አንዳንዴ እኮ ጎዶሎህ ብዙ ይሆናል። ያስጨነቀህ ነገር የማይገፋ ሊመስልህም ይችላል። ኑሮ ያሳስብሃል። የቤተሰብ ጉዳይ ሰላም ይነሳሃል። የሀገር ጉዳይ ያስጨንቅሃል። ብቻ ብዙ ነገር ይረብሽሃል። ማን የማይጨንቀው አለ ብለህ ነው። ማን የማያሳብ አለ? ሁሉም ያስባል። ሃሳብና ጭንቀት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ማንኛውም ጤናማ የሆነ ሰው በሚገጥሙት የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ያስባል፤ ይጨነቃል። ልዩነቱ ግን ሁሉም ሰው እኩል አያስብም፤ እኩል አይጨነቀም። አንዳንዱ አብዝቶ ይጨነቃል። ሌላው ደግሞ ብዙ አይጨነቅም። አንዱ ከመጠን በላይ ሃሳብ ይገባዋል። ሌላው ብዙ አያስብም።
ስለዚህ ሃሳብና ጭንቀት እንደየሰው ባህሪ፣ ችግሮችን የመጋፈጥና ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ይወሰናል። ምንም እንኳን ሃሳብና ጭንቀት የሰዎች ባህሪ ቢሆንም ታዲያ ‹‹ሲበዛ በሽታ ነው›› ይላሉ የአእምሮ ሕክምና ባለሞያዎች። ስለሆነም አብዝቶ ማሰብንና መጨነቅን እንዴት ማቆም ይቻላል? አብዝቶ ማሰብና መጨነቅ የብዙ ሰዎች ችግር ነው። ሰዎች ነብስ ካወቁ ጀምሮ እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ ማሰብና መጨነቅ እንደጥላ የሚከተላቸው ባህሪ ነው።
መጠኑ ይለያይ እንጂ አብዝቶ የማያስብና የማይጨነቅ ሰው የለም። ማሰብ መልካም ነገር ነው፤ ሕይወትንም ይቀይራል። ሲበዛ ነው መጥፎነቱ። ማሰብ ከበዛ እንቅልፍ የሚባል ነገር የለም። በዚህ ምክንያት አንዳንዴ ሰዎች የሚችሉትን ሁሉ መሥራት አይችሉም። ወይም ብዙ ከማሰባቸው የተነሳ ለመሥራት አቅም ያንሳቸዋል። ሲያስቡ ጊዜው ይሄድባቸዋል።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ተመሳሳይ ብዙ ሃሳቦችን አስበው ይደክማቸዋል። ሃሳባቸው ወይ የትናንት ትዝታ ነው፤ አልያም ደግሞ ቁጭትና የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ ነው። አንዳንዴ ምን እንደሚያስቡ ሁሉ አያውቁትም። ግን ሃሳባቸው ጊዚያቸውንና ጉልበታቸውን እየተሻማባቸው ነው። ከሰው በታችም እያደረጋቸው ነው። ጭንቀታምም እያደረጋቸው ነው። ምን ይሻላል ታዲያ? ማመስገን! ስታመሰግን ጎዶሎህ ይሞላልሃል። የምታመሰግነው ፈጣሪህ እስትንፋስ ስለሰጠህ ነው። ዛሬን እንድትኖር አንድ እድል ስለጨመረልህ ነው። ከጭንቀትህ ጀርባ ሌላ ሰላም የሚሰጥ ነገር እንዳለ ማወቅ ከፈለክ፤ የአእምሮ ሰላም ከፈለክ ከአሁኗ ደቂቃ ጀምሮ አመስግን።
