የዓለምን እንዲሁም የሕይወትን ጨለማ ጎን እንጂ መልካም ገጽታና የተሻለ ተስፋ መመልከት የተሳናቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች ዘወትር የሕዝቦቿ ነገ ጨለማ እንደሆነ ከመናገር ቦዝነው አያውቁም። ከውስጥም ከውጭም ሆነው በያዙት የሚዲያ ግብአቶች ሁሉ ደጋግመው የሚነግሩንም ይህንን ነው። የጥፋት ኃይሉ አዲስ አበባን ከቧል፣ ይህን ተቆጣጥሮ እዚህና እዚያ ደርሷል በሚሉ የበሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳቸው ዜጎቻቸው አገሪቱን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ ጭምር መግለጫና ማሳሰቢያዎችን በማንጋጋትም ሌት ተቀን በትጋት ይሠራሉ።
አንድ ወራሪ ኃይል አንድን አካባቢ ተቆጣጠረ ማለት እያሸነፈ ነው ማለት እንዳልሆነ ግን ከገዛ ታሪካቸው እንኳን መማር የተሳናቸው ሆነዋል፡፡ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጥቂቶቹ በስተቀር በርካታ የአውሮፓ አገራትን በቁጥጥሯ ስር አድርጋ ነበር። ዛሬ ግን በዚያ ጦርነት የቱንም ያህል እልቂትና ግፍን ጀርመን ፈጽማ ስሟ በአሸናፊነት መዝገብ ላይ ሰፍሮ አይገኝም። እንዲያውም ያንን ሁሉ እልቂት ከፈጸመች በኋላ ጀርመን ፈርጣማ ክንዷ ዝሎና አስፈሪ አቅሟ ከድቷት እንዳልነበረች ሆናለች።
ዛሬም አሸባሪው ቡድን እዚህ ገባ፣ በዚያ ወጣ የህዝብን ሰቆቃ ከማርዘም የዘለለ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚለውጠው ነገር የለም። ቀድሞውንስ አሸባሪው ቡድን በመላው ኢትዮጵያ ጀሌዎቹን በትኖ የጭቃ ውስጥ እሾህ ሆኖ እየኖረ እንጂ መቼ አገር ለቆ ወጣና። የህዝቡ ትግልና ጦርነቱንም ፈታኝ ያደረገው ይህን የውስጥ ባንዳ ጊዜ ጠብቆ ከየተሸሸገበት እየወጣ አገር የማፍረስ ተግባሩን እንዳይፈጽም እንጂ በጦር ግንባርማ የኢትዮጵያን ሠራዊት እንደ ጀግና ፊት ለፊት ቆሞ ለመግጠም መች ደፈረና?፡፡
በባንዳዎች አሉባልታ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተጀመረውና ከዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢጠናቀቅ እንኳን አንዱ ብሔር ከሌላው ጋር ከእንግዲህ ወዲህ ታሪካዊ ጠላት ሆኖ እንጂ በሰላምና በአንድነት የመኖር ዕድል እንደሌለው በማሟረት ጦርነቱ የተወሰኑ ብሔሮች ጉዳይ ብቻ እንዲመስል የተለየ ገጽታን ለማልበስ የሚሄዱበት ርቀት የትኛው ጥግ ድረስ እንደሚዘልቅ አይታወቅም፡፡
ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት የህልውና ጦርነት ለማየት አይደለም ለመስማት የሚዘገንኑ ወንጀሎች፣በደሎችና ሰቆቃዎች በህዝቦቿ ላይ ተፈጽሟል። በአንድ ወገንና ህዝብ ላይ ብቻ የጦር ወንጀል፣ የዘር ማጥፋትና ማጥራት ወንጀል መፈጸሙን ከሩቅ ሆነው ሲያስተጋቡ የከረሙ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያኔ ያሟረቱት ሁሉ ዛሬ ላይ መና መሆኑን ወደው ሳይሆን የራሳቸው የጥናት ውጤት እውነቱን እንዲጋቱ አድርጓቸዋል።
ኢትዮጵያና ህዝቦቿን እስከወዲያኛው ለመበታተን ያስቀመጡት እቅድ ስላልተሳካም ወደ ሌላ የጥፋት እቅድ ፊታቸውን አዞሩ እንጂ አሁንም አርፈው አልተቀመጡም። የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ነገ ጨለማ እንደሆነ ከማስተጋባት በላይም ሟርታቸው እውን እንዲሆን በተለያየ ስልት ተቀናጅተው እየሠሩ ነው።
ኢትዮጵያ ሁሌም ህይወታቸውን ለመስጠት የማይሰስቱ ጀግኖች ባለቤት መሆኗ ሁሌም ከከበባት ሴራና ከገባችበት አዘቅጥ የሚያወጣት ተአምር አታጣም። ከአስከፊ ጦርነትና እልቂት በኋላም ሕዝቦቿ ያለፈውን ቁርሾ ይቅር ብለው አብረው ይቀጥላሉ። ለዚህም ህያው ታሪኳ ምስክር ነው። አንዳንድ ፀሐፍት ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው›› ሲሉ ይደመጣሉ።
