•በቀጣዩ በጀት አመት አዲስ ቀመር ይዘጋጃል
አዲስ አበባ፡- የፌደሬሽን ምክር ቤት ለታዳጊ ክልሎች ይሰጣቸው ከነበረው ድጎማ በነፍስ ወከፍ የሚደርሳቸው መጠን በአንፃራዊነት በእድገት ደረጃቸውና በህዝብ ብዛታቸው ከፍ ካሉት ክልሎች ጋር ሲነፃፀር ከአስር እጥፍ ወደ አራት እጥፍ መቀነሱ ተገለፀ።
በክልሎች ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን ታሳቢ ያደረገ አዲስ የድጎማ ቀመር በቀጣይ ዓመት እንደሚሰራም ተመልክቷል። በፌደሬሽን ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የክልሎች በጀት ቀመርና የክልሎች የተመጣጠነ እድገት ጥናት ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በቀለ እንደሚናገሩት፤ ድጎማው በተጀመረበት አካባቢ በተለይ ለአራቱ ታዳጊ ክልሎች የሚሰጠው ድጎማ ከሌሎች በተሻለ የእድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙት አንጻር ሲታይ አስር እጥፍ የበለጠ ነበር። በአሁን ወቅት ግን ድጎማው ቀንሶ ወደ አራት እጥፍ ደርሷል።
ለታዳጊ ክልሎች የሚደረገው ከፍተኛ ድጎማ ዓላማው ክልሎቹ እኩል ከሌሎቹ ክልሎች በልማት መራመድ እንዲችሉ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በዋነኛነት ታዳጊ ክልሎች ከነበሩበት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መዘግየት እንዲወጡ ከፍ ካሉ ክልሎች እጥፍ ድጎማ ይደረግ እንደነበር ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ታዳጊ ክልሎቹ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና በአገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻሉ በመምጣታቸው ድጎማው እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል። ያም ሆኖ ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልሎች በተነሱ ግጭቶች የፈረሱ ሆስፒታሎች፣ መሰረተ ልማቶችና ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን፣ ወቅቱን ያገናዘበ የልማት እንቅስቃሴ ለማከናወንና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የድጎማ ቀመር በቀጣዩ ዓመት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ያዕቆብ አባባል፤ የበጀት ቀመሩ ሲታይ ፍትሀዊና የክልሎችን ነባራዊ የውጤታማነት መርህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲሰራ ቆይቷል። በዋናነትም ፍትሀዊ ልማትና እድገት እና በሁሉም ክልሎች ላይ የአገልግሎት አሰጣጡ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ማረጋገጥ እንዲቻል ድጎማው ከፍተኛ እገዛ አበርክቷል። የበጀት ቀመሩ ሲሰራ ቅድሚያ የሚታየው የክልሎች የወጪ ፍላጎት ነው የሚሉት አቶ ያዕቆብ፤ ክልሎች በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ለህዝብ አገልግሎት ለመስጠት፣ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ለሌሎች ስራዎች የሚያስፈልጋቸው ወጪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወጪው የሚወሰነው ፌዴራል መንግስት በትምህርትም ይሁን በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች በአምስት ዓመታት ውስጥ የት መድረስ እንዳለበት ባስቀመጠው እቅድ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። ሁለተኛው የሚታየው እምቅ የገቢ አቅማቸው ሲሆን ክልሎች ከተሰጣቸው ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን ምን ያክል መሰብሰብ ይችላሉ የሚለው እንደሆነ አቶ ያዕቆብ አመልክተዋል። በተጨማሪም ሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ የሆነ ጥረት ቢያደርጉ ምን ያክል የመሰብሰብ አቅም አላቸው የሚለው ታይቶ መሆኑን ተናግረዋል። ቀመሩ መሰረት የሚያደርገው ሁለቱን ነገሮች ሲሆን፤ በሁለቱ መካከል ያለውን የበጀት ክፍተት ለመሙላት ድጎማው እንደሚደረግም ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
የፌዴራል መንግስት በየዓመቱ 30 በመቶ በጀቱን ክልሎች ያላቸው ክፍተት ላይ መሰረት በማድረግ እንደሚሰጣቸው አብራርተዋል። በሌላ በኩል ከድጎማ በጀት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ቅሬታዎች እንደሚቀርቡ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ከነዚህም ውስጥ ብዙ ስራዎች ስለምናከናውን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን የተሻለ ስለሆነ ቀመሩ የገቢ ምንጭን ታሳቢ ማድረግ አለበት የሚለው ሃሳብ ጎልቶ እንደሚነሳም ጠቅሰዋል። በነበሩ ግጭቶች ምክንያት የጤናና የትምህርት ተቋማት በመፍረሳቸው እንዲሁም የህዝብ ቁጥር ሊጨምር ስለሚችል የወጪ ቀመር ለመስራት ብዙ መረጃዎች እየተሰበሰቡ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በዚህም በቀጣይ ዓመት አዲስ ቀመር እንደሚሰራ ያመለክታሉ። የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚወስነው ጥቅል አላማ ያለው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር እንደሆነም አቶ ያእቆብ ጠቁመዋል። ጥቅል አላማ ሲባል ፌዴራል መንግስት ለክልል የሚሰጠው የበጀት ድጋፍ ክልሎች ቅድሚያ ለራሳቸው የሚሰጡት ጉዳይ የሚያውሉት እንጂ የሆነ ጉዳይ አሳኩ ተብሎ የሚሰጣቸው አለመሆኑንም አመልክተዋል።
ጥቅል የተባለው ክልሎች በተቻላቸው አቅም ተመጣጣኝ የሆነ የክልል መንግስታት አገልግሎቶችን ለዜጎቻቸው ለመስጠት የሚስችላቸውን ተመጣጠኝ የበጀት አቅም እንዲኖራቸው ማስቻል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ድጎማው በህገ መንግስቱ የተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ለመፈፀም የሚያስችል የበጀት አቅም እንዲኖራቸው የማድረግ አላማ እንዳለውም ጠቁመዋል። ነገር ግን ይሄንን አላማ አሳክተዋል ወይስ አላሳኩም የሚል ግምገማ አለመኖሩን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
መርድ ክፍሉ