የተከበርከው የትግራይ ሕዝብ ሆይ ፤ ያልተከበርኽው አብዛኛው የሕወሓት ጭፍራ ልሒቃን ሆይ ፤ በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል ከ60 ሺህ በላይ ፤ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆችህን እህት ወንድሞችህ ወላጆችህን ሕይወት ገበርህ ። ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ዘለውና ሩጠው ያልጠገቡ የአብራክህ ክፋዮች አካል ጉዳተኛ ሆነው ። ልጆችህም ሆኑ አንተ በከፍተኛ መስዋዕትነት ያመጣችሁት “ነጻነት” ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር(ደርግ) የከፋ ፈላጭ ቆራጭና ዘራፊ አምባገነን በሆነው ሕወሓት ተነጠቅህ ።
በአንድ ለአምስት ጠርንፎ እርስ በርስህ እንዳትተማመን፤ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገንህ ጋርም በጥርጣሬ እንድትተያይ ፤ ይህ አልበቃ ብሎት ልጆችህን ትርጉም ለሌለው ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግዶ ከኤርትራ ወረራ ነጻ ያወጣውን መሬት የሄጉ የድንበር ኮሚሽን አስረክቦ አጨብጭበህ ባዶ እጅህን እንድትቀር አደረገ ። የልጆችህን ደም የውሻ ደም አድርጎት ቀረ። የሌላውን ኢትዮጵያዊ ደምም እንደዚሁ ።
ትርጉም ላልነበረው ለዚህ ጦርነት በቢሊዮኖች የሚገመት የአገር ሀብት ወደመ። ይህ አልበቃ ብሎት እንደ አስቆርቱ ይሁዳ የሰሜን ዕዝን በመጨፍጨፍና በመዝረፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዳግም በአደባባይ ከዳ። ክህደት ለአሸባሪው ሕወሓት ግብሩ ምሱና ማንነቱ ነውና። ክህደት ጥርሱን የነቀለበት መርገሙ ነው ።
የትግል ጓዶችን ፣ ትግራዋይ ወላጆችን ፣ ትግራይን፣ ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን ወዘተረፈ በአደባባይ ሲከዳ የኖረ ባንዳ ነው። የሚገርመው አሸባሪው ሕወሓት ራሱንም በመክዳት የተካነ መሆኑ ነው። በማርክሲዝም ሌኒንዝም ጀምሮ ፤በአልባንያ ሶሻሊዝም ተከልሶ፤ በልማታዊ መንግሥት ተሰልሶ በነጭ ካፒታሊዝም አደናግሮ እንደገና ወደ ሽፍትነትና አሸባሪነት የተለወጠ የክህደት ስብስብ ነው ። ክህደት ብርቁም ሆነ ድንቁ ያልሆነው አሸባሪው ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ታሪክም ትውልድም ይቅር የማይሉት ክህደት በመፈጸም የሰሜን ዕዝን በማጥቃት ትጥቁንና ስንቁን ከመዝረፍ ባሻገር ወደ 10ሺ የሚጠጉ የሰሜን ዕዝ አባላትን በመጨፍጨፉና በማጥቃቱ አገራችን ተገዳ ወደ ጦርነት ገብታለች። እፉኝቱ አሸባሪው ሕወሓት በሕዝባዊ ተቃውሞና በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠሩ የለውጥ ሐዋሪያት የተናበበና የተንሰላሰለ ትግል ኢ-ፍትሐዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ከነበረው ከማዕከላዊ መንግሥት አገዛዙ ሲነሳና በልክህ ሁን ሲባል በእኩልነትና በፍትሐዊነት ላይ አኩሩፎ በመማጸኛ ከተማው በመመሸግ ዕቅድ “ለ”ውን ከመሳቢያው አቧራውን አራግፎ በመሳብ እንደ አፄ ልብነ ድንግል መሬትን 40 እየገረፈ ጦር አውርድ እያለ የጦርነት ነጋሪቱን መጎሰም ጀመረ ።
