ጠባቧ ክፍል የተለያየ ቀለም ባላቸው አምፖሎች ደማምቃላች፣ ቦግ እልም በሚለው የብርሀን ፍንጣቂ ውስጥ አንዲት ሴት ትታያለች፡፡ ከፊት ለፊቷ ሰላሳ ሁለተኛ ዓመቷን የሚያሳብቅ ሻማ ከነጭ ቶርታ ኬክ ጋር ተሰይሟል። የተለያዩ አይነት መጠጦች እንደ ክብር ዘበኛ የሙዚቃ ባንድ የእድሜዋን ቁጥር አጅበውታል፡፡ ማርታ ወደ ኋላ መለስ ብላ የመጣችበትን ሰላሳ ሁለት ዓመት የህይወት ጎዳናዋን አየችው፡፡
ያልተኖረ ወጣትነት፣ ታይቶ የጠፋ ልጅነት ግሳንግሱን ይዞ ፊቷ ድቅን አለባት። ሁሌ ትናንትን ስታስብ ራሷን ትጸየፈዋለች፡፡ ምድር ላይ በኖረችባቸው ሰላሳ ሁለት ዓመታት ውስጥ አንድም የሚያኮራ ነገር አለማድረጓ ያበሳጫታል፡፡
ጊዜ የእሷን የእድሜ ቁጥር ከማግዘፍ ባለፈ የፈየደላት አንድም ነገር አልነበረም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ ሁሉ ጉዞዋ ውስጥ የኔ የምትለውን የነፍስ አጋር አለማግኘቷ ያስከፋታል፡፡ የእጅ ሰዓቷን አየች፤ ሰላሳ አምስት ደቂቃዎች ቀርተዋታል። ሳምሶን ሊመጣ፤ አስረኛው ወንድ ሆኖ ወደ ህይወቷ ሊገባ እየጠበቀችው ነው፡፡ ሳምሶን ምድር ላይ ከተፈጠሩ ወንዶች ሁሉ አስፈሪ ፊት አለው፡፡
ሲበዛ ጥቁር ነው፣ በጭስ የጠቆረ ግርግም የመሰለ፡፡ ሁሉም ሴቶች መርጠው የተውት የሚመስል አስቂኝ ፍጥረት፣ በጥቁር ጸጉሩ መሀል እንደ ጋን ስር እንጉዳይ ያቸፈቸፈ ሽበት የወጣበት አጭርና ዘርፋጣ ወንድ፡፡ ዘጠኝ ወሯ እንደደረሰ ነፍሰ ጡር ሴት ሆዱ ወደ ፊት የተነረተ ቦርጫም፡፡ ጥርሶቹ በሲጋራና ጫት የበለዙ፤ ለንቦጫም..ሳምሶን ይሄን ሁሉ ነው፡፡ ይሄን ወንድ ልታገባው ነው..፡፡ እድሜው ስንት ይሆን? ጠፋባት፡፡ ብቻ ግን አንቱ አትበይኝ እያለሲቆጣት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ከፊቱ አቀማመጥ ተነስታ ብትገምት እንኳን የእሷን እድሜ ሁለት እጥፍ ቀርጥፎ እንደሚበላ እርግጠኛ ነበረች፡፡ አባቷን ልታገባ ነው፡፡
ከተቀመጠችበት ተነስታ ወደ በሩ ተራመደች። አፍላነት የከዳቸው ጡቶቿ እንደ ንጉስ አሽከር አንገታቸውን ወደ መሬት አጉብጠው እንደ እሷ በትካዜ ተውጠዋል፡፡ የበሩን ጉበን ተደግፋ በሀሳብ ጭልጥ አለች፡፡ ትላንትን ገላ መቅበር ያቃታት ናት፤ ትላንት ዛሬ ቢሆን ትላለች፤ በትላንትናዋ ውስጥ የምታስተካክላቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ትላንትና ሲበዛ ኩራተኛ፣ ሲበዛ ፌዘኛ ነበረች። ውበቷን ሳታስቀድም የተራመደችው አንድም ጎዳና አልነበረም፡፡
