ለዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን ያደረግናቸው ሰው አቶ በላይ ደዊሶ የሚባሉ ሲሆን፤ የብዙ ሙያ ባለቤት ናቸው። ተምረው ያመጡት ሳይሆን በተፈጥሮ የተሰጣቸውን በልምድና በመኖር እያዳበሩት ያገኙት ነው። ለዚህም አንድ መፈክር አላቸው። ‹‹አዕምሮ ከአምላክ የተሰጠ ልዩ ችሮታ ነው። አድሎ የለበትም። አድሎውን የምናመጣው ያልተጠቀምነውና ያልሠራንበት እኛ ነን›› የሚል ሲሆን፤ በዚህ እምነታቸው ደግሞ የማይሞክሩት ሥራና አልሠራውም የሚሉት ነገር እንዳይኖር አድርጓቸዋል። ይህ ባህሪያቸውም የዳበረው አዕምሯቸውን መልካምነት የሚዘራበት፤ ዕውቀትና ጥበብ የሚተከልበት አድርገውት ስለቀጠሉ እንደሆነ ያስባሉ።
ሰዎች በዚህ ጎዳና ከተራመዱ ይህ መለያቸው ይሆናል የሚል አቋምም አላቸው። እንደርሳቸው ሃሳብ ልምዶችና ዝንባሌዎች በየዕድሜ ደረጃችን ሊለዋወጡ ይችላሉ። ያዳበርነውና የኖርንበት በመሆኑ ደግሞ ጥፋ ብንለው በእድሜ ውስጥ አይጠፋም። ዘላለማዊነቱ እስከሞት ድረስ ይከተለናል። ስለሆነም ይህ ጉዟችን በአለበት ከቀጠለ ደምቆ ይታያል እንጂ አይፈዝምም ይላሉ። የወደፊትንም ማየት የሚቻለው አዕምሮን መጠቀም ሲቻል ብቻ እንደሆነ ያሳስባሉ። ምክንያቱም ለዛሬ መድረሳቸው ይህ መርሃቸው እንደሆነ ያምናሉና ነው።
አነሳሳቸው ራሳቸውን በማውጣት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ትምህርት አልሳካ ሲላቸው በቤተሰብ ጫንቃ ላይ ላለመታዘል ወደ ሥራ ገቡ። መጀመሪያ የሠሩትም የሰዎችን ጫማ መስፋት ነበር። ዛሬ ግን ነገሮች ተለውጠው ሆቴል ሰርተው፤ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ተሰማርተው ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ማስጠለል ችለዋል። እናም ብዙ የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው በመሆናቸው ከልምዳቸው ብዙ የምትቃርሙት ነገር አለና ጋበዝናችሁ።
የእናት ልጅ
የተወለዱት በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ ሸፊና በሚባል ቀበሌ ውስጥ ነው። ልጅነት ብዙ ነገር የሚታይበትና አዲስ የአዕምሮ ፈጠራ የሚጀመርበት ነው። በዚህም እርሳቸው ብዙ ነገሮችን እንዲያዩና እንዲመራመሩ ያደረጋቸው ጊዜ እንደነበር ያነሳሉ። ከእነዚህ መካከል ብረታ ብረቶችን በማንሳት የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁሶችን መሥራት የመጀመሪያው እንደነበር አይዘነጉትም። ለእርሳቸው የወዳደቁ ነገሮች ሥራ መፍጠሪያ እንጂ ቆሻሻ አይደሉም። እናም ባትሪድንጋይን ሳይቀር ኤሌክትሪክ ለመፍጠር ይጠቀሙበት እንደነበር ያስታውሳሉ። በተመሳሳይ መንገድ ላይ ሲሄዱም ቢሆን የሚያልፉት ነገር የለም። በሆስፒታልና ክሊኒክ አካባቢ ሊቃጠሉ የተጣሉ መርፌዎችን ለቅመው ውሃ ልክም ለመሥራት የሚሞክሩ ናቸው። ይህ ተግባራቸው ደግሞ ብዙዎችን ያስደምማቸው ነበር። እንደውም ከማስደመሙ አልፎ ጓደኞቻቸው እንዲፈሯቸው ሆነዋል። ምክንያቱም በፈጠራ ሥራቸው ሳይታሰብ የሆነ ነገር ያደርገናል ብለው ይሰጋሉ። በእርግጥ ሁሉም እንዳልነበሩ ያነሳሉ።
