የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥት ያወጀውን የክተት ጥሪ ተቀብሎ እስከ ግንባር ድረስ በመሄድ ሕዝቡ ውስጥም ገብቶ በማነሳሳት ከፍተኛ ሚናን እየተወጣ ይገኛል። እኛም በዚህና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር ሙሐመድ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ወቅታዊ አገራዊ እውነታውን እንዴት ይመለከተዋል?
አቶ ጣሂር፦ አሁን ያለው የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ በጣም አስቸጋሪና በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተሞላ ነው። ይህንን ችግር ተቋቁሞ ኢትዮጵያን ወደፊት ማስቀጠልና አለማስቀጠል በሚሉ መስቀለኛ መንገድ ላይም ነው የምንገኘው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን፣ ተሳስበን፣ ተናብበን እንዲሁም ተደማምጠን የጋራ አቋም መያዝ ከቻልን ደግሞ አገራችንን የምናሻግርበትና እንደ አገርና ሕዝብም መቀጠል የምንችልበት ሁኔታ ይኖራል። ነገር ግን ወደመዘናጋቱ የምንገባ ከሆነ አገራችንን ላናገኛት ከፍ ወዳለ ችግር ውስጥ እንከታታለን።
ኢትዮጵያውያን የሕወሓትን አደገኝነትና ክፋት ካልተረዳን ጥቃቅን ስህተቶችን እየፈጠርን የምንሄድ ከሆነ ጠላት የሚፈልገውን ያህል የውስጥ ባንዳዎችን በማደራጀት በሕዝቡ ውስጥ ውዥንብሮችን በመንዛት አገራችንን አደጋ ላይ ሊጥልብን ይችላል። ይህ ቡድን ባለፉት 50 ዓመታት በታሪክ ለ30 ዓመታት ደግሞ በመንግሥትነት አገሪቱ ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት አገር የሚከፋፍል አብረን እንዳንሆን በሚያደርጉ እኩይ ተግባሮቹ ምክንያት አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርጓት ቆይቷል። በተለይም አብን ቆሜለታለሁ የሚለውን የአማራ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ሲሆን እንደኖረና ሌሎች ብሔሮች እንደጨቆነ ተደርጎ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት በርካታ ጉዳቶች እንዲደርስበት የሠራ ኃይል ነው።
ይህ ኃይል በየዘመናቱ የሠራቸው ክህደቶች መጥፎ ሥራዎች ግፎች ቢኖሩም ባለፈው አንድ አመት በተለይም ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው የሽብርና የውንብድና ተግባር የክህደቱንና የብልግናውን ጥግ ያሳየበት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል። ከዚያ በኋላም እንደ አገር በርካታ ፈተናዎችን ያየንበት ቢሆንም ሕዝብ እንደ ሕዝብ ደግሞ እነዚህን ፈተናዎች በድል ለማለፍ ከምንም ጊዜ በላይ ጠንካራ አንድነቱን ያሳየበት ብዙ ውስብስብ ነገሮች ቢፈጠሩም በልካቸው ለመፍታት የተሞከረበት ወቅት ነው።
አሸባሪው ሕወሓት በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ወረራን መፈጸሙን ተከትሎ ይህንን ለመመከት በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የማይፈልጉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋሮቻቸው የወንበዴውን ቡድን እየደገፉ እድሜው እንዲረዝም የተለያዩ ነገሮችን እያደረጉለት ይገኛሉ።
እነዚህን ነገሮች ጠቅለል አድርገን ስንመለከታቸው ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ ነን፤ ነገር ግን ጠንክረን ከሠራን አንድነታችንን ካጠናከርን ለጠላት የማንበገር ኢትዮጵያውያን መሆናችንን ደግሞ እናስመሰክራለን፤ ችግሩንም በቀላሉ እናልፈዋለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ አገር ከገባችበት የህልውና ስጋት እንድትወጣ እንደ ፓርቲ ያለው አማራጭ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ጣሂር፦ አብን እንደ ፓርቲ በየጊዜው ነባራዊ ሁኔታንና የኃይል አሰላለፍን በከፍተኛ ሁኔታ ይገመግማል። ፓርቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስም ብዙ ሥራዎችን አከናውኗል፤ አሁንም ቢሆን ቡድኑ ይህንን መሰል ጥቃት በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ በተለይም ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን እና እየፈጸመ ያለውን ብሎም ሊፈጽም ያቀደውን ሁሉ እየገመገምን እየተከታተልን የራሳችንን እርምጃ እየወሰድንና ከመንግሥትም ጋር በቅርበት እየሠራን ነው።