ስታመሰግን ነገሮች እንደሚለወጡ ርግጠኛ ትሆናለህ። ከዛ ያላየኸውንም ማመን ትጀምራለህ። እንደው ሰምታችሁ ከሆነ አንዳንዴ ‹‹ማየት ማመን ነው›› ይባላል። ማየት ማመን አይደለም። ማየት ማረጋገጥ ነው። ማመን ያለብህ ያላየኸውን ነው። እምነት ማለት ያላየኸውን ማመን ነው። አመስጋኝ ስትሆን ገና ወደፊት የሚመጣውን ነገር ማመን ትጀምራለህ። አታመሰግንም እንጂ እኮ! ከስንት ጉድ አምልጠሃል። ከስንት ጣጣ ተርፈሃል። አንተ የምታስታውሰው ሰዎች ያደረጉብህን፣ የካዱህን፣ የጎዱህን፣ የጎደለህን ነው እንጂ የተደረገልህን አይደለም።
በነገራችን ላይ አእምሮህ አንተን ለማስደሰት አይደለም የተፈጠረው። አእምሮህ የተፈጠረው አንተን ለማቆየት ነው፤ ለማኖር ነው። ላዛ ሲል ይጨነቃል። ምን ማለት መሰላችሁ? የሆነ ነገር ተፈጠረ ሲባል ….እንዲህ ልትሆን እኮ ነው፣ የኑሮ ውድነቱ መጣ ሲባል እንኳን አንተ በበጎ አታየውም። ገንዘቤን ልጨምር፣ ገቢዬን ላሳድግ አትልም። የኑሮ ውድነቱ ጨመረ ሲባል አእምሮህ በቃ አለቀለህ፣ ቤተሰብህን ምን ልታበላ ነው፣ ደሞ አሁን የወር ኪራይ ይጨምሩብሃል ይልሃል። አእምሮህ ይጨነቃል። ብዙ ነገር ያመጣብሃል። ስለሚያስብልህ ነው።
ነገር ግን እሱን መቆጣጠር መቻል አለብህ። ለምሳሌ አይታችሁ ከሆነ ስለ አንድ ሰው እናትና ሚስቱ እኩል አይደለም የሚያስቡለት። ሁለቱም ይወዱታል። ለምሳሌ ሰውዬው አምሽቶ ከመጣ እናቱ መንገድ ላይ እያለ የምታስበው ‹‹ይሄ ልጅ ተጋጭቶ ይሆን፣ መኪና ገጨው፣ እንደው ተጣልቶ ይሆን፣ እንደው ፈንክተውት ይሆን፣ ከሰው ጋር ተደባድቦ ይሆን›› የሚለውን ሊሆን ይችላል። ሚስት ደግሞ ምንድን ነው የምትለው ባሏ ቢያመሽ? ‹‹አዬ ይሄኔ ከጓደኞቹ ጋር እየጠጣ ነው፣ ፈታ እያለ ነው፣ ከሆነች ሴት ጋር እኮ ሊሆን ይችላል›› ትላለች።
ሁለቱም ይወዱታል። እናት ስትጨነቅ ስለምትወደው ነው። ሚስት ብትቀናም ስለምተወደው ነው። አእምሯችን ግን እንደ እናት ነው የሚጨነቀው። እንዲህ ብትሆንስ እያለ ክፉ ክፉውን የሚያሳስብህ። ስለዚህ በሌለ ነገር ሁሉ እንድንጨነቅ ያደርገናል። ለዚህ ደግሞ መድኃኒቱ ምስጋና ነው። ልክ ስታመሰግን መጨነቅ ታቆማለህ። በነገራችን ላይ ሰው እያመሰገነ ሊጨነቅ አይችልም። ስለዚህ ማመስገን አለብህ። ጭንቀት ሲመጣብህ በአንድ ጊዜ ነው ተኖ የሚጠፋብህ።
የምታመሰግነው የምትፈልገው እንዲሰጥህ አይደለም። አትሸወድ! ከምትፈልገው በላይ የሚያስፈልግህን ፈጣሪህ ያውቃል። አንተ ብትጨነቅ የፀጉርህን ቅንጣት ያህል እንኳ አትጨምርም። አንተ ትለፋለህ ካላመሰገንክ የለፋኸውን ያህል እንኳን መብላት አትችልም። ፈጣሪ ካልፈቀደ አይሆንም እኮ! የሚያስደነግጥ ሀብት ገምብቶ ለጤናው ሲል ጨው የሌለው ሽሮ ሲበላ አላየህም? እሱ ካልፈቀደልህ ትለፋለህ ግን አትበላውም። የምትበላውን ልትገዛ ትችላለህ። ወደ ጉሮሮህ ግን አይወርድም። ባለቤቱ መፍቀድ አለበት። ባለቤቱን አመስግን።
