«ታሪክ ራሱን ይደግማል» አባባልን ያልሰማ አለ ለማለት ይከብዳል፤ ታሪክ ራሱን ሲደግም ያላየ፣ ባያይ እንኳን ያልሰማ የለምና በዚህ ጽሑፍ ታሪክ ራሱን ስለመድገሙ በመረጃና ማስረጃ አስደግፈን እናወጋለን።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ላይ የሚደረጉ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን እንደሚያወግዙ በሰላማዊ ሰልፍ ሲገልፁ የሰሞኑ አዲስ አይደለም። ሁሌም ሲያደርጉት የነበረና ዓለምን እጁን በአፉ ላይ ሲያስጭን የኖረ የአንድነትና የአትንኩኝ ባይነት ድምጽ ነው።
በተለይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት የወሰደውን ሕግ የማስከበር እርምጃ የጁንታው ቡድን ባናፈሰው ፕሮፓጋንዳ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት እውነታውን ባላገናዘበ መልኩ እየወሰዱት ያለውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱና ተግባሩን ሲያጋልጡ ቆይተዋል።
ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነትን መፈፀም ከጀመሩ ወዲህ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎችን (ባለፈው ማርች (2021) የተካሄደውንም ያስታውሷል) በማድረግ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ከመግባትና የማይገባ ጫና ከመፍጠር እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥትን እንዲደግፉ የሚያሳስብ ደብዳቤም አቅርበዋል። ለቻይና፣ ሩስያና ሕንድ ኤምባሲዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ላሳዩት ታማኝነትና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ላደረጉት ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የህዳሴው ግድባችንን በተመለከተም እንደዚያው። በዚህ ተጋድሏቸውም ሊመሰገኑ ይገባል።
ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በየአገሩ ባደረጓቸው ሰልፎች ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ስለ አፍሪካውያን፤ በዓለም ዙሪያ ላሉና በነጭ የበላይነት ስር ለወደቁ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ጮኸዋል። የነጭ የበላይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከስሩ እንዲመነገል፤ በምትኩም እውነተኛ የሰው ልጅ እኩልነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል።
ከመቼውም ጊዜ በላይ ይህ ድምፅ ከፍ ብሎ የተሰማው ደግሞ ሰሞኑን በተካሄደውና ዓለምን ጉድ ባሰኘው፤ በአንድ ቀንና ሰዓት በ27 አገራት የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ነው፤ ጉዳዩ ሰሞነኛ አጀንዳ ሆኖም በከፍተኛ ደረጃ ዓለምን እያነጋገረ ይገኛል።
የተቃውሞ ሰልፉ በቀጥታ በዋናነት አሜሪካ፣ እንዲሁም አንዳንድ የእሷ አጃቢ የአውሮፓ አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያሉትን ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ፤ በአስቸኳይም ከተግባራቸው እንዲታቀቡ የሚጠይቅ ነው። ከዚህም ከፍ ባለ መልኩ ምዕራባውያን በመላ አፍሪካ ላይ የሚያደርሱትን ተፅእኖ እንዲያቆሙ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ላይ እየደረሰ ያለው ወከባና ሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም የሚጠይቁም ናቸው።