በመሆኑም ከዚህ የህልውና ስጋት ለመውጣት እንደ አገር ተባብሮ መቆምና አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ያሉትን በጣም ጥቃቅንና በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን በጊዜ እና ምቹ ሁኔታን ጠብቀን ለመፍታት መጣር ይገባል። እዚህ ላይ አንድነት አብሮ መቆም ብቻ ሳይሆን አንድ ሆኖ መሄድ ያስፈልጋል። አንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ብናሰልፍ ምናልባት በጥሩ አደረጃጀትና የአመራር ክህሎት መምራት ካልቻልን ማሸነፍ ልንቸገር እንችላለን። በመሆኑም አንድነትን ማጠናከር ትልቅ ነገር ሆኖ ሳለ አንድ የሆነን ሕዝብ አቀናጅቶና አስተባብሮ መምራት ደግሞ እጅግ የሚያስፈልግ በከፍተኛ ሁኔታም ሊሠራበት የሚገባ ነገር ነው።
ይህ ጦርነት ከአንድ አካል ጋር የምናደርገው አለመሆኑን መረዳት ይገባል፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና የሚዲያው የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሁሉ ሲደማመር በጣም አስቸጋሪ ኢትዮጵያንም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለማስገባት ያለመ መሆኑን መረዳት ቀላል ነው። በመሆኑም ይህንን ሁኔታ በተባበረ ክንድ ማምከን ያስፈልጋል።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር የህልውና አደጋ ሲባል በልኩ ማየት ማንበብ መረዳት ያስፈልጋል፤ ይህ ማለት ምን ማለት ነው፤ በንግግር ብቻ የህልውና ስጋት ተጋርጦብናል ማለት ብቻውን በቂ ካለመሆኑም በላይ የሚፈጠረውን ችግር በትክክል ገምግመን መፍትሔ ካላዘጋጀን የህልውና ስጋት እንዳለ ብቻ መናገሩ ችግሩን አያስቆመውም። በመሆኑም በትክክል ወቅቱን ገምግመን በተባበረ ክንድ ይህንን አሸባሪ ቡድን መመከት ያስፈልጋል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፦ አሜሪካንን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም አገራትና አንዳንድ ተቋማቶቻቸው ለአሸባሪው ሕወሓት ዕድሜ ለመግዛት እያደረጉ ያለውን ሁለንተናዊ ዘመቻ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ጣሂር፦ ምዕራቡ ዓለም የራሱ ፍላጎት አለው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ደግሞ በታሪክ በጂኦግራፊ፣ በአምራች ሕዝቦቿ የቁጥር ብዛት፣ በቆዳ ስፋቷ እሷን ተጋፍቶ ፍላጎትን ለማሳካት ወይንም ደግሞ በቀላሉ ሊዘውሯት የሚችሉ አገር አለመሆኑን ማወቅ የቻሉ አልመሰለኝም።
በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደምም በቅኝ ግዛት አልገዛም ያለች የብዙ አፍሪካ አገር የነፃነት ተምሳሌት የሕዝቡ የአርበነኝነት ሥነ ልቦና ጠንካራ መሆኑን ምዕራቡ ዓለም በቅጡ የተረዳ አልመሰለኝም። ዞሮ ዞሮ ግን ኢትዮጵያ ይህንን አሸባሪ ቡድን ለመግታት የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ፍትሃዊ መሆኑ አገር የማስቀጠል ጉዳይ መሆኑ ምዕራባውያን የሚስቱት ሃቅ ነው ብለን ግን አናምንም።