እንደው ይመስልሃል እንጂ ካላመሰገንክ ከንቱ ሆነህ ነው የምትቀረው። ጓደኛሞቹ ፊልም ለማየት ሲኒማ ቤት ገቡ። በጣም አሪፍ የተባለ ምርጥ ፊልም ነው። ደሞም የሚገርመው ፊልሙ አጭር ነው። ፊልሙ ጀመረ። ጓደኛሞቹ ፊልሙን ማየት ጀመሩ። አንደኛው፣ ሁለተኛው፣ ሶስተኛው…. ደቂቃ ላይ ነጭ ሰሌዳ ነው የሚታየው። ምንድን ነው ብለው ቢጠብቁ ሶስተኛውም ደቂቃ ነጭ ሰሌዳ ነው። ሰዎች ማጉረምረም ጀመሩ። ፊልሙን አይጀምሩትም ምን አስበው ነው ማለት ጀመሩ። አሁንም ደቂቃዎች ነጎዱ። ስምንተኛው ደቂቃ ላይ አሁንም ነጭ ሰሌዳ እየታየ ነው። ልጁ ለጓደኛው ዞር ብሎ ‹‹ምንድን ነው? ምን ዓይነት ፊልም ነው ልታሳይኝ ይዘኸኝ የመጣኸው? ደሞ እኮ ምርጥ ፊልም ይላሉ አያፍሩም እኮ የማይረቡ ብሎ›› ተበሳጨ። ነጭ ሰሌዳ ብቻ ነዋ! የሚታየው።
ስምንተኛው ደቂቃ መጋመስ ሲጀምር ግን ካሜራው መራቅ ጀመረ። ያ ነጭ ሆኖ ሲታይ የነበረው የጣሪያው ነጭ ኮርኒስ ነበር። ከዛ አሁንም ካሜራው መራቅ ጀመረ። ከጣራው ተነስቶ ዝቅ ማለት ሲጀምር የሆስፒታል አልጋ ላይ አንድ ሰው ተኝቷል። እጁ፣ እግሩ፣ አንገቱ አይንቀሳቀስም። ፓራላይዝድ ሆኗል። ዓይኑ ማየት የሚችለው ጣራውን ብቻ ነው። አስረኛው ደቂቃ ላይ አንድ ጽሑፍ መጣ ‹‹አንተ ለስምንት ደቂቃ ማየት የሰለቸህን ጣሪያ እሱ እድሜ ልኩን አይቶታል›› ይላል።
አይታችሁ ከሆነ ችግሮቻችንን በየትኛውም ሚዛን ብንመዝን ከዚህ ሰውዬ ያለበት ሁኔታ አይበልጥም። ችግራችን ከዚህ አይበልጥም። ስለዚህ መጨነቁን፣ ማማረሩን ተወውና ተመስገን ማለት መጀመር አለብህ ወዳጄ! ቤትህን ዞር ዞር ብለህ እየው እስኪ። በርግጠኝነት ቤትህ ቀጥ አድርጎ ያቆመለህ መሃል ላይ ያለ አንድ ምሶሶ አለ። ያ ምሶሶ ከሌለ ምናልባት ቤትህ የቆመው በግድግዳ ነው ማለት ነው። አሁን ደግሞ ከቤት ውጣና ሰማዩን ተመልከት። ምሶሶ የለው፣ ግድግዳ የለው፣ ደጋፊ የለው ቀጥ ብሎ ቆሟል። ሰማይ ይደፋብኝ ይሆን ብለህ ፈርተህ ታውቃለህ? አታውቅም።
ፀሐይን ተመልከት አልወጣም ብላ አምፃ ታውቃለች። አንድ ሳምንት ፀሐይ ብትጨልም ምድር እንዴት እንደምትሸበር አስበው። አየር እንደ ወርቅ ተቆፍሮ የሚወጣ ነገር ቢሆን ማን እንደሚተነፍሰው አስበኸዋል? አቅሙ ያለው ነዋ። ጤናህን አስበው። ጤናህን ከሰው ለምነህ የምታገኘው ቢሆን ኖሮ የስንት ሰው ፊት እንደሚገርፍህ አስበኸዋል? ፈጣሪህ እንደሰው አቅመ ቢስ አይደለም። ሰማይን ያቆመ፣ ምድርን የዘረጋ፣ ፀሐይን ያወጣ፣ አየሩን ጤናውን በነፃ የሰጠህ እሱ ነው። እጅግ ውዱን ነገር በነፃ ሰጥቶሃል። አንተ ግን በገንዘብ ታማርረዋለህ። በሥራህ ታማርረዋለህ። እንዲህ አጎደልክብኝ እኮ ትለዋለህ።
