የተንኮለኛ በድን አፈር ይበክላል፤
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈተና በዓይነትም ሆነ በውስብስብ ባህርይው ከእስከ ዛሬው የተለየ ስለመሆኑ ተደጋግሞ ሲገለጽ ሰንብቷል። ምናልባትም ክስተቱ በዓለም ድርሳናት ውስጥ እንደ አዲስ ታሪክ ተመዝግቦ ለመፃኢው ትውልድ ማስተማሪያ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። የተለየ ያሰኙትን አንዳንድ ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው እናስታውስ።
ሕወሓት ኢትዮጵያን ለመበታተን ማቀድ የጀመረው ከጽንሰቱ ጀምሮ እስከ መጃጀቱ እንደነበር በአያሌ ማስረጃዎች ሲገለጽ ኖሯል። ህልሙና ቅዠቱ እውን ሆኖ አገሪቱን በመራባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ የተመኘውን ከማድረግና ያሰበውን ከመተግበር ጭራሽ ከልካይ አልነበረውም። በመሆኑም በሴራ ተውጠንጥኖ በመንግሥትነት ሽፋን ሲፈጽም የኖረው ግፍ ግዝፈቱና ዓይነቱ ገና ጠሎ ስላልሰከነ በዝርዝር ለማመላከት ያዳግታል።
የቡድኑን የኢኮኖሚ ብዝበዛና ዘረፋ በተመለከተ ግዝፈቱን በአሀዝም ይሁን በመጠን ለመግለጽ አዳጋች ነው። ከኪዮስክ እስከ ባንክ፣ ከተራ ጉልት እስከ ርስት፣ ከከርሰ ምድር ሀብት እስከ ገጸ ምድር ትሩፋት ያልዘረፈው፣ ያልወረረው፣ ያልመዘበረው፣ ወደ ውጭ ያላሸሸው ሀብት እንደሌለ ከተመራማሪ ምሁር ጀምሮ እቅፍ ውስጥ እስካለ ሕጻን ድረስ ሊረዳው የሚችለው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው።
ይሄ በሕዝብ ልማትና በዕለት ጉሮሮው ላይ ተሰንቅሮ የኖረው ክፉ አጥንት ውጤቱ ምን እንደሆነ እያንገሸገሸንም ቢሆን አንገት እንደደፋን ኖረንበታል። የእነርሱን ልጆችና ዘመድ አዝማድ ወደተለያዩ ሀገራት እያጓጓዙና እያሞላቀቁ ሲያኖሩ “ኢትዮጵያዊ ቅጽል እንጂ፤ ኢትዮጵያዊ ክብር የተነፈገው” ደሃውና ተስፋው የተንኮታኮተበት ዜጋ ለስደትና ለሥራ አጥነት ተዳርጎ መንከራተት ዕድል ፈንታው ነበር።
ሀገራዊው የትምህርት ሥርዓቱ እንዲዘቅጥ፣ ማኅበራዊ ተራክቦው ላልቶ እንዲነትብ፣ “የእከሌ ብሔር” ገዝፎ ሌላው አንገት እንዲደፋ፣ ቢሮክራሲዊ ተመሳቅሎ የእነርሱ ድልቦች ብቻ እንዲፋንኑ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ታውሮ ምርኩዙና በትሩ እንዲነጠቅ፣ መንግሥታዊ ሥልጣኑ ለእርሱና በእርሱ ዙሪያ ላሉት ብቻ ተደላድሎ ፍትሕ የተጠማው ሕዝብ በብረት ዱላ እንዲቀጠቀጥ መደረጉ፣ የዲፕሎማሲው ጉልበት ተልፈስፍሶ ተንበርካኪ እንዲሆንና የተጽእኖ ፈጣሪነት “መቅኒው” መሟጠጡ ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የመከራ ውሽንፍሮች ኢትዮጵያ በሚሏት ሀገር ሲዘንቡ የኖሩ መዓተ-ሕወሓትና መርገምቶች ናቸው።
