አትሌቲክስ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ስፖርታዊ የውድድር መድረኮች በውጤታማነት ስሟን ለዓለም ያስተዋወቀችበትና ገናናነትን ያተረፈችበት መሆኑን ብዙዎችን የሚያስማማ ሀቅ ነው።ኢትዮጵያና አትሌቲክስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች እንደመሆናቸውም ብርቅዬ አትሌቶቿ በዓለማችን ትልቁ የስፖርት መድረክ በኦሊምፒክና በሌሎችም ሻምፒዮናዎች ወርቅ ተለይቷቸው አያውቅም።
ከአትሌቲክስ ልዩ ልዩ ውድድሮች መካከል ደግሞ የረጅምና መካከለኛ ርቀት ሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተጠቃሽ ውጤት ያስመዘገቡባቸው የውድድር ፈርጆች ናቸው።በተለይም በረጅም ርቀት በዓለም ትኩረት ያገኘችበትና ኩራትን የተጎናጸፈችበት ስለመሆኑ የአትሌቶቻችን ድሎች ማሳያዎች ናቸው ።
አትሌቶቻችን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት ዓለምን ያስደመሙባቸው ወቅቶች በርካታ ናቸው።በዚህ ረገድ በሲድኒ ኦሊምፒክ የታየው ወርቃማ ታሪክ «አረንጓዴው ጎርፍ»ን (green flood ) ማስታወስ በቂ ምስክር ይሆናል።
ምንም እንኳን በዚህ ምልክ በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የረጅምና መካከለኛ ርቀት ሩጫ ውድድሮች ፈርጥ መሆን ቢችሉም አሁን ግን ይህ የቀደመ ውጤታማነታቸው አብሯቸው አለመሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ይታያሉ።
ለዚህ የውጤት መራቅም በተለይ በአህጉርም ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዓመታትን ጠብቀው እስካልሆነ በአምስትና አስር ሺ ሜትር የሚካሄዱ ውድድሮች በእጅጉ መቀንስ፣ በምክንያትነት ይጠቀሳል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የጎዳና ውድድሮች መበራከታቸውን ተከትሎ በርካታ አትሌቶች ለአምስትና አስር ሺ ሜትር ውድድር የሚረዳ ልምምድ ከመስራት ይልቅ ለጎዳና ውድድሮች ትኩረት በመስጠት ወደዚያው መፍለሳቸው ዋነኛው ችግር ሆኖ ይጠቀሳል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም በመም ውድድሮች በተለይ የአምስትና አስር ሺ ሜትር የኢትዮጵያን የቀድሞ ስምና ክብር በማስመለሱ ሂደት በአሁኑ ወቅት ዋነኛ ተግዳሮት የሆነውን የአትሌቶች ለጎዳና ውድድር ትኩረት መስጠት እና ወደ ጎዳና ውድድሮች መፍለስን እንዴት በመከላከል ውጤታማ መሆን ይቻላል ሲል የዘርፉ ባለሙያዎች አነጋግሯል።
ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አትሌቲክስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ ተፈራ፤ቀደም ባሉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአምስት እና አስር ሺ ሜትር ውድድሮች የዓለም ትኩረት ማረፊያ የነበረችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርቀቱ ያላት ስምና ክብር በቀድሞው ልክ አለመሆኑን ይስማሙበታል።
