ወይዘሮ ተዋበች አንዳርጌ ይባላሉ። ሁሌም የቀይ ዳማ ፊታቸው ፈገግታ አይለየውም። ረዘም ብሎ ሸንቀጥቀጥ ያለው ሰውነታቸው ቀኑን ሙሉ ያለድካም ለመንቀሳቀስ አግዟቸዋል።
አገርና ዜጋ ወዳድ ናቸው። ለአገራቸው ልዩና መቼም ሊሸረሸር የማይችል ጽኑ ፍቅር አላቸው። ጨዋታ አዋቂና ሳቂታ ቢሆኑም በአገር ጉዳይ ቀልድ አያውቁም። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር መዝመት እንደተሰማ ከጎናቸው ለመሰለፍ ፈጥነው የተመዘገቡትና አንድዬ ወንድ ልጃቸውን ሳይሳሱ ፈጥነው ያስመዘገቡት ለዚህ ነው። ለአገርና ለወገን ጥቅም ሲሰሩ ቢውሉ አይሰለቹም። ደከመኝን አያውቁም።
በአራዳ ክፍለ ከተማም ሆነ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ በሚገኘው የዶሮ ተራ መንደርተኛ አብዝተው ይታወቃሉ። የሚታወቁት ሕብረተሰቡን በማስተባበር የሽብር ኃይሎች ተባብረው በአገራችን ላይ በከፈቱት ጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብና በመስጠት ነው። የአካባቢያቸውን ፀጥታ ነቅተው በመጠበቅም ተጠቃሽ ናቸው። ቀደም ባሉት ዓመታት በዚህ አካባቢ እሳቸውን ያህል ሕብረተሰቡን በማስተባበርና አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ የተዋጣለት ግለሰብ ቀርቶ ተቋም አልነበረም። ዓይናቸው ለየት ያለ ነገር ካየ ልባቸው በፍጥነት ይጠራጠራል። በአካባቢያቸው የሚያዩት ፀጉረ ለውጥ ሰው ዓይነ ውሃው ደስ ካላላቸው እንደ ፖሊስ አስቁመው ማንነቱን ከመመርመር አይመለሱም። ለዚህ አካባቢያቸውን በንቃት ለመጠበቅ ሲሉ በጋራ መኖሪያ ቤት ደረጃ ባለው አደረጃጀት መሠረት የተሰጣቸውና በሥሩም 81 እማወራዎችን የሚመራው የመቶ መሪ ኃላፊነት ረድቷቸዋል።
ወይዘሮ ተዋበች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠትም የሚቀድማቸው የለም። ጎረቤቶቻቸው እንደሚናገሩት ለበጎ ነገሮች ሁሉ ሰው ማግባባትና ማሳመን ይሆንላቸዋል። የማስተባበሩን ሥራ ተክነውታል። በመሆኑም አሁን ላይ ብዙ ሴቶችን በዚህ መልክ በመቅረፃቸው እንደሳቸው ሀብት እያሰባሰቡ ወገንን የሚደግፉ አያሌ ደቀ መዛሙርት ማፍራት ችለዋል። ከአካባቢያቸው አልፈው ለሰሜን ማዘጋጃና ለድፍን አራዳ ክፍለ ከተማም አርአያ የመሆናቸውም ገድልም እየተወሳላቸው ነው። ክፍለ ከተማው ለሠራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀትና ተፈናቃይ ወገኖችን በመደገፍ ቀዳሚ ተጠቃሽና ልምድ ያካበተ እንዲሆን ካስቻሉት ሴቶችም ቀዳሚዋ ተዋበች ናቸው።
እንዳወጉን ወደ እንዲህ ዓይነቱ ሰናይ ተግባር ከገቡ ቆይተዋል። የለውጥ መንግሥት መምጣቱን ተከትሎ የሠላምና የሕዝብ ፀር የሆኑት የጥፋት ኃይሎች በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ብጥብጥና ሁከት በማስነሳት አገር ወደ ማተራመስ ተግባር ከገቡ ጀምሮ ነው።
‹‹ቀደም ሲልም በነዚህ የጥፋት ኃይሎች አማካኝነት በ100ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ተፈናቅለዋል›› የሚሉት ወይዘሮ ተዋበች በግላቸው ተነሳሽነት ሕብረተሰቡን በማስተባበር ለወገናቸው አነሰም በዛ ከዕለት ጉርሳቸው በማቀናነስ የአቅማቸውን ድጋፍ ማድረግ የጀመሩትም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይናገራሉ። በግላቸውም ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆንም ከየክልሉ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከዕለት ጉርስ ጀምሮ የአልባሳት ድጋፍ ለማድረግ ሲታትሩ ከርመዋል። ድጋፉን ሲያደርጉ የቆዩት ደግሞ ሙሉ የትራንስፖርት ወጪያቸውን በራሳቸው ሸፍነው እዛው ተፈናቃዮቹ ያሉበት አካባቢ ድረስ በመሄድ ነው።