አንዳንዶች እርሳቸውን ለመምሰል ይጥራሉ፤ ብዙ ለውጥም እንዳመጡ ያስታውሳሉ። ይህም ቢሆን ለእርሳቸው ሌላ ፈተና ነበር። ከጓደኞቻቸው ጋር በተለያየ የፈጠራ ሥራ ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ስለሚውሉ የጓደኞቻቸው ቤተሰቦች ከብት በማገድና በሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎች ሊታገዙ አልቻሉም። በዚህም የልጆቹ ቤተሰቦች በእርሱ ምክንያት ልጆቻችን አልታዘዝ አሉን ወደማለቱ ገቡ። ይጠሏቸውም እንደነበር አይረሱትም። ሆኖም የልጆቻቸውን ጥበብና ውጤት እንዲሁም የእርሳቸውን ሥራ ሲረዱት ወቀሳቸውን አቆሙ። ያግዟቸውም ጀመር።
እንግዳችን ከቤተሰብ ጋር ብዙ አያሳልፉም። ምክንያቱም በንግድም በጣም ፈጣን ስለነበሩ አካባቢውን ለቀው ብዙ ቦታ ይዞራሉ። ይህ ደግሞ የባትሪ አጠቃቀምንና መሰል አዲስ ነገሮችን የአካባቢው ሰው እንዲያውቀውና እንዲጠቀምበት ለማድረግ የቻሉ ሰው እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በዚህ ሥራቸው ደግሞ የአካባቢው ሰዎች እጅጉን አድርገው ያከብሯቸው ነበር። ትንሽ ቢሆኑም እንደ ትልቅ የሚወደዱበት ጊዜንም ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።
እርሳቸው ልጅነታቸውን የሚያስታውሱት በሄዱበት ቦታ ጎጆ ሰርተው ሲያድሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሚያጠፉት ጥፋት ነው። በባህሪያቸው አንድ ነገር ላይ ሙጭጭ ብሎ መሥራት አይወዱም። በዚህም ቤተሰብ ከብት ጠብቅ ካላቸው በሌላ ሥራ ስለሚጠመዱና ያንን ስለማያስታውሱት ከብቶቹ የሰው ማሳ ውስጥ ገብተው እህሉን ይበላሉ። ጉዳት የደረሰበትም ወላጆቻቸውን ይከሳል፤ ብዙ ካሳም ይጠይቃል። ይህ ነገር ምንም ያልሆነለት ቤተሰብም ለመምታት ብዙ ጊዜ ይዳደዋል። ግን አንድም ቀን ይዘዋቸው መተዋቸው አያውቁም። ጥፋት ማጥፋታቸውን ሲያውቁ ጊዜ ሳይሰጡ ዛፍ ላይ ሳይቀር ቤት እየሰሩ ያድራሉ። በዚህም ቤተሰብ ፈልጓቸው በቀላሉ አያገኛቸውም። ዕርቀሰላም ሲወርድና ሲረጋጉም ነው የሚመለሱት። እንደውም በዚህ ባህሪያቸው ይህ ሥራ እንደቆመላቸው ያስታውሳሉ።
የልጅነት ህልማቸው መጓጓዢያ ነገሮች ማለትም እንደ አውሮፕላን አይነት ነገሮች መሥራት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ በላይ፤ ብዙ ነገሮችን በመፍጠርና ውጤቱን በማሳየት ይታወቃሉ። ነገር ግን በቦታ እጥረትና ሌሎች እገዛዎች ምክንያቱ ከስኬታቸው ላይ መድረስ አልቻሉም። አሁንም ይህንን ህልማቸውን ማሳካት ይፈልጋሉ። ፍላጎታቸውን ለመሙላትም የማይቆፍሩት ድንጋይ አይኖርም።