የዚህም ዋነኛ ምክንያት በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ አገሪቱ በርቀቱ የነበራትን ክብር ነገ ከነገ ወዲያ አስጥብቀው ይቀጥላሉ የተባሉ አትሌቶች ጭምር ወደ ጎዳና ውድድሮች ፈልሰዋል የሚሉት አሰልጣኙ፤አሁን ከአልማዝ አያና ውጪ በርካታ አትሌቶች በጎዳና በተለይ በማራቶን ውድድር መጠመዳቸውን ይጠቅሳሉ።
ይህም ሁሉም ግላዊ ፍላጎቱን ወደ ማርካት ማድላቱና ገንዘብ ላይ በማተኮሩ የተፈጠረ መሆኑን የሚገልፁት አሰልጣኙ፤ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ማናጀሮች ትኩረት የሚሰጡት፣ አሰልጣኞችም የሚያሰለጥኑት አትሌቶችን ለጎዳና ውድድር ለማብቃት መሆኑን ይገልፃሉ።
በተለይ ማናጀሮችና አሰልጣኞች አንድን አትሌት ነገ ስለሚካሄድ የጎዳና ውድድር እንጂ በቀጣይ ወራት ስለሚካሄድ ትላቅ አህጉር አቀፍ ሻምፒዮና ላዘጋጀው የሚል ሀሳብ የላቸውም» የሚሉት አሰልጣኙ፤አትሌቶቹ ወደ ጎዳና ውድድር እንዲያዘነብሉ በማድረጉ በኩል አብዛኛው ችግር ያለው አሰልጣኞቹ ዘንድ መሆኑን ያሰምሩበታል።
‹‹የገንዘብ ጉዳይ ከሆነ ገንዘቡ በትራክ ውድድሮች ላይም አለ ›› የሚሉት አሰልጣኙ፤ በአግባቡ ከተሰራበት የትራክ ውድድርም ገንዘብ እንዳለውና ለዚህም ቀነኒሳ በቀለ፤ደራርቱ ቱሉ እነ ስለሺ ስህን የመሳሰሉ አትሌቶች በትራክ ውድድር ትልቅ ገንዘብ ሲያገኙ እንደነበር በማሳያነት በመጥቀስ ያብራራሉ።
የአገሪቱን የቀደመ የረጅም ርቀት እውቅና እና ክብር መልሶ ለማስቀጠል የመም ውድድር አትሌቶችን በልዩነት መያዝ ይገባል የሚሉት ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ፣ ለዚህም ራሱን የቻለ ህግ መውጣት እንዳለበት ነው የሚጠቁሙት፡፡ይህ እስካልሆነ ድረስ ነገም ከዚህ የከፋ አደጋ ውስጥ እንደምንወድቅ አልጠራጠርም»ይላሉ።
እንደ ዋና አሰልጣኙ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ውድድር በተቃረበ ቁጥር የጎዳና ተወዳዳሪ አትሌቶችን ወደ መም ለማምጣት ሲሞከር ይስተዋላል።ይሁንና በዚህ ዓይነት አካሄድ ውጤታማ ለመሆን መዳከር አግባብ አይደለም። እንደ የውድድሩ ባህሪም የሚገኘው ውጤትም ለየቅል የሆነውም ለዚሁ ነው።
አንድ ሻምፒዮና ሲደርስ አትሌቶች ቢያንስ ከሦስት ወራት ቀድመው ማንኛውንም የጎዳና ውድድር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ አትሌቶች ከመም ውድድሮች ይልቅ ጉዳናን ምርጫቸው ከማድረግ እንደማይ ቆጠቡ ተናግረው፣ይህ አካሄድ የመም ውድድር አትሌቶችን እስከማሳጣት እንደሚደርስም ነው የሚያስገነዝቡት።
ዋና አሰልጣኙ ይህን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚኖርበት፣ለዚህም አዲስ አሰራር መተግበር የግድ እንደሚለው ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነት ጎዳና ላይ የነበሩ አትሌቶች ከተወሰነ ወር በፊት ወደ ትራክ እንዳይመጡ፤የመም ተወዳዳሪ አትሌቶችም ከጎዳና ውድድር እንዳይመረጡ የሚገድብ ህግ መተግበር እንዳለበት ያስገንዝባሉ።
አሰልጣኝ ሙልዬ እያዩም ኢትዮጵያ በተለይ በረጅም ርቀት የመም ውድድሮች የነበራት ዝና መደብዘዙን ይስማሙበታል።የዚህም ዋነኛ ምክንያት የጎዳና ውድድሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እየተሰጣቸው መምጣቱ መሆኑን ያሰምሩበታል።
