በመላው ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ ሰሞኑን በመዲናችን በጸጥታ አካላት በተለያዩ ቦታዎችና አጋጣሚዎች ከሚደረጉ ድንገተኛ ፍተሻዎች ጋር ተያይዞ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ሲፈጠሩ እየታዘብን ነው። በእርግጥ የሚነሱት መነጋገሪያ ጉዳዮች ለአጀንዳነት የሚበቁ እንኳን አይደለም።
ያም ሆኖ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በተለይም በማሕበራዊ ሚዲያው ሕብረተሰቡ የተዛባ ግንዛቤ እንዲይዝ ለማድረግ ለሚጥሩ አካላት አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ ወይም ለመሆን ቅርብ የሆኑ ሰዎችን ውዥንብር ውስጥ እንዳይገቡ ጉዳዩን ማንሳት ጥቅሙ እንጂ ጉዳቱ አይታይም።
እንኳን አገር በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ በደጉም ዘመን መፈተሽ ለብዙሃኑ ደሕንነት መሆኑን ማንም ሊጠፋው አይችልም። እርግጥ ነው መፈተሽ የመንገድ መጨናነቅ ሊፈጥር ይችላል፣ አንድ ሰው ባሰበው ሰዓት ያሰበው ቦታ በጊዜ እንዳይደርስ ሊያዘገየው ይችላል፣ ለመፈተሽ አሰልቺ ወረፋ መጠበቅ ግድ ሊል ይችላል። ይህ ሁሉ ግን ከደሕንነቱ አይበልጥም። ከነገ ሰላሙም አይልቅም።
በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት አንድ ባለ ሥልጣን በአውራ ጎዳና ላይ ያልፋልና ፊትህን አዙረህ ቁም በሚባልባት አገር ለጋራ ደህንነት ሲባል የቱንም ያህል መጉላላትና እንግልት ቢኖር መፈተሹ ቅንጣት ታህል ቅር ሊያሰኝ አይገባም። እንዲያውም ለራሱ ሲባል መሆኑን አስተውሎ በትዕግስት መፈተሽና ከጸጥታ አካላት ጋር መተባበር እንደሚኖርበት ሕዝቡም ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም።
‹‹የማሕበራዊ ሚዲያ አንቂ ነን›› የሚሉ ሰዎችም ይህ አንገብጋቢ የሕዝብ ደህንነት ጉዳይ ይጠፋቸዋል ተብሎ ባይታሰብም ከመንጫጫትና ውዥንብሮችን ከመፍጠር አልቦዘኑም። ከፍተሻ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከአንድ ብሔር ጋር በማያያዝ፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋርም በማገናኘት ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ የሚመስሉ የማሕበራዊ ሚዲያው አንቂዎች ሳይቀሩ በጸጥታ አካላትና ፖሊስ ላይ ያልተገባ ትችቶችን ሲሰነዝሩ ይስተዋላል።
በማንኛውም አይነት ፍተሻ ወቅት አንዳንድ የጸጥታ አካላት ሕብረተሰበን የማመናጨቅ፣ ከመሰላቸት የተነሳ ምንም ነገር በሌለበት ሁኔታ ስሜታዊ የመሆን ዝንባሌ ሊታይባቸው ይችላል። ይህን በትዕግስት ማለፍ ባይቻል እንኳን ፈታሾቹ ሰው መሆናቸውን መዘንጋት አይቻልም። እነሱም ለረጅም ሰዓት ስራ ላይ ውለው በድካምና በመሰላቸት ስሜታዊ ሆነው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ መረዳት ተገቢ ነው።