በሩ ላይ እንደቆመች ዛሬ ቢሆን ወደምትሻም አምና ተጣደፈች። የመጀመሪያውን የፍቅር ጥያቄ ያቀረበላት ወንድ ምሳሌ ነበር፤ በሩ ጉበን ላይ እንደ ቆመች ምሳሌ ትዝ አላት፡፡ ያኔ ገና አስራ ስምንት ዓመቷ ነበር..፡፡ አቤት! ድምጹን ስትወድለት፤ ድምጹ ዛሬም ድረስ ከነውበቱ ይታወሳታል፡፡ ግን ናቀችው፤ ሂድና ቢጤህን ፈልግ ስትል በጓደኞቹ ፊት አዋረደችው፡፡ ያ ማን ነበር ደግሞ የአንደኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ እያለች አላስወጣ አላስገባ እያለ ሲያስቸግራት የነበረው? ትዝ አላት፤ ፍስሀ ነው፡፡ አሁን እሱ ምኑ ይጠላል? ምኑን ጠልታ እንዳባረረችው እሷም አታውቀውም። በህይወቷ ከባድ ጥፋት ያጠፋችው የፍሰሀን የፍቅር ጥያቄ አለመቀበሏ ይመስላታል።
ዛሬ ላይም ሆነ የትላንቱ መልከመልካሙ ፍሰሀ ይናፍቃታል፡፡ ልቧ ወደሌላኛው ወንድ በሀሳብ ተሽቀነጠረ፤ መልህቋን ሳትጥል እዛም እዚም ዋዠቀች፡፡ ያ ማን ነበር ፊቱን ከዝንጀሮ ላይ የሰረቀው የሚመስለው፣ በቤት መኪናው እየመጣ ካልሸኘሁሽ እያለ የሚጨቀጭቃት? አስታወሰችው፤ ማስረሸ ነው፡፡ ይሄን ፊት ይዘህ እኔን ማግባት ያምርሀል? መጀመሪያ መስፍን ኢንጅነሪንግ ሄደህ ፊትህን አስቀይረህ ተመለስ ነበር ያለችው፡፡ አቤት ግፏ..፡፡ ደግሞ ይስሀቅ ትዝ አላት፤ በልቧ ውስጥ እውነት ቢኖር ኖሮ ይስሀቅ የእሷ ባል ይሆን ነበር፡፡
የትኛውም ወንድ እንደ ይስሀቅ እውነት ይዞ አልቀረባትም። ‹የእውነት ነው የማፈቅርሽ፣ ህይወቴን ሙሉ ካንቺ ጋር ማሰለፍ እፈልጋለሁ› እያላት ነበር የገፋችው። ‹የኔ ነፍስ ላንቺ ነው የተፈጠረችው፤ ካንቺ ሌላ ማንንም ማፍቀር አልችልም› እያላት ነበር የናቀችው፡፡ ሌላው ይቅርና እየሰደበችው የሚከተላት፣ እየናቀችው የሚያከብራት የነፍሱ የእውነት ጠልን አይረሳትም። አሁን ላይ ስታስበው ይስሀቅ ወደ ህይወቷ ፍቅርን ብቻ ይዞ አልነበረም የመጣው..ብዙ ነገሮችን ይዞላት ነበር፡፡ ትላንት ይሄን ሁሉ ነበረች፡፡ ፍቅርን በንዋይ የምትመዝን ሴት፡፡
የመጣላትን በረከት ስትገፋ፣ የቀረባትን ስትሸሽ ሀያ አምስተኛ ዓመቷን አከበረች፡፡ የፍቅር ታሪኳ ግን አልቆመም፡፡ ሀያ አምስተኛ ዓመቷ በአሮን ፍቅር ተጀመረ፡፡ በፍቅርሽ ላብድ ነው፣ አንቺን ማግባት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ሲል አሮን አማላጅ ላከባት፡፡
