የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነባራዊ ዓለምአቀፍ ሁኔታን ያላገናዘበና ቁሞ ቀር ነው። አዎ የምዕራባውያን በተለይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከቀዝቃዛው ጦርነት ቆፈን መላቀቅ አልቻለም። በአጭር ጊዜም ይላቀቃል ተብሎም አይጠበቅም። ለአሜሪካ ዛሬም ሶሻሊዝም ቻይና ራሽያ ከእነሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሳይቀሩ የደህንነትና የጸጥታ ስጋት ናቸው።
ኢራንን፣ ሶሪያን፣ ቱርክን፣ ቬኒዞላን፣ ኩባን፣ ኢትዮጵያንና ሌሎችን በአብነት ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ሀገራት ላይ የተከፈተው የተቀናጀና የተናበበ ዘመቻ ከቀዝቃዛው ጦርነት ያደረ ቅርሻ ነው። ሀገራቱን ለማዳከም እንደ ትናንቱ ዓለምአቀፍ ሚዲያውን ዓለምአቀፍ “ግብረ ሰናይ”ድርጅቶችን ዲፕሎማሲውንና እንደ የመንግሥታቱ ድርጅት ያሉ ዓለምአቀፍ ተቋማትን ሲያሻቸው ደግሞ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ይጠቀማሉ። ይሄ ያረጠና የጨረተ ፖሊሲያቸውና ስልታቸው ግን አሁናዊዋ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ገመናው ተጋልጧል። እርቃኑን ቀርቷል።
አሁናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ገጽና መልክዓ (landscape) ካለፉት ስድስት በተለይ ደግሞ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ፍጹም ተቀይሯል። የሕወሓትን የአፈና የዘረፋና የሴራ ፖለቲካ አምርሮ የሚጠላና እንኳን ተመልሶ ወደ አገዛዝ እንዲመጣ ስሙ ሲነሳ እንደ ኮሶ የሚመረውና የሚያንገሸግሸው ትውልድ ተፈጥሯል።
ጥላቻን፣ ልዩነትን ተቋማዊና መዋቅራዊ አድርጎ በጀት መድቦ ይጥር ይግር የነበረው አገዛዝ፤ ፍቅርን ይቅር ባይነትን ሰላምን በሚሰብክና ለተግባራዊነቱ ረጅም ርቀት በሚጓዝ አመራር ተተክቷል። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ብሎ የተነሳ አሸባሪ ባለበት ፤ በኢትዮጵያ ጥቅምና ክብር ለመጣ አንገቴ ይቀላል እንጂ አልደራደርም ያለና በተግባርም ለሀገሩ ህልውና ጦር ግንባር ተገኝቶ ውጊያ የሚመራ ጀግና መሪ ተከስቷል። ዐቢይ በሚመራው የለውጥ ሀዋርያ በማንነት በልዩነትና በጎሳ ፖለቲካ ምትክ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የስበት ማዕከል ሆነዋል።
ኢትዮጵያን እየገዛ ስሟን መጥራት ይጠየፍ የነበረ ቡድን ኢትዮጵያን ጠርቶ በማይጠግብ አገር ወዳድ መሪ ተተክቷል። ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን የሚል መሪ ተፈጥሯል። መደመር ብልጽግና ሐቀኛ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ ሆኗል። የሞግዚት አስተዳደር ላይመለስ እስከወዲያኛው ተሸኝቷል።
አፋሩ ሱማሊያው ሐረሪው ጉምዙ ጋምቤላው ሲዳማው ወዘተረፈ ከአጋርነት ወደ የአገር ባለቤትነት ተለውጠዋል። በነገራችን ላይ የአፋር አስደማሚ ድል አንዱ መነሻ የአፋር ሕዝብ የሀብቱና የሀገሩ ባለቤት መሆኑ በተግባር በመረጋገጡ ነው። በነገራችን ላይ የተቀረው ኢትዮጵያዊም ቀፎው እንደተነካ ንብ ዳር እስከ ዳር የተመመበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነው።
የአሜሪካም ሆነ የምዕራባውያን ቀይ ስህተት የኢትዮጵያን ታሪክ መለስ ብለው አለመቃኘታቸውና ዛሬ የምትገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ በሱዛን ራይስና በወያኔ የተንሸዋረረ ዓይን ማየታቸው ነው። እንደ ዓደዋው ሁሉ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ኢትዮጵያ ላይ ዳግም ውርደትንና ሽንፈትን ሊከናነብ አንድ ሐሙስ ቀርቶታል።
