በእፉኝቱ ትህነግ ስፖንሰር ከሚደረገው ተልዕኮና ስምሪት ከሚሰጠው ዲጂታል ወያኔ ህልቁ መሳፍርት ከሌለው የሀሰት መረጃና ሆን ተብሎ ከተዛባ መረጃ ጭምር እና የሴራ ኀልዮት ጋር ነው ። ይህ የከሀዲና የሌባ ስብስብ ከ27 ዓመታት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በኋላ በህዝባዊ አመጽና በለውጥ ኃይሉ ከመንበሩ ከተፈነገለ በኋላ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ መሽጎ 24 ሰዓት የውሸት ፣ ሆን ተብሎ የተዛባና የሴራ ኀልዮትን ፍላጻ ሲያንበለብል ባጅቷል ። በዚህም በአገሪቱ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል። ንጹሐን ተገድለዋል። ወልደው ከብደው ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል ።
ጥቅምት 24 ቀን ፣ 2013 ዓም በሰሜን ዕዝ ላይ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ በስግብግቡ የትህነግ ከሀዲ ቡድን ግፍ መፈጸሙን ተከትሎ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲንቀሳቀስ እና ተገዶ ወደ ጦርነት ሲገባ የትህነግ የፕሮፓጋንዳ ወናፍ በተናበበና በተቀናጀ አግባብ በማህበራዊና መደበኛ ሚዲያ የሀሰትና የተዛባ መረጃውን በማራገብ ዓለምአቀፍ ጫና እንዲደረግብን አድርጓል ። ጦርነቱን ከአንዴም ሁለቴ እራሱ ለኩሶ እያለ የተወረርሁ ድቤውን ይደልቃል። ያልታጠቀውን መሳሪያ ታጥቄያለሁ ፤ በሰማዩ እንዳሻው ፈንጭቶ ወታደራዊ ኢላማውን መትቶ የተመለሰን ተዋጊ ጀት መትቼ ጣልሁ ፤ ወዘተረፈ አይነት ነጭ ውሸቶችን በፎቶ ሾፕና በቪዲዮ እያቀናበረ በመላው ዓለም በተበኑ ትግራዋይና የውጭ ሀገር ዜጋ በሆኑ ጭፍራዎቹ አማካኝነት እየነዛና እያራገበ ይገኛል ።
በማህበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያው ሀሰተኛው ፣ የተዛባው ሆነ አሳሳቹ መረጃ የትየለሌ በመሆኑ ሕዝብ በአሰስ ገሰስ የመረጃ አረንቋ መዋጡን ለማረጋገጥ የትህነግ ምንደኛ የፕሮፓጋንዳ ጭፍራ ማህበራዊ ሚዲያውንና ዘርፎ ያቋቋማቸውን መደበኛ ሚዲያውን እንዴት በውሸት እንዳጥለቀለቀው መመልከትና መረዳት ይችላል። ከጦርነቱ ይልቅ የመረጃ አውደ ውጊያው አየሩን ፣ ምድሩንና መልካው ብቻ ሳይሆን ቨርቹዋል የሆነውን ዲጂታል ዓለምንም አዳርሶታል ፡፡ይህ አልበቃው ብሎ በሴራ ኀልዮት እያወናበደ ይገኛል ። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሴረኛውን የትህነግ ወታደራዊ ቡደን ውሸትና ቅጥፈት ጠንቅቆ የሚያውቀው ቢሆንም ዛሬም ጥቂት የዋሆችን ማቄሉና ማሞኘቱ አልቀረም ።
የሽብር ቡድኑ የሴራ ኀልዮት ፣ ሚስ ኢንፎር ሜሽን እና ዲስ ኢንፎርሜሽን አዛንቆ ይጠቀማል። እርስ በእርስ የሚመጋገቡና የሚናበቡ መሆናቸው ለፕሮፓጋንዳውና ለሀሰተኛ መረጃው በደንብ አድርጎ እየተጠቀመባቸው ይገኛል። ሚስናዲስ ኢንፎርሜሽን ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ስለሚመስል እየተተካኩ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል ። ብያኔአቸው ግን ለየቅል ነው። ሚስኢንፎርሜሽን የተሳሳተ ወይም አሳሳች መረጃ ሲሆን ዲስኢንፎርሜሽን ደግሞ እውነትን ለመሸፋፈን ወይም የሕዝብ አስተያየት ላይ ተዕጽኖ ለማሳደር ሆን ተብሎ የሚነዛ የሀሰት መረጃ ነው ። እፉኝቱ ትህነግ በፕሮፓጋንዳ ጭፍራው አማካኝነት ስልጣን ላይ እያለም ሆነ ከተፈነገለ በኋላ አሳሳች ፣ እውነት የሚያጠየም እና የሴራ ኀልዮትን እያዛነቀ ሌት ተቀን እየባዘነ ይገኛል ።