እንደ አሰልጣኝ ሙልዬ ገለፃ፤በአሁኑ ወቅት ከ27 ሺ 800 በላይ የጎዳና ውድድሮች በየዓመቱ ይካሄዳሉ። እነዚህ ውድድሮችም ከጊዜ ወደ ጊዜ አዝናኝነታቸው ተመራጭ እየሆነ በመምጣቱም አዘጋጅ አገራት የአትሌቶቹን ቀልብ በእጅጉ መቆጣጠር ከመቻላቸውም በተጨማሪ ፣በተለይ በቱሪዝም ዘርፉ ለገቢ ምንጭነት እየተጠቀሙት ይገኛሉ።
ይህ እንደመሆኑ ኢትዮጵያን በርቀቱ የመወከል አቅም ያላቸው ወጣት አትሌቶች ጭምር ወደ ጎዳና እየፈለሱ መሆናቸውን የሚያረጋግጡት አሰልጣኝ ሙልዬ፤ይህ ማለት ግን የውድድሮቹ መብዛት አትሌቶቹን ወደ ጎዳና ስቧቸዋል አሊያም ማናጀሮቻቸው በሚያሳድሩባቸው ጫና ወደ ጎዳና ውድድር ሄደዋል ለማለት እንደማያስደፍር ያስቀምጣሉ።
አትሌቶች ከትራክ ውድድር ይልቅ ለጎዳና ውድድሮች ቅድሚያ እንዲሰጡ በአሰልጣኝና ማናጀሮቻቸው በኩል ጫና ይደርስባቸዋል የሚለውን አስተያየት አሰልጣኙ አይስማሙበትም፡፡ይህ ማለት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ አትሌቶችን ለጉዳት በሚዳርግ መልኩ ለረጅም ጊዜያት ከሳምንት እስከ ሳምንት በአስፋልት ውድድር ሙሉ ስልጠና የሚሰጡ አንዳንድ ማናጀሮች የሉም ማለት እንዳልሆነም ይጠቁማሉ።
አትሌቶች ወደ ጎዳና ውድድሮች የሚፈልሱት በማናጀሮቻቸው ገፋፊነት ብቻም ሳይሆን በአብዛኛው በግል ውሳኔ ቀደም ሲል የነበሩ አትሌቶችን በመመልከት ነው የሚሉት አሰልጣኙ፤አትሌቶችም በውድድር በመካፈላቸው ብሎም ካሸነፉ የሚያገኙት ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑም የጎዳና ውድድሮችን እንዲመርጡ እያስገደዳቸው መሆኑን ያስገነዝባሉ።
አሰልጣኙ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ትላልቅ መድረኮች የአምስት እና አስር ሺ ሜትር ሩጫ የምስራቅ አፍሪካውያን መድመቂያ ነው፤ ኢትዮጵያውያንም የዚህ ድምቀት ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ ይሁንና ይህ ትዕይንት አሁን ደብዝዟል ከማለት የቀደመውን ስምና ዝናችንን እንዴት መመላስ እንችላለን የሚለውን መመለስ ይገባል ሲሉ ያመለክታሉ።
ለዚህም በቀዳሚነት የመም ውድድር አትሌቶችን እንዴት በብቃት ማፍራት እንዲሁም ወደ ጎዳና የፈለሱትን በምን መልኩ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ማድረግ ይቻላል የሚለውን የሚመለስ ተግባር መፈፀም እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
«ይህን ለማድረግ በቀዳሚነት በትራክ ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶች የሚያገኙትን ጥቅም ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚሉት አሰልጣኙ፤አትሌቶች ወደ ጎዳና የመውጣታቸው ምክንያት ህይወታቸውን ለመደጎም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ይህን ችግር ለመፍታትም በመም ውድድር ለሚካፈሉት ከፍ ያለ ሽልማት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም፣ይህ ሲሆንም ተተኪ አትሌቶች ማግኘት እንደሚቻል ያመለክታሉ።
ከዚህም ባሻገር በዚህ ዘርፍ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ማፍራት እንደሚገባ በመጠቆም፣ ለዚህም የተመረጡት ልጆች ቀጣይነት ባለው መልኩ ህይወታቸውን መምራት የሚያስችላቸው ራሱን የቻለ ፕሮጀክት መቅረጽ እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ።