ለቤተሰቡ የበኩርና ለእናት ብቸኛ የሆኑት አቶ በላይ፤ አባት ቢኖሩም በእናት ብቻ በእንክብካቤ ያደጉት ናቸው። በዚህም እናታቸው ለእርሳቸው ሕይወት መለወጥና የኑሮ መሻሻል መሪያቸው ነበሩ። የዛሬ አቅጣጫ ቀያሻቸውም እንዲሁ። እንዲያውም የመጀመሪያው የሥራ ጉዟቸው ጠንሳሽና መምህራቸው እርሳቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ። ነጋዴነትንም ከእርሳቸው የወረሱት ነው። ብዙ መሥራት፤ አልችለውም አለማለትና ወደፊት መጓዝንም በሕይወት ያስተማሯቸው እናታቸው መሆናቸውንም ይገልጻሉ። በቃላት ሲያስቀምጡትም ‹‹እኔ የእናቴ ልጅ ነኝ›› ይላሉ።
ትምህርት
የትምህርት ሀሁን የጀመሩት በዚያው በትውልድ ቀያቸው ሲሆን፤ በሸፊና በጩሜ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት ነው። ከዚያ ቆንቦኒ ካቶሊክ ትምህርትቤት ውስጥ ገብተው ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ቀጥለውም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት በአካባቢው ስላልነበረ ወደ ይርጋለም ከተማ በማቅናት ትምህርታቸውን ቀጠሉ። እያቆራረጡም ቢሆን እስከ 10ኛ ክፍል ተማሩ። በእርግጥ ለማቋረጣቸው መንስኤ የነበረው ሙያ ተኮር ሥራዎችን መውደዳቸው ነው። በተፈጥሮ የተሰጣቸው ያዩትን ወዲያው የመሥራት ብቃት በትምህርታቸው ብዙ እንዳይገፉ አድርጓቸዋል። ምክንያቱም ፈጥነው ብዙ ነገሮችን በመሥራት ገንዘብ መያዝን ጀመሩ። ገንዘብ የለመደ ሰው ደግሞ ገንዘቡን እንጂ ትምህርቱን ብዙ አያተኩርበትም። እናም በእርሳቸው ሕይወት ውስጥም የተከሰተው ይኸው ነው።
አቶ በላይ ሒሳብ ትምህርት ላይ ልዩ ፍቅር ያላቸው ሲሆኑ፤ በዚህ ብቃታቸው ሁለተኛ ክፍል እያሉ ሦስትና አራተኛ ክፍሎችን እንዲያስተምሩ ይደረጉ እንደነበር አይረሱትም። እያንዳንዱን ክፍልም ሲዛወሩ ይኸው ሁኔታ ነው የቀጠለው። በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለየ ክህሎት እንዲኖራቸውም አግዟቸዋል።
በሙያ ትምህርት በተለያየ መልክ የተሳተፉት ባለታሪካችን፤ ቴክኒክና ሙያ ብዙም ባይቆዩበትም በተወሰነ ደረጃ ተምረዋል። ከዚያ ይልቅ ግን በደርግ ጊዜ የነበሩ አኢወማ፤ አኢሴማ፤ አኢጌማ ማህበራት ለእርሳቸው ብርታት የሰጧቸውና ሙያቸውን ያሳደጉላቸው ነበሩ። በማህበራቱ ውስጥ በመሳተፍ ብዙ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። በዚህም በስዕል፤ በቅርጻቅርጽና ኤሌክትሮኒክስ ሙያ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው አግዟቸዋል። ይህ ደግሞ ብዙ ከተሞች ላይ በመሄድ ግለሰብ ቤቶች ጭምር በመግባት የእጅ ጥበባቸውን እንዲያኖሩ አድርጓቸዋል።
ወሰን የሌለበት ሥራ
መሥራት የሚወድ ሰው ዓይኑ በአንድ አቅጣጫ ብቻ አይመለከትም። እጁም በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ አይጫንም። ሁሉንም ነገር ለመፈተሽ በተለያየ አቅጣጫ ይቧጥጣል፤ ይቆፍራልም የሚሉት አቶ በላይ፤ በዚህም ሥራ ለእርሳቸው የአዕምሮ የልኬት ደረጃን መመዘኛ ነው። ዝቅ አለ ከፍ አለ የሚል መስፈርት የለውም። ማንኛውም ሥራ የሚናቀውም የሚከበረውም በሚሠራው ሰው ብቃትና ልኬት እንደሆነ ያምናሉ። ሲሠሩም ቢሆን
ያንን እያሰቡ ነው። ይህ ብርታታቸው ደግሞ ከጫማ ሰፊነት ወደ ጫማ ሰሪነት አሸጋግሯቸዋል። የአዳዲስ ፈጠራ ውጤት ባለቤትም አድርጓቸዋል። አካባቢው ያላየውን እንዲያይ ያስቻሉ ሰውም የሆኑት ይህ እድል ስለተሰጣቸው ነው።
በባህርይው አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለመሥራት፤ ለመፍጠር ወይም ለማግኘት፤ ፈትሾና አረጋግጦ ለማሳየት የሚጓጓ ሰው የወደፊቱን ለማየት ብዙም አይቸገርም የሚል እምነት ያላቸው እንግዳችን፤ ሥራን ሳይንቁ የመጀመሪያ ሥራቸውን ያደረጉት ጫማ መስፋትን ነው። ይህ ተግባር ለእርሳቸው ጫማ መስራት እንደሆነ ያስባሉ። በዚህም የሰዎችን ጫማ በዝቅተኛ ዋጋ ሲሰፉ ቆይተዋል። በዚያው ልክ ግን አሰራሩንና ሁኔታውን እያዩና እየለመዱ ነው የሄዱት። እጃቸው ላይ የገባ ነገር ሌላ እድልን ሳይሰጣቸው ሊተውት አይፈቅዱምና ሙያዬ ብለው ሲሰሩት ከርመዋልም። የጫማው ስፌት ወደ ጫማ ሥራ ያሸጋገራቸውም ለዚህ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜም ሎርድ የሚባል ጫማ ለገበያ እንዲያቀርቡም ያደረጋቸው መርማሪነታቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ማንነት በዛሬ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በትናንትና በነገ ውስጥ ይገኛል የሚል እምነት ባለቤት የሆኑት አቶ በላይ፤ ማንነት የሚለማ፤ የሚገነባ ወይም የሚታነፅ መሆኑንና ያለቀለት ሳይሆን በመሆን ሂደት ውስጥ የሚለመልም እንደሆነ ያስረዳሉ። ቀጥለውም ማንነት ነገን ማየት እንደሆነም ያመላክታሉ። እያንዳንዱ ተግባራቸው የነገ ጉዟቸው መሪ መሆኑንም ያወቁት ከዚህ አስተሳሰባቸው አንጻር እንደሆነ ይገልጻሉ። በእርግጥ አናጺው ራሱ ባለቤቱ መሆኑን አይክዱም። ከዚያ ባሻገር ግን ሌሎችም እንዳሉበት ሁሉም ሰው ማመን ይገባዋል ባይ ናቸው። እርሳቸውን እናታቸው እንደሰሯቸው ሁሉ ሌሎችንም ቤተሰብ፤ አካባቢ ወይም ጎረቤት ይሰራቸዋል ይላሉ።
እናታቸው ቤተሰቡን ሲያኖሩ የተለያዩ ከተሞች ላይ እየተዘዋወሩ ነግደው በሚያመጡት ገንዘብ ነው። ብቻቸውን ይለፋሉ፣ ይደክማሉ፤ ልጆቻቸው ምንም እንዲጎልባቸው ያደርጋሉም። ይህ ግን ለባለታሪካችን ምቾት አይሰጣቸውም ነበር። ምክንያቱም እርሳቸው የእኔስ ድርሻ የሚሉት ነገር አላቸው። ማንነቴን በራሴ መስራት አለብኝ የሚል መርህን የሚከተሉም ናቸው። ስለዚህም በቻሉት ልክና በአላቸው አቅም ቤተሰቡን ለማገዝ ይሠራሉ። መጀመሪያ ያደረጉትም እናታቸውን በቅርብ ሆነው ማገዝ ሲሆን፤ የንግዱን ሥራ በማከናወን አሻራቸውን አኑረዋል። ቀጠሉና የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ማውጣቱን ተያያዙት። በአንድ ሥራ ላይ ሳይወሰኑም የተለያዩ ነገሮችን የመሞከራቸው ምሥጢርም ይኸው ነው።