ይህ በአንዳንድ አጋጣሚ የሚፈጠር ችግር በትዕግስት የሚያልፍ ነው። ይህ ማለት ግን የፀጥታ አካላት በሕግና በሥርዓት ስራቸውን ማከናወን የለባቸውም ማለት አይደለም። እውነቱን ለመነጋገር ግን በጸጥታ አካላት ላይ ከሚሰነዘረው ትችት ይልቅ የጸጥታ አካላት አገር ከተደቀነባት አደጋ አኳያ ከዚህ በላይ መፈተሽ በቻሉ ነበር። በእርግጥ ፍተሻው ከሰሞኑም በበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የሚደረጉ ፍተሻዎችም ለይስሙላ እንጂ አገር ላይ ከተጋረጠው የደህንነት ስጋት አኳያ እዚህ ግባ የማይባሉ ስለመሆናቸው መታዘብ ይቻላል። የጸጥታ አካላት መወቀስ ካለባቸውም በዚህ መሆን አለበት። መነጋገር ካለብንም የጸጥታ አካላት ፍተሻ የሚያከናውኑበት መንገድ ጉድለቶች ካሉበት በዚያ ዙሪያ መሆን ይገባዋል።
በተለይም በፍተሻና በቤት ለቤት አሰሳ ላይ ወቅት ሕገወጥ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችንና ሌሎችንም ይዘው የተገኙ ግለሰቦች ገንዘብ እየከፈሉ እንደሚለቀቁ ይነገራል። ይህን ከአገር ክህደት የማይተናነስ አስነዋሪ ድርጊት ሊፈጽሙ የሚችሉ አንዳንድ የጸጥታ አካላት አይኖሩም ማለት ባይቻልም ሙያቸውን አክብረው የቀን ፀሐይና የሌሊት ውርጭ ሳይበግራቸው የሕዝቡን ሰላም ለመጠበቅ ዘወትር የሚተጉ በርካቶች መኖራቸውን መዘንጋት እንዴት ይቻላል።
ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ያስቻሉትን የጸጥታ አካላትን የማይወክሉ ካሉ በመረጃና በማስረጃ እኩይ ተግባራቸውን አጋልጦ ለሕግ ማቅረብ ያስፈልጋል። መንግሥትም ለዚህ ትኩረት ሰጥቶ ራሱን መፈተሽ ያለበት ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። በተረፈ ግን ጥቃቅን እንከኖችን አጉልቶ በማውጣት ለምን ተፈተሽኩ በዚህ ወቅት አይሰራም።
ደሴ ላይ ከሕብረተሰቡ ጋር ተመሳስለው በመኖር የአሸባሪው ቡድን ጀሌዎች የሰሩትን ክህደት አዲስ አበባ ላይ ላለ መፈጸማቸው ምንም ማስተማመኛ የለም። ዛሬ መፈተሽንና ፍተሻ የሚያመጣውን መጉላላት ጠልቶ ነገ አንድ ነገር ድንገት ኮሽ ሲል መንግሥት ላይ ጣት መቀሰርና የደሕንነት ሥርዓቱን ማብጠልጠል በየትኛውም መመዘኛ ትክክል ሊሆን አይችልም። ዛሬ መፈተሽ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንነት መተባበር ነገ ጥያቄ ለማንሳትም ሞራል ይሆናል።
በየመንገዱ ድንገት ከሚካሄዱ ፍተሻዎች በተጨማሪ ቤት ለቤት የሚካሄዱ አሰሳና ፍተሻዎች ላይም ሆደ ሰፊ መሆንና ከጸጥታ አካላት ጋር መተባበር ውጤት እንደሚያመጣ ሰሞኑን ፖሊስ ከሚሰጣቸው ሪፖርቶችና መግለጫዎች መረዳት ይቻላል። ጎረቤቴ ነው፣ ዘመድ ወዳጄ ነው፣ አብሮኝ የኖረ ነው ብሎ የጸጥታ አካላትን ስራ ማስተጓጎል ወይም ማሰብ በዚህ ወቅት ቅንጦት ነው። ምክንያቱም ከደሴ ተምረናልና።
