በእኛ አገር ሁሉም ነገር ምክንያት አለው። ዝም ብሎ ነገር የለም። ምናልባት ችግሩ ልክ እንደ የአሁኑ የእነ አሜሪካ አስተዳደር ያንን ምክንያት ለማወቅ አለመፈለግ፤ ወይም ከተገኘም በኋላ ምክንያቱን አለመረዳት፤ መረዳት አለመቻል፤ ለግል እውርና ስውር አላማ ሲባል በጊዜያዊ ድንቁርና ቁጥጥር ስር መዋል። “ጉሮ ወሸባዬ …”ም እንደዛው ነው፤ ያለ ምክንያት አልተፈጠረም፤ ያለ ምክንያትም አልተዜመም፤ ያለ ምክንያትም ሕዝባዊ፣ የሕዝብ ሀብት አልሆነም። አዎ፣ “ጉሮ ወሸባዬ …” ሕዝባዊ/የሕዝብ ዜማ እንጂ የግል አይደለም።
ሕዝባዊ መሆን ደግሞ መታደል ሊሆን ይችላል እንጂ በቀላሉ የሚገኝ፣ አቦ ሰጡኝ አይደለም፤ በመሆኑም፣ “ጉሮ ወሸባዬ …” የሚለው ትውፊት ያለፈባቸውን ታሪካዊና ባህላዊ ውጣ ውረዶች በቀላሉ መገንዘብ ይቻላልና፣ “ጉሮ ወሸባዬ …”ን ዛሬም፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ብናነሳው አውዱ አሳምሮ ይፈቅድልናልና “ጉሮ ወሸባዬ …”ን እያዜምን እንቀጥል።
በስነቃል ጥናት ሂደት የማይዘለሉ ጽንሰ ሀሳቦች ቢኖሩ የስነቃሉ (ተረቱ፣ ፉከራው፣ ቀረርቶው፣ ሽለላው …) መከሰቻ ስፍራ፣ ከዋኙ፣ አከዋወኑ ወዘተ (ወይም፣ በ”ማን፣ ምን፣ በምን፣ ለምን፣ እንዴት፣ የት፣ መቼ?” ጥያቄዎችን መመለስ) ናቸው። አንባቢ እነዚህን ታሳቢ እያደረገ፣ የጎደሉትን እየሞላና በራሱም እያጣጣመ “ጉሮ ወሸባዬ …”ን እንዲያዜም እናሳስባለን። ይህንን ስንል ይህ ጽሑፍ “ጉሮ ወሸባዬ …”ን ከወቅቱ አኳያ ብቻ ስለሚቃኝ እንጂ የንፉግነት ባህርይ ኖሮን አይደለም።
“በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሃ ይጠጣል” እንደሚባለው፣ እድሜ ለአሸባሪዎች አገርና ህዝብ ጦርነት ውስጥ ከገቡ አንድ አመትን ዘለሉ። ይሁን እንጂ ያ ሁሉ ሰቆቃና እሮሮ መጥቶ መጥቶ ማለቂያ ምዕራፉ ላይ ደርሷል። ለመቋጫውና ለአሸባሪው ቡድን ግብአተ መሬት ማጠቃለያ ለመስጠትም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ከሄዱ እነሆ ሳምንት እያለፋቸው ነው። በጦር ግንባር ጦር እየመሩ ነው እያልን ነው። ከሚመሩት ጦር ግንባርም በእለት እለት የድል ዜና እየተሰማ ይገኛል። ለዛሬው “ጉሮ ወሸባዬ …”ም መነሻ ምክንያት ይኸው መሆኑን መግለፅ ተገቢ ነው።
ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ፣ (2 ጊዜ)
ዘማች ድል አ’ርጎ ሲገባ።
ዋናው ይሄ ነው። እኛ ግን ለዛሬው፣ ከያዝነው ጉዳይና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር አብሮ ተባብሮ እንዲሄድልን፤
“ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ፣ (2 ጊዜ)
ዐቢይ ድል አ’ርጎ ሲገባ።” ብለነዋል፤ ዐቢይም፣ ዘማችም፣ ጠቅላይ ሚኒስትርም፣ የጦር መሪም አዋጊና ተዋጊም ሆነው ግንባር ገብተዋልና “ዐቢይ ድል አ’ርጎ ሲገባ።” የሚለው ትክክልና ተገቢውን ቦታ አገኘ እንጂ የዜማና ግጥም መፋለስ አያጋጥመውም።
“አፋር እያለ ኢትዮጵያ አትደፈርም፡፡” ላሉት ለአቶ አወል አርባ (የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳደር)ም ይሄው “ጉሮ ወሸባዬ …” ይገባቸዋልና “ጉሮ ወሸባ …” እንልላቸዋለን። ሱማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጎን እንድትሰለፍ በማድረግ የጋራ ፊርማቸውን ለማኖር እንዲበቁ ላደረጉት ለሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሙስጠፌም “ጉሮ ወሸባዬ …” ስንል በክብርና በፍቅር መሆኑ ይታወቅልን ዘንድ አደራችን ከባድ ነው።
በሰሜን ሸዋ ጠላቱን እምሽክ እያደረገ ላለው ከ”ጉሮ ወሸባዬ …” በተጨማሪ “የሸዋ አበባ ያብባል ገና”ን እናዜምለታለን።
“ወንድማማች እና እህትማማች ሕዝቦች ነን እኔ በዚህ ላይ ችግር የለብኝም፡፡ የኔ ችግር ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን ከሚሉ ሐይሎች ጋር ነው፡፡” በማለት ፊቱን ወደ ግንባር ያዞረውና መላ አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ያስተላለፈው ኃይሌ ገብረሥላሴም ሆነ ከሞቀ አልጋቸው ወደ አገር ቤት በመግባት ግንባር የተሰለፉት አትሌት ሌሊሳን፣ አርቲስትና አንቂው ታማኝ በየነ፤ እንዲሁም ጠሚውን ተከትለው ወደ ግንባር ላቀኑት ሁሉ ይገባቸዋልና ለእነሱም “ጉሮ ወሸባዬ ወሸባ …” ስንልላቸው በጋራ ነው።
“ይህንን የጋራ ዜማ በጋራ ለማዜም የተጣደፈው ሕዝብ ብዛት ስንት ነው?” ሁሉም ጊዜው ሲደርስ ይታያልና እስከዛው በግልም “ጉሮ ወሸባዬ …” ማለት ይቻላልና እያልን መቆየት እንችላለን። መልሱን “አሁኑ የግድ” ከተባልንም ከ110 ሚሊዮን እንደማያንስ እቅጩን መንገር እንችላለን።
ምንም እንኳን “ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ” ለሁሉም ነው ብንልም ልክ ከኢትዮጵያ ወራሪ ፋሺስት ጣሊያን ጋር እንኳን ሳይቀር አብረው፣ ለሆዳቸው አድረው፣ የወገናቸውን ስጋ የበሉ፣ ደማቸውን የጠጡ አድር-ባይ ባንዳዎች ሁሉ፣ ዛሬም ያንኑ የደገሙትን አይመለከትምና እን ባንዶች ይህንን አሁኑኑ ሊያውቁት ይገባል – “ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ” አይመለከታቸውም!!!
በዚህ ባለንበት ወቅት “ጉሮ ወሸባዬ” ሊዜምላቸው የሚገቡ መሰረታዊያን ቢኖሩ ሁለት ናቸው። የዚህ ከባእዳን ጋር ወግኖ አገሩን ለጠላት የሸጠ፣ የእናት ጡት ነካሽና የታሪክ አተላ ግብአተ መሬት ሲፈፀምና በጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አህመድ የሚመራው ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ድል አድርጎ ሲመለስ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ
ህዝብ ታላቁን የህዳሴ ግድባችንን አጠናቅቆ ሲያስመርቅ። በቃ – ሁለቱም እኩል “ጉሮ ወሸባዬ” ያስፈልጋቸዋልና ለዜማው ቢቸኮል ማንንም ሊገርም አይገባም።
በአገራችን:-
ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ፣
ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ፣
ጀግናው ድል አድርጐ ሲገባ።
ተብሎ ሲዜም ዛሬ አዲስ አይደለምና ለዜማው መዘጋጀታችን ለማንም ብርቅ ሊሆን አይገባም። የሚጠይቅ ካለም “ልማዱ ነው የኛ ልጅ … አሃሃ … ልማዱ ነው …” ስንል እንደኖርነው ሁሉ እኛም “ልማዴ ነው …” ብለን ልንመልስለት ወቅቱም፣ ታሪክም ግድ ይለናልና “ጉሮ ወሸባዬ” ስንል በጋራ ነው። በጋራ የምንልበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ዜማው በጋራ መዜም ስላለበት ወይም ሕዝባዊ ትውፊት ስለሆነ ብቻ አይደለም፤ በጋራ፣ (ድምፃዊያን አንድ ላይ እንደሚሉት) የምናዜምበት ዐቢይ ምክንያት በዐቢይ አዋጊነት በጀግናው ሰራዊታችን ተዋጊነት የጋራ ጠላታችን ስለተደመሰሰ ነው።
“ጉሮ ወሸባዬ” በቅድሚያ የሚመለከታቸው፣ ከመሪነት መንበራቸው ወርደው ወደ ጦር ግምባር በማምራት እየተዋጉና እያዋጉ የሚገኙትን፤ በድል ላይ ድል እያበሰሩን ያሉትን ጠ/ሚ ዐቢይን ሲሆን፤ በእግረ መንገዳችን ግን አንድ በድሮዎቹ ጀግኖች መሪዎቻችን ጊዜ የተከሰተ ስህተት በእሳቸውም እንዳይደገም ከወዲሁ ጥንቃቄ አንዲያደርጉ በማሳሰብ ነው።
ዐቢይ ድል አድርገው ሲመለሱ፤
ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ፣ (2 ጊዜ)
ዐቢይ ድል አ’ርጎ ሲገባ።
በእኛ በኩል እያልን አደባባይ ወጥተን ለማዜም፣ እግረ መንገዳችንንም በሽለላ፣ በቀረርቶ፣ በፉከራ … ድላችንን ለአለም ለማሰማት ዝግጅታችንን ጨርሰናል። ይህንን ባልንበት አንደበታችን፤
እምዬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ።
የሚለውን የምሬት ቃል-ግጥም እንዳንደግመው ስጋት አለና ዐቢያችን ይሄንንም ልብ እንዲሉልን ባንዳንና አሸባሪን በአንድ ጉድጓድ እዛው ጨርሰው፣ ቀብረውልን እንዲመጡልን ከወዲሁ አደራ ስንል በተለመደው አክብሮትና ፍቅር ነው።
ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ፣
ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ፣
ዐቢይ ድል አ’ርጎ ሲገባ።
ኢትዮጵያ አሸነፈች!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014