በግፈኛውና በአሸባሪው ሕወሓት ምክንያት አገሬ ውሎዋን ጦር ሜዳ ካደረገች እነሆ በአንድ ዓመት ላይ አንድ ወር ተደመረ፡፡ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከጀግኖቹ ልጆቿ ጋር በዐውደ ግንባር እየተፋለመች ያለችውም መንግሥቷን እንዲመራ የሥልጣኑን ብኩርና ያጎናጸፈችውን ፊት ቀደም ልጇን – ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ወክላ
ነው፡፡ የሉዓላዊነት አደራና የዜግነት ክብር ተቀዳሚ እጣ የወደቀበት ጠብመንጃ አንጋች ጀግናው ሠራዊትና ከጎኑ የተሰለፈው ሕዝባዊው ማዕበልም ፍልሚያውን በማፋፋም “ተከተል አለቃህን፤ ተመልከት ዓላማህን” በሚል መርህ ወራሪውን ኃይል አይቀጡ ቅጣት እየቀጡት ወደ መቃብሩ እየሸኙት እንደሆነ ተከታታዩ ድል እየተበሰረልን ነው፡፡ የተጠቃለለው ምሉዕ የዕልልታ ብስራት በቅርቡ የአገራችንን አየር እንደሚያውድ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ቢሆንልንማ ኖሮ ይህ የአሸባሪ ወራሪ ኃይል ሙሉ ለሙሉ ተደምስሶ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እንደ ዓድዋ ድል በሰዓታት ተጠቃሎ በመቃብሩ ላይ ጉሮ ወሸባዬ ቢዘመር ደስታችን እጥፍ ድርብ በሆነ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የጦርነት ተጋድሎ ታሪክ የአሁኑን መሰል የግፈኞች የግፍ ክስተት ተፈጽሞ የታለፈ፤ ተመዝግቦም የተነበበ ሰነድ ስለመኖሩ ማስረጃ ለማቅረብ ያዳግታል፡፡
በዓድዋው ጦርነት የተንበረከከውም ሆነ በፋሽዝም ጥላ ስር ተሰልፎ የወረረን ዳግማዊው የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያ ላይ ዐይኑን ጥሎ ዘገር የሰበቀው በዋነኛነት “ስምሽን እንደያዝሽ ላሰልጥንሽ፤ በአገዛዜ ሥር ሆነሽ ላበልጽግሽ” የሚል የዕብሪት፣ የአምባገነንነትና የኮሎኒያሊዝም ጥማት ተጠናውቶት ነበር፡፡ የሩቅ ቅዠቱም የአገሪቱን ሀብት ለማጋበስና የራሱን ታላቅነት ለማግዘፍ አስቦ እንጂ እንደ አሸባሪው ሕወሓት “አፈራርሼ እበትንሻለሁ፤ አዳክሜ እገነጣጥልሻለሁ” በሚል አረመኔያዊ ኪዳን የአደባባይ መሃላ ገብቶ አልነበረም፡፡ ለነገሩማ ማስተያያ ታሪክ ብናጣለት በማይሆን ምሳሌ አነጻጸርነው እንጂ የፋሽስት ወራሪውም ሆነ የአሸባሪውና የግፈኛው ሕወሓት የመጨረሻ ግባቸው “እሳት ካየው ምን ለየው” መሆኑ ጠፍቶን አይደለም፡፡
የደም ጥማተኛው የሕወሓት ቡድን የዘመተው በታላቂቱ ኢትዮጵያና በአይበገሬው ሕዝቧ ላይ ብቻ አይደለም፤ በራሱም ላይ ጭምር እንጂ፡፡ ባይሆንማ ኖሮ የተፈጠረበትን ምድር ክዶ፣ አገራዊውን ባህልና ወግ ሽሮ፣ የሕዝቦችን የዘመናት ሁለንተናዊ የትሥሥር ገመድ በጣጥሶና ቢያንስ ቢያንስ ባያምንበትም እንኳን “ኢትዮጵያዊ” ሲባል የኖረበትን ክብርና መርቻት ነበር የሚላትን አገር አዋርዶና አራክሶ ለመዳፈር ወኔና ድፍረት ማግኘቱ የሚገርም ብቻ ሳይሆን እንቆቅልሽ ጭምር ነው፡፡
