(ክፍል አንድ)
የአሜሪካ የቂም መወጣጫ ፖሊሲ፤
ዘመንና ዕውቀት ያልተዋጀበትን ድርጊት ለመግለጽ ሲፈለግ “ካረጁ አንባር ይዋጁ” የሚለው የስላቅ መግለጫ ብሂል ይበልጥ ተመራጭ ይሆናል። የፖለቲካና የማሕበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች የዛሬውን የአሜሪካ የተንሸዋረረ ጥልቅ የፖሊሲ አስኳል የሚተቹት የራሱን ዳቦ በብቱ ታቅፎ የሌሎች እኩዮቹን ድርሻ ጠቅልዬ ካልነጠቅሁ የሚል ስግብግ ባህርይ በተላበሰ ታዳጊ ሕጻን እየመሰሉ ነው።
ለዚህ እውነታ ማረጋገጫነት “የታላቋ አገር” ሹማምንት፣ የፖሊሲ ቀማሪዎችና አስፈጻሚዎች የሚጠቅሱትን “ካሮት ወይንም ዱላ” (Carrot or Stick) በመባል የሚታወቀውን የአምባገነንነት መርሃቸውን ማስታወሱ ብቻ በቂና ከበቂም በላይ ነው። ይህንን የጉልበተኝነት ማሳያ አባባል “እንድረዳህ ገብር፤ ከተቃወምክ በትር” በማለት በተቀራራቢ አገራዊ ምሳሌያዊ አነጋገር ልንተረጉመው እንችላለን።
“የካሮቱና የዱላው” ምሳሌ የተቀዳው ከእንስሳት ጋላቢ ድርጊት ተኮርጆ ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት በቅሎ የሚያሰግር ወይንም አህያ የሚጋልብ ሰው በጀርባው ላይ የተፈናጠጠበትን እንስሳ ፍጥነቱን ለማስጨመር የሚጠቀመው በረጅም ዱላ ላይ ካሮት አንጠልጥሎ የማማለል ዘዴ እየተጠቀመ ነበር። ድርጊቱ የሚታይ እንጂ የማይበላ “መና” የሆነበት እንስሳም ከፊቱ ላይ የተንጠለጠለው ካሮት ካሁን አሁን ይወድቅልኛል እያለ በመጎምዠት አፉን አሞጥሙጦ በፍጥነት ሶምሶማ ጉዞውን ወደፊት ይቀጥላል።
ይህ ዘመን የመሸበት አሮጌ የማታለያ ዘዴ በብዙ ቀደምት የጥበብ ሥራዎችና የጽሑፍ ቅርሶች ውስጥ ተደጋግሞ የተገለጸ መሆኑ ብቻም ሳይሆን እየዋለ እያደረም ለበርካታ አምባገነን መንግሥታት እንደ ፖሊሲ መተርጎሚያና ማስፈጸሚያ፣ ለአመራር ጥበብ አሰልጣኞችና ለማኔጅመንት ምሁራን ደግሞ እንደ አስተዳደር ስልት እየተጠቀሰ “ገናና ተጠቃሽ” ምሳሌ ሊሆን በቅቷል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በተግባር ካልተረጎምኩ በማለት ላብ እየደፈቃት የምትፎክረው ይህንን “የፖሊሲዋን ንክር” ለማስተግበር ነው። ሲያሻት በዲፕሎማሲ አተካሮ ፊት ለፊት ግብ ግብ ገጥማ፣ ስትፈልግ የጊዜያዊ ጥቅም “ካሮት እያጎረሰች በምትጋልብባቸው” ግለሰቦች፣ ሚዲያዎችና ተቋማት አማካይነት፣ ከፍ ሲልም በአስገዳጅ የቅድመ ሁኔታዎች “ዱላ” እያስፈራራች ለማዘዝ ወይንም ለማንበርከክ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቷ እያስተዛዘበ ነው።
“እኔ ካልኩት ውጭ ወይ ፍንክች” እያለች በሉዓላዊነታችን ጉዳይ እንድንደራደር የምትጎተጉተው ዘመንና ወቅት የማይዋጀውን ይህንን ፖሊሲዋን ካልተቀበላችሁ እያለች በማስገደድ ነው። “እንኳንስ ሲሸጡኝ ሲያስማሙኝ አውቃለሁ!” አለ የሀገሬ ሰው። አላወቁ ከሆነ ይወቁት፤ አውቀው የሚያደርጉ ከሆነም አይበጃቸውም።