በተለይ በሰሜን ዕዝን አረመኔያዊ ክህደት መፈጸሙን ተከትሎ መንግሥት ሉዓላዊነትን ለማስ ከበር ከወሰነበት ደቂቃ አንስቶ ምን አልባት በየዕለቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሀሰተኛ ፣ እውነትን የሚበርዙና የደባ መረጃዎችን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያ እያንበለበለ ይገኛል። በጀግናው የመከላከያና የሚሊሻ ኃይሎች በቀናት አውደ ውጊያ ድባቅ ሲመታ ያለ የሌለ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና የዘረፈውን ሀብት ለፕሮፓጋንዳ ማሽነሪው እያዋለው ይገኛል ። አማራ ኦሮሞ እየተሴረብህ ነው ፤ መከላከያው ተከፋፍሏል፤ የመዋጋት ሞራል የለውም፤ የአማራ ልዩ ኃይል ተከዳ፤ ወዘተረፈ የሚሉ የሴራ ኀልዮትን እያንበለበለ ውዥንብር ይፈጥራል ።
ለመሆኑ የሴራ ኀልዮትስ ምን ድን ነው !?ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ፣ ባለስልጣናት አልያም የተወሰኑ የፖለቲካ፣ የአይዶሎጂና የኢኮኖሚ ቡድኖች ሚስ ጥራዊ ዕቅድ ውጤት የሆነ ሁነት ወይም ክስተት የሴራ ኀልዮት Conspiracy Theory ሲል ይበይነዋል የእንግሊዘኛው መዝገበ ቃለት ሜሪያም ዌቢስተር። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባሰናዳው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ፤ አድማን ፦ ሴራ ዱለታ ፤ ሲል በአጭሩ ይተረጉመዋል።
ሆኖም በባለስልጣናት፣ በመንግሥት ሆን ብሎ ጉዳት ለማድረስ በሚስጥር የሚፈፀም ደባም የሴራ ኀልዮት ነው ሲሉ ድርሳናት ትርጉሙን ሰፋ ያደርጉታል፡፡ ታዋቂው የፖለቲካ ሊቅ ማይክል ባርኩን በበኩሉ ኀልዮቱ አፅናፈ ዓለም universe በአፈታት በአቦሰጥ ሳይሆን በንድፍ design ትመራለች በሚለው ተረክ ላይ የተዋቀረ ነው ሲል ይሞግታል። እንደ ባርኩን ትንተና የሴራ ኀልዮት 3 መገለጫዎች አሉት። የመጀመሪያው ምንም ነገር በአጋጣሚ አይሆንም ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ምንም ነገር ላይ ለዩን እንደምናየው፣ እንደመሰለን አይደለም። ሶስተኛው ደግሞ ሁሉም ነገር እርስ በርሱ የተያያዘ ነው ብሎ የምናል፡፡ ሌላው የኀልዮቱ ባህሪ ይላል ባርኩን ውሸት መሆኑን በመረጃ ለማስተባበል ፈታኝ መሆኑ ነው ፡፡
የኀልዮቱ መነሻ የመሪዎች ግድያ ሲሆን ዘመኑም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ መሆኑን ድርሳናት ያትታሉ፡፡ ከእያንዳንዱ ክስተት ጀርባ ሴራ ደባ አለ በማለት በዜጎች በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን የሚቀፈቅፍ ኀልዮት ነው፡፡ በታላቁ መጽሐፍ፦” በእግዚአብሔር እናምናለን፡፡ “እና “ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ያያሉ ፡፡ “ ከሚለው ቅዱስ ቃል ላይ ተመስርቶ በአሜሪካ የአንድ ዶላር ላይ ፈጠሪ ሁሉን እንደሚያይ ፤ አሜሪካ በቅጥሩ በጥበቃው ስር እንደሆነች የሚወክለውን ምስል ( the all seeing eye) ሳይቀር በአሜሪካ መስራች አባቶች የተሸረበ ሴራ ተደርጎ መቆጠሩ ኀልዮቱ ምን ያህል ጥርጣሬን ለመዝራት ምን ያህል ምቹ እንደሆነ ያሳያል ፡፡
አንዳንድ የስነ ልቦና ሊቃውንት ኀልዮቱ በማኪ ያቬሊያዊ ፅንሰ ሀሳብ በዜጋውና በሕዝብ መካከል ፍርሀትን በመንዛት ላይ ያተኮረ መሆኑን ይተነትናሉ። በዓለማችን በሴራ ኀልዮት አብነትነት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል የአሜሪካዊ 35ኛ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ላይ የሀገሪቱ የስለላ ድርጅት ( ሲ አይ ኤ ) እጁ አለበት ፡፡ እ አ አ በ1971 አፓሎ የተሰኘች የአሜሪካ መንኮራኮር ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ማረፏን የሚክደው እንዲሁም በተለምዶ በ9/11 አልቃይዳ በዓለም የንግድ ድርጅት ህንፃዎች ፣ በፔንታጎንና በመንገደኞች አውሮፕላን ከ3ሺህ በላይ አሜሪካውያንና የውጭ ዜጎች ባለቁበት የሽብር ጥቃት አሁንም ሲ አይ ኤ ተሳትፎበታል ። ኤች አይ ቪ / ኤድስን አሜሪካ ነች ጥቁሮችንና ሌሎች ለመጨረስ በቤተ ሙከራ የፈጠረችው እና የእንግሊዟን ልዕልት ዲያና ፈረንሳይ ፓሪስ በመኪና አደጋ የሞተችው በሀገሪቱ የስለላ ድርጅት ኤም አይ 6 እና በንጉሳዊ ቤተሰቡ ሴራ ነው የሚሉ ይገኙበታል ፡፡