ይህም ክፋቱ አልበቃው፣ አላጠግበው፣ አላረካው ብሎ በሕዝብ ቁጣና አመጽ፣ በፖለቲካ ብስለትና ማስተዋል ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ራሱን ከፌዴራል መንግሥት አካልነት በማራቅና በማግለል “በመቀሌ የግንብ አጥር” ውስጥ ተወሽቆና ተሸሽጎ መኖርን ምርጫው አድርጎ ነበር። ሰይጣናዊ ድርጊቶቹ ጫፍ ደርሰው በይፋ የተገለጸው ግን ጀግናውን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ከተዳፈረ በኋላ ነው።
“እልኽ ምላጭ ያስውጣል” እንዲሉ ጀግናውን አንበሳ ሠራዊት መተናኮሉ ያነሰ ይመስል የአሸባሪው ቡድን ዕብሪትና ትእቢት ገንፍሎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ጦር በማዝመትና ቀማኛና ዘራፊ ሽፍቶች በማሰማራት ያፈሰሰውን የንጹሐን ደም፣ ያወደመውን የግለሰቦችና የመንግሥት ንብረት፣ ያደረሰውን የአካላዊና የሥነ ልቦና መቃወስ ጊዜው ጊዜ ስለሚጠይቅ አሟጦ ለመዘርዘር ያዳግታል።
ይህ አሸባሪ ቡድን ከጦርነት ፉከራውና ድርጊቱ ተሽመድምዶ እንደ ገል እየተፈረካከሰ ያለው የሚመካበት ወታደራዊ ኃይሉ ስለተንኮታኮተ ብቻ አይደለም። ወኔውና እብሪቱ ተሟጦ ተደፍቶበታል። ትምክህቱና ኩራቱ እንደ ትቢያ በኖ እየተነፈሰ ነው። በሀገር ውስጥ የዘረጋው የሴራ ሰንሰለት እየተበጣጠሰ “ቀለበቶቹ” በቁጥጥር ሥር መዋል ጀምረዋል። የዲጂታል ወያኔ ልሳኖቹ ሞገሳቸውና ቀልባቸው ተገፎ “አለን” እያሉ የሚንተባተቡት በማኑዋል ምላሳቸው ብቻ ሆኗል።
በመላው ዓለም ያሰማራቸው የዲፕሎማሲና አግባቢ ሆድ አደር “የሪሞት ኮንትሮል መቆጣጠሪያ” ማማዎቹ መሠረታቸው ተናግቶ መሰነጣጠቅ ጀምረዋል። በዘረፋ ያከማቸው ሀብት እንደ ጉም እየተገፈፈ ካዝናው ወደ መዛግ ተሸጋግሯል። ሕወሓት ለመሞት መጣጣር ብቻ ሳይሆን የመገነዣ ከፈኑን ተከናንቦ ለመቀበሪያ ሳጥኑ መድፈኛ ሚስማሩንና መዶሻውን እያቀበለ “ፈጥናችሁ አፈር አልብሱኝ” በማለት በመማጸን ላይ ነው። ችግሩ የዚህ ክፉና ጨካኝ ቡድን መሪዎችና ጀሌዎች አፈር ቢለብሱም እንኳን በድናቸው የሚበክል አሲድ ሆኖ ምድሪቱን ማርከሱ የማይቀር መሆኑ ነው። ለማንኛውም ሳጥናኤል ነፍሳቸውን ተቀብሎ ሲኦልን ለማደሪያቸው እንዳዘጋጀላቸው የተረዱት ቀደም ሲል ነው። ስለዚህም ነበር “በኩነኔ ጸሎት” በመማጸን “የቁም ተስካራቸውን አብልተው” በተግባራቸው ብቻ ሳይሆን በቃላቸው ጭምር መስክረው ያረጋገጡት። ስለሆነም አንባቢያን ሆይ! በለሆሳስ ንባባችን መካከል “እንኳንም ለሲኦል ቤታችሁ አበቃችሁ!” ብለን ብንመርቃቸው ተገቢ ይሆናል።
ሣልሳዊው የአፍሪካ ድል፤
መላው የአፍሪካ ሕዝቦችና የተቀሩት ጥቁር የዓለም ዘሮች አንገታቸውን ቀና አድርገው በራሳቸው የነጻነት አጥቢያ ከዋክብት መድመቅ የጀመሩት የአድዋ ድል ነፀብራቅ ቦግ ብሎ ከበራላቸው በኋላ ሲሆን፤ ብርሃናቸው ይበልጥ ደምቆ እየፈካ የሄደው ደግሞ በፋሽስት ኢጣሊያ ላይ ዳግማዊ የድል ዜና ከተበሰረ በኋላ ነበር።
