ሆ ብዬ እመጣለሁ ሆ ብዬ በድል ጥንትም ያባቴ ነው ጠላትን መግደል:: ልበ ሙሉ ጀግና ፣ፍራት የሌለብኝ እኔ ለኢትዮጵያ ፣ ቃልኪዳን አለብኝ::
የአያት የቅድመ አያት ፣ ወኔ ያልተለየኝ ዛሬም ለኢትዮጵያ ታጋይ ተጋዳይ ነኝ! ጀግኖች በደማቸው ፣ ያቆዩዋትን አገር ዛሬም በልጆቿ ፤ለዘለዓለም ትኑር በአያት በቅድመ አያት፣ የኖረች ተከብራ በዓድዋ በማይጨው የኖረች ተከብራ አልያት በቁሜ እምዬ ተደፍራ! ሆ ብዬ እመጣለሁ ሆ ብዬ በድል፣ ጥንትም ያባቴ ነው ጠላትን መግደል! ይህን ዘፈን ስንሰማ የሆነ አንዳች ስሜት ውስጣችንን ውርር ያደርገናል:: እንደ ዓድዋ፣ ፋሽስት ጣልያን ከኢትዮጵያ የተረታበት ቀን የድል በዓል፣ ካራማራ ያሉ የድል በዓላት ሲከበሩ በብሮድካስት የመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ የምንሰማው ነው::
በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ እንደ አሁኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር እንቅልፍ የማይተኙት ምዕራባውያን እና በእነርሱ የሚጋለቡ እንደ ትህነግ፣ ሸኔ ያሉ የአገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸውን ለማንበርከክ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ወጣቶች፣ በጠቅላላው ሕዝቡ እንዲነሳ ለማድረግ ሲታሰብ የሚለቀቅ ዜማ ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጣውን ሲያሳይ በየሬዲዮውና ቴሌቪዥኑ የምንሰማው ነው::
በአንጋፋው ጌታመሳይ አበበ እና በኋላም በአርቲስት ደሳለኝ መልኩ የሚቀነቀነው ይህ ዜማ የሕዝብ ሆኗል ማለት ይቻላል:: አሁን ላይ በሕብረ ዝማሬ የሚዜም ሆኗል::
ይህ ‹‹ሆ ብዬ እመጣለሁ›› የተሰኘው የድል ዜማ በአሜሪካና በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች እነ ግብጽ ጭምር ‹‹አይዞህ!›› ይባል የነበረው የሶማሊያው ተስፋፊ ፕሬዚዳንት የዚያድ ባሬ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ወረራ በፈጸመበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ይህን ጠላት መክተው ሲመለሱ የተዜመ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ:: የዚያድ ባሬ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ሲገባ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀፎው የተነካ ንብ ሆነ::
የሚገርመው ደግሞ በወቅቱ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውስጥ ቀውስ ውስጥ ነበረች:: ጠላት መጣ ሲባል ግን ኢትዮጵያውያን የውስጥ ጣጣችን ይቆየን ብለው ‹‹ሆ›› ብለው ዘመቱ፤ በዚያን ጊዜ ከመደበኛው ሠራዊት በተጨማሪ 300ሺ ሚሊሺያ ታጠቅ ጦር ሰፈር ገብቶ ስልጠና እንዲወስድና እንዲዘምት ተደርጓል:: ኢትዮጵያ ጥንትም የጀግና አገር ነበረችና ሰራዊቱ በቁጣ ‹‹ሆ›› ብሎ ሄዶ የሶማሊያን ወራሪ ሀይል አይቀጡ ቀጥቶ የሀገሩን ዳር ድንበር አስከብሮ ‹‹ሆ›› ብሎ በድል ተመልሷል::
እነሆ ይህ የድል ዜማ ዛሬም የወኔ ማናሳሻ እና የድል ታሪክ ሰነድ ሆኖ እያገለገለ ነው:: የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ በመጡ እና ኢትዮጵያውያን ይህን ለመቀልበስ ሆ ብለው በሚወጡት ወሳኝ ወቅት ሁሉ ሠራዊቱን ሕዝቡን ለማጀገን እየተዜመ እዚህ ደርሷል::
ይህ ብቻም አይደለም፤ በአማኑም ቀን ሲለቀቅ የግጥሙና የዜማው ሀይል እንኳን በጦር ሜዳ የዋለውን ያልዋለውንም ልብ በመስረቅ ትኩረትን የሚስብ ነው:: በአገራዊ ክስተት ውስጥ ኪነ ጥበብ (በተለይም ሙዚቃ) ከፍተኛ ሚና አለው:: ከጥንት ጀምሮ የነበሩ የጦርነት ታሪኮችን መለስ ብለን ብንመለከት ቀረርቶና ሽለላ አይለያቸውም:: የሙዚቃ ታሪኮችንም ካየን ብዙ ዘፋኞች ከሠራዊት ቡድን የወጡ ናቸው::