እነዚህ የአገርና የሕዝብ ፀር የሆኑ የጥፋት ኃይሎች በየጊዜው በሚፈጥሩት ብጥብጥና ሁከት አያሌ ዜጎችን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ላይ ግልፅ ኢሰብአዊ ጥቃት በመፈፀም በይፋ ወደ ጦርነት በመግባት አገርን ወደ መበተንና ዜጎችን ወደ ማፈናቀል ተሸጋግረዋል የሚሉት ወይዘሮዋ በነዚህ ምክንያትም ለተፈናቃይ ወገኖችና ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን የሚያደርጉትን ድጋፍ በተጠናከረ ሁኔታ ማድረግ መጀመራቸውን ያወሳሉ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ለሠራዊቱ በሚደረግ የስንቅ ዝግጅት፣ በጥሬ ገንዘብ በሚደረግ ድጋፍ እንዲሁም ለተፈናቃዮች በሚደረጉ የተለያዩ (ምግብና አልባሳት) ድጋፎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። እኛ ባገኘናቸው ወቅት ማለትም ኅዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም በሕልውና ዘመቻው ለተፈናቀሉና በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደብረ ብርሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ወደ ዛው ለማቅናት በግላቸው በተኮናተሩት መኪና ላይ ያሰባሰቡትን የአልባሳትና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያስጭኑ ነው። በሚያስጭኑበት ወቅት የወንዱን በወንድ፤ የሴቱን በሴት፤ የህፃናቱን በህፃናት እንዲለይ አድርገው ነው።
ወይዘሮ ተዋበች እንዳወጉን፣ እኛም እንዳስተዋልነው ወይዘሮዋ ለቀውሱ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ወገኖቻቸውን ለመታደግ የተነሱት ከመኮሮኒ ጀምሮ የተለያዩ የሴትና ወንድ እንዲሁም የህፃናት አልባሳትና ጫማዎችን በማሰባሰብ ነው። ሦስት ኩንታል ወይም 150 ኪሎ ግራም መኮሮኒ ሲገኝበት አንዱን ኩንታል የገዙት ከራሳቸው ኪስ በወጣ ገንዘብ ነው። ድጋፉን ደብረ ብርሃን ከተማ ድረስ ወስደው አስረክበው ለመመለስ ለደርሶ መልስ የዋለውን 2ሺህ 500 ብር ወጪም ከሰባት ልጆቻቸው የወር ቀለብ ላይ ቀንሰው ነው። ልጆቻቸው ጦርነቱ በድል እስከተጠናቀቀ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማገዝ ቁርስና ራት ለመተው ተስማምተዋል። ምሳ ብቻ እንዲያቀርቡላቸውም ቃል አስገብተዋቸዋል።
‹‹ለአገሬ እና ለወገኔ እንኳን ከወር ቀለቤ ላይ ቀንሼ ሙሉ ቀለቤን ሰጥቼ ከነልጆቼ ጾሜን ባድርም አይቆጨኝ›› የሚሉት ወይዘሮ ተዋበች የሰባት ልጆች እናት ናቸው። ከሰባቱ ውስጥ ስድስቱ ሴቶች ሲሆኑ አንዱ የቤቱ ብቸኛ ወንድና የበኩር ልጃቸው ነው። ዘንድሮ 22ኛ ዓመቱን ይዟል። በመሆኑም በጣም ይሳሱና ይወዱታል። ሰርክ ከአጠገባቸው እንዲርቅ አይፈልጉም። ይሁንና እንዲህ የሚሳሱለትንና በፍፁም ከአጠገባቸው እንዲርቅ የማይፈልጉትን አንድዬ ወንድ ልጃቸውን ዶክተር ዐቢይ ወደ ጦር ግንባር መሄዳቸውን በዜና ማሰራጫዎች መገለፁን ተከትሎ ፈጥነው ወደ ወረዳ በመሄድ ዘምቶ በሹፌርነት ሙያው ሠራዊቱን እንዲያገለግል ሲያስመዘግቡት የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ቅሬታ አልተሰማቸውም። ይሄንኑ ስሜታቸውንና እርምጃቸውን ‹‹ከሀገሬ የሚበልጥብኝ ምንም ነገር የለም›› ሲሉ ይገልፁታል። ለእርምጃው ያነሳሳቸውን ሁኔታ ሲገልፁትም ‹‹አንድም ሆነ ሁለት ልጅ የሚያድገው በአገር ነው። አገር ከሌለች ልጅም አይኖር፤ አያድግም›› በማለት ነው።