እነዚህ ብስራቶች በቅኝ ግዛት ሥር ወድቃ ለነበረችው ታላቋ አፍሪካ የፈጠሩት መነቃቃት በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። በፓን አፍሪካኒዝም የአርነት መርህ መሠረት ልጆቿ የየሀገራቸው ተጨባጭ ዐውድ በሚፈቅድላቸው ስልት ትንቅንቁን በማጋጋላቸውም ቅኝ ገዢዎቻቸውን አንበርክከው ነፃነታቸውን ሊጎናጸፉ በቅተዋል።
የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግሉን ያቀጣጠሉት ቀዳሚ የአፍሪካ አባቶች የከፈሏቸው መስዋዕትነቶች ከሚገመተው በላይ የመረሩ ነበሩ። ከቅኝ ግዛት ትግሉ መጠናቀቅ ማግሥት በተለየ ባህርይው ያቆጠቆጠው የምዕራባውያንና
የአሜሪካ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሴራ ግን ዛሬም ድረስ በአፍሪካውያን ትግል ተሸንፎ እጅ ሊሰጥ አልቻለም። እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየለዋወጠ ለአፍሪካ ዕድገትና አንድነት የማሰናከያ ዓለት በመሆን አህጉሪቱን ውስብስብ ፈተናና አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በአሸባሪው፣ በዘራፊውና በጨካኙ የሕወሓት ወራሪ ሽፍታ ላይ እያሳረፈች ያለው ዱላና እየተመዘገበ ያለው ድል በተለይ ለአፍሪካ ሀገራት ትርጉሙ ላቅ ያለ ሊሆን ይችላል የሚባለውም ስለዚሁ ነው። የአህጉሪቱን ሰላምና ጸጥታ ክፉኛ እየተፈታተኑ ያሉ የየሀገራቱ የሽብር ቡድኖች “የሕወሓትን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም!” ወደሚል የሥነ ልቦና አረንቋ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ሀገራችን መንገዱን በሚገባ አመላክታቸዋለች። ይህንን ጉዳይ አንድ ብለን እንቀጥል።
ከአሁን ቀደም በየትኛውም ሀገር ዜጎች ተደርጎ በማያውቅ ንቅናቄ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵ ያውያን ከወንድምና እህት የኤርትራ ዜጎች ጋር በመተባበር በዓለማችን ታላላቅ አደባባዮችና በወሳኝ የመንግሥታት ቢሮዎችና የኤምባሲ ጽ/ቤቶች ፊት ለፊት “ከውዷ ኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ!” በማለት የሚያደርጓቸው ሰላማዊ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን የሚያስደምሙ ክስተቶች ብቻም ሳይሆኑ የተኙትን የሚቀሰቅሱ፣ ያሸለቡትን የሚያጀግኑ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ጭምር ናቸው። “ለካስ እንዲህም አለ!” በማለትም ዜጎቻቸው መነቃቃት መጀመራቸውን ደጋግመን እያስተዋልን ነው። ለአፍሪካውያን ወገኖቻችንያበረከትነውን ይህንን በረከት ሁለት ብለን በመቁጠር ንባባችንን እንቀጥል።
በእርዳታና በልማት ስም “ካሮትና ዱላ” እያሳዩ አፍሪካን ካልጋለብንብሽ የሚሉ መንግሥታትና የተራድኦ ተቋማት በኢትዮጵያ መንግሥት ቆራጥ አቋም ሴራቸው በድፍረት እየተጋለጠ “ከስንዴ በላይ ሉዓላዊነት” ግድ ብሎን አልደፈር ባይነታችን አንገታቸውን እያስደፋቸው መሆኑ ለአፍሪካውያን ራስን የመቻል ጥረት እንደ ጽኑ መልሕቅ አርአያ እየሆነ ስለሆነ የሚያስተላልፈው መልዕክት ትርጉሙ የላቀ ነው። ይህንን አስተዋጽኦ አራት ብለን እንያዘው።