እንደ መቋጫ
እውነተኛ መረጃን ተደራሽ በማድረግ የተጋነኑና በማህበረሰቡ ዘንድ ሽብር የሚለቁ መረጃዎችን መከላከል ይቻላል ፡፡ መንግሥትም ሆና ባለድርሻ አካላት ወቅታዊና እውነተኛ መረጃዎችን ከስር ከስር የማድረስ ኃላፊነት አለባቸው ፡፡ እግረ መንገድ ሕዝብን ካልተገባ ፍርሀትና ውዥንብር መከላከል ይቻላል። ዳሩ ግን ትክክለኛ መረጃን የማድረስ ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው ጉዳይ ሳይሆን የሁሉንም ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑ ሊጤን ይገባል ፡፡ አንድ መረጃ ከማጋራት ወይም ከመለጠፍ በፊት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይሁን ለሌላ ተግባር በምንጭነት ከመጠቀም በፊት ከሌሎች ምንጮች ጋር ማመሳከር የተቀናጀ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ።
የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምንጠቀም ሰዎች ስለምናጋራው ጽሑፍ ፣ ምስልና ድምፅ ቆም ብለን ማሰብ ፣ ለዋቢነት ፣ ለአጋዥነት ስለምንከፍተው ድህረ ገፅ ፣ ጦማር ታማኝ ምንጭ መሆን አለመሆን ማጣራት በማስከተል አስተያየት (ኮሜንት) ከመ ስጠታችን በፊት ማውጣት ፣ ማውረድና ማመ ዛዘን ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ከቻልን ሀሰተኛ፣ የተዛባና የጥላቻ መረጃ ዘርጋፊዎችን ፣ ነዥዎችንና ለፋፊዎችን በሒደት ማስቆም እንችላለን።
መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከወሰነ በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት ከጎኑ ከመቆሞ ባሻገር በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እና ግምቱ ቀላል ያልሆነ የአይነት ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን እንዳረጋገጠው ሁሉ በውጭም በአገር ቤት ያሉ ዜጎች በተወሰነ ደረጃ የዲጂታል ወያኔን ፕሮፓጋንዳ በጀግንነት እየመከቱ ቢሆንም ፤ እውነትን ይዞና ተገዶ ወደ ጦርነት እንደገባ ሀገርና ሕዝብ ለዛውም ከትህነግ ጋር ለሚደረግ የጸረ ፕሮፓጋንዳ ትግል ሁሉም ዜጋ በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ሊንቀሳቀስና ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና ሚሊሻ በጦር ግንባር ያስመዘገበውን አንጸባራቂ ድል እኛ በእሱ መስዋዕትነት በሰላም እየኖርን በእጅ ስልካችንና በኮምፒዩተር ቁልፎች የምንደኛውንና የቅጥረኛውን የዲጂታል ወያኔ ጭፍራ ፕሮፓጋንዳ መክተን የፕሮፓጋንዳ አውደ ውጊያውን ማሸነፍና የጀግናው ሰራዊታችንን አኩሪ ድል መደገምና ማህበራዊም ሆነ መደበኛ ሚዲያውን በሀገር ፍቅር ሱናሚና በአርበኝነት ማጥለቅለቅ ይጠበቅብናል ።
ለሀገራችን ሁላችንም አምባሳደር ፣ ጋዜጠኛና ሕዝብ ግንኙነት ነንና ። ይህ ዘርፈ ብዙ ጦርነት በድል እስኪደመደም ሁላችንም የእውነት ፣ የፍትህና የሉዓላዊነት ሰራዊት መሆን አለብን ። ለዚህ ክቡር አላማ የህይወት መስዋዕትነት ብንጠየቅ እንኳ ወደ ኋላ የማንል ጊዜያችንን ፣ እውቀታችንንና ገንዘባችንን ሰውተን የድሉ ተቋዳሽ መሆን ይጠበቅብናል ።
እናሸንፋለን !
አንጠራጠርም።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2014 ዓ.ም