ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በአንድነት በመመከት አንፀባራቂ ታሪክ አላቸው። ልጆቻቸው በታሪኩ የሚታወቁት አገራቸውን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች ሲጠብቁና ደማቸውን አፍስሰው የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉላት ነው። ለኢትዮጵያውያን አገራቸው መኩሪያቸውና መከበሪያቸው ናት። ስለ ፍቅር እጅ፣ ስለ ጠብ ከሆነም ነፍጥ በማንሳት የሚታወቁት ኢትጵያዊያን በአገራቸው ክብር አይደራደሩም።
ኢትዮጵያ ባህር ተሻግረውና ድንበር ጥሰው ሊያስገብሯት ሊወሯትና ቅኝ ሊገዟት አልመው ለመጡ ጠላቶቿ በየትኛውም ወቅት ሸብረክ ብላ፣ እጇን ሰጥታ አታውቅም። ጠላቶቿን በሙሉ እያሳፈረች ዘመናትን በድል ተሻግራለች።
የኢትዮጵያን የጀግንነት ገደልና ቆራጥነት በአብዛኛው በሕዝቦች ብቻ ሳይሆን በመሪዎች ፊት አውራሪነት የታጀበ ነው። በተለይ በጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ መሪዎች ግንባራቸውን ለጥይት በመስጠት ሕዝባዊ ጦራቸውን በአውደ ውጊያ መርተዋል።
አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ፣ አፄ ዮሐንስ በመተማ፣ አፄ ምኒልክ በዓድዋ፣ መንግስቱ ሃይለማርያም በሶማሊያ ጦርነት ከአገርና ከሕዝባቸው ጎን ተሰልፈው ተስፋፊ ወራሪዎችን ከተፋለሙ መሪዎች መካከል የቅርብ ትውስታዎቻችን ናቸው።
በየዘመናቱ የተነሱ ጠላቶቿን በሕዝቦቿ አንድነትና የጋራ ክንድ እያሳፈረች ዘመናትን የተሻገረችውና ለጥቁሮች የነፃነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በዚህ ዘመንም ጠላት ፈታኞቿ አልተኙላትም። ከውጭ እጅ እና አንገታቸው የረዘመ ከውስጥ እይታቸው የተንሸዋረረ ብሎም የጨለመ ጠላቶቿ እየፈተኗት ናቸው።
በተለይም የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በሕዝብ የጋራ ትግል ሥልጣኑን ከተነጠቀ በኋላ የሥልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ኢትዮጵያን መምራት የምችለው ብቸኛ ድርጅት ‹‹እኔ ብቻ ነኝ›› በሚል ትእቢት ተወጥሮ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎም ኢትዮጵያ ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተገዳለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር የዶክተር ዐቢይ አሕመድም ለሠላም የዘረጉት እጅ ተቀባይ ባለማግኘቱ የአሸባሪውን ቡድን ግብአተ መሬት በማፋጠን ሂደት መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲተባበር በማድረግ ረገድ በርካታ ተግባራት አከናውነዋል። በሳል ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀናት በፊት ደግሞ ኢትዮጵያ የሚለው ስም የአሸናፊዎች ስም እና የነጻነት ምልክት ነው ሲሉ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደረገውን ሁለንተናዊ ትግል ቢሮ ሆነው ከመምራት ባለፈ በአካል በውጊያው ግንባር ከሠራዊቱ ጋር ጦሩን ለመምራት ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት መከፈል የሚገባውን መስዋትነት በተግባር ሊያሳዩ ከፊት ቀድመዋል።
እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ስትፈርስ ቆሜ አልመለከትም፣ ሕዝቤ ሆይ ግንባር እንገናኝ›› ብለው፣ ግንባር በመገኘት በ21ኛው ክፍለ ዘመን መሪዎች ሊያደርጉት አይደለም ሊያስቡት የሚከብዳቸውን ውሳኔ ወስነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦሩን በግንባር ሆነው ለመምራት መዝመት ትርጓሜ እንዴት ትመለከቱታላችሁ? ውጤቱንስ? የሚል ጥያዌ በማንሳት ለተለያዩ ምሁራንና የፖለቲካ አመራሮችና ስመጥር ግለሰቦች አዲስ ዘመን ጥያቄ አቅርቧል።
አስተያየታቸው ካጋሩን መካከል የስነ ልቦና ባለሙያና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ወይዘሮ ሠላም ተሾመ አንዷ ናው። ወይዘሮ ሠላም እንደሚሉት ለአንድ አገር ሉዓላዊነት ነጻነትና እድገት የመሪና የተመሪ ሁለንተናዊ መግባባት እጅጉን ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ በድርጅትም በአገርም መሪነት ሲባል ደረጃው ይለያይ እንጂ መሪ ጠቢብ ሆኖ ተመሪውን ከኋላ ሲያስከትል የመምራት መመራት ሂደት እጅጉን ይሰምራል። ውጤታማም ይሆናል። መሪ ጥበበኛና አዛዥ ብቻ ሳይሆን ሰርቶ የሚያሳይና ታዛዥ ሲሆን ደግሞ በየትኛውም ደረጃ በመሪና በተመሪ መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ ይሆናል። ይህም ለሁለንተናዊ ውጤታማነት ሁነኛ መሠረት የሚጥል ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ውሳኔም ወቅቱን ታሳቢ ያደረገና ከመሪነት ጥበብ ውስጥ አንዱ እና ዋናው እንደሆነና ውጤቱም በርካቶችን እንደሚያነቃቃ አፅዕኖት የሚሰጡት የስነ ልቦና ባለሙያዋ፣ ‹‹በሕዝብ ስነልቦና ውስጥም አገርን በሚመለከት ከቃል በላይ ተግባር ትልቅ ትርጉም፣ አቅምና ተጽእኖ እንዳለው ምስክር የሚሰጥ ነው›› ይላሉ።