ሁሉም ቢሆኑ ይህ ቡድን በአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በነበረበት ጊዜ ምን ዓይነት ጥፋቶችን ሲሰራ በሕዝቡ ላይ ምን ዓይነት በደሎችን እንደፈጸመ ለይስሙላ ምርጫ ብሎ እያደረገ ምን ዓይነት ሸፍጥ ሲሠራ እንደኖረ አሁን ደግሞ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን አስነዋሪተግባር በደንብ አድርገው ያውቃሉ። ነገር ግን ለሕዝቡም ሆነ ለአገር ደንታ የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ እነሱም ለሚፈጽሙት አፈና ይጠቅመናል ብለው ስላሰቡም ቡድኑ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ አጥብቆ የመፈለግ ሁኔታ እያሳየ ነው።
ይህም ቢሆን ግን እነዚህ የጠሉንን ሊጣሉን የፈለጉትን ብሎም ከችግር እንዳንወጣ እንዲያውም በችግር ላይ ችግር እየደራረቡብን ያሉትን አገሮች የምናስተናግድበት መንገድ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ ነው። ጥንቃቄ ማድረግ ሲባል ደግሞ አሜሪካ ወይም ምዕራቡ ዓለም ብለን ጠቅለል አድርገን የምንነሳውን ነገር አቁመን በትክክል በኢትዮጵያ ላይ ችግር ያለባቸውን አገሮች ለይቶ መጥራቱ ያዋጣል። አልያ ግን ሁሉንም ዓለም ብለን መነሳት ተገቢም አይደለም።
ኢትዮጵያበጣም ትልቅ አገር በርካታ ወዳጆችም ያሏት ናት፤ አሁን ደግሞ እንድትቀጥል የማይፈልጉ ያፈጠጠ ሥራን እየሠሩ ያሉ አገራትን አሉ፤ በመሆኑም እነሱን በግልጽ እየታገልን በስማቸው እየጠራን እየተከላከልን አገራችንን ማስቀጠል ከድህነት የተላቀቀችና ዜጎቿ በሰላም ወጥተው የሚገቡባት ማድረግ ይጠበቅብናል።
እነሱ ብዙ ማይሎችን አቆራርጠው መጥተው አገራችን ላይ ያልተገባ ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲንቀሳቀሱ እኛ ደግሞ የሚገባንና አገር እንዲኖረን የምናደርገውን ነገር አጠናክረን መቀጠል ያስፈልገናል። ምክንያቱም ማንም አገር አዝኖልን አይ እነሱ እኮ ይህ ይገባቸዋል መብታቸው ነው ብሎ ሊቆምልን አይችልም። በመሆኑም ራሳችንን ልናስከበር፣ አገራችንን ልናስቀጥል፣ ጥቅማችንንም ልናስጠብቅ የምንችለው እኛው ከተረባረብን ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አዎ ሁሉንም በጅምላ መውቀሱ ተገቢ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሉዓላዊነታችንን እየተጋፉን ላሉ አገሮች እንኳን የሚመጥን የመከላከያ መንገድ እየተጠቀምን ነው? መመከቻውን መንገድስ አግኝተነዋል ማለት ይቻላል?
አቶ ጣሂር፦ በዲፕሎማሲ በቃ የሚባል ነገር የለም፤ አንዳንድ ጊዜ «ነገርናቸው ነገርናቸው እነሱ ግን ያው ናቸው» ሲባል እሰማለሁ፤ ግን እንደዚህ አይደለም። በተለይም ከነጮቹ ጋር በመግባባት ነገሮችን ለማስተካከል የሚደረጉ ጥረቶች ላይ መዘናጋትም ሆነ በቃ ብሎ ማቆም አያስፈልግም። ምናልባት አንዳንዶቹ እያወቁ ነው የሚያጠፉት ብንል እንኳን በእነሱ ምክንያት እየተሳሳተ የሚሄደው ኃይል ብዙ በመሆኑ ያንን ለመቀነስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለያዩ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሚሠሩ ሰዎችና ዕድሉና አጋጣሚው ያለን ሁላችንም በዚህ ተግባር ላይ በመሳተፍና እውነታውን በመግለጽ የበኩላችንን መወጣት አለብን። ምናልባት ይህንን ስናደርግ አገራቱ በመሪዎቻቸው አማካይነት ችግሩን ቢያንጸባርቁም ከዜጎቻቸው ደግሞ ደጋፊ እናገኛለን፤ በመሆኑም በደፈናው ጠላቶቻችን ናቸው፣ እኛ እንድንኖር አይፈልጉም፣ በማለት ፈርጆ መሄድ አዋጭ ነው የሚል እምነት የለኝም፤ በመሆኑም በተቻለ መጠን ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረግ ስለ እውነታው ማስረዳት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎቻችን ምዕራቡን ዓለም በሚያስረዳ መልኩ የተቃኙ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ሁኔታዎችን ለመቀየር ያግዛል። በሌላ በኩልም የተሻለ ኃይል ለማሰባሰብ ጥረቶችን ማድረግ አዋጭ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በአገራችን ላይ የጀመሩት የተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አላማው ምንድን ነው?