እውነቱ ንገሩን ካሉ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ እነርሱ ገና ማሰሯቸውን ጥደው (Melting Pot-እንዲሉ) የዓለም ዜጎችን ከአጥናፍ አጥናፍ በስደትም፣ በወረራም ሆነ ዛሬ በሎተሪ ዘዴ እንደሚያደርጉት ዘመኑ በሚፈቅደው የተለያዩ ዘዴዎች እያሰባሰቡ እንደ አገር ሉዓላዊ ክብር ከመጎናጸፋቸውና በሀብታቸው በረከት ከመመካታቸው አስቀድሞ ይህቺ ገናና አገር በታሪኳና በጀግንነቷ ነዎሩ እየተባለች “ይሰገድላት” እንደነበር ትናንትን እያስታወስን እንሞግታቸዋለን።
ዛሬም ያ የኢትዮጵያዊነት ሥረ ነገር ጣዕሙም ሆነ ክብሩ፣ ወኔውም ሆነ የደም ውርሱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት በሚኖሩት ልጆቿ ስሜትና መንፈስ ውስጥ እንዳልቀጠነ በመላው ዓለም ታላላቅ ከተሞች አደባባዮች
ላይ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አድርገው እያውለበለቡ “No More!” በማለት መልዕክት የሚያስተላልፉትን የቁርጥ ቀን ልጆቿንና ወዳጆቿን ቢያደምጡ ይበጃቸዋል።
“የካሮትና ዱላው አጋፋሪዎች!”
አሜሪካ ከላይ የጠቀስነውን ከዘመንም ሆነ ከዐውድ ጋር የተፋታውን ፖሊሲዋን ለማስተግበር ቆርጣ የተነሳችው በኢትዮጵያ ጉዳይ “ከእኛ ወዲያ ለአሳር” በሚል ትምክህት የናወዙ ሹማምንቶቿና ዲፕሎማቶቿ ለመንግሥታቸው በሚሰጡት የተሳሳተ መረጃና ምክር መሆኑ ሴራቸው በአደባባይና በግላጭ እየተሰጣ ለትዝብት ዳርጓቸዋል።
ከብዙዎቹ መካከል ሁለቱን የአሜሪካ ተቀዳሚ ሹመኞች ብቻ ለአብነት በመጥቀስ እውነታውን ለማሳየት እንሞክር። ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው ከአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ትራፊዎች ጋር ካልተደራደራችሁ በማለት ተጽእኖ ለማሳረፍ ተግተው ከሚሰሩት መካከል አንደኛዋ “የካሮቱ” ሌላኛዋ “የዱላውን” ብሂል (Metaphor) እንዴት ሊወክሉ እንደሚችሉ ቀዳሚና ወቅታዊ ተግባራቸውን እያስታወስን ጥቂት እናሰላስል።
ጋየል ስሚዝ (Gayle Elizabeth Smith) በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የጤና ሚኒስቴር (Health Secretary at the U.S Department of State ) የዓለም አቀፍ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምላሽ ሰጪ አስተባባሪ በመሆን እያገለገሉ ያሉ ጎምቱ ሹመኛ ናቸው። እኚህ ወ/ሮ ፖለቲካዊ እትብታቸው እንደምን ከሕወሓት ጋር ተጣብቆ እንደኖረ ማሳያዎችን እናመላክት። ይህ አሸባሪ ቡድን ለሥልጣን ከመብቃቱ አስቀድሞ በረሃ እያለ ሴትዮዋ ለአንድ የሚዲያ ተቋም ተባባሪ ጋዜጠኛ (Freelance journalist) በመሆን ቡድኑ ከመሸገበት ዋሻ ድረስ ዘልቀው እየገቡ ቤትኛነታቸውን ያስመሰከሩ ሴት ነበሩ። በተለይም ከቡድኑ ዋነኛ ሰው ከተጋዳላይ መለስ ዜናዊ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንደነበራቸው የማይሸሸገው ዜና መዋዕላቸው ይመሰክራል።
ይሄው ግንኙነታቸው ከፍ ወዳለ ደረጃ ደርሶም ለብዙዎች እንቆቅልሽ ቢሆንም እ.ኤ.አ በ1986 ዓ.ም የማሕበረ ረድዔት ትግራይ (ማረት) አማካሪ ተደርገው በመሾም በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው የርሃብ ወቅት አሸባሪውን ቡድን በመደገፍ ትልቅ ውለታ የዋሉ ሰው ናቸው። ይህንን ሹመታቸውን ተከትሎም ሴትዮዋ ለትህነግ ጥቅም የቆሙ “ጥልቅ ብዬ” መሆናቸውን ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር ትልቁን ሚና በተጫወቱት ሚ/ር ኸርማን ኮኸን ሳይቀር መብጠልጠላቸው አይዘነጋም።
የአሜሪካ መንግሥት ለተለያዩ አገራት በጅቶት የነበረው ሃያ ቢሊዮን ዶላር ያለአግባብ በእኒሁ ሴት አማካይነት እየባከነ እንደነበርም በስፋት ሲወራ ባጅቷል። ሴትዮዋ ከ2015 – 2017 ዓ.ም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅት (USAID) ኃላፊ ሆነው በሠሩባቸው ዓመታትም ከወያኔ ሥርዓት ጋር የቀረበ ግንኙነትና ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር በስፋት ይታወቅ ነበር።
ቀደም ባሉት ዓመታት በልማት ስም የፈጸሙት ደባ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ወቅትም ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ባላቸው ሹመትና የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዋና ባለሥልጣን ከሆኑት ከሕወሓቱ ሥራ አስፈጻሚ ከዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ምን ሊሠሩ እንደሚችሉ ሰንጠረዡን በማገጣጠም (Jigsaw game እንዲሉ) በአገራችን ላይ እየተውጠነጠነ ስላለው የተራቀቀ ሴራ መገመት አይከብድም። “ለካሮቱ” አስፈጻሚነት እኒህ ሴት ከበቂ በላይ ማስረጃ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሌላኛዋ ተጠቃሽ “ዱላ አቀባይ” እንስት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የጆ. ባይደን የአገር ውስጥ ፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ሱዛን ራይስ ናቸው። እኚህ “የአገራቸው የፖለቲካ ዋና አዳዋሪ እንዝርት” የሚሰኙት ፖለቲካኛ የትኛውም ኢትዮጵያዊ በቅርበት ሊያውቃቸው ይችላል ተብሎ ስለሚገመት በዝርዝር ማንነታቸው ላይ ብዙም የጠለቀ መግለጫ መስጠቱ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ሴትዮዋ ለኢትዮጵያ የወቅቱ መንግሥት ያላቸው የጠቆረ ፊት ለምን ሊፈጠር እንደቻለ የጋዜጣው ዐምድ እንዳይወስነን በመስጋት እንጂ በርካታ ምክንያቶችን መዘርዘር አይገድም።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ አል ማርያም ማርች 29 ቀን 2021 ሴትዮዋን የገለጹበት አረፍተ ነገር ብዙ ሃሳቦችን ስለሚጠቀልል እንዳለ እንጥቀሰው፤ “Susan Rice works for the TPLF, not to the people of the United States”። የኢትዮጵያና የኤርትራን ጉዳይ በአፍራሽነት የሙጥኝ ብለው ነክሰው መያዛቸውን ለመግለጽም በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች “Containment of Ethio-Eritria Sovereignty” የሚሰኘውን የሴትዮዋን መርህ “The Susan Rice Doctrine” በማለት ይገልጹታል።
እኒህ ሴት በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊን የቀብር ሥነ ሥርዓት ለመታደም ተገኝተው ካደረጉት ንግግር መካከል “[Meles Zenawi] uncommonly wise, able to see the big picture and long game” የሚለው አረፍተ ነገር “ከአስከሬን ስንብት ማስተዛዘኛ” ላቅ ያለ ፖለቲካዊ ትርጉም እንዲሰጥ ተደርጎ መቀናበሩን ብዙዎች አስተያየት ሰጥተውበታል። “የበትር ወዝዋዧ እመቤት” ማስፈራሪያ በተለያዩ መልኮች እየተገለጸ መሆኑን በህዳሴው ግድባችን ላይ ከሚያራምዱት አቋም፣ ከወራሪው ትህነግ ትራዤዲና ከሰብዓዊ የተራድኦ አቅርቦት ጋር ተያይዞ በገሃድ እያስተዋልን ነው።
ዛሬ አሜሪካ ይሏት ጀብደኛ አገር በኢትዮጵያ ላይ እያራመደች ያለችው “የካሮት ወይንም የዱላ” ፖሊሲዋ ተተግብሮ ኢኮኖሚያችን እንዲሽመደመድ፣ ፖለቲካችን እንዲላቁጥ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጥረታችን ሸብረክ እንዲል፣ የሰብዓዊና የልማት ድጋፎች እንዲነጥፉ፣ ወራሪዎች የልብ ልብ እንዲሰማቸው የተዘመተብን በእንደነዚህ መሰል “ውስጥ አዋቂ” ነን ባዮች በሚጎነጎን ሴራ ጭምር እንደሆን እኛን ባለጉዳዮቹን በሚገባ ገብቶናል፤ የዓለምን ማኅበረሰብንም “አሃ!” አሰኝቶ በማስገረም ለእውነት እንዲቆሙ እያባነናቸው ነው። የዓለም አቀፎቹ “ነፃ ተብዬ” ሚዲያዎች እያላዘኑ ያሉት ይሄንን የሻገተ የበላይነት ስሜት “ድል ለማጎናጸፍ” መሆኑም እርቃኑ እየተገላለጠ ስለሆነ የእውነት አሸናፊነት ጉልበት እያገኘ በመሄድ ላይ ነው።
“አያውቁንም እኛን አያውቁንም!” ያለው ዜመኛ ማን ነበር? መልኩና ዓይነቱ ይለያይ ካልሆነ በስተቀር እንደዛሬው ኢትዮጵያ ያልተገፋችበት ዘመን አልነበረም። ተንገዳግዳ ካልሆነ በስተቀር ውድቀትን አልተለማመደችም። ዘመናዊ ጦር የታጠቁ ወራሪዎችም እንዲሁ በየዘመናቱ “ጋሻና ጦሯን” ከእጇ አስጥለው ሉዓላዊነቷ ላይ ለመዘባበት ያላደረጉት ሙከራ አልነበረም። “ለሠርግና ምላሽ” ተምመው ቢመጡም “የቀብር ሥርዓታቸው” ተፈጽሞ መርዷቸውን ተከናንበው ተመልሰዋል።
የዛሬው ፈተናችንም በራሳችን እኩያንና በባዕዳን ጣልቃ ገብነት እጅግ የተወሳሰበ ቢመስልም በመሪዎቻችን በሳል አመራር፣ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንና በሕዝባዊ ተፋላሚዎች ተጋድሎ፣ በሕዝባችን ብርቱ ደጀንነትና በወዳጆቻችን የክፉ ቀን ብርቱ ድጋፍ ኢትዮጵያ ተሸንፋ አንገቷን አትደፋም። ጠላቶቿ እንደሚመኙትም እንደ ሸክላ ገበቴ ተፈረካክሳ አትበታተንም። ምስክሩ ታሪካችን፤ መሃላው ደግሞ የዚህ ትውልድ ኪዳን ስለሆነ ሉዓላዊነታችን አይደፈርም፣ ክብራችንም አይዋረድም። ፈጣሪ የአገሬ ቀኝ እጅ ስለሆነ ባለ ግራኝ እብሪተኞቹ ምኞታቸው አይሰምርም። እውነታው ይሄ ነው፤ መዝሙራችንም “ድል በድል” የሚሸት ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2014