ይህ ደግሞ በመግቢያችን ላይ «ታሪክ ራሱን ይደግማል» እንዳልነው የዓድዋ ድል በመላው አፍሪካና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ፈጥሮት የነበረው ዓይነት ስሜትና ስሜቱም ፈንቅሎ በመውጣቱ አፍሪካን ከቅኝ ተገዥነት ያወጣ አስተሳሰብ ነበርና ነው ተመሳስሎውን እዚህ ማንሳት ያስፈለገበት ዐቢይ ምክንያት።
ምንም እንኳ በ”Ethiopia: What is the African #NoMore movement about?” እና ሌሎች ርእሶች ስለሰልፉ በርካታ ጉዳዮች የተባሉ፤ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚጠበቀው በላይ ጉዳዩን ያዘዋወሩት ቢሆንም እኛም እንደ ባለጉዳይ ስለእውነታው አንዳንድ ነገሮችን ማለት ወደድን።
በሰልፎቹ የሽብርተኛው ሕወሓት፣ የጆ ባይደን፣ ሳማንታ ፓወርስ፣ ብሊንከን እንደ አጠቃላይም የአሜሪካ ማንነት፣ ሴራና ስውር አላማ አንድ ሁለት … ተብለው ተነስተዋል፤ ገመናቸውም እየተገላበጠ ተተርኳል። ዓለም ሁሉ ያውቀው ዘንድም ተሰራጭቷል። አሜሪካ በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ እያደረሰች ያለችው ጫናና አሻጥር እስኪበቃው የተኮነነ ሲሆን መፍትሄውም አርፋ መቀመጥ እንደሆነ፤ ያንን ማድረግ ካልቻለች ደግሞ በኋላ ማጣፊያው ሊያጥራት እንደሚችል በአደባባዮች ተለፍፏል።
የአሜሪካና ተከታዮቿ ድርጊት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሆን ኢትዮጵያን ማፍረስ ደግሞ ከላይ የነበረውን አፍሪካ ላይ ተጭኖ የነበረውን የነጭ የበላይነት ባፍጢሙ የደፋውን፤ ዛሬም እንደ አዲስ በርካታ የአፍሪካ መገናኛ ብዙኃን በአርማነት ከሎጓቸው ስር “A New Paradigm Change For Liberation” በማለት የሚገልፁት የ«ኢትዮጵያዊነት» (“Ethiopianism”) ፍልስፍናን ከጥቁር ሕዝብ ልብና አእምሮ ውስጥ ለመፋቅ የሚደረግ ጥረት ነውና በጥቁር ሕዝብ ዘንድ ይህ ፍፁም ተቀባይነትን ሊያስገኝ የሚችል እንዳልሆነ በግልፅ ተስተጋብቷል። ብዙዎች ክስተቱ «ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!!!» ወደ ተግባር እየተለወጠና እያሸነፈች ስለመሆኗ ማረጋገጫ ነው ብለዋል። «በቃ አሸንፋለች።» እንዲሉ የተገደዱም ብዙዎች ናቸው።
ይህ የኢትዮጵያዊነት (ዝቅ ብለን በሚገባ እናየዋለን) እና ፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ W.E.B Du Bois የኢትዮጵያ ኮከብ (“Star of Ethiopia”) በማለት የገለፁትን ኢትዮጵያን መሠረት ያደረገን ፍልስፍና ባለቤቱ ከሆነው ጥቁር ሕዝብ ልብ ውስጥ ለመፋቅ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ በቀጥታ በጥቁር ሕዝቦች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው፤ አንታገሰውም በማለት ከአፍሪካ ሚዲያ ጀምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮች፣ ተቋማትና የመሳሰሉት ጉዳዩን በብርቱ ጉዳይነት ይዘውት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