አንዳንድ ነገሮች እንዳሉህ እንኳን የምታውቀው ሲጎድሉብህ ነው። ስታጣቸው ነው። ጤናህን የምታጣጥመው የታመምክ እለት ነው። ለካ ጤነኛ መሆን እንዴት ደስ ይላል የምትለው ከባድ ህመም ሲገጥምህ ነው። ስለዚህ ሲጎድልብህ እንዳታዝን፤ ሲጎድልብህ እንዳትነቃ አሁን እጅህ ላይ ያለውን እይና ተደሰት። አመስግን። ውዱን ነገር በነፃ ሰጥቶህ በርካሽ ነገር ታማርረዋለህ። ሕይወት ከገባህ አመስግን ወዳጄ! ማማረሩን፣ ማዘኑን፣ ተስፋ መቁረጡን አቁምና ፈጣሪህን አመስግን። ላደረክልኝ ሁሉ ምን እከፍልሃለሁ ተመስገን! ከማለት ውጭ ምን እመልሳለሁ በልና ደጋግመህ አመስገን።
የዛሬ ሳምንት እንደምትሞት ቢነገረህ አሁን ያስጨነቀህ ነገር በሙሉ ተራ እንደሆነ ይገባሃል። ከጎደለህ ይልቅ የተደረገልህ ይበልጣል። ተመስገን በል ወዳጄ! ቀንህን አብራው። ሕይወትህን ተስፋ ለኩስባት። ያኔ መኖር ጀምረሃል። ያኔ ዓይንህን ገልጠሃል። ያኔ ከፊትህ የተገተረው ችግር ዓይንህ እያየ ይደረመሳል። ነፃ ትወጣለህ። ምስጋና ነፃ ያወጣሃል ወዳጄ!
አእምሮህ ውስጥ ሊበላህ ያሰፈሰፈ አውሬ አለ። አትችልም! የሚል። የሚመጣው ጊዜ አስፈሪ ነው፣ ይቅርብህ አርፈህ ተቀመጥ፣ ቁጭ በል የሚል አውሬ አለ። ሌላኛው አውሬ ደግሞ ትችላለህ! ጀግና ነህ አንተ እኮ ትሞክራለህ፣ ፈጣሪ ብዙ ነገር አድርጎልሃል የሚል አውሬ አለ። ትልቁ ነጥብ ምን መሰለህ? የትኛውን አውሬ ነው የምትመግበው? አብዝተህ የመገብከው አውሬ ማሸነፉ አይቀርም። አእምሮህ ውስጥ ትችላለህ! የሚለውን አውሬ አብዝተህ የምትመግበው ከሆነ ማሸነፉ አይቀርም። እሱን ልትመግበው የምትችለው ፈጣሪ ያደረገልህን እያሰብክ ማመስገን ከቻልክ ብቻ ነው። ምስጋና ብቻ ነው ኃይል የሚሰጥህ።
ከዚህ በኋላ አንተ አመስጋኝ ነህ። በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብትሆን አታማርርም፤ አትነጫነጭም፤ ብሶት አታወራም። ያኔ ነገሮች መስተካከል ይጀምራሉ። ፈጣሪማ ለእኔ እያደላ ነው ትላለህ። በኑሮህ አመስጋኝ መሆን ትጀምራለህ። ደስታህ ከማንም አይደለም ከራስህ ነው የሚመነጨው። የሆነ ሰው ከመሬት ተነስቶ ሊያስከፋህ አይችልም። የሆኑ ሁኔታዎች ደስታህን ሊነጥቁህ አይችልም። እውነተኛ ደስታ ያለው ውጭ አይደለም። ውስጥህ ነው። የመርከብህ ካፒቴን አንተ ነህ። የምትሾፍረው አንተ ነህ። ማንም አይደለም። ካጣኸው ይልቅ ያገኘኸው ይበልጣል። ከተደረገብህ ይበልጥ የተደረገልህ ይበልጣል። እጅህ ላይ ያለውን አላየህም እንጂ ካንተ በላይስ እድለኛ የለም። አንተ ላይ ሥልጣን ያለው ፈጣሪህ ብቻ ነው። ስለዚህ አመስግን ወዳጄ!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም