…..
እጅ ስጥ አለኝ ፈረንጅ..
እጅ ተይዞ ሊወሰድ
ምን እጅ አለኝ የእሳት ሰደድ
አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ?
………
እነዚህ ስንኞች የተወሰዱት ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን እሳት ወይ አበባ የግጥም መድብል የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ ከሚለው ግጥም ላይ ነው። ስንኞቹ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ መዝሙር ያህል ናቸው። ጽናትን ከብርታት፣ እውነትን ከፍትህ በአንድ ካቆራኘ የጥልቅ አገር ፍቅር ስሜት መግለጫ አልፋና ኦሜጋ ግጥም የተወሰዱ ስንኞች ናቸው።
በእነዚህ ስንኞች እውነት ተረማምደን አገራችንን ከብዙ ባዕዳን ኃይሎች ወረራ፣ ሴራና ደባ ታድገናል። ከዚህ የእውነትና የጽናት አብራክ ውስጥ በቅለን አገራችንን ከነጮች የራስ ወዳድነት አዘቅት ታድገናል። ጥቁርነትን ከሞሶሎኒና ከቤንቶኖኒ እጅ ነጥቀን ዘላለማዊ ነፃነትን ጽፈናል። ዛሬም አገራችንን ከአሜሪካና ከምዕራባውያን ንክሻ እንደምንታደግበት አምናለሁ። በዚህ የግጥም ስንኝ ውስጥ እኔና እናንተ ህያው ሆነን አለን። ትናንትን ከዛሬ፣ ነገንም ከከርሞ እያቆራኘን ኢትዮጵያዊነትን እንሰብካለን።
የትናንቱ ቅኝ ግዛት ዘምኖና ተሻሽሎ ዛሬን ፈጠረ…፣ ጊዜ ዘመን አልፎ ሄዶ እንሆ ዛሬ ላይ ጣለን። ዛሬ ዘመናዊነትን ኩሎ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በልጽጎ አፍሪካን ለአዲስ ባርነት እየዳረጋት ነው። ለነጮቹ ደግሞ በረከት ሆኖ የአፍሪካን አንጡራ ሀብት እንዲመጠምጡ በር ከፍተ፤ በእዚህ የተነሳ ፍልሚያው ቀጥሏል።
የአባቶቻችን አገር ኢትዮጵያ ዛሬም ዘመናዊ ባርነቱን አልቀበልም ብላ ስልጡን ነን ከሚሉትና ከባለፈርጣማ ጡንቻዎቹ አገራት ጋር ግብ ግብ ገጥማለች፤ የህልውና
ግብ ግብ። ግፍ ያገነናቸው አሜሪካውያን፣ ትዕቢት ያነቃቸው ምዕራባውያን ከትቢያ ወዳጆቻቸው ጋር ለአሸባሪ ቡድን በመወገን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት የነፃነት ምድር የሆነችውን አገር ሊያንበረክኩ እጅ ስጡ እያሉን ነው ‹‹… እጅ ተይዞ ሊወሰድ ፤ ምን እጅ አለና የእሳት ሰደድ…አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ…›› እንዲህ ብሎ ማን በነገረልን።
ሀበሻና ፈረንጅ ከትናንት እስከዛሬ ጣውንታሞች ናቸው። በአበሻዊነት ውስጥ ምን እንዳዩ እንጃ ከኋላችን አይጠፉም። ዘመን ሄዶ፣ ጊዜ ነጉዶ ዛሬም ከኋላችን ናቸው። እንደ ዝንጀሮ ግልገል ኮቴያችንን ይለካሉ። እንዳንደርስባቸው ሰግተው። ሀጢያታቸው እያባነናቸው። ያሳድሙብናል ብለውም ሊሆን ይችላል።
አንድ ወቅት ላይ በመግቢያችን እንደገለጽነው የክንዳችንን ብርታት ያላወቁ እንግሊዞች እጅ ስጡ ሲሉን ነበር፣ አንድ ወቅት ላይ ኢትዮጵያዊነት ያልገባቸው ጣሊያኖችም እጅ ስጡ ሲሉን ነበር፣ አንድ ወቅት ላይ ግብጽና ሶማሊያም እጅ እንድንሰጥ ጠይቀውን ነበር፤ ሁሉም ግን በእሳት ለበቅ ተጠብጥበው እላያቸው ላይ ቋያ ነዶ እጅ ስጡ ሲሉን እጅ ተውን ተመልሰዋል። ኢትዮጵያዊነት ይሄ ነው።
አሁን ተራው የአሜሪካ ሆኗል፤…ከወዳጆቿ ሽንፈትና እጅ መስጠት ካልተማረች ህብረት ባገነነው ሰደድ እሳት እጃችን ዝም እናሰኛታለን። ሲነኩን አንወድም። ከእውነታችን አንድ ዘለላ እንኳ እንድትጎድል አንሻም።
ኢትዮጵያዊነት የእሳት አፎት ነው…አፍሪካ አፍሪካን ሆና የቆመችው፣ ጥቁርነት ክብርና ዋጋ አግኝቶ የጸናው ኢትዮጵያውያን በከፈልነው ዋጋ ነው። አሁንም ምዕራባውያኑ ሊጭኑብን የፈለጉት ዘመናዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት የአፍሪካ ቀንድ የሆነችውን ኢትዮጵያ በማዳከም የሚጀምር ነው። ይሄ እንዳይሆን በቻልነው ሁሉ ታግለን አገራችን ነፃነቷ የተጠበቀ መሆኑን ማሳየት ይኖርብናል።
ሁሉም የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያን እየጠበቁ እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ መንቃት የአፍሪካ መንቃት ነው። ትናንትና አፍሪካውያን የነቁት በኢትዮጵያ ነበር። ትናንትና አፍሪካውያን ቀና ያሉት በአባቶቻችን እንቢተኝነት ነው። ዛሬም እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ነገር ነው።