የ“big lie” ሀሳብ ባለቤትና ፋሺስቱ Goebbelsን “If you tell a lie big enough and keep repeating it, people will eventually come to believe it.” (ትልልቅ ውሸትን በደንብ አድርገህ ዋሽ፤ ደግመህ ደጋግመህ ይህንን ካደረክ ሰዎች ያንን አምነው እንደ እውነት ይቀበሉታል) ፋሽስታዊ መርህ በተግባር እያዋለ ካለው ሕወሓት ጋርና ጎን በመቆም የሀሰት ዜናን በመርጨት ሥራ ላይ የተጠመዱት የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃም በሚገባቸው ቋንቋ ሥራቸው የተተረከላቸው ሲሆን «ኢትዮጵያን አትንኩ» ተብለውም አስፈላጊው ምክርና ትምህርት ተሰጥቷቸዋል – በሰልፉ። ይማሩበታል ወይም «ካፈርኩ አይመልሰኝ» እንዲል ተረትና ምሳሌያችን በዚያው ይቀጥላሉ የሚለው ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል።
በሰልፉ ኢትዮጵያን መንካት የታላቁን የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ Long Walk to Freedom መጽሐፍን መካድ ነው። ይህ ደግሞ በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ፋይዳቢስ ብቻ ሳይሆን ክህደትም ነውና በሁሉም ዘንድ የእነ አሜሪካ ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባር ውጉዝ ከመአሪዎስ መሆኑ አንድም ሳይቀር ተነግሯል።
ኢትዮጵያን መንካት የእነ ጋርቬይን፣ ንኩሩ ሁማን፣ ጆሞ ኬኒያታን፣ ንጉስ ኃይለሥላሴን እና ሌሎች በርካቶችን ውለታ መብላት ብቻ ሳይሆን ክህደትም ነውና አይደረግም በሚል ስምምነት ላይ ተደርሷልና እነ አሜሪካ በሰልፉ ይደሰታሉ ማለት ከእባብ የእርግብ እንቁላል … ነው የሚሉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
ክዋሜ ንክሩማህ በ1963 “Ethiopia shall rise.” በሚል ርእስ የግጥም መጽሐፍ ለንባብ ያበቃውን ሰው ታሪክ በነጭ መሰረዝ፤ ከነጭራሹም መካድ ነውና ጉዳዩ ሁሉንም ያሳስባል ተብሎ በሰልፎቹ ተነግሯል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ«እንነሳለን» የግጥም መድብላቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ ወደቀች ሲሏት የምትነሳ፤ ፈረሰች ሲሏት እያደር የምትገነባ፤ አለቀላት ስትባል የምትነሳ ነች። ሁሌም ጠላቶቿን እያሳፈረች ስትመልስ የኖረች አገር ነች። ይህ የክዋሜ ንክሩማህና የፕሮፌሰር መስፍን በተደጋጋፊነት የኢትዮጵያን መነሳት መመስከር በብዙዎች ውስጥ ጽናትን ፈጥሯልና አሜሪካንና አውሮፓዊ አጃቢዎቿን «ትርፉ ትዝብት ነው» እስከ ማለት ተደርሷል – በሰልፉ።
ሁሌም እንደነ ኃይለሥላሴ ጉግሳ (“1935 to 2021: From Haile Selassie Gugsa to the TPLF” ድንቅ ጽሑፍን ይመልከቱ) ዓይነት ባንዶችን (የሰሞኑን የእነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሀቅን አገር ክህደትንም ከዚሁ ጋር ያገናዝቧል።) የማታጣው ኢትዮጵያ እነሱ ይፈርሳሉ እንጂ እሷ አትፈርስም ተብሎም በመፈክር ከመገለፁም በላይ «ኢትዮጵያ ታሸንፋለች» በሚለው የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል – በ27 ከተሞች በተደረገው ሰልፍ። «ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት እየተዋጋች ነው!» የሚለውም ተገቢውን ግንዛቤ አግኝቷል – በሰልፉ።