የ55 ዓመቷ ወይዘሮ ተዋበች እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን ተገንዝበው ነው የዘመቱት። መሪ የሚኖረው ሕዝብ ሲኖር ነው ብለው በተማሩት የውትድርና ጥበብና ታክቲክ ሕዝቡን ለመታደግ ነው። ይሄን የመሪ ፈር እንደ ጥንቱ የአፄ ምኒልክ ዘመን ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ተብሎ ሁሉም እንዲዘምት አስገዳጅ አዋጅ ባይታወጅም ‹‹ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ›› ብለው ጥሪ ላቀረቡት ንጉስ ምላሽ እንደሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ጥሪ ምላሽ መስጠትና ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሰለፍ አለበት ብለው ያምናሉ።
‹‹ጁንታው ለእኩይ ዓላማው ከሰባት ዓመት ልጅ ጀምሮ ነው ያስታጠቀው›› የሚሉት ወይዘሮዋ ሆኖም የሳቸው ሴት ልጆች ዕድሜያቸው ባይፈቅድም እራሳቸው ለመዝመትም መመዝገባቸውን ገልፀውልናል። ፈጥነው መዝመት ቢፈልጉም እየሰሩት ያለው ሥራ ከዘመቻ በላይ ነው በሚል ሳያሰልሱ የተጠመዱበትን የድጋፍ ተግባር ታሳቢ በማድረግ ወረዳው እስከ አሁን ያላዘመታቸው መሆኑንም አልሸሸጉንም።
ወይዘሮ ተዋበች እንዳወጉን ለመከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው የሂሳብ ቁጥር በጥሬ ገንዘብ ገቢ እንዲሆንም ያደርጋሉ። በዓይነትም በጥሬ ገንዘብም እስካሁን ያስገቡት በቤት ላይ እንደሚውለው ጉልበታቸው ሁሉ ከቁጥር ባያገቡትም ቃል ከገቡላቸው ውጪ በቅርቡ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎችን በማስተባበር ለሠራዊቱ 25ሺህ ብር እንዲገባ አድርገዋል።
‹‹ሴት ሁሌ ደጀን ነች። በኔ አስተሳሰብ ሴት ከሌለች አገር የለም›› ያሉንና ሌላዋን የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አስራት ተፈራን ያገኘናቸው በአራዳ ክፍለ ከተማ ጊቢ ውስጥ ሴቶች ተደራጅተው ለሠራዊቱ በሚያደርጉት ስንቅ ዝግጅት ላይ ዳቦ ቆሎ ሲቆርጡ ነው። በየትኛውም ሥፍራ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ሲከናወን ሳያሰልሱ ይሳተፋሉ።
ወይዘሮዋ አስራት እንዳጫወቱን በአካባቢያቸው ባለው ስንቅ ዝግጅትና የአካባቢ ፀጥታን የመጠበቅ አደረጃጀት 81 ሴቶችን ይመራሉ። ከእንጀራ መጋገር፣ ወጥ መሥራትና ልብስ ማጠብ ጀምሮ ለባለቤታቸውና ለቤተሰባቸው በየመመገቢያ ሰዓቱ ምግብ እስከ ማቅረብ የቤት ውስጥ ሥራ በሙሉ የእርሳቸው ነው። ልጅ መንከባከብና ትምህርት ቤት ማድረስ እንዲሁም እንደ ልቅሶና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች መሣተፍም እንደዛው። የሽብር ቡድኑ የመጀመሪያዋን የጥፋት ፊሽካውን እስከ ነፋበት እለት ድረስ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ይህንኑ ተግባር በማከናወን ነበር። ‹‹ሆኖም አሁን ቅድሚያ የምሰጠው ለሠራዊቱ ስንቅ ዝግጅትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የማድረጉ ተግባር ነው። ለዚህ ጉዳይ ሁሌም ዝግጁ ነኝ። እንጀራ እጋግርም ሆነ ልብስ አጥብ እንደሆን እዚህ ቦታ ስንቅ ዝግጅት ወይም የፀጥታ ችግር አለ ተብሎ ሲደወልልኝ እርግፍ አድርጌው ነው የምሄደው›› በማለት ሴቶች በደጀንነት እየከፈሉት ያለውን መስእዋትነት ገልፀውልናል።
ሴቶች ለአገርና ወገናቸው በግንባር ከመሰለፍ ባሻገር በደጀንነት ከፍተኛ መስእዋትነት እየከፈሉ መሆናቸውን፤ በተለይ በወረዳው ያሉ ሴቶች እያከናወኑት ያለው ተግባር ለሌሎች ወረዳዎች አርአያ እንደሚሆን ከወረዳ አራት ያገኘነው መረጃ አረጋግጦልናል።