ይህ ቡድን ሕሊናው በስብሶ እንጂ እንደምን “የራሴ” የሚለውን የመከላከያ ሠራዊት፣ ወንድም ሕዝብና ሉዓላዊ የአገር ክብርን ለማዋረድ ተዳፈረ? በደም የተሳሰረን ቤተሰባዊ ውል አፈራርሶ በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ ላይ ለመዝመትስ እንደምን የሞራል ወኔ ሊያገኝ ቻለ? በማያዳግም እርምጃ መወገዱ የሚበጀው የአገራችንን የከበረ ታሪክ ስለሚያቆሽሽና ስለሚያጎድፍ ብቻ ሳይሆን በዓለም የታሪክ መዝገብ ላይ ተግባሩ መስፈሩ በራሱ መርዝ የመትከል ያህል ስለሚከፋ እንዳያቆጠቁጥ ተደርጎ መወገዱ የግድ ነው፡፡ ቀብሩን አፋጥኖ ፍጻሜውን መደምደሙ አስፈላጊ የመሆኑ ማረጋገጫም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በዐውደ ግንባር ላይ ተገኝተው እየፈጸሟቸው ያሉት ተጋድሎዎችን ብቻ ለአብነት ማስታወስ ይቻላል፡፡
ለቴክኖሎጂ የገበሩ መዳፎች፤የግምባሩ ዐውደ ውጊያ በአግባቡና በወጉ እየተመራና ድሉም እየጎመራ እንደሆነ ከላይ ለማስታወስ ተሞክሯል፡፡ ችግሩ ማስተዋልና ጥበብ ያላሰከነው፣ ሁሉም ተኳሽና አስተኳሽ፣ ዘማችና አዝማች ለመሆን የሚወራጭ ሠራዊት እንደ አሸን ፈልቶ ግራ ማጋባቱ ነው፡፡ አሁን አሁን በዐውደ ግምባር ላይ ከሚወነጨፈው አረር ይልቅ ከየመዳፉ ላይ የሚተኮሰው “እንዲህ ሆነ፣ እንዲያ ተደረገ፣ ይሄኛው ቦታ ተያዘ፣ ያኛው አካባቢ ተለቀቀ፣ እከሌ ተማረከ፣ አከሌ ደግሞ ሞተ ወዘተ.” የሚለው የአሉባልታ ሚሳኤልና ያልተረጋገጠ የወሬ አዳፍኔ የብዙኃንን ስሜት እያስበረገገ “ምርኮኛው” መብዛቱ ነው፡፡ “የመዳፉ ዐውደ ግምባር” ምንነት ግልጽ እንዲሆንልን ከአሁን ቀደም በዝርዝር ለማሳየት የሞከርኩትን የቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገት በተመለከተ ጥቂት ጉዳዮችን ለማስታወስ ልሞክር፡፡
የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ “ድክ ድክ” ማለት በጀመረበት ሰሞን መረጃዎች በአንድ ቋት ውስጥ መታጀላቸውና የግንኙነቱ መረብም ነገሮችን ወደ ማቅለል ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ያስተዋሉ ጠቢባኑ “ግዙፏ ዓለማችን እንደ አንድ መንደር ጠበበች” በማለት የምድራችንን ሕዝበ አዳም በደስታ አፍነከነኩ፡፡
የቴክኖሎጂው ሩጫ ፍጥነቱን ጨምሮ ዴስከ ቶፕ የምንለው የጠረጴዛ ኮምፒውተር በስፋት መተዋወቅ ሲጀምርና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በመረጃ አቀባባይ ሳተላይቶች አማካይነት እንደ ነሐሴ ዝናብ መዥጎድጎድ ሲጀምሩ “አገር ጉድ በል! ዓለማችን እንደ መንደር ሳይሆን የቤት ያህል ጠበበች” እየተባለ ይፎከር ገባ፡፡
ዓለምን በቤት ጥበት መመሰሉ እየመሸበት ሄዶ ላፕቶፕ የጭን ኮምፒውተሮች (Lap – ጭን መሆኑን ልብ ይሏል) የግለሰቦችን ቤት ማጥለቅለቅ ሲጀምሩና በትንንሽ ሻንጣዎች እየተሸከሟቸው እንደ ልብ መንቀሳቀስ ሲጀመር “አዬ ጉድ! አዬ ጉድ! ዓለም ከአንድ ቤት ሳሎን ጠባ ጉልበታችን ዘንድ ደረሰች” እየተባለ ዝማሬው መቅለጥ ጀመረ፡፡ እረፍት የማያውቀው የቴክኖሎጂው ሩጫ ሚኒማውን አሻሽሎ ዛሬ ብዙዎቻችን በመዳፋችን እያሽሞነሞንን የምንገለገልባቸው ስማረት የእጅ ስልኮች (Palm top computers) መተዋወቅ እንደ ጀመሩ “ዓለም፣ ዓለም ምን ይመስልሻል፤ በመዳፋችን ሥር ወድቀሻል!” እየተባለ መዘመር ጀመረ፡፡
