ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ትምህርት እንዴት ነው? እየጎበዛችሁ ነው አይደል? ልጆቼ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ በቱሉ ዲምቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሆኃተ ሰላም የተሰኘ ቤተ-መጻሕፍት ምርቃት እና የንባብ ቀን አካሒዶ ነበር። በዝግጅቱም የሕጻናት መጻሕፍቶች አውደ ርዕይ፣ በወጣቶች የሰርከስ ትርኢት፣ በኮሜድያን አስረስ በቀለ የተዘጋጀ አስተማሪ አጭር ጭውውት ለሕጻናቱ ቀርቦ ነበር።
የሕጻናት መጻሕፍቶች አውደ ርዕይ ላይ ሕፃናቱ በየድንኳኑ እየገቡ ሲያነቡ፤ ስእሎችን ሲሰሉ ነበር የዋሉት። በዝግጅቱ ላይ አንባቢ ልጆችን ለመፍጠር የሚሰራው የኢትዮጵያ ሪድስ ገበታ የልጆች የሕዝብ ቤተ መጽሃፍት በዝግጅቱ ላይ የተሳተፈ ሲሆን በጊዜያዊነት ባዘጋጀው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ልጆች መጥተው እያነበቡ፤ ብሎም ስዕል እየሳሉ ነበር የዋሉት።
ታዲያ የኢትዮጵያ ሪድስ ገበታ የልጆች የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ባዘጋጀው ድንኳን ውስጥ ስታስተባብር ያገኘኋት ወይዘሮ ሰምሃር ሃይሉ በእጇ ላይ አንድ መጽሐፍ ይዛ ተመለከትኳት። ስለ መጽሐፉ ስጠይቃት ከልጆች ጋር ረጅም ጊዜ በመስራቷ የተነሳ የፃፈችው መሆኑን ነግራኛለች። የመጽሐፉ ስም “አቶ ዳቦና አቶ መጽሀፍ “ ይባላል።
ልጆች በየእለቱ ዳቦ መመገብ እንደማይጠሉት ሁሉ መጽሐፍንም እለት በእለት ማንበብና መውደድ እንደሚገባቸው ለማስተማር እንደፃፈችው የነገረችኝ ደራሲዋ ልጆች ለእድገታቸው ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ አእምሯቸው ያደገ የተሟላ ስብእና ይኖራቸው ዘንድ ማንበብ የሚያስፈልጋቸው እንደሆነ ተናግራለች።
ይህ መጽሐፍ የሚተርከው ከዕለታት አንድ ቀን አቶ መጽሐፍና አቶ ዳቦ መንገድ ላይ ተገናኝተው ስለጠቀሜታቸው የተከራከሩትን ነው። አቶ መጽሐፍ “ልጆች ማንበብ ይወዳሉ፤ ስለዚህ ከዳቦ ይልቅ መጽሐፍን ይወዳሉ” ሲል አቶ ዳቦ ግን “ልጆች መጽሐፍ የማይወዱና ዳቦን ብቻ ይመርጣሉ” በማለት ይናገራል። በኋላም በክርክሩ የተገኙት የልጆቹ ወላጆች “መጽሐፍም፣ ዳቦም እኩል ለሰው ልጅ ጠቀሜታ አላቸው” በማለት ሁለቱም ከስህተታቸው እንዲታረሙ አደረጓቸው።
ልጆቼ ወይዘሮ ሰምሃር እንደተናገረችው ልጆች ተወዳጅ እንዲሆኑ በራስ መተማመን ያላቸውና ጠንካራ መሆን ይገባቸዋል። ይህ ስብእና እንዲኖራችሁ ደግሞ በትእግስት ቁጭ ብላችሁ ማንበብን ብትለማመዱ መልካም ነው።
ወይዘሮ ሰመሃር ልጆች በራስ መተማመን እንዲኖራቸው፤ በእውቀትና በሸነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ የንባብ ባህላቸው ላይ መስራት የሚገባ መሆኑን ተናግራ ወላጆችም አቅም በፈቀደ መጠን ለልጆች መጽሐፍትን ከመግዛትም በላይ ቁጭ ብሎ በማንበብ ማገዝ ይገባቸዋል።
ልጆቼ ከያአንዳንዱ ጠንካራና ስኬታማ ሰው ጀርባ እውቀት ይታያል ያንን እውቀት ደግሞ ለማግኘት መጽሐፍትን ማገላበጥ የግድ ነው።
ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ብዙዎቻችሁ ስልክና ታብሌት ላይ ጊዜን እንደምታጠፉ አውቃለሁ። ይህ ግን ተገቢ አይደለም፤ በተለያዩ ጌሞች ጊዜያችሁን ከማጥፋት ይልቅ የእውቀትን ሚስጥር ለመረዳት መጽሐፍትን ማየት የአስተሳሰብ አድማሳችሁን ያሰፋላችኋል፤ ጎብዝ አንባቢ ሁኑ።
ማንበብ እወዳለሁ፤
ሁል ጊዜ አነባለሁ፤
የእውቀትን ሚስጥር፤
የጥበብን ሚስጥር፤
እኔ ለንገራችሁ፤
በየመጻሕፍቱ ታገኙታላችሁ …..
የሚለው መዝሙር አስታውሻችሁ የዛሬውን ፅሁፌን ላብቃ። መልካም የንባብ የትምህርት ጊዜ ይሁንላችሁ እወዳችኋለሁ፤ ቻው ቻው፡፡
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ኅዳር 19/2014