አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በንጽጽር መንግስታዊ ህግና መልካም አስተዳደር ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በክልሉ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች በጥቅሉ ለ25 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ያገለገሉባቸው የሥራ ዘርፎችም በመምህርነት፣ በምክር ቤት የስልጠና ኤክስፐርትነት፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነትና ዳኛ በመሆን፣ በፍትህ ቢሮ በወንጀል ጉዳይ መምሪያ ኃላፊነት፣ ቀጥሎም የፍትህ ቢሮ ኃላፊ በመሆን የሰሩ ሲሆን፣ ክልሉ አዲስ አበባ ላይ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ በተደረገው የአመራር ለውጥ ወደ ጋህአዴን ሊቀመንበርና የክልል ፕሬዚዳንትነት ከመምጣ ታቸው በፊት ደግሞ የክልሉ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ነበሩ፡፡
ክልሉ ለተከታታይ 14 ቀናት ያህል የአመራር ግምገማ ሲያካሂድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ስለቆይታቸው፣ ስላለው የጸጥታ ሁኔታ፣ እየተካሄደው ስላለውም ኢንቨስትመንትና ስለሌሎች ጉዳዮች አዲስ ዘመን ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመሆን የተመረጡት በቅርቡ ነውና በክልሉ አፋጣኝ ምላሽ የሚያሻው ነው ብለው አስቀድመው መስራት ያስቡት ሥራ ይኖር ይሆን?
አቶ ኡሞድ፡- አዎ! ክልላችን ችግር ውስጥ መሰንበቱን ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የጸጥታ ችግር እንዲፈታ በትኩረት ለመስራት ነው ያቀድነው፡፡ በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ግምገማ የጸጥታ ችግር መኖሩን አስተውለናል፡፡ በመሆኑም አሁን በዋናነት የጀመርነው ሥራ ክልሉ ሙሉ ለሙሉ ከጸጥታ ችግር ተላቆ የቀድሞው ሰላም እንዲመጣ ነው በትጋት በመስራት ላይ የምንገኘው፡፡
በእርግጥ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የልማት ስራዎች አሉ፡፡ ህዝባችንም ተጠቃሚ የሆነበትም አካሄድ አለ፡፡ ነገር ግን ካለው የህዝብ ፍላጎት አንጻር ሁሉም ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህም የቆሙት የልማት ስራዎች ሁሉ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ እና ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማድረግ የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራትን ይጠይቃል፡፡
ለአብነት ያህል ቀደም ሲል በመንደር የማሰባሰብ ሥራ ነበር፡፡ ይህም በተሻለ ሁኔታ ሲሰራ እንደነበር ቢታወቅም በመሃል ግን ግለቱ እየቀነሰ መምጣቱ ይታመናል፡፡ ስለዚህም ለዚህ ሥራ ትኩረት ሰጥተን እንንቀሳቀሳለን ብለን አስበናል፡፡ሌሎቹም የልማት ስራዎች በአግባቡ ወደ ሥራ እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ሲባል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እነዚህም ስራቸው እንዲነቃቃና ብሎም እንዲጠናቀቅ የማድረግ ሥራ ለመስራት አስበናል፡፡ ቀደም ሲል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እንደተነገረው፤ በተያዘው ዓመት የሚጀመር ፕሮጀክት የለም፤ ነገር ግን የተጀመሩት እንዲጠናቀቁ የማድረጉ አካሄድ ትልቁ ስራችንና ዋና ትኩረታችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ፕሮጀክቶች የትኞቹ ናቸው? ለአብነት ያህል ቢጠቅሷቸው?
