ትንቅንቁ እንደቀጠለ ነው። ጠላቶቻችን መንቀዥቀዣቸውን አላቆሙም። እኛ ኢትዮጵያውን በአቋማችን እንደፀናን ነን። “ የራሳችንን እጣ ፈንታ እራሳችን እንወስናለን፤ ለዚህ የሚሆን አቅም እና ዝግጁነት አለን ” ካልን ሰነባበትን።ጠላቶቻችንም “ጠፍጥፈን የሰራንላችሁን አሻንጉሊት ቤተመንግስት አስገቡልን” በሚል አተካራ ውስጥ ናቸው።እውነታው በእንቆቅልሽ የተሞላ ነው ።
ነብሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “ህሊና የሌለው ሰው ምንኛ የታደለ ነው” ይሉ ነበር። እውነታቸውን ነው። ተጋላቢ የሰው ፈረስ የሚፈለጉ ህሊና ቢሶች ምንኛ የታደሉ ናቸው? እኛ አንድ እናት አገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅ የማንተኛውን ያክል እነርሱም መፍረሳችን እውን ሳይሆን የሚያንቀላፉ አይመስለኝም።
በየዕለቱ አዳዲስ ሴራዎች ይጠነሰሳሉ። አንዱ ሲከሽፍ ሌላው ይሞክራሉ። በዚህ ስንደፍንባቸው በዚያኛው ቀድደው ለመውጣት ይፍጨረጨራሉ። በጉያችን ውስጥ ተወሽቀው የ”ሽሹ” ነጋሪታቸውን ሲደልቁ ይውላሉ። እርሱን የሚሰማ ሲጠፋ ባንዳ የማደራጀት ተግባራቸውን ለአፍታም ሳይዘነጉት እዚህም እዚያም በንዋይ አቅላቸውን የሳቱ አድር ባዮችን በመልእክተኝነት ለመጠቀም የቻሉትን ያደርጋሉ።
የሴራው ክር እየተተረተረ ፤ጉንጉኑ በተፈታ ቁጥር የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደ ተባይ እየተንጠባጠቡ ነው። ባለፈው ሳምንት የእነ ልደቱ (ክህደቱ)፣ ታምራት ላይኔ፣ ስዬ አብርሃና ሌሎች ቡድኖች ወንዝ የማያሻግር “የሽግግር ህልም” የኢትዮጵያ ህዝብ አክሽፎታል። ይሄን የተረዱት ምእራባውያን ሳይዘናጉ አዲስ ጥንስስ ይዘው ብቅ ብለዋል።
ከሰሞኑ ደግሞ እንደ ሳር ውስጥ እባብ ሲሽሎከለኮ የከረሙ ባንዳዎች የምእራባውያኑን ህልምና አሸባሪውን ሕወሓት ከመቃብር የማውጣት ህልማቸውን ለማሳካት ሲጣጣሩ ሌሎች ደግሞ አሻጋሪዎች ነን በሚል “የሽግግር መንግሥት” የመመስረት የጓዳ ሴራቸው አደባባይ ወጥቷል። የሴራ ክራቸው ተተርትሮ ደባቸው ሲጋለጥ ከደሙ ንፁህ ነን የሚል ኑዛዜ ውስጥ ገብተዋል።
ለእኛ ግን እውነቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። ከእባብ እንቁላል ጫጩት እንደማይፈለፈልም የተፈጥሮ ህግ አስተምሮናል። “ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ሽብርተኛን ካላዘልሽ” በሚል ፍትህ ተነፈገች እንጂ ልጆቿ ሰላም አጥተው አስታራቂ ሽማግሌ አልናፈቁም። ላለፉት በርካታ ዓመታት ከአሸበሪው ሕወሓት ጋር እንደ “ፓራሳይት” ተጣብቀው ሀገርና ህዝብን ብዙ ያስከፈሉ “የሳር ውስጥ እባቦች” ዛሬ የዲፕሎማሲና የሽምግልና ካባ ደርበው ያለሃፍረት በአደባባይ ሲዘባነኑ ማየትን የመሰለ ክህደት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከዚህ ቀደም ገጥሟት አያውቅም።
“የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” እንዲሉ አባቶቻችን “አዛኝ ቅቤ አንጓች” ሆነው “የአገራችን ሰላም ማጣት አሳስቦን እንጂ ከኢትዮጵያውያንና ከመንግሥታቸው ጀርባ ለመዶለት ፈልገን አይደለም” የሚል ማስተባበያ ይዘው ዳግም በክህደት ጎዳና ላይ ሲንጎማለሉ እንደማየት የሚያበሽቅ ነገር አለ እንዴ ?
በጠላቶቻችን ሴራ ከምንጠፋ ህልማቸውን አክሽፈን በእራሳችን እጅ ብንሰዋ እንደምንመርጥ ከዘመናት በፊት በአጤ ቴዎድሮስ ወኔና ክንድ ለአለም በተግባር አሳይተናል። የሚያሳዝነው ይህንን የደመቀ የታሪክ እውነታ ዘንግተው ዳግም በባንዳዎች እየተነዱ የታላቁ ምኒልክ ቤተመንግስት ለመግባት መሻትን ምርጫቸው አደረጉ?