ውሎ ሲያድርም “ሱፐር” የሚል ዝና የተጎናጸፉና በሁለት ጣት ብቻ የሚዘወሩ ኮምፒውተሮችና (Finger top computers) ሚጢጢዬ ማሽኖች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ የመዝሙሩ ቅላጼ ተለውጦ “ፍጥረት ሆይ ስማ! የሰማህ ላልሰማ አሰማ ዓለም በሁለት ጣታችን ውስጥ ገብታ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራችን ሥር ተማረከች” እየተባለ ጮቤ መረገጥ ተጀመረ፡፡
የቴክኖሎጂው ፈጣን ዕድገት እዚህ ደረጃ ደርሶ እያለ በእኛ አገር ግን “ልማድ ይከብዳል ከግንድ” እንዲሉ የለመድነው ፈሊጥ አልለቅ ብሎን በየሚዲያዎቻችንና በየመድረኮቻችን “ዓለም እንደ መንደር ጠባለች!” እያልን ባረጀ ቢሂል ለመግባባት እንሞክራለን፡፡ ገመናዋ ጠቦ ጠቦ በሁለት ጣቶች ውስጥ የተወሸቀችው ዓለም ራሷ በዚህ ያረጀ አባባል ሳትታዘበን የቀረች አይመስለንም፡፡ ማረጋገጫውን የፈለገ ሰው አድካሚና ምሁራዊ ጥናት ሳያስፈለግ እያንዳንዱ ሰው በቀን ውስጥ በመዳፉ የሚይዘውን የእጅ ስልኩን በጣቶቹ ሳይነካካ እንደማይውል ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በምስል ወዘተ… መረጃዎችን ለመፈለግ መዳፍና ጣት ከምንግዜውም ይልቅ ሥራ የበዛባቸው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከእረኝነት ሜዳ እስከ ትምህርት ቤት፣ ከቤተ እምነት እስከ ቤተ መንግሥት፣ ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፣ ከአፍሪካ እስከ ካሪቢያን፣ ከጋሪ እስከ መኪና፣ ከአውሮፕላን እስከ መርከብ የቦታ ርቀትና የሰዓታት ገደብ ማዕቀብ ሳይጣልበት የሰው ልጅ በቀላሉ የእጅ ስልኮቹን በመዳፎቹ ውስጥ አስቀምጦ በጣቶቹ እየጠነቋቆለ እውነትም ይሁን ሀሰት፣ ይጥቀምም ይጉዳ በኢንፎርሜሽን ውሽንፍር ለመደብደብ ራሱን ያልሰዋ ሰው ለማግኘት በእጅጉ አስቸጋሪ ወደ መሆን ደረጃ እየተሸጋገረ ነው፡፡
በቴክኖሎጂ ጉዳይ ይህንን ያህል ከተንደረደርን ዘንዳ ወደ ርዕሰ ነገራችን ሃሳባችንን እንሰብስብ፡፡ የአሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ኃይል ከመጀመሪያው ዕለት ጀምሮ ውጊያውን ማፋፋም የጀመረው በመደበኛው ዐውደ ውጊያ ብቻ ሳይሆን “በመዳፍ ጦርነት” ጭምር የውሸትና የክህደት ፕሮፓጋንዳ በማጧጧፍ ነበር፡፡ ይህንን የውሸት ፋብሪካ ሠራዊትም “ዲጂታል ወያኔ” የሚል “ወታደራዊ ማዕረግ” ሰጥቶት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በእነዚህ እኩይ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የጥፋት ኃይሎች አማካይነት በኢትዮጵያ ላይ ያልተነዛና ያልተፈበረከ የሀሰት ዓይነት አልነበረም፡፡
