ህዳር 20 ቀን በጋሻና ውጥረቱ አይሏል::የጠላትና የወገን ጦር ተፋጠዋል፤ ጠላት በጋሸና ግንባር የሠራው 14 ኪሎ ሜትር ከፍተኛ ምሽግ ሊሰበር ቀን ተቀርጦለታል:: የወገን ጦር አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ማጥቃት ለመጀመር ትዕዛዝ እየጠበቀ ነው:: የኢትዮጰያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖው በጋሸና ግንባር የሚገኘውን የሽብር ቡድኑን ምሽግ ለመስበርና በቆፈረው ምሽግ ለመቅበር ህዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ ማጥቃት ጀመሩ:: ታንከኛው አስር አለቃ ጌቱ ፈይሳም በዚሁ ግንባር ጠላትን ተፋልሟል::
አስር አለቃ ጌቱ ፈይሳ በመከላከያ ሠራዊት የታንክ ሹፌር ነው::አሸባሪው ሕወሓት በጋሸና የቆፈረው ምሽግ አደገኛ ነው፤ የወገን ጦር ይህን ምሽግ ደርምሶ ጠላትን ለመቅበር ማጥቃት ጀመረ፤ ቡድኑ ይህን ምሽግ ተጠቅሞ ያለ የሌለ አቅሙን አሟጦ ቀኑን ሙሉ ሲከላከል ውሎ ሲከላከል ማደሩን ይናገራል:: ውጊያውም ቀጠለ ፣ ወገንም ፋታ የለሽ ማጥቃቱን መቀጠሉን ያወሳል፡፡
እሱ የሚያሽከረክረው ታንክም በጠላት ላይ እሳት እየተፋ ማደባያቱን ቀጥሏል:: ታንኩ ወደ ጠላት ምሽግ ተጠግቶ ፋታ የለሽ ጥቃት እያደረሰ ነው:: በወታደራዊ ቋንቋ ታንኩ «ረገጣ ገባ» ይላል:: ወጊያውን ጨለማው አላቆመውም::በጨለማ ውጊያ ታንኩ መብራት ቢኖረውም መብራት መጠቀም ራስን ለጠላት ታንክና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ለአደጋ ያጋልጣል ይላል ጀግናው አስር አለቃ ጌቱ::
በጨለማ ወስጥ ጦርነቱ ቀጥሏል:: አስር አለቃው የሚያሽከረክረው ታንክም ወደፊት እና ወደ ኋላ እየተንቀሳቀሰ ያለ ከልካይ ጠላትን ማደባየቱን ቀጥሏል::በዚህ ጊዜ ነው ታንኩ ቦታ ለመያዝ ወደ ኋላ ሲንቀሳቀስ ጨለማ ስለነበር መንገድ ስቶ ወደ ገደላማ ቦታ ገባ:: ነገር ግን ታንኩ ጨርሶ ገድል ውስጥ አልገባም:: ይህን በቅርብ ርቀት የተመለከተው የጠላት ኃይል ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ታንኩን ለማቃጠል ወደ ታንኩ መጠጋቱን አስር አለቃ ጌቱ ይመለከታል:: በታንኩ ውስጥ የሚገኘውን ክላሹን አቀባብሎ ታንኩን ለማቃጠል የመጣውን ጠላት አንድ በአንድ መልቀሙን ይናገራል::
በዚያ ጊዜም የወገን ጦር እያጠቃ ወደፊት እየገሰገሰ ወደ ታንኳ መጠጋቱን አስር አለቃ ጌቱ ይገልጻል:: ከገደል አፋፍ ላይ የቆመው ታንክ ለወገን ጦር ሽፋን ለመስጠት በሚያደርገው እንቅስቃሴም መንገድ ጠርዝ ላይ የነበረው አካሉ ወደ ገደል ውስጥ በመግባቱ መገልብጡን ይናገራል፡፡
ይህ ሲሆን አስር አለቃ ጌቱ ታንኩ ውስጥ ነበር:: ታንኩ የተገለበጠው በበሩ በኩል በመሆኑ መውጣት አስቸጋሪ ሁኖበታል:: ከአርባ ቶን በላይ የሚመዝን ታንክ ገፍቶ ማንሳት ከባድ በመሆኑም ጓዶቹ መሞቱንና መኖሩን ማወቅ አልቻሉም:: በዚህ ምክንያትም የአስር አለቃው ምድብተኞችም ጓዳቸው ታንኩ ውስጥ ተሰውቷል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል:: ከዚህ ተነስተውም ለበላይ አካልም አስር አለቃ ጌቱ ተስውቷል ብለው ሪፖርት ማድረጋቸውን ነግረውታል::
ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው ፤ ሌሊቱም ሊነጋ ነው:: የብርሃን ወጋግን እየታየ ነው:: ሞቷል ተብሎ ሪፖርተ የተደረገው ወታደር ከተገለበጠችው ታንክ ስር ብቅ አለ:: ጠላትም በቅርብ ርቀት ስለነበር የጥይት እሩምታ ከፈተበት:: እሱም በክላሹ ጠላትን እየተከላከለ ከወገን ጦር ጋር መቀላቀል ቻለ:: ሞቷል ብለው ሪፖርት አድርገው የነበሩ ጓደኞቹ ያዩትን ማመን እንደከበዳቸው ያስታውሳል::
ታንኳ በተገለበጠች ጊዜ ከታንኳ ውስጥ ለመውጣት አስቸጋሪ ነበር የሚለው አስር አለቃ ጌቱ፤ ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ የታንኩን በር ከፍቶ ሊወጣና ከወገን ጦር ጋር ሊቀላቀል መቻሉን ይናገራል:: ጠዋት ላይ ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጠላት ሲመካበት የነበረው ምሽግ በወገን ጦር ሲደረመስ በማየቱ ደስታውን እጥፍ ድርብ ማድረጉን ይናገራል::
እንደ ጀግናው አስር አለቃ ጌቱ ገለጻ፤ በወቅቱ የነበረው ውጊያ በጣም ከባድ ነው:: ምክንያቱም ወያኔ ምሽጉን የቆፈረው በዶዘር ነው:: ወያኔ ከቆፈረው ምሽግ በተጨማሪ በምሽጉ ዙሪያ በሚገኙ የአርሶ አደር ቤቶች ውስጥ መሽጎ ስለነበር ምሽጉን መስበር አስቻጋሪ አድርጎታል:: ሆኖም በክንደ ነበልባሉ መከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጠዋት የጁንታው ምሽግ ተደረማመሰ:: ጁንታውም «እግሬ እውጪኝ» ብሎ ፈረጠጠ::
«የዱባ ጥጋብ ያለስንቅ ያዘምታል፡፡» እንዲሉ አሸባሪው ሕወሓት አቅሙን ሳያውቅ በጥጋብ ተነሳሰስቶ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ቢወርም የወረረበትን ቀን እስኪረግም ድረስ በጀግናው መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ በአፋር ልዩ ኃይልና በሌሎች የፀጥታ ኃይሎች እየተቀጠቀጠ ይገኛል:: የወገን ጦርም ድል በድል እየተጎናጸፈ መሆኑን አስር አለቃ ጌቱ ፈይሳ አውስቷል፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም