አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ ግዳጁን በውጤት የሚያጠናቅቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ክልሎች በዘርፉ መስራት የሚገባቸውን ስራ ባመስራታቸው የውስጥ ሠላምን የማረጋጋቱ ተግባር ለሠራዊቱ ሸክም እንደሆነ ተገለጸ።
የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር ዓይሻ መሃመድ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት፤ ክልሎች የሚጠበቅባቸውን የቤት ስራ በአግባቡ ባለመወጣታቸው በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች አለመረጋጋቶች ይታያሉ። እነዚህን አለመረጋጋቶች ከመከላከልና ከመፍታት አኳያም የክልል ሃይሉ በሚፈለገው ልክ ባለመስራቱ የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶች ለመከላከያ ሸክም ሆነው እንዲመጡ አድርጓል።
እንደ ኢንጂነር ዓይሻ ገለፃ፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመረጋጋትና ግጭቶችን ለማረጋጋት መከላከያ ሚኒስቴር እየሰራ ነው። በክልሎች በሚፈጠሩ ችግሮችም የክልል አስተዳደሮቹ ሲጠይቁ ነው የሚገባው። በገባባቸው የማረጋጋት አካባቢዎችም ችግሩ በፍጥነት ተፈትቶ ወደ ቀድሞ ሠላም ሲመለስ ይታያል። ሠላም እንዲከበር በማድረግ ሂደቱም በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ ችግሮችን ሳይፈታና ሠላሙንም ሳያረጋጋ የተመለሰበት ሁኔታ የለም።
ነገር ግን አሰራሩን ካለመገንዘብ ቶሎ እንዲገባ የሚመጡ ጥያቄዎች አሉ። “ሠራዊቱ ሕዝባዊ ባህርይውን ተላብሶ የሽምግልና ሚናም ይጫወታል” ያሉት ሚኒስትሯ፤ በዚህም ሕዝብን የማወያየትና የመፈናቀል አደጋ የገጠማቸውንም ለመደገፍ ከራሱ ራሽን ቀንሶ በመመገብ ጭምር በየካምፑ እያቆየ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ዘረፋ ሲኖርም ተከታትሎ ሀብቱን የማስመለስ ሥራም በመሥራት ከሕዝቡ ጋር በቅርበት ለችግሮች መፍትሄ እያፈላለገም እንደሆነ ጠቁመዋል። በዚህም ሕዝቡ በተቋሙ ትልቅ አመኔታ እንዲጥልና መከላከያ ካለ ደህንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ እንዲያምን ስላደረገው ሠራዊቱ በገባባቸው አካባቢዎች ችግሮች በቶሎ እንደሚረግቡ እንዳስቻለውም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ የተቋሙ ተልዕኮ አገርን ከውጫዊ ኃይልና ውስጣዊ የፀረ ሠላም ኃይል መጠበቅ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ዓይሻ፤ በእያንዳንዱ ብሔር መካከል፣ በየቀበሌና ጉራንጉር ምን ሊከሰት ይችላል? በሚል የሚሰራ እንዳልሆነ ተናግረዋል። የውስጣዊ ሠላም መደፍረስ ሲከሰት በተቻለ መጠን ክልሎች የማረጋጋት ሃላፊነት እንዳለባቸው በመግለጽም፤ ክልሎች በዛ ደረጃ መሥራት ያለባቸውን ሥራዎች ያለመስራታቸው ደግሞ እነዚህ ሃላፊነቶች ለመከላከያ ሸክም ሆነው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
በፍዮሪ ተወልደ