አዲስ አበባ፡- ልዩ ፍላጎትን አስመልክቶ በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ፖሊሲ ተቀርጾለት እየተሰራ ቢሆንም በአካል ጉዳት ላይ የተመሰረተውን ብቻ እንጂ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ያካተተ እንዳልሆነ ተገለጸ፡፡
በመንግስት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ዲን አቶ ጥበቡ በላይነህ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ልዩ ፍላጎት ማለት ጉዳት የደረሰበት ብቻ አይደለም፡፡
ከማህበረሰቡ ወይም ካለበት ደረጃ ልቆ የወጣ አቅምና እውቀት ያለውም የራሱ የሆነ ልዩ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ይሁንና በአገር ደረጃ ይህ ሀይል ድጋፉን ተነፍጓል፡ ፡ በተለይ በሚኒስቴር ደረጃ እገዛ እንደሚደረግለት የተቀመጠ ቢሆንም ድጋፉ ግን የሚታይ አይደለም፡፡ የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ተማሪዎች ማህበረሰቡ የረሳቸውና መንግስትም ከፖሊሲ ማውጣት ውጪ ያልሰራባቸው ናቸው የሚሉት አቶ ጥበበ፤ በሰውኛ ባህሪ ጉዳት የደረሰበት ቶሎ ይስበዋል። ይሁንና ልዩ ተሰጥኦም ያላቸው ልጆች ከዚህ ትይዩ መታየት ይኖርባቸዋል።
አብዛኛው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጉዳትን መሰረት አድርገው ብቻ ነው የሚንቀሳቀሱት። ይሁንና እነዚህን ልጆች መደገፍ ከተቻለ አገር ትጠቀማለች፡፡ እነርሱም ቢሆኑ በፍላጎታች ላይ ተመርኩዘው የተሻለ ስራ እንዲሰሩ እድል ያገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደነዚህ አይነት ተማሪዎችን መንግስት ከፖሊሲ ማውጣት ውጪ የመማሪያ ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠርላቸው እንደሚባ የጠቁሙት አቶ ጥበቡ፤ ማህበረሰቡ ላይም ቢሆን የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ሊሰራ ያስፈልጋል። አንድ ልጅ ልቆ ሲወጣ ታመመም ሊባል ይችላል። ይህ ደግሞ የፈለገውን የፈጠራ ስራ እንዳያከናውን ይገድበዋል።
በመሆኑም በሁለቱም በኩል ጥብቅ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል። ዓለምን የለወጡ አካላት ከፍተኛ ውጤት ያላቸውና የተማሩት ብቻ አይደሉም የሚሉት አቶ ጥበቡ፤ እንደ አርበርታንስታይን ያሉ ሰዎችን ማውጣት ካስፈለገ በእነዚህ ተማሪዎች ላይ መስራት ግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተረሱት መካከል ብዙ ሥራዎችን ሰርተው አንቱታን ያተረፉ ተማሪዎችን ለማፍራትም ከፖሊሲ ማውጣት ያለፈ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል። እንደ አቶ ጥበቡ ገለጻ፤ አሁንም መሆን ያለበት የተማረ ፍለጋና ውጤት ተኮር ስራ መስራት ሳይሆን ታች ላይ ያሉትንም የልዩ ተሰጥኦ ባለቤቶችን ማንሳትና እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው