የዓድዋ ከተማ ድምቀት የጀመረው ከዋዜማው ምሽት ነበር። የከተማው ወጣቶች ዓድዋ በሚል ቲሸርት ደምቀዋል። በመስመር ግራና ቀኝ ሰንደቅ ዓላማ ይውለበለባል። ከሶሎዳ ተራራ ስር የሚገኘው መድረክ የዓድዋ ከተማን አመሻሽ አድምቆታል።
የተለያዩ ድምጻውያን በመድረኩ ላይ ይጫወታሉ፤ ታዳሚው በጭብጨባና ፉጨት አጅቧቸዋል። ከዋዜማው ጀምሮ የደመቀችው የዓድዋ ከተማ ገና ከማለዳው ከሶሎዳ ተራራ ፊት ለፊት ያለው የከተማዋ መስመር ከህጻን እስከ አዋቂ ባሉ ሰዎች ተዘጋግቷል፤ ወጣቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያውለበልባሉ። ካህናትና ዲያቆናት ይህንን በዓል ለማክበር በአልባሳታቸው አጊጠው ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስታውሳሉ። ወዲህ መድረኩ በማርሽ ባንድና በመከላከያ ሰራዊት አባላት ስርዓት አሰላለፍ መድረኩ ልዩ ድባብ ፈጥሯል።
ይህ ሁሉ የሆነው 123ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ለማክበር ነው። በወቅቱ ከመላው ኢትዮጵያ ተሰባስበው ጠላትን ድል እንዳደረጉት ሁሉ፤ ይህንንም ቀን ለማክበር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ታዳሚያን ተሰባስበዋል። በተለይም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን፣ አርቲስቶችንና የተለያዩ ማህበራትን በመያዝ ወደ ስፍራው ጉዞ አድርጓል። ይህም ለወጣቶችና ተማሪዎች የመነቃቃትና ታሪክ የመጠየቅ ስሜት ፈጥሯል።
123ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በሶሎዳ ተራራ ስር ሲከበር በተለያዩ ዝግጅቶች ነበር። በዓሉንም ለማክበር የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል። የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ የዓድዋ በዓል በኢትዮጵያወያን ኩራት ብቻ ሳይሆን ትምህርትም የሰጠ ነበር።
የውጭ አገር ስምምነት ሲደረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚጠይቅ የውጫሌ ውል ሁነኛ ማሳያ ነው። አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ግን ጀግኖች አባቶቻችን አልተቀበሉትም። የአሁኑ ትውልድም የውጭ ጣልቃ ገብነትን መቀበል የለበትም። የትግራይ ክልል መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ለውጭ ወራሪና ለጦርነት ተጋላጭ ቢሆንም፤ ጠላትን የማሸነፍ ልምድ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚረግጥ ከሆነ የአገሪቱን መንግሥትም ቢሆን ይታገላል ብለዋል። የዓድዋ በዓልና የዓድዋ ተራራ ተገቢው አያያዝ እንዳልተደረገለትም ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የገለጹት።
አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ መሆን ሲገባው ግን አልሆነም፤ በቀጣይ ግን እዚህ ላይ ይሠራል ብለዋል። ለዚህም የክልሉ መንግሥት ለጥናትና ምርምር ዓላማ ለሚውለው ፓን አፍሪካኒዝም ዩኒቨርስቲ ግንባታ ከቦታ ጀምሮ 250 ሚሊዮን ብር እንደመደበ አስታውቀዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፣ ዓድዋ የአንድነት ማህተም መሆኑን አብራርተዋል። ማህተም ማለት የተጻፈ ነገር ማረጋገጫ ነው፤ ዓድዋም የአንድነት ማረጋገጫ ሆኗል። የዓድዋ ጀግኖች የመከፋፈል ባህሪ ቢኖራቸው ኖሮ ለዛ እጅግ ብዙ ምክንያት ነበራቸው። በወቅቱ ድርቅና ረሃብ ነበር። አንድነታቸው በልጦ ግን አሸንፈዋል።
መጣላትና መለያየት ጥበብና እውቀት የማይጠይቅ የሰነፎች ሥራ መሆኑንም ተናግረዋል። የእለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በዓሉን ከማክበር ባሻገር ማስተማር እንደሚገባ ተናግረዋል። ድሉ የአንድነት ማሳያ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣አሁን ለአለው ትውልድ ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን ገልጸዋል። አሁን በአገሪቱ ያለው ችግር ከወቅቱ የዓድዋ ጀግኖች ጋር ሲነጻጸር ከአቅም በላይ አይደለም። ያኔ የነበረውን ከፍተኛ ችግር ተቋቁመው ማሸነፍን አሳይተውናል ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011
በዋለልኝ አየለ