በአገሪቱ የሚገኙ ከተሞች በየጊዜው እየጨመረ የሚገኘውን ህዝብ ለማስተናገድ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመኖርያ ቤቶች ግንባታና በልዩ ልዩ የስራ እድል ፈጠራ ላይ የሚታዩ ለውጦች ማሳያ ናቸው፡፡ ነገር ግን ህገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ፣ ሰነድ አልባ ለሆኑ ቤቶች ሰነድ የመስጠት ስራ፣ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ፈጣን አለመሆን እንዲሁም የመስሪያ ቦታ ሳይዘጋጅ ለወጣቶች ብድር መስጠት ከተሞች ያልተሻገሯቸው ችግሮች እንደሆኑ ይገለጻል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም በዚህ ዙሪያ ሰሞኑን ከሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ በሁሉም ክልሎች የተደረገው የመስክ ምልከታ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ሪፖርቱ በዋነኝነት በከተሞች ስራ እድል ፈጠራ፣ የከተሞች የመልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ስራዎች፣ የከተማ ፕላን ዝግጅት፣ የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት እና የመሬት መረጃ አያያዝ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
በሶማሌና በሐረሪ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተደረገውን የመስክ ምልከታ የመሩት ወይዘሮ ገነት ገብረእግዚአብሄር እንዳሉት፤ በሶማሌ የስራ ባህል የዳበረ አለመሆን፣ በከተሞችና በዞኖች ውስጥ አመራር መቀያየር፣ የህግ የበላይነት ባለመኖሩ የመሬት ወረራ መስፋፋቱ፣ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር አድሎ መኖር እንዲሁም ወጣቱ ተደራጅቶ ቢሰራም የገበያ ትስስር ባለመኖሩ ውጤታማ አለመሆን በመስክ ምልከታው ተስተውሏል፡፡
በክልሎቹም ይሁን በድሬዳዋ የመሬት ወረራን ለመከላከል ምንም ስራ አለመጀመሩ፣ 16 ሺ 800 ዜጎች ቤት ለማግኘት 120 ሚሊዮን ብር የቆጠቡ ቢሆንም እስካሁን ቤቶቹ አለመገንባታቸው፣ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የቅንጅት ችግርና የወሰን ማስከበር ላይ ክፍተቶች በመኖራቸው መጓተት መፈጠሩ እንዲሁም በሶማሌ ያለ አግባብ የተያዙ የጋራ መኖርያ ቤቶች የዳያስፖራ ቤቶች ማስመለስ በቀጣይ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
የከተማ የምግብ ዋስትና ስራው ውጤታማ መሆኑ፣ ለአንድ ሺ 539 ነዋሪዎች ምትክ ቦታ እንዲሰጥ መደረጉ፣ የመምህራን የቤት እጥረት ለመፍታት 27 ሄክታር መዘጋጀቱ እንዲሁም ሰፊ የሆነ ህገወጥ ቦታ የያዙ አመራሮች የወሰዱትን ለመመለስ ፈቃደኛ መሆናቸው በሪፖርቱ እንደ መልካም ጎን ተነስቷል፡፡ በትግራይና በአፋር ክልል የተደረገውን የመስክ ምልከታ የመሩት አቶ በቀለ መንግስቱ፤ ለጥቃቅንና አነስተኛ የመሸጫ ቦታ እጥረት መኖር፣ ከመሬት ጋር በተያያዘ ኪራይ ሰብሳቢነት መበራከት፣ በክልሎቹ የተፈጠረው የስራ እድል ከስራ ፈላጊው ጋር አለመመጣጠን፣ የመስሪያ ቦታ ሳይኖር ብድር መስጠት፣ ለተደራጁ ወጣቶች የተሰጡ ሼዶችን በአግባቡ አለማስተዳደር፣ የሚዘጋጁ የከተማ ፕላኖች ህዝቡን ያማከለ አለመሆን እንዲሁም ለልማት ተነሺዎች በወቅቱ ካሳ አለመክፈል መስተዋሉን ያብራራሉ::
በትግራይ ክልል ከሆስፒታሎችና ከመኖሪያ ቤት የሚወጡ ቆሻሻዎች ብክለት ማስከተላቸው፣ በክረምት ከተራራዎች የሚፈሰው ጎርፍ ስጋት መፍጠሩና ሴቶችን የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራው ስራ ግልፅ አለመሆኑ በመስክ ምልከታው ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ተብሎ መለየቱን ይናገራሉ፡፡ በአፋር ክልል ደግሞ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ችግር፣ ለነዋሪው መብራት ለማስገባት የሚያስፈልገው ወጪ ምን ያክል እንደሆነ ሳይለይ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ መጠየቅ፣ ቦታ ሳያዘጋጁ ለወጣቶች ብድር መስጠትና በግንባታዎች ላይ ተቋራጮችን ተወዳዳሪ የማድረግ ሁኔታው አነስተኛ በመሆኑ ትኩረት እንደሚፈልግ ያስረዳሉ፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አጠቃላይ ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ጥዑመፅጌ በርኸ፤ በግማሽ ዓመቱ የመኖሪያ ቤት ልማት በሚፈፈለገው ፍጥነት አለመሄዱ፣ የኢንዱስትሪ ልማት የሚካሄድባቸው ከተሞች የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ያሉ አማራጮችን አሟጦ አለመጠቀም፣ በገጠር ቤቶች ልማትና አቅም ግንባታ ስራዎች ባለቤትነት ወሰዶ የሚሰራ አካል ባለመኖሩ ስራዎች መጓተታቸውን ይናገራሉ፡፡
በአጠቃላይም በግማሽ ዓመቱ ለ325 ሺ 864 ዜጎች የስራ እድ መፈጠሩን በመጥቀስ፤ በመንግስት ግዙፍ ፕሮክቶችና በተለያዩ ተቋማት ሃያ ሺ 506 የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እና 24 ሺ 615 የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በክልሎች ከተጀመሩ የህብረት ስራ ማህበር ቤቶች 12 ሺ 393 ቤቶች መጠናቀቃቸውንም አመልክተዋል፡፡ በገጠር ቤት ግንባታ ሁለት ሺ 125 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን፣ 22 ሺ 625 ቤቶች መገንባታቸውን እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የመጠጥ ውሃ እና የደረቅ ቆሻሻ መጣያ ቦታ መሟላታቸው መረጋገጡንም ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
መርድ ክፍሉ