ይሄ ምንም የማይካድ ሀቅ ነው። ኢትዮጵያን የማስተዳደር ዕድል የገጠማቸው የአገር መሪዎች ሁሉ በየቦታው ከተነሱባቸው አማጽያን ጋር በመዋጋት ወይም አልገብር ካለው ጦረኛ ጋር ለማስገበር፣ ወይም ስልጣናቸውን ሊነጥቅ ከመጣ ጉልበተኛ ጋር ሲዋጉና ሲፋለሙ የንግሥና ዕድሜያቸውን ይጨርሳሉ፡፡ አልያ ደግሞ ድንበሩን ገፍቶ ከመጣ ወራሪ ጋር ጦርነት ሲፋለሙ ኖረው ያልፋሉ፡፡ ከዚያም ሕዝቦቿ አብረው ይቀጥላሉ። ለዚህም ከጦርነት በኋላ ሌላው ዓለም ላይ የማይታይ ተቻችሎና ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ አብሮ የመቀጠል ጥበብ ተችሯቸዋል።
ታሪክ እንደሚነግረን ከሆነ ኢትዮጵያ አሁን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የገጠማትን የሚመስል የማዕከላዊውን መንግሥት ስልጣን ተነጥቀው በተባረሩና በትረ ስልጣኑን መልሰው ለመያዝ በሚያልሙ ግዙፍ ኃይሎች ፈተና ውስጥ ስትወድቅ የመጀመሪያዋ አይደለም። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይህን መሰል ትልቅ ፈተና ውስጥ ገብታ ትልቅ የሰውና የንብረት ውድመትን አስከትሎ ያለፈ ጦርነት አይታለች። ይህ ጦርነት ስመ ገናናው የሰገሌ ጦርነት እንደነበር አይዘነጋም።
አሸባሪው ቡድን በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጠነሰሳቸው ግጭቶች በርካቶች ውድ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችም ሀብትና ንብረታቸውን በትነው ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል።
እነዚህ ዘግናኝ እልቂቶች በንጹሐን ላይ ሲፈጸሙ ሆን ተብሎ አንድ ብሔር ሌላውን እንዳጠቃ በሚመስል መልኩ ነበር የተከወኑት። ይህ ደግሞ ሕዝብ ለሕዝብ እንዲጋጭና በአገሪቱ የእርስበርስ ጦርነት ተቀስቅሶ አገር እንዲበተን ለማድረግ የተሸረበ ሴራ መሆኑ ለማንም የተደበቀ አይደለም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የተፈጠረው ሰቆቃና የደረሰበት በደል የቱንም ያህል መሪር ቢሆን በበቀል ስሜት አንዱ አንዱን ሲያጠቃ አላየነውም። ይልቁንም አስከፊውን ጊዜ በብልሐት እያሳለፈ እዚህ ደርሷል። ነገም አስከፊውን ጊዜ የሚያልፍበትና አብሮ የሚቀጥልበት ብልሐት አይጠፋውም።
በዚህ ትውልድ ዕድሜ እንኳን እነ ሶርያ፣ሊቢያና የመሳሰሉት አገራት ሲበተኑና ሲፈራርሱ፣ ዛሬም ድረስ እንደ አገር መቀጠል ሲሳናቸው ለመመልከት ተችሏል። እነዚህ አገራት ከነበሩበት የሀብት ማማና የብልጽግና ጎዳና ወጥተው ለዚህ አስከፊ ደረጃ የተዳረጉት ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ፈተና የበለጠ ገጥሟቸው አይደለም። ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የተጋፈጠችው ፈተናና ያሳለፈችው እንቅፋት እንደነ ሶሪያና ሊቢያ ብትሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ስሟን እንኳን መስማት ብርቅ ይሆንብን ነበር። ግን አልሆነም። ያልሆነውም ዝም ብሎ በዘፈቀደ ሳይሆን በሕዝቦቿ የመጠቀ ሕሊናና አስተሳሰብ እንጂ።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ከሚጠብቃት ፈተና ይልቅ ያለፈው ያስፈራ ነበር። ዛሬ ላይ የቱንም ያህል ጠላቶቿ ተረባርበው አንገቷን ሊያስደፉ ጡንቻቸውን አፈርጥመው ብቅ ቢሉም ካሳለፈችው ፈተና አይከብድም። እንዲያውም የጠላቶቿ መጠንከር የሕዝቦቿን የተሸረሸረ የሚመስል አንድነት ጠንክሮ እንዲወጣ እያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ዛሬ ከተጋረጠባት ፈተና ይልቅ ነገዋ በብሩህ ተስፋ የተሞላ እንጂ የጨለመ እንዳይሆን ያደርገዋል።
ሁሌም ቢሆን የነገን ተስፋ የሚወልደው ዛሬ ነውና ነገ አስፈሪ አይሆንም። ነገ አስፈሪ እንዳይሆን ግን እንዲህ ያለውን አስከፊ ጊዜ ኢትዮጵያና ህዝቧ ሊያልፉት የሚገባቸው በጥንቃቄና ከታሪክ በመማር መሆኑን ደጋግሞ መገንዘብ ግን አስፈላጊ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ግንባር ማቅናታቸውን ባሳወቁበት መግለጫ እንዳሉትም ‹‹ኢትዮጵያ ከትናንትናዋ ይልቅ ነገዋ ታላቅ ነው። መከራ ማለፍ ነባር ችሎታዋ ነው። ይሄንን የገጠመንን መከራም እናልፈዋለን። ኢትዮጵያ ማሸነፏ አይቀርም። አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡››
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 22/2014