ወይዘሮ ተዋበች 14 ኩንታል አገልግሎት የሰጡ አልባሳት፣ ሁለት ኩንታል ጫማ፣ አንድ ኩንታል ብረት ድስት፣ አንድ ኩንታል ሳህንና ትሪዎች እንዲሁም 150 ኪሎ ግራም መኮሮኒ ባለፈው ቅዳሜ በሕልውና ጦርነቱ ተፈናቅለው በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን የወረዳ አራት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የሺሞላ ፀጋዬ ገልፀውልናል። በዚህ በኩል የካበተ ልምድ ያላቸውና ለሌሎች ሴቶችና ተቋማትም አርአያ መሆን የቻሉ መሆናቸውንም ኃላፊዋ ጠቅሰውልናል።
በጡረታ ከመገለላቸው አስቀድሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በበረራ ክፍል አስተናጋጅነት ሲሰሩ የነበሩት የአዲስ አበባ፣ ቀበና አካባቢ ነዋሪዋ ወይዘሮ ቦጋለች ከበደ ሌላዋ የደጀንነት መስዕዋትነት የከፈሉና አሁንም እየከፈሉ ያሉ እናት ናቸው። አገር ተወራ የቅንጦት ኑሮ አያሻም ቦጋለች ለአገርና ወገን ያላቸው ፍቅር ቪላ ቤታቸውን እስከ መሸጥ አድርሷቸዋል። ከቤታቸው ሽያጭ ላይ ለመከላከያ ሠራዊት የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል። አንዱን ሚሊዮን ብር ደግሞ የአእላፋት ኢትዮጵያውያኖች የወደፊት ተስፋ ለሆነው ለህዳሴው ግድብ ለግሰዋል።
ወይዘሮ ቦጋለች እንደሚሉት ያለ አገር ቤትና ንብረት ዋጋ የለውም። ሕይወትንም ማቆየት አይቻልም። የትኛውም ዓይነት ኢትዮጵያዊ ይህንን በውል መገንዘብና ‹‹እኔ ሞቼ ኢትዮጵያ ትቁም›› ብሎ የዘመተ መሪውን መከተል ይገባዋል። ኢትዮጵያ አገሬና ሕዝቦቿ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ዓይነት መሪ በማግኘታችን ዕድለኞች ነን ባይ ናቸው።
ወይዘሮ ቦጋለች እንደሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግምባር መዝመት የዓላማ ፅናትና ቁርጠኝነታቸውን፤ ለአገራቸው ያላቸውን ጽኑ ፍቅር ያሳያል። ከአገር አፍራሾች ጋር ያበረ የምዕራባዊያኑ ሴራ ያለመንበርከካቸውንና ነፃነት ወዳድ መሆናቸውን ሁሉ ያመለክታል።
ወይዘሮ ቦጋለች ከበደ “የየትኛው አገር መሪ ነው ይሄን ያደረገው?” በማለትም ከጠየቁ በኋላ የየመኑ መሪ አሊ አብደላ ሳልህ፣ የሶሪያው በሽር ልአሳድ፣ የኢራቁ መሐመድ ሚፍታህም ሆኑ ሌሎች እንዳላረጉት ይገልፃሉ። እሳቸው ቤታቸውን ሸጠው ለሠራዊቱ ደጀንነታቸውን ያሳዩት በዚሁ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁርጠኛ አቋም ተነሳስተው መሆኑን በመግለጽ ሀሳባቸውን አሳርገዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አድነው አበራ እንደገለፁልን ከሆነ ሴቶች በሕልውና ዘመቻው ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለመከላከያ ሠራዊቱ በስንቅ ዝግጅትና በጥሬ ገንዘብ እያደረጉት ያለው ድጋፍ በገንዘብ ሊሰላ የማይችል እጅግ ከፍተኛ ነው። አርአያነቱም የጎላ ነው። ለሠራዊቱ ጉልበት ለተፈናቃዮች አለኝታ እየሆነም ይገኛል። የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የሙያና ሲቪክ ማህበራት፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የግል ባለሀብቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ይህንን አርአያነት ያለው የሴቶች ሰናይ ተግባር ተከትለው የየበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2014