ስምና ክብራቸውን፣ የሙያ ሥነ ምግባራቸውንና ቃል ኪዳናቸውን እንዳልባሌ ነገር አርክሰው በሉዓላዊ ጉዳዮቻችን እየገቡ ካልፈተፈትንና ካልፈነጨን እያሉ የሀሰት መርዝ እንዲነሰንሱ የተሰለፉብን አንዳንድ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት ደጋግመው የቀመሙብን መርዝ በተባበረ የኢትዮጵያውያን ድምጽ ውሸታቸው መጋለጡ ለአፍሪካውያን ቤተሰቦቻችን ትልቅ ድፍረትን የሚያጎናጽፍ ጀግንነት ነው። ይህንንስ ጉዳይ አምስት ብለን ብናስመዘገብ ተገቢ አይሆንም?
”ነቅናቂው ነቅንቆ ቢያነቃንቀው፣
የተነቀነቀ ነቅንቆ ጣለው።‘
የሚለው የቀደምት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዝነኛ የትግል ግጥም ለእነዚህ ተንበርካኪ የሚዲያ ተቋማት በዚህ አጋጣሚ ቢጠቀስ ከወቅቱና ከዐውዱ ጋር በሚገባ የሚገጥም ስለመሰለን አስታውሰነዋል።
ቀዳሚዎቹ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ መሪዎች፤ ማርክስ ጋርቬዬ፣ ክዋሚ ንኩርማ፣ ጁሊዬስ ኔሬሬ፣ አሊ ሙዙሪ፣ ጆሞ ኬኒያታ፣ አህመድ ሴኩቱሬ፣ ፍራንዝ ፋነን፣ አሞጽ ዊልሰን እና በርካታ ያልተጠቀሱ ባለዝና የጥቁር ሕዝቦች መሪዎችና የአፍሪካ አባቶች የዛሬውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) በሳል የአመራር ስልትና ጥበብ በሕይወት ኖረው ቢመለከቱ ኖሮ ምን ብለው ይመሰክሩ ይሆን? ምናልባት እንዲህ ብለው ተስማምተው በአንድ ቃል አድናቆታቸውን ሳይገልጹ ይቀራሉ፤ “እኛ በዘመናችን ካፈጠጠውና ካገጠጠው የቅኝ ግዛት ጦርነት የደም መስዋዕትነት ከፍለን በመፋለም አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ተላቃ ነፃነቷን እንድትጎናጸፍ አድርገናል።
ታላቅ ወንድማችን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከመሯት ምድር የበቀልከው አንተ ጥበበኛ መሪ ዐቢይ አሕመድ ሆይ አፍሪካን የፊጥኝ አስረን ካልበዘበዝን ከሚሉ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ተናንቀህ ከዘመነ አቻዎችህ ወንድምና እህት መሪዎች ጋር አህጉራችንን እንድትታደጋት በህያው ድምጻችን አደራ ብለንሃል! ጦርነቱ የእናንተ ድሉ ደግሞ የመላው አፍሪካ ስለሆነ እንኳንም ደስ አለህ!” አይሉም ትላላችሁ? የጠቅላይ ሚኒስትራችን መልስስ ይህ ሊሆን እንደሚችል መገመት አንችልም።
”የጀግኖች ደም ጥሪ ቃሉ ቀሰቀሰኝ፣
ለታሪክ አደራ ለድል ታጠቅ አለኝ።”
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿና በአምላኳ ተራዳኢነት ሁሌም እንዳሸነፈች ትኖራለች። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014