መሞከር አዲስ እድልን፣ አዲስ ስኬትን ይሰጣል ብለው የሚያምኑት አቶ በላይ፤ ቀለም ባልነበረበት ወቅት ሳይቀር ቀለማትን ከተለያዩ ነገሮች እየፈጠሩም ሥራቸውን ያከናውኑ ነበር። ዋና የመፍጠሪያ ቁሳቸውም አፈር፣ ባትሪ ድንጋይን የመሳሰሉት እንደነበሩ ያስታውሳሉ። መድሃኒአለም ትምህርት ቤት በሚማሩበት ወቅትም እንዲሁ ዛሬ ድረስ እንደሚያስገርማቸውና እምነታቸውን እውን እንዳደረገላቸው ይናገራሉ። ይህም ማህተም ቀርጸው ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረጉት፤ የሰርግ መጥሪያዎችንም እንዲሁ ለረጅም ዓመታት በስዕልና በጽሁፍ የሠሩት፤ የቢሮ የመንገድ ታፔላዎችና ግራፎችንም መጠቀም እንዲጀመር ያደረጉት ሥራን ከደፈሩ የሚመጣውን ውጤት በቀላሉ ማየት እንደሚችሉ ያስረዳቸው እንደሆነ ይገልጻሉ።
በባህሪያቸው አንድን ሥራ ሲያከናውኑ ቀጣዩን ነገር አይተው እንዶሆነ የሚያስረዱት ባለታሪካችን፤ ከአሰራሩ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለውን ሂደት በደንብ መመራመር ይወዳሉ። ይህ ደግሞ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑ እንዳገዛቸው ያምናሉ። ለዚህ እንደ አብነት የሚያነሱት በተለያዩ ሙያዎች ላይ እየሠሩት ያለውን ተግባር ነው። በወንዶገነት ከተማ የቤተክርስቲያን ንብረት የሆነውን እንደአኮርዲኖችና ጊታሮችን የመሳሰሉ ሙዚቃ መሳሪያዎች ማንም ትምህርት ሳይሰጣቸው የመጠገንና መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረጋቸው ምስጢርም የእጅ ጥበብን ማድነቃቸውና እንዴት እንደሚሰራ መመራመራቸው ነው።
የቡና እና ሻይ ማሺነሪዎችንም ቢሆን እንዲሁ ከይርጋለም እስከ ሃዋሳ ያሉ ቦታዎች ላይ በመሄድ የመጠገናቸው ነገር የመጣው አልችለውም ስለማይሉ፤ ስለሚሞክሩና መሳሪያው እንዴት እንደሚሰራ ስለሚመራመሩ ነው። እርሳቸው ፍሪጅና መሰል ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችንም ይሠራሉ። በተለይም በኤሌክትሮኒክስ የሚሠሩ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን። የቤት ውስጥ ኢንስታሌሽኖችንም ቢሆን በአግባቡ ያከናውናሉ። የኤልፓ መስመር ዝርጋታንም እንዲሁ ለዓመታት ሠርተውበታል። በእርግጥ ከኤሌክትሮኒክስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያዳበሩትና ልምዳቸውን ያጠናከሩት መጀመሪያ ላይ እንደ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እንዲሁም ሰዓት መጠጋገንን በጀመሩበት ጊዜ ነው። ከዚያ ደግሞ ሳይክልና ሞተር ያከራዩ ነበርና ፈታተው ይገጣጥሙታል። ስለዚህም ልምዳቸው እየካበተ ሲመጣ ከፍ ወዳለ ሥራ ራሳቸውን አዛወሩ። ውጤታማነታቸውንም እያዩ ቀጠሉ።
እንግዳችን ጋራዥ ውስጥ ሳይቀር በመካኒክነት ያገለገሉ ናቸው። አሁንም ቢሆን ከሙያው አራቁም። ምክንያቱም የራሳቸው ጋራዥ ከፍተው ሙሉ የመኪና ኤሌክትሪክና ሞተር አውርዶ የመሥራት ብቃትም ስላላቸው ይሠራሉ። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ለማሰልጠንና የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ ያስቻላቸው እንደነበርም ይናገራሉ።
የበፊቱን ታሪኩን የማያውቅ ሰው የወደፊቱን አይረዳም፤ ሊቀጥልም አይችልም የሚሉት አቶ በላይ፤ መነሻቸውን አንድም ቀን ረስተውት አያውቁም። ሰዎችም በሥራ እንደሚለወጡ የሚያስተምሩት ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ነው። ዝቅ ብሎ መስራት ከፍታ ላይ ያደርሳል የሚል መርህም አላቸው። በዚህ ውስጥ እችላለሁ የሚለው ልምድ እንደሚጎለብት ያምናሉ። ለዚህም ደጋግሞ መሞከር፣ መውደቅን የሥራና የስኬት ጉዞ እንደሆነ ማመን ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ለጉዳዩ በአብነት የሚያነሱት የሞተር ሳይክል ቤኒዚን ሲወደድ ያደረጉትን ነገር ነው። በወቅቱ ቤኒዚን በቀላሉ መግዛት ብቻ ሳይሆን ማግኘትም አዳጋች ነው። እናም ብዙዎች ሞተራቸውን እንዲያቆሙት ተገደዋል። ከእነዚህ መካከልም እርሳቸው አንዱ ሆነዋል።
ለችግሩ መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው የአመኑት አቶ በላይ፤ ወደሥራ ሲገቡ መጀመሪያ ያደረጉት ወደ ናፍጣ ቀይሮ እንዲሠራ በራሳቸው ሞተር ላይ መሞከር ነው። የናፍጣ ሰጪ ፓንፕ በሞተራቸው ላይ በመግጠም ሰርተውታል፤ ውጤታማም ሆነውበታል። ይሁንና አልቀጠሉበትም። ምክንያቱም ናፍጣው ጭስ ያበዛ ነበር። ይህንንም ለመቀየር የተወሰኑ ጥረቶችን አድርገዋል። ነገር ግን የገንዘብ እጥረት ስላጋጠማቸው ውጤቱ ላይ መድረስ አልቻሉም።
እንግዳችን ገና ቴክኖሎጂው ሳይታወቅና እንዲህ በስፋት ሳይነገር በ1977 ዓ.ም ጀምሮ በገጠራማው ክፍል ባዮጋዝን ለመብራት እንዲጠቀሙ ሲያደርጉም የነበሩ ናቸው። ይህንን ሲያደርጉም ከከብት እበት ብቻ ሳይሆን ከሰው ጽዳጅም ጭምር እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ አዲስ ነገር የመሞከር ልምዳቸውም አሁን ላይ ሆቴል ከፍተው እንዲሠሩ አግዟቸዋል። እያንዳንዱ የሆቴል ሥራ በራሳቸው አቅም የተሰራ ሲሆን፤ በተለይም ባህላዊ ነገሮችን እንዳይለቁ ከማድረግ አንጻር በጣም ተጠበውበታል። ራሳቸው በሚፈልጉት መልክም ከቤቱ ዲዛይን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሠርተውታል።
ሆቴሉ በሲዳምኛ ‹‹ኢንጆሄ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በአማርኛ ‹‹ይመችህ›› የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል። ስፍራው በብዙ ነገሮች የተከበበ በመሆኑ ለስራ አማራጭም ሆነ ለቱሪዝም ፍሰቱ ጥሩ አጋዥ የሚሆን ነው። እናም ከ 10 ያላነሰ ቤተሰብን ለማስተዳደር ያግዛቸው ዘንድ አስመርቀው ሥራ አስጀምረውታል። በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተሰማሩ ከ50 የማያንሱ ሠራተኞችንም አሳትፈው የሥራ እድል ፈጥረውበታል። ከዚህ በተጓዳኝ የመንገድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ስላሉም ብዙ ማሽነሪዎችን በማከራየት የገቢ ምንጫቸውን ከፍ ያደርጋሉ።
