የኢትዮጵያ የምግብና ስርአተ ምግብ ፖሊሲ ለመጀመሪየ ጊዜ ህዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም መፅደቁ ይታወሳል። ሀገሪቱም ከምግብና ከስርአተ ምግብ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን እ.ኤ.አ በ 2030 ዜሮ ለማድረግ ቁርጠኝነት ያሳያችበትና ቃል የገባችበት ነው።
በምግብና ስርአተ ምግብ ላይ መስራት ለእድገትና ብልፅግና መሰረት ከመሆኑ አኳያም ፖሊሲው ተግባራዊ ቢሆን የኢትዮጵያን እድገት እንደሚያፋጥን ተስፋ ተጥሎበታል። ፖሊሲው የፀደቀበትን ቀን አስመልክቶም የኢትዮጵያ የስርአተ ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ በየአመቱ ጉባኤውን ያካሂዳል። ዘንድሮም ሶስተኛ አመታዊ ጉባኤውን ከሰሞኑ አካሂዷል።
የምግብና የስርአተ ምግብ ፖሊሲው መፅደቁን ተከትሎ ኔትዎርኩ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም ከተቋቋመ ወዲህ በተለይ ወጣቶችንና ታዳጊዎችን ያካተተ ፎረም አቋቁሞ በስርአተ ምግብ አመራር ላይ ልዩ ልዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በምግብና በስርአተ ምግብ ዙሪያ በመንግሥት በኩል የተቀመጡ ግቦችንና ስትራቴጂዎችን ከማሳካት አኳያም በስርአተ ምግብ አመራር ላይ ያተኮሩ ስራዎችም ተሰርተዋል።
የምክርና የልምድ ልውውጥ መድረኮችን በማዘጋጀትም ሰፊ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በተለይ ደግሞ በአቅም ግንባታው ዘርፍ ኔትዎርኩ ወጣቶችን ያማከሉ ስራዎችን መስራት ጀምሯል።
የጤና ሚኒስቴርን በማገዝ በተለይ ደግሞ የስርአተ ምግብ ፕሮግራምን ለማሳለጥ የሚረዳ የስርአተ ምግብ አመራር ስልጠና ማንዋል ዝግጅትን በማገዝ በሀገር አቀፍ ስልጠናው እንዲሰጥ አድርጓል። በተዋረድ ክልሎችም ስልጠናውን እንዲያገኙ ተደርጓል። በስርአተ ምግብ ዙሪያ ያሉ ሴት አመራሮችን የማብቃት ስራዎችንም በቀጣይ ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ወይዘሮ እስራኤል ሃይሉ የኢትዮጵያ የስርአተ ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ መስራችና ሰብሳቢ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ኔትዎርኩ ከተመሰረተ ሶስት አመት አልፎታል። በነዚህ አመታት ውስጥም የስርአተ ምግብን የሚመሩ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ያሉ የበላይ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህም አመራሮቹ በስርአተ ምግብ ዙሪያ የተሻሉ ስራዎችን እንዲሰሩና በግለሰብ ደረጃም ሆነ በተቋማቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያመጡ ረድቷቸዋል።
የኢትዮጵያ የምግብና ስርአተ ምግብ ፖሊሲና የብሄራዊ የምግብና የስርአተ ምግብ ስትራቴጂ ፀድቀው ወደትግበራ መግባታቸውን ተከትሎ ፖሊሲውንና ስትራቴጂውን በትክክል ከማስፈፀም አኳያ ብቁ አመራሮችን የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ ላይ ኔትዎርኩ በርካታ ድጋፎችን ማድረግ ይፈልጋል። አብዛኛዎቹ የኔትዎርኩ አባላት በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ በመሆናቸው በትርፍ ግዜያቸው ተጨማሪ ስራዎችን እየሰሩ ተቋማቸውንና በተቋማቸው ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችን ስልጠና በመስጠት ያግዛሉ። በቀጣይም ይህንኑ በማጠናከር በተለይ ደግሞ ማማከርና ስልጠናዎችን በማካተት ከላይ እስከታች በስርአተ ምግብ ዙሪያ ያሉ አመራሮችን የማብቃት ስራዎችን ለማከናወን ታቅዷል።
እንደ ሰብሳቢዋ ገለፃ በወጣቶች ላይ ሰፊ ስራዎችን ለመስራት በኔትዎርኩ የአቅም ግንባታ ዘርፍ ስር የወጣት መሪዎች ፎረም ተቋቁሟል። ይህም ወጣቶች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እድሜያቸው እስከ 30 ዓመት ያሉትን በመያዝ በስርአተ ምግብ አመራር ዙሪያ ስልጠናዎችን በመስጠት ለማብቃት ያስችላል። ከዚህ ባለፈ ወጣቶቹ በጎ የሆነ ለውጥ እንዲያመጡና ሀገራቸውንም እንዲለውጡ የሚሰጧቸው ልዩ ልዩ ስልጠናዎች አሉ።
የስርዓተ ምግብ ትግበራ ሁሉንም ሴክተሮች የሚመለከት ጉዳይ እንደመሆኑ ትግበራው ውጤታማ እንዲሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የምግብና ስርአተ ምግብ ካውንስል እንዲቋቋም ሰነዱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገብቷል። በምግብና ስርአተ ምግብ ዙሪያ ጤና ሚኒስቴር የሚመራው ኤጀንሲ እንዲቋቋምም ስራዎች ተጀምረዋል። ከዚህ አንፃር ይህን የሚደግፈው አዋጅ ከፀደቀ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ጠንካራ የሆነ አመራር እንዲኖርና በዘርፉ ለውጥ ያለው ስራ እንዲሰራ የሚረዳ ተቋማዊ አደረጃጀት ስለሚኖር የስትራቴጂውን ትግበራ በሚገባ ያሳልጣል።
የኢትዮጵያ ምግብና የስርአተ ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ ከምግብና ስርአተ ምግብ በጋር የተያያዙ የሚታዩ የአመራር ችግሮችን ለመፍታት እንደመቋቋሙ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እገዛ ያደርጋል። ሀገሪቱም ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፋ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች። ይሁንና ችግሩ በጤና ሚኒስቴርና በኔትዎርኩ በኩል ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ በተለይ ለውጥ ያለውና የተቀናጀ ስራ እንዲሰራ የኔትዎርኩ ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ለዚህም በተለይ የወጣቱን የአመራር ብቃት እንዲያጎለብት ኔትዎርኩ ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎችን ይሰጣል። ከስልጣናው በኋላም ወጣቶቹ የራሳቸውን የድርጊት መርሃ ግብር እንዲቀርፁ ይደረጋል። ከዛም ራሳቸውን አይተው ለውጥ የሚያመጡበትና ባገኙት ስልጠና ተቋማቸውን የሚቀይሩበት ሁኔታ ይፈጠራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2014