እኔ ተፈትሻለሁ ጎረቤቴስ? ማለት ወዳጅና ባልንጀራን አሳልፎ ከመስጠት ወይም ከመጠርጠርና መተማመንን ከመናድ ጋር ፈጽሞ ማያያዝ ተገቢ አይደለም። እንዲያውም ወዳጅና ጠላትን ለይቶ ለማወቅ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ተማምኖም ለመቀጠልና ነገም ለሚመጣ አደጋ ተደራጅቶ አካባቢን ለመጠበቅ የመሰረት ድንጋይ ሊሆን ይችላል።
‹‹ምን ያለበት ዝላይ አይችልም›› እንደሚባለው አንድ ሰው ምንም ችግር ከሌለበት ለጋራ ደህንነት ሲባል መፈተሽን ሊቃወም አይችልም። ዘርና ማንነትን መሰረት አድርጎ ሳይሆን ማንኛውም የጸጥታ አካል የፈለገውን አካል በፈለገው ሰዓትና ቦታ እንዲፈትሽ የሕዝቡ ሆደ ሰፊነት ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊ ነው። በዚህ የጸጥታ ስጋት ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ተደርጎ የሚጠረጠረው የጥቂት ብሔር ተወላጅ ብቻ አይደለም። የጥፋት ሃይሉ ቀለብ የሚሰፍርላቸውና ጥቅማቸው የቀረባቸው በርካታ ግለሰብና አካላት ከየትኛውም ብሔር ሊኖሩ እንደሚችሉ ለማንም የተደበቀ አይደለም።
እነኚ ግለሰቦችም ይሁኑ የተደራጁ አካላት ደሴ ላይ የተፈጠረው ሁኔታ በሌሎች ከተሞችም እንዲፈጠር ከመስራትና ከመዘጋጀት ባለፈ በጸሎት ጭምር ሌት ተቀን አይታትሩም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ማንም ቢሆን ይፈተሽ፣ ቤቱም ይበርበር፣ ፍተሻው ሲጠናቀቅ ማን ነጻ ማን ስጋት እንደሆነ በግልጽ መለየቱ አይቀርም። ዛሬ በየዋህነት የታለፈ ነገር ነገ ችግር ይዞ እንደማይመጣ ማንም እርግጠኛ መሆን አይችልም። የዛሬ ወዳጅ ነገ ከጀርባ ስለት ይዞ ብቅ እንደማይል አንድም ሰው እርግጠኛ መሆን አይቻለውም። ይህ በማህበረሰቡ መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠርና መተማመን እንዳይኖር አጀንዳ የመፍጠር ጉዳይ ተደርጎ መታየት የለበትም።
ይህ ወዳጅና ጠላትን የመለየት ጉዳይ ነው፣ የነገን ሰላምና አብሮነት የመሰረት ድንጋይ የመጣል ጅማሬ ነው፣ የነገ የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ ጭምር ነው። አገር ከገባችበት ቅርቃር በፍጥነት እንድትወጣ የሚረዳ ትብብር ነው፣ እየተከሰተ ያለውንና ነገም ሊከሰት የሚችለውን እልቂት የማቆም ጉዳይ ነው። ነገ ወዳጅ ብለን በምናስበው ከጀርባ መወጋት ቁስሉ አካላዊ ብቻ አይደለም። መተማመንን እስከወዲያኛው የሚያጠፋ፣ መተዛዘንና መደጋገፍን ከማህበረሰቡ እሴቶችና መዝገበ ቃላት የሚሰርዝ አደጋ አስከትሎ ሊያልፍ የሚችል ነው። ስለዚህ ከጀርባ ከመወጋት ዛሬ መፈተሽ፣ ያልተፈተሸውን ማስፈተሽም ለማንም ግልጽና ሌላ ተጨማሪ ምክንያታዊነት የሚፈልግ ጉዳይ አይደለም። እንፈተሽ፣ እናስፈትሽ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/2014