ዘመናዊው ቅኝ ግዛት እንደ ድሮው ጊዜ በመሣሪያና በታንክ አይደለም፤ ልክ አሁን አሜሪካና ግብረአበሮቿ በድሃ አገራት ላይ እንደሚሆኑት በማዕቀብና እርዳታ በመከልከል ስውር ተልዕኮን ማስፈጸም ነው። አሸባሪ ቡድኖችን በመደገፍ የአገርን ሉአላዊነት በመድፈር የግል ጥቅምን መፈጸም ነው። በአውቅልሀለሁ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን መፍጠር ነው።
ይሄ ደግሞ አሁን ላለንበት ሥልጡን ዘመን የማይመጥን እጅግ አደገኛ የሆነ ዘመናዊ ባርነት ነው። አሁን ላይ እየታገልነው ያለነው ይሄንን ነው። አሁን ላይ እጅ አንሰጥም በሚል የጋራ እምነት የቆምነውም በዚህ የተነሳ ነው። ምዕራባውያን ይህን ሊያስፈጽምላቸው ቀብድ የሰጡትን ተላላኪያቸውን አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ወደ ሥልጣን ለመመለስና ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሠሩ ነው፤ እኛም እጅ አንሰጥም ብለን ስለ አገራችን፣ ስለነፃነታችን፣ ስለርስታችን እየታገልን ነው።
አሁን ላይ አፍሪካ በዘመናዊ ቅኝ ግዛት ስር ናት። በአፍሪካ ላይ እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ የዘመናዊው ቅኝ ግዛት ምልክት ነው። ከትናንት እስከዛሬ አፍሪካ በራሷ እውነት ስር ቆማ አታውቅም፤ በጣልቃ ገብ አገራት የፖለቲካና የኢኮኖሚ አሻጥር እንደደማች ነው።
በተለይ አሁን በግሎባላይዜሽንና በአንዳንድ ዘመን አመጣሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የምዕራባውያኑ ጫና ከመቼውም ጊዜ በላይ በአፍሪካ ላይ ዓይን አውጥቶ የመጣበት ወቅት ላይ ነን። ጊዜው በአንድነት የምንቆምበት ነው። ጊዜው ካለማንም ጣልቃ ገብነት የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን የምንፈታበት ነው። ጊዜው አንድ አፍሪካ አንድ ሕዝብ የምንፈጥርበት ነው።
ትናንትና የኃያላኑ ደባ በአፍሪካ ላይ ምን እንደነበር እናውቃለን፤ ዛሬም ወርቅ ሊያነጥፉልን አልመጡም፤ ወርቃችንን ሊወስዱብን እንጂ። የአውሮፓ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ ተዝቆ በሄደ አንጡራ ሀብት እንደተገነባ ሁላችሁም ታውቃላችሁ። ጊዜው ህልውናን የማዳን ነው። አፍሪካውያን ከአውሮፓና ከምዕራባውያን የቅኝ ግዛት ጫና ለመውጣት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያን በመከተል ሁሉም የአፍሪካ አገራት ራሳቸውን ከነጮች የበላይነት መከላከል ለነገ የማይሉት ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያውያን እጅ አንሰጥም ብለን በጋራ ተነስተናል፤ ይሄን እንቢተኝነት ሁሉም የአፍሪካ አገራት ቢቀላቀሉት ከተደቀነባቸው የህልውና ስጋት ይተርፋሉ። ትናንትም ዛሬም ኢትዮጵያ የአፍሪካ መሪ ሆና አለች።
የአሁኑ ግን እንደ ትናንት ቆመው የሚያዩት ሳይሆን የነጮችን ሴራ ለማፍረስ በጋራ የምንተባበርበት መሆን አለበት። ምክንያቱም ትግሉ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው የአፍሪካ አገራት ጋር ስለሆነ ነው።
አዎ ስለ ኢትዮጵያ እጅ አንሰጥም..ስለአገራችን ዝም አንልም። ክንዳችን የእሳት እቶን እንደሆነ ልናሳያቸው ይገባል። ትናንትን የሚመስሉ በርካታ ዛሬዎች በራስ ወዳዶቹ ነጮች እየተፈጠሩ ነው። አፍሪካን ማዕከል ያደረገ..የአፍሪካውያንን የነፃነት እምብርት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ። አይሳካላቸውም እንጂ ነጮቹ ሁልጊዜ እንደቋመጡ ናቸው። አሸባሪውን ትህነግን ደግፈው በአስታራቂ ስም ሽር ጉድ የሚሉት እነባይደን ከኋላቸው ምን እንዳለ በደንብ እናውቃለንና አትድከሙ፤ ኢትዮጵያ አትፈርስም በሉልኝ።
በእያንዳንዳችን ቤት ትናንት መልኩን ቀይሮ መጥቷል። ትግላችን ለህልውናችን ነውና በአንድነት በመቆም የተቃጣብንን ሴራ ልናከሽፍ ይገባል። ኢትዮጵያዊነት ትናንትም ዛሬም ማሸነፍ ነው። እንደምናሸንፍ ሳይታለም የተፈታ ነው…ላይሆንላቸው ነገር በከንቱ ባያደክሙን እንዴት ጥሩ ነበር፤ ከደከሙም የአያቶቻቸውን ታሪክ ይደግሙታል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2014