ዛሬ በኢንተርኔት የመገናኛ መረብ የጠነሰሱት ሴራ ከሽፏል። ሆኖም የሴራ ክራቸው ተተርትሮ አላለቀም፤ በሌላ ቀጣይ ክፍል ተመልሰው ማንኳኳታቸው የማይቀር ነው። ለዚህ ጥሩ መልስ እንዲሆን “ባንዳዎችን” መቀጣጫ ማድረግ ያስፈልጋል። ጠላቶቻችን ሳይሆኑ በክፉ ጊዜ ከጠላቶቻችን ጋር ያበሩት ዋናዎቹ እባጮች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም።
በርካታ ሴራዎችን ባከሸፍን ቁጥር ከትናንት እየተማርን ለነገ የክፉዎች መግቢያ ቀዳዳን እየዘጋን መሄድ ይኖርብናል። እነ ዶክተር እሌኒ (አገር ማፍረስም ድኩትርና ከሆነ) ፣ የሽምግልና ሳይሆን የሴራ ቆብ ያጠለቁት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ በአገር ክህደት ሊከሰሱ ይገባል። ብጫቂ ወረቀት ላይ የይቅርታ ደብዳቤ ፅፈው እጃቸውን እንደ ጲላጦስ ታጥበው ከደሙ ንፁህ ነን ስላሉ የሚራራ ልብ ሊኖረን አይገባም።
ቢሳካላቸው አገር አፍርሰዋል። ቢሆንላቸው ኖሮ ጌቶቻቸውን (አሸባሪዎቹን ትህነጎች) ቤተመንግስት ድረስ አዝለው ለማስገባት ተማምለው ነበር። የጠላቶቻችንን ሴራ እየተከታተልን የምናከሽፈውን ያህል ባንዳዎችን መቀጣጫ እንዲሆኑ በማድረግ አገራችን ዳግም እነዚህን የመሰሉ እኩያን መፈልፈያ እንዳትሆን መስራት ይኖርብናል።
የአሸባሪው ትህነግ ጉድጓድ ተምሶ አልቋል። እንዳንቀብረው እየታገሉን ያሉት የጡት አባቶቹ ናቸው። ለእነዚህም እኛ ኢትዮጵያውያን መላ አናጣም። ፈር የለቀቁትን ወደ አገራቸው ሸኝተናል። በየ ኤምባሲዎቻቸው ጎሬ ሰርተው አገር እንዴት እንደሚፈርስ ስልጠና በመስጠት ጊዜና አቅማቸውን የሚያባክኑትም ቢሆኑ ኢትዮጵያዊነት ልኩ የት እንደሆነ ቢያስተውሉ መልካም ነው።
ኢትዮጵያዊያን እንደቀደመው ዘመን “ከደጃፋቸው ፍቅር እንጂ ሞፈር ” እንደማይቆረጥ ግልፅ አድርገዋል። ይሄንን ደግሞ በጨዋ ደንብ ከሰሞኑ ለመልካም ግንኙነታችን ቆርሰን በሰጠናቸው ደጃፍ ላይ ተገኝቶ ድምፁን አሰምቷል። ጠላቶቻችን በወሬ እንደማንፈታ፤ በማስፈራራት እንደማንርበደበድ ቀስ በቀስ እያወቁ ይመስለናል። አውቀውም እንደማይተኙልን ጠንቅቀን እናምናለን።
የኢትዮጵያ ህዝብ “መሪ የሚወልድ መሪ የሚከተል ነው” የምንሰራውን እናውቃለን። የምንሾመውን የምናነግሰውንም እንዲሁ። አሁን ህልውናችንን የምናስጠብቅበት፣ ክንዳችንን የምናሳይበት ግዜ ላይ ነው። ለዚያ ደግሞ መሪያችንን ከፊት ጀግኖች ሰራዊታችንን ከኋላ አሰልፈናል። ልዩነቶቻችንን ደግሞ ወደ ጎን ትተናል። እንደምናሸንፍ እናውቃለን። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ስሪቱ እራሱ “ከማሸነፍና አልደፈርም ባይነት” ተጠንስሶ የተቀመመ ነው። እስከ ድሉ ድረስ ግን መከራችን እንደሚበዛ፤ እንቅፋታችን እንደ “አሸን” እንደሚፈላ እናውቃለን። ለዚያ ነው ለጠላቶቻችን እንዲህ የሚል መልእክት የምናስተላልፈው።
ክንዳችን ብርቱ ነው። በከንቱ አትታገሉን። እልሃችን እስከ ቀራኒዮ። ላያዛልቅ አቅማችሁን አትጨርሱ። ኢትዮጵያ በሉአላዊነቷ ላይ ለሚቆምር ትምክህተኛ እጅ ሰጥታ አታውቅም። ለዚህም መሰለኝ ንጉሷ የነጭን መረን የለቀቀ ክህደት ተረድቶ “እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፤ እጅ ተይዞ ሊወሰድ፤ አያውቅም እንዴ ክንዴ እንደሚነድ” ሲል ኢትዮጵያዊነት ሲነኩት እንደ እሳት የሚፋጅ መሆኑን በተግባር ያሳየው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 19 ቀን 2014 ዓ.ም