አቶ ጣሂር፦ እነ ሲኤን ኤንና የሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን ነገር ከባድ ነው እንደምናውቀው የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎቻቸውን ሲሠሩ የፍትሃዊነት (ባላንስ) ግዕጸኝነትና ተዓማኒነት ብዙ ጊዜ የሚነሱ ነገሮች ናቸው፤ ነገር ግን ብዙ ነገር እናውቃለን ከእኛ በላይ ብለው የሚሉ የኃያላን አገራቱ መገናኛ ብዙኃን እነዚህን ነገሮች ሲደፈጥጧቸው እየታየ ነው። እነሱ ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸው የመሪዎቻቸውን ፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈጸም ላይ ካደረጉም ዋል አደር ብለዋል። አሁን ላይ እንዲያውም እንደ እከሌ መገናኛ ብዙኃን እኮ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ነው የሚሠሩት ለማለት በፍጹም የማይቻልበት ሁኔታ ነው ያለው። የአንድ ፖለቲካ ቡድን ከቆመባቸው የሎቢስ ግሩፕ ጋር አንድ ላይ ተናበው የመሥራት፣ ያንን ሃሳብ ደግሞ ትኩረት ሰጥቶ የማናፈስና ለፕሮፖጋንዳ የመጠቀም ሁኔታ በነ ሲኤን ኤንና በሌሎችም ይስተዋላል።
የአሜሪካን መንግሥትን ፍላጎት የሚያስጠብቅ፣ እነሱ የሚሰሩትን ተልዕኮ ሊያስፈጽም የሚችል ተቋም አድርገው ተቀርጸዋል። በመሆኑም እንደ ሚዲያ የተዛባ መረጃ ስለሰበሰቡ ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት አዲስ አበባ ችግር ውስጥ ገብታለች የሚል ምናልባትም ከድምጸ ወያኔና ከትግራይ ቲቪ ያልተናነሰ እንዲያውም በባሰ ሁኔታ ዓለም አቀፍ የጠላት ፕሮፖጋንዳ ማሸን ሆነው ነበር። ይህ ደግሞ በቀጥታ ለማንበርከክ የሚደረግ ጥረት ነው።
በሌላ በኩልም በእርዳታ ስም ወደ አገር እየገቡ መረጃዎችን ይዘው የመውጣት ለሥራ ይዘዋቸው እንዲገቡ የተፈቀዱላቸውን የመገናኛ መሣሪያዎች ለጠላት መረጃ ማቀበያ እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ ከሚከተሉት የፖለቲካ ፍላጎት አንጻር እየሄዱበት ያለው ተግባር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ይህ ሁኔታ አልበቃቸው ከማለቱ የተነሳ አሁን ላይ የጦር መሣሪያ ግዢ እንዳይደረግ ዜጎቻቸው አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ዓለም አቀፍ ተቋሞቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ የማድረግ የተጠናከረ ዘመቻን በመሥራት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እናንተን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
አቶ ጣሂር፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ማዕቀፍ ማለትም በዘርም ይሁን በዜግነት የሚቋቋሙት የሕዝባችንን ነፃነት እናረጋግጣለን በገዢው ፓርቲ የሚደርሱ በደሎችን የመከላከልና የማጋለጥ ተግባር እንፈጽማለን ብለው ነው፤ ምርጫ በሚመጣበት ወቅት ደግሞ ፖሊሲና አማራጮቻችንን ለሕዝብ በማቅረብ የመንግሥትን ድክመቶች ተናግረን አሸንፈን መንግሥት እንሆናለን በሚል ነው። በዚህም የፓርቲ ፖለቲካ ጥቅል አጀንዳው ኃይል ይዞ ሁለንተናዊ ጥቅምን የማስከበርና ሕዝብን የማገልገል ነው።