በመዳፋቸው ውስጥ የምትገኘውን የእጅ ስልካቸውን በጣቶቻቸው እየነካኩ በፌስ ቡክ፣ በቴሌግራም፣ በኢንስታግራም፣ በኢሜይል፣ በቫይበርና በዩቲዩብ ወዘተ… ጦርቱን ቀድመው በመክፈታቸው ስንትና ስንት አገራዊ ጉዳት እንደደረሰ እንዘነጋም፡፡ እነዚሀ እኩያን የሚበትኑትንና የሚዘሩትን የሀሰትና የአሉባልታ ወሬዎች አውቀውም ይሁን ባለማወቅ ብዙ ዜጎቻችን የፈጠራ ወሬዎቹን መልሶ በማዝመርና በመቸርቸር ራሳቸውን መጋት ብቻም ሳይሆን ሌሎችም እንዲጎነጩ በማድረግ ብዙ መደነጋገሮችና ጥፋቶች መፈጸማቸው አይዘነጋም፡፡ ብዙዎችም ለእንጀራ ማዕዳቸው የገቢ ምንጭ በማድረግ ነገሮች እንደምን ከቁጥጥር ውጭ ሊወጡ እንደቻሉ አብነቶችን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡
ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር እየተካሄደ ያለው የጦር ሜዳ ፍልሚያ ያለምንም ጥርጥር በቅርቡ ፍጻሜ አግኝቶ ጀግኖቻችንን በሆታና በዕልልታ መቀበላችን አይቀርም፡፡ ቀኑም እጅግ ቅርብ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በፍጥነት ተጠናቆ የማይዘመርለት ውጊያ በመዳፍ ላይ የእጅ ስልኮች የሚደረገው ጦርነት ብቻ ነው፡፡ ይህ የጥፋት ወረራ በተሸናፊው ኃይል “የዲጂታል ወያኔ አባላት” አዳዲስ ስልቶች ተነድፎለት ለዘመቻ እየተዘጋጁ እንደሆነ ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ የሆነ ማንኛውም ዜጋ ከዚህ በኋላ በረቀቁ ስልቶች ለሚደገሱለት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ጦርነቶች እንደ ካሁን ቀደሙ “ገበርኩ” ብሎ እጅ እንዳይሰጥ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታ ጭምር ነው፡፡ ቢቻልም ከወዲሁ ያለማሰለስ በዚህ ጉዳይ ለሕዝቡ ተገቢው ትምህርትና ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ዝግጅት ቢደረግበት አይከፋም፡፡
የአሸባሪው ሕወሓት ግባ መሬት ቢፈጸምም የሚበሰብሰው አጥንታቸው ራሱ መርዝ ስለሆነ አፈሩን መበከሉ አይቀርም፡፡ ውሸትና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በደማቸው ውስጥ የሚዘዋወርና በመቂኒያቸው ውስጥ የተከማቸ አሲድ ስለሆነ እየጠፉም ቢሆን “ለማጥፋት” ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው በተለያዩ አገራት ለስደት በላኳቸው ጀሌዎቻቸው አማካይነት መንፈራገጣቸው አይቀርም፡፡ ዛሬ ዓለም እውነቱን ለመፈተሽ ቆም ብላ ከማሰላሰል ይልቅ ለሚነዛው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ቀልቧን መስጠቱን ስለምትመረጥ እኛም ከወዲሁ ዝግጅት አድርገን መረጃዎችን “ከመዳፋቸውና ከጣቶቻቸው ላይ ልናስጥላቸው” ግድ ይላል፡፡
“የእውነት ዜና እግር ከማውጣቱ አስቀድሞ የሀሰት ወሬ ክንፍ አውጥቶ ይበራል” እንዲል የቻይናዎች ብሂል፤ “ክፉን እስከ ክንፉ” ነቅሎ ለማስወገድ ከወዲሁ የመዳፍ ውጊያውን ለማክሸፍ ነቅተን መጠባበቅና በርትተን መፋለም ይኖርብናል፡፡ በቅርቡ ድል በድል ለመዘመር ብቻም ሳይሆን የአሸባሪውን “የዲጂታል ሠራዊት” ኃይል እንዴት እንደምናሽመደምድም ከወዲሁ ዝግጅት ለማድረግ መበርታት ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 22/2014