በአዲስ የዓድዋ ትውልድ በሳልሳዊ ምኒልክና በፓን አፍሪካኒዝም የአባቶቻችን የማይበገር መንፈስ እንደትላንቱ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ በቃ ! #No more እየናኘ ነው። ንቅናቄው ከኢትዮጵያ ከአፍሪካ አልፎ አሜሪካንና ምዕራባውያንን በድንጋጤ ክው ያደረገ ዓለምአቀፍ ክስተት ሆኗል።
ለዚህ ሁሉ ንቅናቄ መግፍኤው አሜሪካ አዲስ ወይን በአሮጌ አቁማዳ እንዲሉ አዲስ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መንፈስ በረበበባት ዓለም በተለይ በሀገራችን ያፈጀና ያረጀ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለመትከል የመጣችበት መንገድ ስህተት መሆኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚያ ሰሞን በተዘጋጅ የአዲስ ወግ ወይይት ተገኝተው፤ “ኢትዮጵያዊያን ከታሪክ መገንዘብ ያለብን፤ አሁን ያለው ጦርነት ባህሪ እንዳለ 1983 ዓ.ም ኢትዮጵያ ላይ ተካሂዷል” ያሉት ለዚህ ነው። እውነትም በተግባር ነጮቹና ሕወሓት የታሪክ ገጽ እየገለጡ በተመሳሳይ ስልት እየፈተኑን ይገኛሉ።
ይህንን መረዳትና ማስረዳት የኢትዮጵያን ፈተና ባጠረ ጊዜ ለመቋጨት እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ ሃሳቡን ላፍታታው። እንደ 83ቱ የዛሬ ፈታኟ አሜሪካና ምዕራባውያን ሲሆኑ፤ የአፈታተን ስልታቸውና ሁኔታዎችም ከቀደመው ጋር ተመሳሳይ ነው።
ኢትዮጵያ የትናንት ፈተናዋን ድጋሚ እየተፈተነች ትገኛለች። ሆኖም ከ1970ዎቹና 80ዎቹ ጀምሮ የፈተናትን ፈተና በ2010 ላይ አሸንፋዋለች። ፈታኟን ከመንበሩ አውርዳ ወደመጣበት በረሃ ሸኝታዋለች።
ሕወሓት ከ80ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያን ተጭኖ ከቆየበት የስልጣን መንበሩ ከወረደና ዳግም ወደ ትግራይ በረሃዎች ከተወሸቀበት አንስተው ለመታደግ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ዳግም አብረው በተመሳሳይ ስልት ኢትዮጵያን እየፈተኗት ነው። ይህንን ፈተና ኢትዮጵያዊያን ዳግም በህብረት ያሸንፉታል። የሕወሓትና አዛዮቹ ምዕራባዊያን የፈተናቸው ስልትና አካሄድ ግን የትናነቱን የደገመ ነው።
ይህ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ግንዛቤ የተያዘበት አይመስልም። አሁናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መልክዓ (po[1]litical landscape) ከ1983ቱ በእጅጉ የተለየ ነው። ዛሬ ሕዝቡ የሀገሩን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድት ለማስከበር በሁሉም መልክ ለመታጠቅ፣ ለመዝመትና ደጀን ለመሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴና ዝግጁነት ሲኖር፤ በአንጻሩ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ግን ሠራዊቱና ህዝቡ በስርዓቱ ላይ የነበረው እምነት በየጊዜው ተሸርሽሮ ያለቀ ፤ ከግንባር የሚሸሽ ሠራዊት ፣ ልጆቹን ከዘመቻ የሚደብቅ ወላጅ፣ በግዳጅ የሚያዘምት ስርዓት ፣ ከስልጠና የሚጠፋ ምልምል በርካታ ነበር።
በእንቅርት ላይ እንዲሉ በጊዜው የጋራ ሀገራዊ ቁጭት የሚፈጥር አጀንዳ የተዳከመበት፤ የማሸነፍ እምነትና ጽናት የኮሰመነበት ፤ በተቃራኒው ዛሬ የአሸናፊነት እምነት ፅናትና ዝግጁነት የተሰነቀበት መሆኑ ይለያል። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ያለምንም ጥርጥር ይሄን ጦርነት ታሸንፋለች ያሉት።