ፍትሐዊነትን እኩልነትነትን ዴሞክራሲያዊነትንና እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት ሊፋለም ክተት ማለት ትጥቅና ስንቅ ማደርጀት ጀመረ ። ከ200ሺህ በላይ ልዩ ኃይል አሰለጠነ ፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሚሊሺያዎችን አደራጀ ። ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት የያዘውን ሰሜን ዕዝን ስለአጠቃ ልቡ በእብሪት እንደ ፈርኦን ደነደነ ።
ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሠራዊት ተጠቅቶበት። የሠራዊቱ ሞራል በክህደት በተጎዳበት ለ20 ዓመታት በቀበሮ ጉድጓድ ሆኖ ትግራይን ሲጠብቅ የነበረ ጓዱ በትህነግ ከሀዲዎች በግፍ መስዋዕት ሆኖ ፤ ተጨፍጭፎ እና የጦር መሳሪያው ተዘርፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን መልሶ በማደራጀትና በኢትዮጵያዊ ወኔና ጀግንነት በእግሩ ከ700 ኪሎ ሜትር በላይ ተራራ ቧጦ ቁልቁለት ወርዶ በየደረሰበት ከደርዘን በላይ ከባባድ ጦርነቶችን አካሂዶ ሰላማዊ ሰው ሳይጎዳ መቐሌን መቆጣጠሩ የአንድ ረጅም ልቦለድ ወይም ፊልም አጭር ታሪክ (ሲኖፕሲስ) ወይም ፊልም ቅምሻ (ትሪለር ) እንጂ በገሀዱ ዓለም ለዛውም በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ብሎ ለመቀበል ይከብድ ይሆናል።
ቢከብድም ይህ እውነት በምስራቅ አፍሪካዋ የአናብስት ምድር ኢትዮጵያ እውን ሆኗል። ከአገር በተዘረፈ ሀብት እስካፍንጫው ከታጠቀ ፤ ለበርካታ ዓመታት ሲዘጋጅ ከኖረና ከልዩ ኃይሉ ውጭ ከ200 ሺህ በላይ ዘመናዊ ስልጠና ወስዶ የታጠቀን ሠራዊት ብትንትኑን ማውጣት ለዛውም ያለምንም ተጓዳኝ ጉዳት (ኮላተራል ዳሜጅ ) ሲወሳና ሲዘከር የሚኖር ገድል ነው ።
ታዲያ የሆሊውድ ፊልም አጭር ታሪክ እንጂ በገሀዱ ዓለም የተፈጸመ ነው ብሎ ሰው ለማመን ቢቸገር አይፈረድበትም። በዓለማችን በስኬታማነታቸው በምሳሌነት ከሚጠቀሱ ወታደራዊ ዘመቻዎች ሳይቀር የበለጠ ውጤታማ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ሆኖም እብሪተኛው አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው በዚህ አሳፋሪ ጦርነት በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ የድሃ ትግራዋይ ልጆች ሞተዋል ። አካል ጉዳተኛ ሆነዋል ።
ከስምንት ወራት በኋላ መንግሥት ለሰብዓዊነት፤ ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠትና የግብርና ሥራውን እንዲያከናውን ብሎ የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ከክልሉ ሲወጣ ፤ የሽብር ኃይሉ ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርጎ በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራውን አስፋፋ። ለዚህ እብሪታዊ ወረራው በመቶ ሺህዎች የሚገመቱ ወጣቶችን እናቶችን አባቶችን ቄሶችን ሼሆችን ነፍሰ ጡሮችን እመጫቶችን ወዘተረፈ በማዕበል እየማገደ በየግንባሩ በየቀኑ ብዙ ሺዎችን ሙት ቁስለኛና ምርኮኛ እያደረገ በደም ግብር ሰክሮ ትግራይን ትውልድ አልባ የመናፍስት ክልል እያደረገው ይገኛል ።
ከተሞችን ወና እያደረገ ማሳዎችን ጦም እያሳደረ ሁለንተናዊ እልቂት እያስከተለ ነው ። ሕጻናትን በአደንዛዥ እጽ እያሰከረ በየቀኑ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩትን እየማገደ እያስፈጀ ነው ። ምን አልባት አገሪቱ እስከዛሬ አካሂዳዋለች ከሚባሉ በሺህዎች በሚቆጠሩ ጦርነቶች እንኳ ይህ እብሪተኛና የሽብር ስብስብ የማገዳቸውን ያህል ሙት ቁስለኛና አካል ጎዳተኛ አልሆነም ቢባል ማጋነን አይሆንም ።
በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመ ይገኛል ። በሰሜንና በደቡብ ጎንደር ፤ በሰሜንና ደቡብ ወሎ ፤ በሸዋና በአፋር ግንባሮች እንደ ቅጠል የረገፈውን የቆሰለውን ፤ ይህን መጣጥፍ እየጫጫርሁ እያለ እንኳ ያለቀውን ወጣት ባሰብሁ ባሰላሰልሁ ቁጥር የትግራይን ሕዝብ ምንም እንኳ በሕወሓት የአንድ ለአምስት ጥርነፋ የታፈነ ቢሆንም በቃ ለማለት እንዴት እንጥፍጣፊ ወኔ ያጣል ፤ አብዛኛው የትግራይ ልሒቃንስ ይሄን እልቂት እያየና እየሰማ እንዴት በቃ ማለት ይቅርና ከአመክንዮና ከተጠየቅ በዚህ ደረጃ ወርዶ ከእብሪተኛው ጋር የጦርነት ነጋሪት ይጎስማል ።
አሸባሪው ሕወሓትን በቃ ለማለትስ ዋጋው ስንት ነው!? የአምስትና የስድስት ዓመታት ሕጻናት ለሌላ ዙር እልቂት እስኪማገዱ !? ነው ከመጪው ትውልድ “ተበድሮ” ሕዝባዊ ማዕበል (የአብኑ ጋሻው የስኒ ማዕበል ይለዋል፤) እስኪያስነሳ !? መቼም ምድር ዝቅ ሰማይ ከፍ ቢል እብሪተኛው ሕወሓት ይሄን ጦርነት አያሸንፍም ። እዚህም እዚያም በሕዝባዊ ማዕበል ጊዜያዊ የውጊያ በለስ ቢቀናውም 110 ሚሊዮን የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግስትን ሊያሸንፍ አይችልም ። ለዛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ የተፋው ጭላጭ እንኳ ማህበራዊ መሠረት የሌለው ሕወሓት ። ወደ ትፋቱ የሚመለስ እሪያ እንጂ ሰው ለዛውም ኢትዮጵያዊ የለም ። አሸባሪው ሕወሓት ለጊዜያዊና ርካሽ ዕብሪታዊ ድል በተሳሳተ የጦር ስሌት በጣት የሚቆጠሩ ሚሊዮኖችን ይዞ 110 ሚሊዮን ሕዝብ ካላት አገር ጋር ሕዝባዊ ጦርነት ሲቀሰቅስ በስሙ ለሚምልለትና ለሚገዛለት የትግራይ ሕዝብ ቅንጣት ታክል ርህራሄና ደንታ እንደሌለው ያሳያል ። የሚያሳዝነው ነበልባሉን ከስር ከስር በትግራዊ ብላቴናዎች የሚቆሰቁሰው የሽብር ኃይሉ አመራርም ሆነ ልጆቹና ቤተሰቦቹ ዳር ቆሞ ተመልካች መሆናቸው ነው። ልጆቹና የቅርብ ዘመድ አዝማዶቻቸው በአውሮፓና በአሜሪካ ከሕዝብ በተዘረፈ ሀብት የተቀማጠለ ኑሮ ይመራሉ። እዚህ ተራው ትግራዋይ እብሪትና ማንአህሎኝነት በፈጠረው ጦርነት በረሃብ በእርዛት ይገረፋል።