አቶ ኡሞድ፡- ስታዲየም፣ መንገዶች በተለይ የጋምቤላ ከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዲሁም የከተማው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲሆኑ፣ በገጠሩ አካባቢ ደግሞ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችና የጤና ኬላዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የግብርና ልማት ተቋማትም እንዲጠናቀቁ የማድረግ ሥራ ለመስራት ነው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ብለን የያዝነው፡፡በእርግጥ በክልሉ ያሉት እነዚህ ብቻ ስራዎች አይደሉም፤ ነገር ግን ባለን አቅም የጠቃቀስኳቸውን አስቀድመን ለማከናወን በማሰብ እንጂ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በሙስናም ሆነ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ አካላት በክልሉ ይኖራሉ ተብሎ ይታሰባል። አስቀድማችሁም በግምገማችሁ ነቅሳችሁ አውጥታችኋልና ቀጥሎ ባደረጋችሁት እንቅስቃሴ የመለየት ሥራ ሰርታችኋል?
አቶ ኡሞድ፡- አዲስ አበባ በነበረን የግምገማ ቆይታ እንደ አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ ክልሉን በዋናነት ካዳከማቸው ጉዳዮች መካከል ሙስና እና ብልሹ አሰራር ነው፡፡ በተለይ ከከተማ ቦታ አሰጣጥ እንዲሁም ከኢንቨስትመንት መሬት አሰጣጥ አኳያ ሲታይ ችግሮች ነበሩ፡፡ የእነዚህን የመሬት አሰጣጥ ሥራ ክልሉ ከፌዴራል ጋር በመሆን በጉዳዩ መክረን አልሚ ካልሆኑ ልማታዊ ባለሀብቶች መሬቱ ተነጥቆ ወደ መንግሥት የሚመለስበት እንቅስቃሴ እንዲኖር ሥራ ይሰራል፡፡
የከተማ መሬትም ቢሆን ህገ መንግስቱ በማይፈቅደው መልኩ ወስደው ምንም አይነት ልማት ያልሰሩ ብዙ አሉ፡፡ በህገ ወጥ መልኩ ቦታውን የያዙ አካላትም ሊኖሩ ይችላሉና እነዚህንም እንደ አቅጣጫ አስቀምጠን እንዲጣራና በሚገኘው ውጤት መሰረት በህግ የሚጠየቁ ካሉ እንዲጠየቁ ይደረጋል፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋርም ተያይዞ ያለው በእርግጥ በክልላችን በነበረው አለመረጋጋት ዜጎች የመታሰራቸው ሂደት የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ተጣርቶ እስከሚቀርብ ድረስ ድምዳሜ ላይ መድረሱ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ የክልሉም አመራር ለ14 ቀናት ባደረገው ግምገማ እነዚህ ጉዳዮች ላይም ትኩረት አድርጎ ተወያይቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክልሉንም ራሳቸውንም ለመጥቀም ሲሉ እናለማለን በሚል ልማት ላይ የተሳተፉ ባለሀብቶች አሉና የሚጠበቀውን ያህል የክልሉን ወጣት ስራን በመፍጠርም ሆነ በሌላ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል?
አቶ ኡሞድ፡- በዚህ ረገድ እንኳ የክልሉ ወጣቶች ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ እኛ በአሁኑ ወቅት የለየነው የትኩረት አቅጣጫ የክልሉ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ በተለይ በአልዌሮ ግድብ ላይ ወጣቱ በመስኖ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆን አንድ ፕሮግራም አለ፡፡ ከዚህ አኳያ አልዌሮ አካባቢ እንዲሆን አቅጣጫ በሚሰጥበት ጊዜ የአልዌሮ አካባቢ ደግሞ በአንድ ሳዑዲ ስታር በመባል በሚታወቅ ድርጅት ለስምንት ዓመታት ያህል መያዙ ነው የተስተዋለው፡፡ ድርጅቱ ከወሰደው አስር ሺ ሄክታር መሬት ላይ እስካሁን በትክክል አለማ ተብሎ የሚወሰደው ከአንድ ሺ ሄክታር መሬት የማይበልጥ የሩዝ ምርት ነው፡፡
በመሆኑም ከትናንት በስቲያ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት የድርጅቱን ተወካይ በማስጠራት ያሳወቅነው ነገር ቢኖር ድርጅቱ ከያዘው አስር ሺ ሄክታር መሬት አምስት ሺ ሄክታሩ ወደ መንግስት እንዲመለስ ተደርጎ የክልሉን ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲያደርግ መታቀዱን ነው፡፡ ይህን ለማሳያነት አነሳሁልሽ እንጂ ሌሎችም በቀጣይ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የክልሉ ወጣቶች ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ የሆኑበት ጊዜ ስላልነበር ነው ላለፉት ጊዜያት የክልሉ ወጣቶች ላይ ሲንጸባረቅ የነበረው የድንጋይ ውርወራ ጎልቶ የቀጠለው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ስለነበሩና እንዲሁም እነርሱም ተጠቃሚ ስላልነበሩ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሌሎችስ ላይ የተጀመረ የማጣራት እንቅስቃሴ ይኖር ይሆን?