ዜጎችም የሀገራቸውን ሉዓላዊነት የግዛት አንድነትና ህልውና ለማስከበር ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከአርቲስት እስከ አትሌት ከገዢ እስከ ተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ከቀድሞ ሠራዊት ወታደር እስከ ጄነራል ከአራሽ እስከ ቀዳሽ ከእኔ ቢጤ ድሀ እስከ ቢሊየነር ወዘተረፈ ያለማንም ጎትጓችነትና ቀስቃሽነት ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ጦር ግንባር ተመዋል።
ስለሀገራቸው ህልውና በመስዋዕትነት ስለአረጋገጡት ለውጥ ፖሊሲው ሳይነጋገሩ በጥቅሻ ተግባብተዋል። ከደጀን እስከ ጦር ግንባር እንድ አንድ ቃል ተናጋሪ ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነዋል። የጀግኖች አባቶቻቸው የዓድዋ ልጆች መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የአሜሪካ የምዕራባውያን የሕወሓትና የቡችሎቹ የእነ ኦነግ ሸኔ ትንተና ልብ ያላለውና የሳተው ይሄን ነባራዊ ሁኔታ ነው። በዚህ የተሳሳተ ትንተና የደረሱበት ድምዳሜ ደግሞ የ1983ቱን ተውኔት በ2014 መቼት(setting ) መድረክ ሆነና አረፈው።
ይሁንና ለዚህ ትንተናቸውና መደምደሚያቸው የእኛ ስህተት ድካምና ዳተኝነት በግብዓትነት ማገልገሉን አምኖ መቀበል ያሻል። በዘመቻ መሀል ስለሆንን ሌላውን እናቆየውና የጎንዮሽ ጉዳት የሌላቸውን ድካሞቻችንን እናንሳ ። በህዝቡና በታችኛው አመራር ዘንድ የጠላቶቻችንን የትግል ስልት ያለመረዳት ዛሬም ትላንትም በውል የመገንዘብ ችግር ነበር።
ከላይ እስከታች የጠላትን የውስጥና የውጭ ስልት ባለመረዳት በፖለቲካ አመራሩ በሠራዊት አመራሩ በሠራዊቱና በህዝቡ በኩል በስፋት የሚታይ ችግር ነበር። ይህም ጠላትን በአንድነት ለመመከት ዕድል ያልፈጠረ ከመሆኑም በላይ የተግባር ቅንጅት በማሳጣት ለሽንፈት ዳርጓል።
የተግባር ቅንጅት ጉድለት መኖሩ፤ ላለፉት 45 ዓመታት የተዘራው ጥርጣሬ እና በወሬ የሚፈታ ሰው ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ፤ በዚህ ዓመት ጎልቶ የተስተዋለ ድክመት ነበር። በዚህ የተነሳ ያልተገባ መስዋዕትነት ከፍለናል። ምንም እንኳ መጨረሻ ላይ ጦርነቱን እንደምናሸንፍ ጥርጥር ባይኖረንም ጠላት እዚህም እዚያም ጊዜያዊ የውጊያ በለስ እንዲቀናው አዛዮቹም የልብ ልብ ተሰምቷቸው የ83ቱን ሀገር በሽብር የመፍታት ፍኖተ ካርታ አቧራውን አራግፈው ለትግበራ እንዲነሱ አድርጓል።
እንደተለመደው ለዚህ እኩይ ዓላምአቸው ግብ ዓለምአቀፍ ሚዲያውን ተቋማትንና ድርጅቶችን እንደ ውሻ ፈተው ለቀውብናል። ዛሬም በአለፍ ገደም ቀጥለውበታል። ሆኖምየጦርነቱ ባህሪ ሲቀየር ውሾቻቸውን ሳይወዱ ያስታግሷቸዋል። ባያስታግሷቸውም ውሾቹ እየጮሁ ግመሉ ጉዞውን ይቀጥላል። አበው የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን እንዲሉ አሜሪካና ምዕራባውያን በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ቀይረው በሕወሓት የሚመራ አሻንጉሊት ለማቆም ቀን ከሌት ላይ ታች ሲሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከሀገራቸውና ከመንግሥታቸው ጎን እንዲቆሙ አደረገ።
በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳና በደቡብ አፍሪካ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝንና ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ #ይበቃል ! #በቃ ! #No more የሚል ትዕይንተ ሕዝብ በ30 ሀገራት ተካሄደ።