እኛን መሰል የፖለቲካ ፓርቲዎች አነሳሳችን ሕዝባችንን መጥቀም ነው፤ በመሆኑም ሕዝባችን ደግሞ እኛ መንግሥት ከመሆናችን በፊትም ቢሆን ወንድ ሴት የዛኛው የዚህኛው ሳይል ሙሉ ሕዝቡን ለማጥቃት የመጣ ኃይል አለ፤ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳ አሸባሪ አለ፤ ለሕዝብ ነው የቆምኩት ያለ ፓርቲ የጠላትን ኃይል መበጣጠስ ግዴታ ሆኖበት ይመጣል ማለት ነው። በታሪክ አጋጣሚ እኛ ያለንበት ሁኔታ ይህ ነው።
ችግር ውስጥ ገብተናል ችግር ውስጥ የገባነው ደግሞ በተለመደው ሁኔታ ገዢው ፓርቲ አገሪቷን ሊያፈርሳት ነው ምናምን ብለን ሳይሆን ፖለቲካል ታሪኩ የተበላሸ ራስ ወዳድ የሆነ ድርጅት አገራችንን ሊያፈርስ ሕዝባችንን ሊበቀል ተማምሎ የወጣ ኃይል ስላለ እሱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታግሎ በማስወገድ ድልን ለመጎናጸፍ ነው። በነገራችን ላይ ይህንን ጦርነት በድል ከተወጣን በኋላ በሌሎች ጉዳይ ላይ መደበኛ የሆነ የፓርቲ ፖለቲካ ክርክር የፖሊሲ አማራጭ የሕዝብ ጥያቄ የሚባሉ ነገሮችን ሁሉ ከዚያ በኋላ ማስተናገድ ይቻላል፤ መወያየት መከራከር መተጋገል ይቻላል የሚል አቋም አለን።
በመሆኑም አሁን ላይ ችግራችን ይህንን አገር አፍርሶ ሕዝባችንን ለመበተን የተነሳን ኃይል መመከት ነው። ከፖለቲካ ፓርቲዎች ትክክለኛ አማራጭ ሊሆን የሚገባው ይህ ነው። እንደ አብን መጀመሪያም የተቋቋምነው የሕዝባችንን ችግር ለመፍታት፣ ነፃነቱን ለማስገኘት፣ ተጠቃሚነቱን አረጋግጠን የኑሮ ሁኔታውን ማሻሻል ነው፤አሁንም በዚህ ጊዜ ከሕዝባችን ጎን መቆም መቻል አለብን ብለን ነው እየሠራን ያለነው።
አዲስ ዘመን፦ መንግሥት ላወጀው የክተት ጥሪ ፓርቲያችሁ ምን ምላሽ ሰጠ?
አቶ ጣሂር፦ አገር ችግር ከላይ ስትወድቅና መንግሥት የመጀመሪያውን የክተት ጥሪ በማሰማት አንድ ላይ መቆም አለብን ሲል በእኛ በኩል ቀደም ብለንም አምስት ወራት ገደማ አጠቃላይ እየመጣ ያለውን አደጋ ቀድመን የመገምገም ሁኔታ ላይ ነበርን። በየቤታችንም አልገባንም ነበርና ጥሪውንም በታላቅ ደስታ ነው የተቀበልነው፤ በዚህም ሕዝባችንን እያደራጀን እያነቃን በየቦታው ካሉ የመንግሥት መዋቅሮች ጋር እየተነጋገርንና እየተማመንን በተሻለ ሁኔታ ሕዝባችን ተማምኖ ወደ ትግሉ እንዲገባ ራሳችን ገብተን በማሳየት ነው የጀመርነው።
አሁን ለይ ከመንግሥት ጋር ብዙ የማያግባቡን ነገሮች እንኳን ቢኖሩ አገር ያለችበትን ሁኔታ በመመልከት ቅራኔዎቻችንን ወደጎን በመተው ሥራው ላይ ጠንካራ ተሳትፎን በማድረግ ለሌሎችም ምሳሌ ለመሆን ነው የሞከርነው።
ሕዝቡን ስናነሳሳ የነበረውም በተለይም ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ እየዞርን እናንተ ከእኛ በላይ ቅራኔ የለባችሁም፣ እኛ ተሳደናል፣ የስም ማጥፋት ሥራዎች ተሰርቶብናል፣ ፓርቲያችን ላይ በርካታ የሐሰት መረጃዎችና ውዥንብሮች ተለቀውብናል፣ ተንገላተናል፣ ቤተሰቦቻችን ችግር ውስጥ ገብተዋል፤ ነገር ግን አሁን አገር ችግር ውስጥ ናት። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቢደመሩ አገርን ከማዳን የሚያስቀሩ አይደሉም በሚል እንቅስቃሴ በማድረግ ጠላትን ድባቅ ለመምታት የተነሳነው።
አሁንም በየአካባቢው በየደረጃው ያሉ አመራሮቻችን እስከ ግንባር ድረስ በመግባት መስዋትነት በመክፈል ለወታደሩ ሎጂስቲክ በማቅረብ በጉልበትም በማገዝ ስንቅ በማቅረብ ቁስለኛ በማንሳት እንዲሁም የሕዝብ ንቅናቄዎችን በመሥራት ቀጥተኛ ተሳትፎን እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይስ ምን ለማድረግ አቅዳችኋል?