አቶ ኡሞድ፡- አዎ! አስቀድሞም የተጀመረ የማጣራት ሂደት አለ፡፡ ይሁንና የት የት አካባቢ እንደሆነ ለጊዜው ግልጽ አይደለም፡፡ ይሁንና ከህግ ውጭ ሁሉ የተኬደባቸው ጉዳዮች አሉና በጊዜው የሚታወቁ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለሁሉም ግን በመጀመሪያ የማጣራቱን ሥራ አጠናክረን በመቀጠል ወጣቱ ብሎም የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው እየሰራን ያለነው፡፡
ሌላው ከማዕድናት ጋር ተያይዞ በክልላችን ወርቅ የከበረ ድንጋይም ሆነ ሌላውም መኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህን ሀብት የያዙት ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ይሁንና በእነዚህ ማዕድናት ወጣቱን የምናሰራ ከሆነ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋልና ይህንንም እንደ አንድ አቅጣጫ ይዘናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግን ተከትላ ስደተኞችን በአገሪቱ እያስተናገደች መሆኑ ይታወቃል፤ ከሰፈሩበት አካባቢ አንዱ የእናንተ ክልል ነው፤ በክልላችሁ የሚገኘው የስደተኛ ቁጥር ደግሞ ከክልሉ ህዝብ ቁጥር እንደሚልቅ ይገመታልና ይህ እያመጣ ያለ ተጽዕኖ አለ?
አቶ ኡሞድ፡- ስደተኞችን ከሚያስተዳድረው አካል ዘንድ ነው ችግር ያለው፡፡ እንዲያም ሆኖ የዓለም አቀፍ ህግን ማክበር ግዴታ በመሆኑ ያንን እናከብራለን፡፡ ነገር ግን ደግሞ የስደተኞች አስተዳደርም ህግጋትን ማክበር እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ እንደሚታወቀውም የስደተኛው ቁጥር ከክልሉ ነዋሪ ይልቅ ይበልጣል፡፡ የቀጣዩ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ምን ይዞ እንደሚመጣ ለጊዜው ባይታወቅም የክልሉ ህዝብ ቁጥር ወደ 400 ሺ ሲሆን የስደተኞቹ ግን እስከ 419 ሺ የሚጠጋ ነው፡፡ ለጋምቤላ ከተማ ቅርብ የሆኑ የስደተኞች ካምፖችም አሉ፡፡ ስደተኞች ደግሞ ወደ ከተማ እየመጡ ነውና የመውጣት መግባታቸው ሁኔታ በህግ አግባብ መሆን እንዳለበት ነው መግለጽ የምንፈልገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስደተኞቹ ከካምፓቸው ወጥተው ወደከተማው መምጣታቸው የሚፈጥረው ችግር አለ?