የሰሜን ዕዝ፣ የምሥራቅ ዕዝ፣ የምዕራብ ዕዝ፣ የደቡብ ዕዝ የሚባሉ የኪነት ቡድኖች በርካታ ድምጻውያንን ፈጥረዋል:: ይህ የኪነጥበብ ሚና ዛሬም ቀጥሏል:: አገራችን በሕልውና ዘመቻ ላይ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የቀደሙትን ዜማዎች አውጥቶ ሕዝቡን ሠራዊቱን ከማነቃነቅ በተጓዳኝ አዳዲስ ሥራዎች እየወጡም ናቸው::
የሙዚቃ ባለሙያዎች ድምጻውያን በግልም በቡድንም እየሆኑ ሠራዊቱን የሚያጀግኑ፣ የቀድሞ ሠራዊቱን ወኔ የሚያነሳሱ፣ ወጣቶች እንዲቀላቀሏቸው ሕዝቡ አጋርነቱን እንዲገልጽ የሚያደርጉ ዜማዎችን እያወጡ ይገኛሉ:: ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ የሚለውና የአገራችን እድገት የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ ሆኖ እየሰራ ያለው ትህነግ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሰሜን እዝን ከካደበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያውያን በጦርነት ላይ ይገኛሉ:: ዳሩ ግን ያሰበው ሳይሳካ ቀርቶ የጫረው እሳት ራሱን አቃጠለው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹ሆ›› ብሎ ተነሳበት::
ሁሉም በየዘርፉ ለአገሩ ዘብ ቆመ:: የሙዚቃ ባለሙያዎችም/ አርቲስቶች/ በሙያቸው ይህን ጠላት ተዋግተውታል:: አሁን ያለንበት የሕልውና ዘመቻ በሙዚቃው እንዴት ይገለጻል? በሕልውና ዘመቻው ከአዲስ ዓመት መግቢያ ጀምሮ እስከ ከዚህ ሳምንት ድረስ አንጋፋና ወጣት የኢትዮጵያ ድምጻውያን አገራቸው ያለችበትን ሁኔታ በጥበባቸው አንፀባርቀዋል::
በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር ዛሬም ጀግኖች እንዳሏትና ከመበታተን እንደታደጓት አሳይተዋል:: ከዚህ ቀደም ስለኢትዮጵያ በሚል የወጣ የጋራ ሥራን በእዚህ አምድ ተመልክተናል:: ፡ ‹‹የኛ›› በሚል የቡድን ስም የሚታወቁት አምስቱ ሴቶች ‹‹እወዳታለሁ›› በሚል በዚሁ ሳምንት ሥራዎቻቸውን ለቀዋል:: በዚሁ ገጽ እንዳስነበብናችሁ በርካታ ነጠላ ዜማዎች ተሰርተዋል:: የግጥሞቻቸው ይዘት አገራቸውን ለማፍረስ የተነሳውን ከሃዲ ቡድን እንደማይሳካለት መንገር ነው:: የጥንት ገናና እና አገር አስከባሪ ሕዝቦቿን ታሪክ መንገር ነው::
እነዚህ ሙዚቃዎች በታሪክ ውስጥ ምን መልክ ይኖራቸዋል? በቀጣይስ ምን ይሰራል? የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት እና የሙዚቃ ባለሙያው ዳዊት ይፍሩ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኪነ ጥበብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁልጊዜም ግንባር ቀደም ናቸው::
በርካታ ድምጻውያን ውጊያው ያለበት ቦታ ከመሄድ ጀምሮ ሠራዊቱ በሚሰለጥንባቸው ቦታዎች እየሄዱ በጥበብ ሥራዎቻቸው ወታደሩን አበረታተዋል፤ ከወታደሩ ጋር ያለውን ሕይወት ተጋርተዋል:: ይህን ሲያደርጉ በሙዚቃው ሙያ ውስጥ በተለያየ ዘርፍ ያሉ ሰዎች ሙያዊ ድጋፍ አድርገዋል:: በዜማ፣ በግጥም፣ በመሳሪያ… በሙዚቃ ውስጥ በሚያስፈልጉ ሁሉ ትብብር ተደርጎ ተሰርቷል:: እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ አሁን ያለው አገራዊ ክስተት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎች ተሰርተዋል:: እነዚህ ሥራዎች የሙዚቃ ሥራ ውስጥ ላለ ሰው ኩራቶች ናቸው፡ እንዲህ አይነት አዳዲስ ክስተቶች ሲከሰቱ አዳዲስ ፈጠራዎችም ይዘው ይመጣሉ፤ አዳዲስ ርዕሶች ይወጣሉ:: መልዕክቶቻቸውም ‹‹ኢትዮጵያ አትሸነፍም›› የሚሉ ናቸው::