የአንድ አገር መሪ አገርን ብሎ ግንባር ሲገኝ ለሕዝብ የሚሰጠው ስሜት ግዙፍ ስለመሆኑ አፅእኖት የሚሰጡት የስነ ልቦና ባለሙያዋ፣‹‹የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተግባር የተረጋገጠ አገርን መውደድና አገርን የማክበርና የመጠበቅ ተምሳሌትነትም እያንዳንዱ ሰው እኔስ ምን እያደረኩ ነው በሚል ስሜት ራሱን እንዲጠይቅና ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው›› ይላሉ።
የስነ ልቦና ባለሙያዋ ሠላም እንደምታስረዳው፣ አገር ሁሉም ዜጋ በያለበት ቦታና በየተሰማራበት የሥራ መስክ በሚያሳርፈው አሻራና ድምር ውጤት የሚገነባ ነው። የአገርን ሉዓላዊነትና ነጻነትና ክብር የማስከበር የመጠበቅ ሥራ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። የአገርን ሠላም የማስጠበቅ ኃላፊነትም በመከላከያ ሠራዊት አባላት ወይንም በሌሎች የፀጥታ አካላት ብቻ የሚከወን አይደለም። ሁሉም ዜጋ የየራሱን ድርሻ መወጣቱ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው።
ይህን ታሳቢ በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ሲቃኝ፣ ዜጎች ስለ አገራቸው ቆም ብለው እንዲያስቡ ክብርና ነጻነትን ከጠላት የመታደግ ኃላፊነት እንዳለባቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ ስለመሆኑ የሚጠቁሙት ባለሙያዋ፣ ‹‹ትርጉሙም የአገሬ ጭንቀት የእኔም ነው፣ ጠላቶቻችን የመፋለም ተጋድሮም እኔንም ይመለከተኛል እንዲሉ የሚያደርግ ስለመሆኑም ያመላክታሉ።
‹‹በዛሬ ተግዳሎ ሁሉ አልፎ ታሪክ ሆኖ ሲወሳም ለነገው ትውልድ የሚያስተላልፈው መልእክት ግዙፍ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡት ባለሙያዋ፣ ‹‹በትውልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያዊነት ታላቅነት አልሸነፍ ባይነት መሆኑን የማስረገጥ፣ ትውልዱም አገሩን እንዲጠብቅ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንዳለበት የሚያስተምር ነውም›› ይላሉ።
ይህን እሳቤ የሚያጠናክሩት አንጋፋው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌዴሌቦም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ጋር በሚካሄደው ጦርነት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርአያ ለመሆንና በተግባርም ለመዋጋት መወሰናቸው እንደ ታሪክ ሊቀመጥ የሚችል መልዕክት ነው ብለውታል። ውሳኔው ታሪካዊና ወቅቱን የጠበቀ ነው ሲሉ ገልፀውታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔና ዘመቻው አገር የማጽናትና ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን የነፃነት፣ ታሪካዊ ስምና ክብር የማቆየትና አገር ከነክብሯ የሚያስቀጥል በመሆኑ አድናቆት የሚቸረው ከመሆን ባለፈ የመሪውን ስብእና የሚያስመለክት ስለመሆኑ የሚያስረዱም በርካቶች ናቸው።
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ንጉስ በላይም፣ አገሪቱ ከተጋረጠባት አደጋ ለማዳን እየተደረገ ባለው የሕልውና ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ዓውደ ውጊያ መዝመታቸው ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ታላቅ ክብር የሚያሳይ ነው ሲሉ ይገልፁታል።
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትም ሆነ፤ መሪ መሆን የሚቻለው አገር ሲኖር ነው ብለው ዘምተዋል፤ የሚሉት ዶክተር ንጉስ፣ ዕድሜው አገርን ለማዳንና ለመታደግ የደረሰ ዜጋ ሁሉ የእሳቸውን ፈለግ በመከተል መዝመትና ለአገሩ ያለውን ክብር የሚያሳይበት ጊዜ ስለመሆኑም ሳይስገነዝቡ አልለፉም።