አቶ ኡሞድ፡- ከመውጣት ከመግባት አንጻር የሚፈጥረው ችግር ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ከተማ ሊያስተናግደው ከሚችለው ቁጥር በላይ ሲሆን በሰዎች መካከል ያለመግባባት ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በተጨማሪም በከተማ ያለው የሸቀጥ አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎችም በገበያ ላይ የሚገኙ ነገሮች የመወደድ ነገር ይከተላል፡፡ እነዚህና መሰል ነገሮች ከአስተዳደር ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው መፍታት ይቻላል የሚል አመለካከት ነው ያለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ጊዜ በአመራር ደረጃ ያለውን ግምገማ አዲስ አበባ ላይ ጨርሳችሁ እርስዎ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ግምገማው እስከ ወረዳና ቀበሌም ድረስ እንደሚወርድ አመልክተው ነበርና ተካሂዶ ይሆን?
አቶ ኡሞድ፡- ወርዷል ማለት ይቻላል፡፡ በአመራር ደረጃ ያሉት የክልል ሴክተር አመራሮች፣ የሦስቱ ብሄረሰብ ዞን ካቢኔዎች፣ የምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ የ13ቱ ወረዳዎች ካቢኔዎች፣ የምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች እና ከጋምቤላ ከተማ አስተዳደር 540 ሰዎችን ጨምሮ ግምገማው ተካሂዷል፡፡ በዚህ ውስጥም የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ እንዲሁም የተባረሩና በማስጠንቀቂያ የታለፉ አካላት አሉ፡፡ በመጨረሻም በማዕከል ደረጃ ክልል ላይ አንድ ትልቅ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት ነው በእቅድ የያዝነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጥሪ መሰረት በውጭ አገር የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት መግባታቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መካከል ወደ ክልላችሁ የገቡ ፓርቲዎች አሉና ከእነርሱ ጋር በምን አግባብ ነው ለመስራት ያቀዳች ሁት?
አቶ ኡሞድ፡- በእርግጥ እንደ አገር የተደረገ ጥሪ አለ፡፡ ይህን ተከትሎ የገቡም አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄና የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስለመሆናቸው ህጋዊ እውቅና አሊያም ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጣቸው እውቅና የለም፡፡
ወደ አገር ቤት ከመጡ በኋላ በዋናነት ትኩረት ሰጥተን እንነጋገርባቸዋለን ብዬ ከያዝኳቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሰላም ጉዳይ ነው፡፡ በሰላም ጉዳይ በአግባቡ ከተግባባን አብረን መስራት እንችላለን፡፡ በእርግጥ እስካሁን የህዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላት አላጋጠሙንም፡፡ የሚያገጋጥመን ከሆነ ግን በህግ አግባብ የሚታይ ይሆናል፡፡ በጥቅሉ ግን የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ከማድረግ አንጻር ከተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ጋር አብረን በመሆን መስራት ይቻላል፡፡ ወሳኙ ግን የህዝብ ሰላም ተጠብቆ መሄድ በሚችል ሁኔታ መጓዝ መቻሉ ነው፡፡ ስለዚህም ለህዝብ ሰላምና ልማት ትኩረት እስከሰጡ ድረስ በአንድ ላይ የማንጓዝበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ወደ ክልሉ ፕሬዚዳንትነት ከመምጣትዎ በፊት የክልሉ ህዝብ በዴሞክራሲ እጦት፣ በመልካም አስተዳደር ችግርና በሙስና ምክንያት ሲንገላታ እንደነበር ይነገራል፡፡ አሁን በእርስዎ አመራር ምን ያህል በተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ተዘጋጅተዋል?
አቶ ኡሞድ፡- በክልሉ ካለው አመራርና ህዝብ ጋር በመሆን ለውጥ ለማምጣት እጥራለሁ፡፡ ትግሉ የአንድ ሰው ሳይሆን አጠቃላይ የስርዓቱ ነው፡፡ እንደ አገር የተጀመረ ለውጥ አለና ይህንኑ ለውጥ አስጠብቆና አስቀጥሎ ለመጓዝ አቅሜ በፈቀደው ሁሉ እንቀሳቀሳለሁ፡፡ ውጤቱን ግን አብረን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ድንበር ላይ እንዳሉት ሌሎች ክልሎች ሁሉ ጋምቤላ ክልል ድንበር ላይ የሚያዋስነው እንደ ደቡብ ሱዳን አይነት አገር አለና ከእነሱ ጋር በንግድ ለመተሳሰር እቅድ ይኖራችሁ ይሆን?