የቀደመውን ሙያቸውን ላለመልቀቅም ሁለት ቦታ ላይ የሞተርና የሳይክል ጋራዥ ከፍተው ይሠራሉ። የእንጨት ቤትም እንዲሁ አላቸው። ነገር ግን ብዙ የሚሰሩባቸው ቦታዎችና የሥራ አይነቶች በመኖራቸው ሁሉንም መምራትና መሥራት ስለማይችሉ ለቤተሰባቸውና ለአፈሯቸው ልጆች አውርሰዋል። ራሳቸውንም ወደ ኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በማስገባት ተጨማሪ ሥራዎችንም ያከናውናሉ። ያው የአገሪቱ ሁኔታ ብዙ ነገሮች እንዲቀዛቀዙ ቢያደርግም።
እንግዳችን በደርግ ጊዜ ወትድርና የዘመቱ ሲሆን፤ በወቅቱ ሙያውን አይረዱትምና በዚያ መቆየትን አልፈለጉም። በዚህ ላይ ደግሞ የእጅ ሙያቸው ብዙ ነገሮቻቸውን አሳምሮላቸው ስለነበረ አካባቢያቸውን ለቆ መሄዱ የራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር። እናም ብዙም ሳይቆዩ ከመተመደቡበት ሐረር ጠፍተው 12 ቀን በእግራቸው ተጉዘው ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመልሰዋል። ግን ዛሬ ለአገር መዝመትን እየተረዱት ስለመጡ በጣም ይፈልጉታል። መዝመት በአካል ብቻ ሳይሆን በድጋፍም ነው ባይ ናቸውና አሁን ይህንን ለማድረግም ዝግጁ መሆናቸውን አጫውተውናል። በአገር ከመጣ ምንም የምደራደረው ነገር የለም ነውም ያሉን።
የሕይወት ፍልስፍና
ሕይወት ጊዜ የተወሰነላት ምድራዊ ስጦታ ነች። በዚህም ማንም ሰው የተሰጠውን ጊዜ ተጠቀምኩ ለማለት የሚያልፈው ቀንም ሆነ ሌሊት ሊኖር አይገባም። ይህን ካደረገ ደግሞ ብዙ እውነታዎችን ለልቡ፣ ለነፍሱና ለስጋው ይገልጣል። ያላብሳልም የሚል አቋም አላቸው።
ደጋግሞ መሞከር የሕይወትን ጉዞ መቀጠል ነው። የራስን ደስታ ማለምለምም ነው። እድልና ተስፋም ተባብረው የሚመጡበት አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም በመሞከር ውስጥ ስኬት ሩቅ አይደለም። ስለዚህ ደጋግሞ ሞካሪነት መለያ ባህሪያችን መሆን አለበት ብለው ያምናሉ።
ሌላው አዲስን ነገር ማሰብ አዲስን ነገር መፍጠር ነው ብለው ማመናቸው ሲሆን፤ ለፈጠራ ሥራው ሲባል አዲስ ስልት ይቀየሳል። በሥራው ደግሞ የምንፈልገው እንኳን ባይሆን ያልታሰበ ነገር ያሳየናል። እናም ለእኛ ባይሆንም ለሌሎች ችግር ፈቺ የምንሆንበትን አጋጣሚ ያቀዳጀናል ባይ ናቸው። ፈጠራዎቻችንም ለችግራችን መፍትሄ ማፈላለግ ላይ መሰረት ያደረጉ ቢሆኑ በቀላሉ ብዙ አጋጣሚዎችን ይፈጥርልናልና ሁልጊዜ አዕምሯችንን በፈጠራ ሥራ ማስጠመድ ይገባል ብለው ያስባሉ።
መልዕክት
ማንም ሰው እናቱ ሆድ ውስጥ አልተማረም። ስለዚህም እሠራለሁ ብሎ ከተነሳ ያሰበው ላይ ይደርሳል። ውጤታማነቱንም በሠራው ልክ እንደሚያገኘው እምነት አለኝ። በዚህም ወጣቱ መንግስት እስኪቀጥረው ከመጠበቅ ይልቅ ራሱ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን በማጎልበት ራሱን መሸጥና ማሸነፍ አለበት። የዚያን ጊዜ ሥራ የለኝም አይልም። የሚነካውም አይኖርም። ሌሎችን ሰብሳቢ እንጂ ከሌሎች ጠባቂም አይሆንም። አገሩንም ከጥገኝነት የሚያላቅቀው ይህንን ሲያደርግ ነው። እናም ተቀጣሪነትን ሳይሆን በራስ መሥራትን