ልጆቹ በ25 ኪሎ የነቀዘ ስንዴ ልዋጭነትና ማስፈራሪያነት ከጉያው እየተነጠቁ ፈንጂ መጥረጊያ የጥይት ማብረጃና ሰብዓዊ ጋሻ ይሆናሉ ። ሥልጣንና ጥቅምን እንደ ጣኦት የሚያመልከው ይህ ስብስብ ግብሩ ክቡር የሆነው የሰው ደም ነው። ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በትግራይ ባረበበው ፍርሃት ራሱን ወደ ጣኦትነት ቀይሮ እየተመለከ ይገኛል ። የትግራይ ሕዝብ ከአምላኩ ከተቀረው ኢትዮጵያዊና ከኤርትራዊ ወገኑ በጥል ግድግዳ የለየውን የሽብር ኃይል በቃ ብሎ ለመነሳት ምን እንዳያጣ ነው ዝምታን የመረጠ የሚለው ጥያቄ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አእምሮ ይመላለሳል።
ልጆቹን ክብሩን እምነቱን ህልሙን ራዕዩን ወዘተረፈ የነጠቀው ኃይል ምን የከፋና የባሰ ነገር እንዳያመጣበት ነው በቃ ! ለማለት ድፍረት ያጣው !? በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በ30 የዓለም ከተሞች ጣልቃ ገብነትን ሽብርን ውሸትን በቃ ! ሲሉት የከሀዲውና የሽብር ቡድኑ የቅድሚያ ቅድሚያ ገፈት ቀማሽ የሆነው ትግራዋይ በቃ ለማለት ድፍረት ያጣው ምን የከፋ ነገር እንዳይመጣበት ነው ? ለዘመናት በክፉው በደጉው ቀን አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብለህ ተጋብተህና ተዋልደህ ከኖርኽው ከአማራ ከአፋርና ከመላው ኢትዮጵያዊና ከኤርትራውያን ጋር እንድትቆራረጥ አደረገህ ። በየሰዓቱ ጠላት እየቀፈቀፈልህ በጥርጣሬ እንድትተያይ አደረገህ ። በገዛ አገርህ ባይተዋርነትና ባዕዳነት እንዲሰማህ በአገርህ በወገንህ ተስፋ እንድትቆርጥ አሴረብህ ። አጥንትህን ከስክሰህ ደምህን አፍስሰህ ባቆምካት አገር ላይ እንድትነሳ ሸፍጥ ሰራብህ ።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ብሎ ተማምሎ ማገደህ ። እንግዲህ ምን ቀረኽና ምንስ የባሰ ሊመጣ ነው በቃ ለማለት አንደበትህ የተያዘው !? የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዳግም ጭቆና የማይንበረከክ መሆኑን እና አሸባሪው ሕወሓት ዳግም አይደለም ኢትዮጵያን ትግራይን እንደማይገዛ እያወቅህና ይሄን ህልቆ መሳፍርት ዋጋ ከከፈልክ በኋላ በቃ ያላልኸው የበቃ ዋጋው ስንት ቢሆን ነው ? ከሕወሓት በላይስ ምን ጠላት አለህና ነው የሥልጣን ጥሙን ለማርካትና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ጠላት እንደጫጩት እየፈለፈለ ከወገንህ የሚያናክስህ ?።
የትግራይ ሕዝብ ሆይ ! ዛሬም በቃ ! ለማለት አረፈደምና ንቃ ! ተደራጅ ! ተነስ ! በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች የምትኖር ትግራዋይ ሆይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመህ ሰንኮፉን የምትነቅልበት ጊዜው አሁን ነውና ሕወሓትን በአንድ ድምጽ በቃ በለው ። እጣ ፈንታህ ከኢትዮጵያና ከሕዝቧ ጋር እንጂ ነገ የታሪክ አተላ ከሚሆነው አሸባሪ ጋር አይደለም ። በቃ !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ህዳር 19 ቀን 2014 ዓ.ም