አቶ ኡሞድ፡- በእርግጥ ይህ መልካም ነበር፤ ይሁንና የደቡብ ሱዳን ያለመረጋጋት ሁኔታ እንዲህ አይነቱን ተግባር ለመተግበር አዳጋች ነው፡፡ በእርግጥ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ መረጋጋቱ ሲመጣ ግን የንግድ ትስስሩን ማካሄድ ይቻላል፡፡ የእኛ ስጋት ደቡብ ሱዳን ያለመረጋጋቱ ነው፡፡ ይሁንና አሁን ላይ የተጀማመሩ መልካም ነገሮች አሉና እነሱ ሰምረው የደቡብ ሱዳን ሰላም ከተመለሰ ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ጋር ታደርግ የነበረው የንግድ ትስስሩ ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ በተከበረው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላይ እንዲውል ከተደረገው ገንዘብም ሆነ ከሌላው በጀት ላይ አንዳንድ ብልጣብልጦች በልተውታል የሚሉ አካላት አሉ፤ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ኡሞድ፡- በጥቅሉ ገንዘቡ ተበልቷል ብሎ መደምደም ያስቸግራል፡፡ ገንዘቡ በግለሰቦች ተበልቷል የሚል የተጣራ ነገር የለም፡፡ እዚህ ላይ የምለው ነገር የለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው በቅርቡ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በተማሪዎች መካከል ችግር ታይቶ ነበርና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ይህ ችግር እንዳይገጥመው የተደረጉ ቅድመ ሁኔታዎች ይኖሩ ይሆን?
አቶ ኡሞድ፡- አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ችግሩ ሲከሰት እንዳጋጣሚ አዲስ አበባ ነበርኩ፡፡ ችግሩ ወደ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲም ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት ስለነበረኝ እዚህ ላይ መሰራት እንዳለበት በማመን አንዳንድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በዚህም መሰረት የማረጋጋቱን ተግባር የሚወጡ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡ በእርግጥ ዩኒቨርሲቲው ራሱ የጀመረው የማረጋጋት ሥራ ነበር፡፡ እኛም የጀመርነው ሥራ አለ፡፡ አሁንም ችግር እንዳይኖር የተጠናከረ ሥራ በመሰራት ላይ ሲሆን፣ ተማሪዎችም ተረጋግተው በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በራሱ ችግሩ እንዳይፈጠር አስቀድሞ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ በመሆኑ የሚመሰገን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ የአመራር ፍልስፍና መሰረት ተደምረዋልን? ለዚህ ምን ማሳያ ይጠቅሳሉ?
አቶ ኡሞድ፡- አዎ ተደምረናል፡፡ ማሳያው ባለፈው ሰፊ ጊዜ ተወስዶ በግምገማ አማካይነት የተደረገው ለውጥ በራሱ እማኝ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በክልሉም የተለያዩ ድጋፎች እየተሰጡ ነው፡፡ በፖለቲካውም ሆነ በልማቱ በፊት የነበሩ ድጋፎች እንዲቀጥሉ ነው እየተደረገ ያለው፡፡ ሌላው ቀርቶ ዶክተር ዐብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ ከጎበኟቸው ክልሎች አንዱ የጋምቤላ ክልል ነው፡፡ በጉብኝታቸውም ወቅት ከህዝቡም ሆነ ከአመራሩ ጋር ተወያይተዋል፡፡ አሁን ላይ የተጀመረው ለውጥ በምን አይነት አግባብ መካሄድ እንዳለበት አቅጣጫ የተቀመጠበትም ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ የክልሉ ህዝብ ለውጡን በመደገፍ ላይ ነው ያለው፡፡ በመሆኑም ይህንን ድጋፍ በማስቀጠሉ በኩል ከክልሉ አመራር ብዙ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ኡሞድ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