ይህን፣ በሄርሜላ አረጋዊ ተጠንስሶ በኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በጋራ የተዘጋጀውና በ27 ከተሞች የተካሄደን ሰልፍ «እነማን ድጋፍ አደረጉለት?» ብሎ ከመጠየቅ «ማን ነው ድጋፍ ያላደረገለት?» ብሎ በመጠየቅ ጥቂት የሆኑትን መጥራቱ ነው የሚቀለው። በአፍሪካውያን እሚታገዘው #NoMore ድረ-ገጽ (እባክዎ ይህንን ገጽ ይጎብኙ፤ ፌስቡከር ከሆኑም ልክ እንደ ቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይክ እና ሼር ያድርጉት)፣ ሰልፉን ያደራጀውና ያዘጋጀው Horn of Africa Hub፣ Answer Coalition የሚባለው ድርጅት ወዘተ ሰልፉን ውጤታማ ካደረጉት መካከል ናቸው።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው፣ በምዕራባውያን በአፍሪካ ላይ የሚደረግን ጣልቃ ገብነትን፤ የአህጉሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ብዝበዛን የሚቃወመው፣ ሕወሓትን በገዛ አገሩ ላይ የውክልና ጦርነት (ቃል በቃል ስንጠቅስለት “western proxy” ይለዋል) የሚያካሂድ ቡድን ነው ብሎ የሚያምንና ያጋለጠ፣ የባይደን አስተዳደር እንደገና ተመልሶ ወደ ድሮው «አፍሪካውያን ያልሰለጠኑና የሰለጠነው ሰው ሸክም ናቸው» (White man’s burden) የሚለው አስተሳሰብ ውስጥ የተዘፈቀ፤ ይህንንም «ሌሎችን የመከላከል ኃላፊነት አለብን» (“Responsibility to Protect (R2P)) በሚል የቋንቋ ድሪቶ የሚገልፅ አመራር ነው በማለት የሚተች፣ ኢትዮጵያን እንደነ ሊቢያ የማድረግ እቅዳቸው እንደማይሳካላቸው አጥብቆ የሚናገርና በግሪን ፓርቲ የሚደገፈው Black Alliance for Peace (BAP) እና እሱን የመሳሰሉት ሁሉ ከሰልፉ ጎን፣ ፊትና ኋላ ሆነው በተሳካ ሁኔታ ዳር ይደርስ ዘንድ አስችለውታል – በ«ኢትዮጵያ ታሸንፋለች» የታጀበውን ሰልፍ።
(ይህ ኢትዮጵያ ስትነካ የጥቁር ሕብ ከያለበት «ሆ!!!» ብሎ የመነሳት ጉዳይ ዛሬ ሲታይ አዲስ ይመስላል እንጂ ዕድሜ ጠገብና የደለበ ታሪክ ያለው ነው። ተዋረድ ያለው የጣሊያን ጦር ያለ አጥቢያው ሲጋልብ በመጣበትና ሊወርረን ባሰፈሰፈበት ወቅት ጥቁር ከያለበት (ከእንግሊዝ፣ አሜሪካ – በተለይም ከኒውዮርክ…)
ተደራጅተው አገራችንን ከጠላት እንከላከላለን፤ እኛ እያለን ነጭ አይደፍራትም ወዘተ ወዘተ በማለት ከያለበት የተነሳው አፍሪካዊ ቁጥሩ ቀላል አልነበረምና የዛሬውም ድንገት መጥ ክስተት ሳይሆን ያለና የነበረ የጥቁር ሕዝብ ታሪክ መሆኑን ለመግለፅ ነው።) ወደ «ኢትዮጵያዊነት/ ኢትዮጵያኒዝም» እንምጣ።
ለመሆኑ «ኢትዮጵያኒዝም ምንድን ነው፣ ለምንስ አብዝቶ ተቀነቀነ?» የሚል ጥያቄ ቢነሳ ተገቢ ነውና ከፈረሱ አፍ እንዲሉ፤ ስለ ኢትዮጵያኒዝም፣ ስለ ፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴዎች የተለያዩ ምልከታዎችና ምክረ-ሃሳቦችን በማቅረብ ተሰሚነት ካላቸው ኢትዮጵያውያን ምሁራን አንዱ ከሆኑት ከፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ጥናት በመጥቀስ እንመልከት።
የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የተጀመረው በአሜሪካ ነው። ከዚያ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ቅኝ ወደተያዙ የአፍሪካ አገሮች ተዛመተ። እነ ካሜሮን፣ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ናይጄሪያ … ወደ መሳሰሉት አገሮች ነው የተስፋፋው። የመስፋፋት ማዕከላት የነበሩት ደግሞ ቤተ-ክርስቲያኖች ናቸው። ቤተ-ክርስቲያኖች የሃይማኖት አስተምህሮ ዘረኝነት ይደርስባቸው ነበር። ያንን እንዴት እንቃወመው ብለው ሲያስቡ ነው የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ የመነጨው። ነጮች ሲሰብኩ ጥቁሮችን የሠይጣን ምሳሌ፣ ነጮቹን የመላእክት አምሳል አድርገው ነበር። ነገር ግን «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲታይ ነጮቹን የሚወክል ስም የለም።