የዶክተር ንጉስን እሳቤ የሚጋሩት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ አገር ከነክብሯ ለማስቀጠል የአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና መሪዎችን ባህሪ ወሳኝ መሆኑን አፅእኖት ሰጥተውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአባቶች የጀግንነት ስሜትና ወኔ በውስጣቸው መኖሩንና የተግባር ሰው መሆናቸውን የሚመሰክር መሆኑን የሚጠቁሙት ፕሬዚዳንቱ፣‹‹ውሳኔውን ተከትሎም ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያዊ ቁርጠኛ መሪ እንዳለው በተግባርም ጭምር ተመልክቶበታልም ነው›› ያሉት።
በኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አገር ኢትዮጵያዊነትም አሸናፊነት መሆኑ በትላንት ታሪካችን በዛሬው ሥራችንም እየታየ ያለ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያም በአገር ፍቅር ለእናት አገር የሚከፈለውን መስዋትነት በመክፈል ላይ ይገኛል። እዚህ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርን ለማዳን ግንባር ድረስ መዝመትም ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሞራል መነሳሳትን ፈጥሯል።
አሁን ላይም በርካቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተከትለው ወደ ግንባር ለመክተት በቁጭት ተነስተዋል። አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴን ጨምሮ ሌሎችም ስመጥርና የአገር ምልክት የሆኑ ግለሰቦች ግንባር ለመዝመትና ለአገራቸው ጀርባ ሳይሆን ደረታቸውን ለመስጠት ዝግጁ ስለመሆናቸው እወቁት ብለዋል።፡
ይህን የሚያጠናክሩት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ ውሳኔው ሕዝቡ የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር በወኔና በቁጭት እንዲነሳ ስለማድረጉን አሳውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር የመዝመት ውሳኔ ከሁሉ በላይ የአሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ወረራ አገርን የማፍረስና እንደ ሕዝብ የመጥፋት አደጋ ተደቅኖብናል የሚለውን ሀሳብ ለመረዳትና ለመዝመት እድል ሰጥቷል ነው››ያሉት።
በእርግጥም በአሁንማ በርካታ በተለይም ወጣቶችም ከዚህ ቀደም በጀግኖች አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ተጋድሎ አገራቸው ታፍራና ተከብራ እዚህ መድረሷን ስንዘክር እኛም በተራቸው የተላለፈልንን አደራ የመወጣት ኃላፊነት አለብን እንዲሉ እያደረገ ይገኛል። አገር መሪ ግንባር እየተዋጋ ቁጭ ብሎ የሚመለከት ወጣት አይኖርም እያለ፣ ከደጀንነት ወደ ግንባር በመሄድ እንደአባቶቹ ታሪክ የመሥራት ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ እየታየ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት ገዛኸኝ ገብረማርያም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመት በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ መልእክት የሚያስተላልፍ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ።
ውሳኔን ተከትሎ የአዲስ አበባ ወጣቶች ከበፊቱ የበለጠ መነቃቃትና ቁርጠኝነት የመፍጠሩን የሚገልፀው ወጣት ገዛኸኝ፣ ባለአደራው ትውልድ ከአባቶቹ የተረከባትን አገር አስከብሮ ለመጪው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያሳስብ መልዕክትም ጭምር መሆኑን ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ በጠላቶቿ በተፈተነችበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ትድን ዘንድ፣ የቱንም አይነት መስዋዕትነት ለመቀበል ዝግጁ መሆን የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነና ፖለቲካዊም ሆነ ሌሎች ልዩነቶችን ወደ ጎን በማለት አገር የማዳን ጥሪን ከመቀላቀል ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ እየታየ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ለአገር ሕልውና ዘመቻው ግንባር ተገኝተዋል። አንዳንዶችም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ የሚደነቅና ውጤታማነቱ ከፍተኛ መሆኑን እየገለፁ ናቸው።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ምክትል ሊቀ መንበርና የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበበ፣ ውሳኔው ኢትዮጵያ የመጣችበትን የጀግንነት ታሪክ የሚደግም ነው›› ይሉታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ የበላይ አዛዥ እንደመሆቸው መጠን በቅርበት ተገኝተው ጦሩን የማጀገንና የማበረታታት ሥራ መሥራታቸውና ያላቸውን ወታደራዊ ልምድና የማዋጋት ሚና ለመወጣት መወሰናቸው ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ትልቅ አንድምታ እንዳለውም አፅእኖት ይሰጡታል።