‹‹አገር በተጎዳች ጊዜ ሁሉም ወደ አንድ መስመር ነው የሚያመራው›› ይላሉ ባለሙያው:: ተበታትነው የነበሩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በዚህ ሥራ ተሰባስበዋል:: አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ እንደሚሉት፤ የጥበብ ሥራ አንዱ ከአንዱ ባይነፃፀርም በቀደመው ዘመን የነበሩ የሙዚቃ ሥራዎች ፖለቲካን የሚገልጹት በውስጠ ወይራ አገላለጽ ነበር::
ያኔ የዘመኑ ባህሪ ስለሆነ ነው፤ ‹‹እገሌ›› ብሎ መጥቀስ ከባድ ነበር:: አሁን ላይ ግን ነፃነቱ አለ፤ ሳንሱር የለም:: ይህ የተሻለ ዕድል ፈጥሯል:: በዚህም ምክንያት አሁን ላይ ፖለቲካንም ሆነ ሌላውን ነገር የሚገልጹ ዘፈኖች ማንም በሚረዳው መንገድ የሚሰሩ ናቸው:: በዚያ ላይ ደግሞ የከያኒው የአገላለጽ ሁኔታ ይወስነዋል:: ሙያዊ ድጋፉ አሁንም እንደሚቀጥል የተናገሩት ጋሽ ዳዊት፤ መከላከያውን ግንባር ድረስ ሄዶ የማበረታታት እና አብሮ የመሥራት ሥራው ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል:: በነገራችን ላይ የእነዚህ ድምጻውያን ሥራዎች የበለጠ ገናና የሚሆኑት ከዛሬው በላይ ወደፊት ነው:: ምክንያቱም ዛሬ ላይ ከዜናው ጋር እኩል ናቸው::
ሰዎች በሰበር ዜናዎች ተወጥረዋል፤ ቀልባቸው ያለው ትንታኔዎች ላይ ነው:: እነዚህን ዘፈኖች የበለጠ የምናብላላቸው ምናልባትም ይሄ ቀን ሲያልፍ ነው:: ዛሬ ላይ ወኔን ለማነሳሳት እና ለሠራዊቱም አቅም ለመሆን ሲያግዙ ለቀጣይ ደግሞ የታሪክ ማጣቀሻዎች ናቸው:: አዎ! ዘፈን የታሪክ ማጣቀሻ ይሆናል::
የታሪክ ጸሐፊው ተክለጻድቅ መኩሪያ በመጻሕፍቶቻቸው ውስጥ የተለያዩ ስነ ቃል ግጥሞች አሉ:: የለቅሶም ሆነ የሠርግ ዘፈኖች ግጥሞች አሉ፣ የአዝማሪ ግጥሞች አሉ:: በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ታሪክ ሲተረክ ያንን ክስተት የሚገልጹ ዘፈኖች ማጀቢያ ይደረጋሉ::
በሌላ በኩል አንዳንድ ሕብረ ዝማሬዎች ደግሞ የሕዝብ ይሆናሉ:: ለምሳሌ ‹‹ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ›› የሚለው የሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ግጥም በየአጋጣሚው በህብረት ሲዜም እንሰማለን:: ሕብረ ዜማው በተሾመ ሲሳይ ዜማ ተደርሶለት በምድር ጦር ኦርኬስትራ ቅንብር እና ህብረ ዝማሬ የተዘጋጁት ነው::
ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ ረጅሙን ጉዞ ጥንቱን አውቄ ተነስቻለሁ ትጥቄን አጥብቄ መብት ነፃነት እንዲሆን አቻ ተነስቻለሁ ለትጥቅ ዘመቻ ልሙት ልሰዋ ደስ ብሎኝ ስቄ ለአገሬ ክብር እኔ ወድቄ ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ ግፍ እና በደል ከዓለም ይጥፋ መብት ነፃነት ይደግ ይስፋፋ ልሙት ልሰዋ ደስብሎኝ ስቄ ለአገሬ ክብር እኔ ወድቄ ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ እነዚህ ሕብረ ዝማሬዎችም ሆኑ በተናጠል የተሰሩ የእነ ጥላሁን ገሠሠ ዘፈን እነሆ ዛሬ የፕሮግራም ማጀቢያ ብቻ ሳይሆን የታሪክ መጻሕፍትም ማጣቀሻ ሆነዋል:: የዛሬዎቹ ጀግኖች ከያኒያንም የነገ ታሪክ ማጣቀሻዎች ናችሁ::
ለዛሬ ደግሞ የሠራዊቱ ወኔ ናችሁ:: እነሆ የዳግማዊ ዓድዋ ታሪክ እየጻፋችሁ ነው:: ለዛሬው በዓድዋ ጊዜ በእንጉርጉሮ ይዘፈኑ ከነበሩ ግጥሞች ከተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ›› መጽሐፍ ላይ ባገኘነው በእነዚህ ስንኞች እንሰናበት:: ጥሊያን ኮሶ ጭኖ ሸዋን ሊያጠጣው ገና ሲበጠብጥ ዳኘውን ቀናው ቅዳሜ ተግዞ እሁድ ተበራየ መስኮብም ገረመው ጣሊያንም ጉድ አየ! አገርክን ምኒልክ እንዳሁን ፈትሻት ባያይህ ነውና ጠላትህ የሚሻት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኀዳር 23 / 2014