አቶ ጣሂር፦ ይህ ትግል በተደራጀ ሁኔታ ነው መመራት ያለበት፤ ከዚህ አንጻር ሕዝባችን የመታገያ አጀንዳዬ ምንድነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ስላለበት ከምንም በላይ ሕዝባችንን የማነሳሳት ሥራ እንሰራለን። እግረ መንገዳችንን ደግሞ ለምንድን ነው የምንታገለው ምን ለማግኘት ነው የሚለውን የማንቃት ሥራ እንሠራለን።
መደበኛ ከሆነው የጸጥታና የመንግሥት መዋቅር እንዲሁም ጠቅላላው ዘመቻው ከሚመራበት የዘመቻ መምሪያ ጋር በመሆን በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ገብተን በመሳተፍና በሚሰጠው አጠቃላይ የመንግሥት ስምሪት መሠረት አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን የማድረግና ሕዝባችን አሸናፊ ሆኖ አገራችን የምትቀጥልበትን መንገድ የመፈለግ ሥራ አለን። በቀጣይ ደግሞ ትግሉ ምናልባትም ሕይወታችንን ሊፈልግ ሁሉ ይችላልና እሱን ዋጋ ሁሉ ከፍለን ሕዝባችንን መታደግ ነው የምንፈልገው።
አዲስ ዘመን፦ መላው ሕዝባችን ይህንን ፈተና በድል ለመሻገር ምን ማድረግ ይኖርበታል ይላሉ?
አቶ ጣሂር፦ ከምንም በላይ ጽናት ያስፈልጋል። አገራችን በታሪኳ በበርካታ ሁኔታዎች ተፈትናለች፤ ወረራ ተፈጽሞባታል። ለዚህ የዚያድ ባሬ ወረራ የዓድዋን ጦርነት ማየትና መቃኘት መገምገም ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ፈተና ቢገጥማትም ሕዝቡ አንድ ላይ «ሆ» ብሎ በመነሳቱ እነዚያን ችግሮች እንዴት መመከት እንደተቻለ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል።
በመሆኑም አሁንም ጠላት የፈለገውን ነገር አደረኩ ቢል ጀሌዎቹን እየተጠቀመ ጥሩ ጥሩ ፕሮፖጋንዳዎችን ለመሥራት ቢሞክርም ይህንን ነገር ቀልብሰን አገራችን ድል እንደምታደርግ ምንም ዓይነት ጥርጥር ሊገባን አይገባም። እዚህ ላይ ግን አገራችን ትቀጥላለች፤ ወረራውም ይቀለበሳል ብሎ ማለት ወይም መቀመጥ ብቻ ሳይሆን ከእኔ ምን ይጠበቃል? ምን መሥራት አለበኝ? ነፃነቴን ለማግኘት እኔ ምን እያደረኩ ነው? የሚለውን መጠየቅ ይገባል። ሌሎች በሞቱልን በቆሰሉልን ምቾት ቀጠና ላይ ሆነን ችግሩ እንደሚቋጭ ድል አንደምናደርግ አድርጎ መመልከትን መተው ያስፈልጋል።
በመሆኑም ይህ ቀን ያልፋል፤ ኢትዮጵያም ታሸንፋለች፤ ይህ እንዲሆን ግን የሁላችንም ርብርብ ወሳኝነት እንዳለው መረዳት በጣም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ጣሂር ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2021