አላማው አድርጎ መንቀሳቀስ እንዳለበት ይመክራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ያልሰራናቸው ነገሮች አሉ። ለሌሎች አለማት ብዙ ነገራቸውን ተጠቅመው የሌሎችን ለመጋራት ይሠራሉ። እኛን የሚፈልጉትም ያንን ለመጠቀም ነው። እኛ ግን ከዚያ በተቃራኒው ነው ያለነው። እናም ዓይናችን ይህንን ማማተር አለበት። በእርግጥ ከዚህ ጎን ለጎን እንዳንሰራ የሚገድቡንም እንዲሁ። እናም አሁን አገር ከችግር እንድትወጣ ከተፈለገ ያልዘመተው አገሩን በሥራ ለመለወጥ ከምንጊዜውም በላይ መታተር አለበት። ለሌሎች ለመድረስና ብዙዎችንም ለመታደግ ከዚህ ውጪ አማራጭ የለምም ይላሉ።
ፈተናዎች የሚፈራና የማይጋፈጥ ሰው በምግብ ሳይቀር ሊሞት ይችላል። ምክንያቱም በምግቡ ውስጥ አንድ ነገር አለ ብሎ ያምናልና ነው። እናም ሰዎች ማመን ያለባቸው በፈተና ውስጥ ጣፋጭ ሕይወት እንዳለችና እርሷን ፈልጎ ማግኘት ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ነው። ያን ጊዜ ሁሉም ሰላም ይሆናል። ዛሬ አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለምና ሁሉም ተስፋ እያደረገ በሚችለው ሁሉ እየሠራ ሊጓዝ ይገባል የመጨረሻ መልእክታቸው ነው።
የሕልውና ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሆነ የጠቀሱት ባለታሪካችን፤ አሁንም ቢሆን ይህ ጉዳይ አገርን የማዳንና ያለማዳን በመሆኑ ማንም ወደኋላ የሚልበት እንዳልሆነ ይናገራሉ። በአካባቢያቸው በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ እየተሳተፉ በቻሉት ልክ ጥበቃው ላይ መሰማራታቸውንም አጫውተውናል። ሁኔታው ከዚህ ሲልቅም አገር መምራቱን ትቶ ወደ ጦርነት የዘመተው ጠቅላይ ሚኒስትራችን እያለ እኛ ላንከተለው የምንችልበት ምክንያት አይኖርምም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲዘምት ሥልጣን አላሳሳውም፤ ሀብት ንብረትም እንዲሁ። ምክንያቱም ሥልጣንና ሀብት የሚኖረው አገር ስትቆም ብቻ ነው። ስለዚህም መጀመሪያ በአካባቢያችን የተቻለንን እናደርጋለን። ሥራዎችን እያከናወንን በጦር ሜዳ ያሉትን ወገኖቻችንን እንደግፋለን። ከዚያም መስዋዕትነትን መክፈል ካለብን ከወንድሞቻችን ጎን ሆነን አገራችንን እንታደጋለን። አሁን ማኅበረሰቡ ሁለቱንም ጎን ማየት አለበት የሚል እምነት አለኝ። የዘመተውን ለመደገፍ ጠንክሮ መሥራት የመጀመሪያው ሲሆን፤ ከሥራው ባሻገር መዝመት የሚፈልግም ዘመቻውን መቀላቀል ይገባዋል ይላሉ። ዝም ብሎ መቀመጥ አይደለም በአገር ላይ ከፍተኛ ጫና ወድቆ በሰፈር ውስጥም የተወሰኑ ሰዎች ግጭት አያስችልም። እናም አንድም በመዝመት አንድም በመሥራት አገራችንን ካለችበት ችግር እንታደጋት ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። ምክራቸውን ተቀብለን እንተግብረው በማለት አበቃን። ሰላም::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ኅዳር 19/2014