ኢትዮጵያዊ አሜሪካውያን ኤርትራዊ አሜሪካውያን ሶማሊያውያን አሜሪካውያን አፍሪካዊ አሜሪካውያን ካሪቢያዊ አሜሪካውያን እና የተለያዩ ድርጅቶች ንቅናቄውን ዓለምአቀፋዊ እያደረጉት ይገኛል። አፍሪካ፣ ቻይና፣ ራሽያ፣ ቱርክ፣ ኢራንና ሌሎች ሀገራትን ንቅናቄውን እየተቀላቀሉት ነው።
ታዋቂው ትውልደ ሴኔጋላዊ አሜሪካዊ ኤኮን ሳይቀር ንቅናቄውን ደግፏል። አሜሪካና ምዕራባውያን የማትነካ ሀገር ነክተው ያልጠበቁትና ያላሰቡት ዓለምአቀፋዊ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ቡርኪና ፋሶ፣ አልጀሪያ፣ ኒጀርና ሌሎች የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የነበሩ ሀገራት ፈረንሳይን #በቃ ! #No more ማለት ጀምረዋል። የባይደን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ልሒቃን ዘግይቶም ቢሆን እነ ራይስ ሳያሳስቷቸው እንዳልቀረ የተረዱ ይመስላል።
የባይደን አስተዳደር ይህ ስህተት በቨርጂኒያ ምርጫ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በቀጣይ ምርጫዎች ተመሳሳይ ዋጋ እንዳይከፍሉ ሰግተዋል። ማጣፊያው አጥሯቸዋል ። አፍሪካዊ እህት ወንድሞቻችን የምዕራባዊያንን በተለይም የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት ላይ የጋራ አቋም እየያዙ ይገኛል።
ኬንያውያን፣ ዩጋንዳውያን፣ ናይጀሪያውያን፣ ላይቤሪያውያን፣ ቡርኪናፋሶውያን፣ አልጀሪያውያን፣ ጅቡቲያውያን ወዘተረፈ የነፃነት ቀንዲላቸው ከሆነችው ኢትዮጵያ ጎን ቆመዋል። ልሒቃኖቻቸው ኢትዮጵያ የእኛንም ጦርነት እየተዋጋች ስለሆነ ከጎኗ ልንቆም ይገባል እያሉ ነው። ሆኖም እንደ ታላቁ ዓድዋ ሁሉ ኢትዮጵያ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አልቀበልም። ጥቅሟንና ክብሯን አሳልፌ አልሰጥም። ለምዕረባውያን አልላላክም የሚል መሪ ስላገኘች የራስ ምታት ሆኖባቸዋል።
ለራስ ምታታቸው ለእነ ሊቢያ ያዘዙትን መድህነት እንዳለ ለኢትዮጵያ አዘዙ። ኢትዮጵያን መሪ በማሳጣት አዳክሞ እንደነ የመን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ ማፍረስ። ይህ የአሜሪካም ሆነ የምዕራባውያን ውሳኔ ከታሪክ ያልተማሩ መሆኑን አደባባይ አወጣው። ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት የውስጥ ልዩነት ቢኖራቸው ነፃነታቸውን ሉዓላዊነታቸውንና የግዛት አንድነታቸውን ለመጠበቅ በአንድነት እንደሚቆሙ አልገመቱም።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነፃነትና የፓን አፍሪካኒዝም እርሾ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የፀረ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ችቦ ማቀጣጠያ መሆኑን ዘንግተው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲቸው አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል። መውጫቸውን ሳያስቡ ዘው ብለው የገቡበት የኢትዮጵያ ጉዳይ ዙሪያው ገደል ሆኖባቸዋል። በኢትዮጵያ የተቀጣጠለው የፀረ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ (neocolonialism)ንቅናቄ “#በቃ #No more”አህጉራዊና አለምአቀፋዊ ድጋፍ እያገኘ ነውና ከዚህ በላይ አንገብጋቢ ጉዳይ ካልገጠመኝ በተከታዩ መጣጥፌ እመለስበታለሁ ። እናሸንፋለን ! አንጠራጠርም።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኀዳር 23 / 2014