እንደ አሰልጣኙ ገለፃ፤ትራክ ላይ የሰራ አትሌት ውድድር ለማግኘት አንድና ሁለት ዓመት መጠበቅ ግድ ይለዋል።ከዚህ ባንፃሩ የጎዳና ውድድሮችን ቶሎ ቶሎ ማግኘት ይችላል።ይህ በሆነበት የጎዳና ውድድር መምረጡ አይቅሬ ነው።በመሆኑም መሰል ችግሮችን ለመፍታት የውድድር ተደራሽነት መስፋት ያስፈልጋል፡፡ በመም ውድድሮች በተለይ በአምስትና አስር ሺ ሜትር የኢትዮጵያን የበላይነት የውጤት ክብር ለማስቀጠል ውድድሮችን በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ በማዘጋጀት ተደራሽነቱን ማስፋት ያስፈልጋል። ምንም እንኳን የጎዳና ላይ ሩጫዎች ተበራክተው የትራክ ውድድር ቢያንስ ሁለቱን ለማስታረቅ አትሌቶቹ ራሳቸውን ሳይጎዱ የሚካፈሉባቸው የልምምድ ዓይነቶችን ማዘጋጀትም የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል።
«የጎዳና ላይ ውድድር የግል ህይወትን ማሻሻያ እንጂ ለክብር እና ለአገር ተብሎ የሚሮጥበት አይደለም» የሚሉት አሰልጣኝ ማሙዬ፤ከሁሉም በላይ አትሌቶች ለአገርና ለክብር ያላቸውን ስሜት በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር በድጋሚ እንዲያ ረጋግጡ ግንዛቤ የማስረፅ ተግባር ማከናወን እንደሚገባም ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንትና ተወካይ አትሌት ስለሺ ስህን፤ በአሁኑ ወቅት የአስርና አምስት ሺ ሜትር የመም ውድድሮች ከቀደመው ጊዜ አንፃር ሲታይ በእጅጉ መቀነሳቸውን ጠቅሶ፣ ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል ለማለት እንደማያስደፍር አሁንም ትልልቅ ውድድሮች እንዳሉ ያብራራል።
የግል ጥቅም አትሌቶቹ ወደ ጎዳና ለመውጣታቸው ምክንያት እንደማይሆን የሚናገረው አትሌት ስለሺ፣ በመም ውድድሮች ላይ ውጤታማ መሆን ከማራቶን ባልተናነሰ በስፖንሰር፤በዳይመንድ ሊግ የመመረጥ እና ሌሎችም ረብጣ ሽልማቶች የሚያስገኝበት ሁኔታ እንዳለም ያስረዳል።ለዚህም አሁንም በመም ውድድር አልማዝና እና ገንዘቤ እንዲሁም ሰለሞን ባረጋ እየሮጡ መሆናቸውን በአብነት ይጠቅሳል።
‹‹እርግጥ ነው ማራቶን ጥቅም ሊኖረው ይችላል።ይሁንና ማራቶን በመጪዎቹ የአትሌቲክስ ዕድሜዎች የሚደረስበት ውድድር ነው›› የሚለው አትሌት ሰለሺ፤ ከጎዳና ውድድሮች በተለይም አንድ ጊዜ ማራቶን ላይ ገብቶ ሁለትና ሦስት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ጨርሶኑ መጥፋት ጉዳት እንጂ ጥቅም እንደሌለውም ነው ያብራራው።
በአሥርና አምስት ሺ ላይ የሚቆይ አትሌት ወደ ማራቶን ሲሄድ ውጤታማ መሆን እንደሚ ችልና በተለይ ወጣት አትሌቶች በልጅነት ዕድሜያቸው ወደ ማራቶን ከሚገቡ በመም ውድድሮች ላይ ብዙ ዓመታት መስራት ቢችሉ ውጤታማ ስለመሆናቸው ጥርጥር ሊገባቸው እንደማይገባም ይጠቁማል።
እንደ አትሌት ስለሺ ገለፃ፤ይህን ችግር ለመፍታት በቀዳሚነት አትሌቶች ቸኩለው ወደ ጉዳና መውጣታቸው ስህተት እንደሆነና በቀጣይ የሩጫ ህይወታቸው ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ጠንቅቀው እንዲረዱት ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዓይነት ውድድር ውስጥ ለማለፍ እንደማይጠቅም በውድድሩ ቢያልፉም ውጤታማ እንደማይሆኑ ማስረዳት ይገባል፡፡ በመም ውድድሮች በስለው ወደ ጎዳና ውድድሮች ቢሄዱ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ ማስገነዘብ የግድ ይላል።ከሁሉም በላይ የአገር ፍቅር ስሜት የሚባለው እንዲሰርፅባቸው ማድረግ ይገባል።