በቤተሰቡ ሀብትና በሚነዳው መኪና ሊያማልላት ሞክሮ አልቻለም፤ በመጨረሻ ብዙ ጥሮ ምሳ ሊጋብዛት ቀጠራት፤ ከዛን ቀን ወዲህ ግን ደግማ አላገኘችውም፡፡ ትላንትና እንዲህ ነበረች፤ በኩራትና በማንአለብኝነት የተሞላች፡፡ በነፍሷ ውስጥ ፍቅርና እውነትን አንቃ የገደለች፡፡ የሰዎች እንግልት ያስደስታታል፣ አፍቅረዋት ሲያጧት፣ ተመኝተዋት ሲከተሏት ነፍሷ ሀሴት ታደርግ ነበር፡፡ መፈለጓን፣
መወደዷን የምትለካው በሰዎች ጭንቀትና መከራ ነበር። በሆነ አጋጣሚ ደጀኔ ከሚባል ሰው ጋር ተዋወቀች። ከብዙ ውትወታ በኋላ ሊገናኙ ተቀጣጠሩ። ከእሱ ጋር መታየት የሰማይን ያክል ከብዷት ነበር። ስትቀርበው ግን እንደምታየው አይነት አልነበረም፡፡ ማንም የሌለው ብዙ ነገር ነበረው፡፡ ሲበዛ ደግ ነበር፡፡ እሱ ጋ ያየችውን መልካምነት እስካሁን ድረስ የትኛውም ወንድ ጋ አላየችውም፡፡ ግን ምን ያደርጋል አትመጥነኝም ብላ አባረረችው፡፡ እድሜዋ ሄደ፡፡
የሰፈሩ ሰው ቆሞ ቀር እያለ ይሰድባት ጀመር፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ የእድሜዋ ማምሻ ላይ ለአርባ አራቱ ተስላ እንደምንም ብላ ከአንድ ሰው ጋር ተዋወቀች፡፡ በዝናብ ስትደበደብ አይቶ መኪና አቆመላት፡፡ እንደ ድሮው ቢሆን ዞራም አታየውም ነበር። ሳታመነታ ገባች፤ ቤቷ አደረሳት፡፡ ዝም ብሎ መለያየት ነውር ሆኖ ስልክ ተለዋወጡ፡፡ ሁለት ቀን ተደዋወሉ..በሶስተኛው ቀን አብረን እንደር አላት፤ ካላገባኸኝ አብሬህ አላድርም ብላው ተለያዩ።
በሌላ ቀን ሱፐር ማርኬት ውስጥ ገባች፤ ትርፍ ጊዜዋን የምታሳልፈው ወንድ በመፈለግ ሆኗል፡፡ ለይምሰል ጉዳይ ያላት ትምሰል እንጂ በምትሄድበት ሁሉ ፍላጎቷ ባል የሚሆን ወንድ መተዋወቅ ነበር፡ ፡ ቶሎ ተዋውቃ ቶሎ ማግባት ትሻለች፤ ቆሞ ቀር ከመባል ለመዳን፡፡ ግን እንዳሰበችው የሆነ ምንም ነገር አልነበረም፤ ሰላሳኛ ዓመቷን ለብቻዋ አከበረች፡፡ አንድ ቀን ራሷን ጠልታ ስለሞት እያሰበች ለብቻዋ ቁጭ ብላ ነበር፡፡ ከኋላዋ አንድ ድምጽ አስደነበራት ወደ ኋላዋ ዞረች ሲጋራ ከሚያጨስ አንድ ሰው ጋር ተገናኘች፡፡ ከሳምሶን ጋር.. በሰላሳ ሁለተኛ ዓመት የልደት በአሏ ላይ እመጣለሁ ብሏት እየጠበቀችው ነው፤ ይመጣ ይሆን?
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኀዳር 24 / 2014