ኢትዮጵያ የጥቁሮች አገርን ብቻ ነው የሚጠቅሰው። እናም «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» ሲል እግዚአብሔር ጥቁሮችን ይሰማል ማለት ነው ብለው ያምናሉ። የዚህ እንቅስቃሴ አራማጆች ለተጨቆኑ የጥቁር ሕዝቦች «ኢትዮጵያን ማኒፌስቶ» የሚል እ.ኤ.አ በ1820 አወጡ። እነ አሜሪካና ሌሎች የበለፀጉት አገራት የስጋ ምግብ ሲሰጡ ኢትዮጵያ ግን የመንፈስ ምግብ ሰጠች ማለት ነው። በዚህ ከሁሉም ትበልጣለች። በአፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴ የተቋቋመው በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና መነሻነት ነው። የመጀመሪያዎቹ የእንቅስቃሴ አራማጆች በኢትዮጵያዊነት ፍቅር የወደቁ ነበሩ፤ በዚህም ታስረዋል ተገድለዋል።
ኢትዮጵያዊነት በዘርና በቋንቋ የሚለካ አይደለም። ሰዎች የመጣባቸውን ችግር ለመቋቋም ባደረጉት ትግል፣ ባገኙት ውጤትና ስኬት ውስጥ ያለፈ ፍልስፍና ነው። ኢትዮጵያዊነት የብሔር ትርጉም ያለው አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያዊነትን ከዘር – ከአማራ፣ ከትግሬ ከጉራጌ ጋር ወዘተ ያያይዛሉ፤ ነገር ግን ይሄ ስህተት ነው።
«ፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ምን ያህል አፍሪካን ያስተሳስራል ይላሉ?» ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም ፕሮፌሰሩ «እኛ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያዊነትም ባለፈ አፍሪካዊነት ላይ አስቀድመን ብንንቀሳቀስ ለእኛም ሆነ ለአፍሪካውያን ትልቅ ድል ነው። ሕዝቡ የፓን- አፍሪካኒዝምን ጽንሰ ሃሳብ ቢረዳ፣ ሌሎች አፍሪካውያን በፊት ከሚሰጡን ፍቅር የላቀ ፍቅር ይሰጡን ነበር። አሁን ያሉት ፖለቲከኞች በዚህ መንፈስ እንዲራመዱ እግዚአብሔር ይርዳቸው። ከዘረኝነት ወጥተው በኢትዮጵያዊነት እና በአፍሪካዊነት እንዲያስቡ እንፀልይላቸዋለን።» በማለት ነው የመለሱት።
ሰሞኑን «የአፍሪካ የነፃነት እናት የሆነችው ኢትዮጵያ በበረከተባት ጫና ብትዳከም አፍሪካ ያለጥርጥር ወደ ዳግም ቅኝ ግዛት ትገባለች ሲሉ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው ማፖንጋ ጆሽዋ 3ኛ ገለፁ።» በሚል የተሰማው ዜና፤ በዜናውም ማፖንጋ ጆሽዋ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ምልክት ነች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጦርነት ጀርባ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት አለበት፤ ጦርነቱ ኢትዮጵያ ላይ ቅኝ የመግዛት ፍላጎት ባላቸው አካላት የተከፈተ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ አፍሪካውያን አንድነታቸውን ማሳየት አለባቸው፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው የጣልቃ ገብነት ችግር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ፣ የመላው ጥቁርም ችግር በመሆኑ አፍሪካውያን በሙሉ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ያሉትን ከፕሮፌሰሩ አስተያየት ጋር አስተሳስሮ በማየት አንዳች ማጠቃለያ ላይ መድረስ ይቻላል።
እንግዲህ እውነቱ ይህ ነው። ጠላቶቻችንም ሊሰሙ የማይፈልጉትም ሆነ ሊያጠፉን ያለ እረፍት ሲሰሩ የኖሩትና እየሰሩም ያሉት ይህንን እውነት ከስሩ ለመንቀል ነው። ለዚህም ነው አዋቂዎች «ኢትዮጵያውያን አንድ ሁኑ፤ ጠላታችሁ ብዙ ነውና» በማለት ሳይታክቱ የሚመክሩት።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2014