አንድ አትሌት ወደ ጎዳና የሚወጣው በአሰልጣኝ አሊያም ማናጀሩ ከፍተኛ ጫና እያሳደረበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ መሆኑን የሚመሰክረው አትሌት ስለሺ፤እነዚህ ገንዘብ ተኮር የሆኑ አሰልጣኝና ማናጀሮችን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ይህን ችግር መፍታትም የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት መሆኑን ይናገራል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ፤በዓለም አቀፍ ደረጃ የመም በተለይ የአሥርና አምስት ሺ ሜትር ውድድሮች እየቀነሱ መምጣታቸውን ጠቅሶ፣ ፌዴሬሽኑም ራስ ምታት እንደሆነበት ይገልጻል፡፡ በተጠቀሱት ውድድሮች ሚኒማ ለማሟላት አትሌቶች ወደተለያዩ አገራት በመላክ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየከፈለ መሆኑንም ይገልፃሉ።
ከመልክዓ ምድር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን የሚያስቀም ጠውን ሚኒማ ማሟላት አይቻልም፤ይህ እንደመሆኑ ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን በመምረጥ ወደ ተለያዩ አገራት በመውሰድ እያወዳደረ መሆኑንም ያስረዳሉ።
የረጅም ርቀት ውድድሮች እያበቃላቸው፤ የጎዳና ላይ ውድድሮች እየተበራከቱ መምጣታቸውና ሽልማታቸውም እየገዘፈ በመሆኑ አሰልጣኞች፤ ማናጀሮች እንዲሁም አትሌቶች ወደ ጉዳና እየፈለሱ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑንም እንደሚያሳስበው ያስረዳሉ።
ይህ ችግር እያደር በመባባሱም ፌዴሬሽኑ በተለይ አጭር ርቀት ላይ እንዴት እንስራ የሚለውን አቅጣጫ እስከመከተል እንዳደረሰው የሚገልፁት አቶ ዱቤ፤ፌዴሬሽኑም ክልሎችና ክለቦችን በመደገፍ የትራክ አትሌት የማይጠፋበት ሁኔታ እንዲፈጠር የበኩሉን እያደረገ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
አሁን የመም ውድድሮችን የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመለየትና ለማብቃት እንቅፋት ከሆኑት መካከል አንደኛው የመወዳደሪያ ቦታ እጥረት መሆኑንም የሚያስረዱት አቶ ዱቤ፤በቀጣይ የመም ውድድር ራጮችን ፍፅሞ ከማጣት ቀድሞ መሰል የመወዳደሪያ ቦታ እጥረቶች መስተካከል እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ያቀርባሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ስፖንሰር አድራጊ ተቋማትን ፈልጎ እንዲሁም የአገር ውስጥ ውድድሮችን በማዘጋጀት ተወዳዳሪ አሸናፊዎች የተሻለ ጥቅማ ጥቅም የሚያገኙበትን አሰራር መዘርጋት እንዲሁም ለትራክ ተወዳዳሪዎች የሚሰጠውን ሽልማት ከፍ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
ታምራት ተስፋዬ
İzmir resmi escort sayfası
Sakarya escort profilleri
Casibom resmi sayfası