እኛም ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ላለችን አንድ አገር ያለንን አንድ ሕይወት ለመስጠት ዝግጁ ነን የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ፓርቲያቸው በርካታ አባላቱን ወደ ግምባር መላኩንና እንደ ምክር ቤትም በሁሉም ክፍለ ከተማ ግብረ ኃይል በማቋቋምና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ከአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ አስፈጻሚዎች ጋር በተናበበ መልኩ የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም ኢትዮጵያ ለማዳን የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆናቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም።
ውሳኔው በወታደሩ ስነ ልቦና ላይ የሚፈጥረው ተነሳሽነት ከፍተኛ ስለመሆኑም ያሰምሩበታል። ውሳኔውን አገርን ለማዳን ከተጀመረ ወሳኝ እርምጃ ጋር የሚያነፃፅሩት፣ የቀድሞ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ብርጋዴር ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ይህን እሳቤ ያጠናክሩታል።
ብርጋዴል ጄኔራሉ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታም፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር በመሄድ በጦር ሜዳ በመገኘት ሠራዊቱን ለመምራት በመወሰናቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎችን የጀግንነትና የድል አድራጊነት ዓርማ አድሰዋል ነው››ያሉት።
እንደ ብርጋዴል ጄኔራል ዋሲሁን ገለጻ፤ አሸባሪዎች ወረራ በማካሄድ በንጹሐን ላይ አረመኔያዊ ተግባር ሲፈጽሙ የአገሪቷ መሪ በበኩላቸው የከሃዲዎቹን ተግባር ለመከላከል በጦር ግንባር መገኘታቸው በራሱ የድል አድራጊነት ስነልቦናን ያጠነክራል።
ጦር ሜዳ ተገኝተው ጦሩን ለመምራት በመቻላቸው በግዳጅ ለሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊቱና ለሚመሩት ሕዝብ ትልቅ አክብሮት እንደሚያሳይ ያመላከቱት ብርጋዴል ጄኔራሉ፣ አሁን ባለው የመሪዎችና የሕዝቡ ወኔ ወራሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ይደመሰሳሉ ነው ያሉት።
በእርግጥም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር መገኘት ለወታደሩ ከፍተኛ መነሳሳት በመፍጠሩም ድል ከኢትዮጵያ ጎን ቆማለች። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም ቀደም ሲል በሽብር ቡድኑ ስር የነበሩ የተለያዩ ቦታዎች በአስደናቂ ብቃት በጥቂት ቀናት ውስጥ እያስለቀቀ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣው ይገኛል።
ይሁንና ለሁለንተናዊና ፈጣን ድል አሁንም ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም ሰንደቋን ከፍ አድርገው ወደ ታላቅነት ክብሯ የሚመልሱ አገር ወዳድ ልጆች ሁሌም ደጀን መሆናቸው የግድ ይላል። እንደ የአስተያየት ሰጪዎቹ የጋራ ምክረ ሃሳብ ከሆነም፣ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ጠላቶች የተቃጣባትን የሕልውና ጦርነት ለመቀልበስ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ርብርብ የሚጠይቅ ነው። አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ መከተል ይገባል።
ወጣቱም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪውን በመከተል አገርን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ወራሪ ኃይሎችን መደምሰስና ሕልውናን ማስጠበቅ ይገባዋል። በጦር ሜዳ ግንባር መገኘት የማይችልም፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ በማቀበልና በፍቃደኝነት የተሰለፈውን ሕዝብ በማበረታታት እገዛ ማድረግ ይኖርበታል። ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2014