ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተችው እንቁ ስጦታዎች መካከል ቡና ዋነኛው ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚ ጠቁሙት፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም በየቀኑ ከአራት ቢሊዮን ስኒ በላይ ቡና ይጠጣል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ስኒው የሚጠጣው በሽያጭ መልክ ከተዘጋጀው ነው።
በአሁኑ ወቅት ቡና በ50 አገሮች የሚመረት ሲሆን፣ ከ120 ሚሊዮን በላይ የዓለም ህዝብም ኑሮውን ይደግፍበታል። ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያ አንዷና የቡና መገኛ አገር ብትሆንም የዘርፉ ምርታማነት ግን ገና አላደገም፤ በዚህም የተነሳም ከቡና ተጠቃሚ እየሆነች ነው ለማለት አያስደፍርም።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሆና ከዘርፉ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን ባበቋት ማነቆዎች ላይ የተደረገ የውይይት መድረክ በቅርቡ በአቤጋ ማኔጅመንትና በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አዘጋጅነት ተካሂዷል።
ቡናን በመላክ ስራ ከላይ የተሰማሩትና የሆራይዘን ፕላንቴሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ጀማል አህመድ እንደሚሉት፤ አሁን ባለው ሁኔታ ሀገሪቱ ቡና ለውጭ ገበያ እያቀረበች ሲሆን፣ሀገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ሲታይ ገቢው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ይህንን ማሻሻል ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ቡና የተለየ ጣዕም ያለውና ተፈላጊ ቢሆንም፤ ምርታማነትና የዝግጅት ጥራት ግን ከፍተኛ ችግር ያለበት ነው፤ ይህንን ለመቀየር ደግሞ አርሶ አደሩ እንዴት ቢሰራ ምርታማነቱ ሊጨምር ይችላል የሚለውን በትኩረት መፈተሽ ይገባል፡፡ በተለይም የአርሶ አደሩን ማሳ በማደስ፣ የቆዩ ዝርያዎችን የተሻለ ምርት በሚሰጡ መቀየር ከተቻለ በቡና ምርታማነት ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
ምርታማነትን በማሻሻል በኩል መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች የራሳቸውን ተሞክሮ በማጣቀስ ሲናገሩም «እኛ ከውጭ የምናስመጣው የቡና ዝርያ የለም፤ ሆኖም ለአካባቢው የተሻለ የተባለውን ለምሳሌ በበቃ ላይ በ 1980 ዓ.ም በዘመቻ የተተከለውን የቡና ዘር በማንሳት ለአካባቢው ተስማሚ የሚሆኑ ዝርያዎችን ከግብርና ምርምር ጋር በመሆን በመትከላችን አሁን ምርቱን በሶስትና አራት እጥፍ ለማሳደግ ተችሏል » ይላሉ።
‹‹ዝርያው አገር ውስጥ ያለው ቢሆንም፤ በአሰራርና ቦታውን አመቺ ለማድረግ በተሰራ ስራ ምርታማነት ላይ ለውጥ መጥቷል›› የሚሉት አቶ ጀማል፣ ‹‹ይህ አይነቱ የአሰራር ዘዴ ደግሞ መንግስት ወደ ገበሬውና ወደ ሌሎች ቡና አምራቾች በማውረድ ተግባራዊ ቢያደርገው ምርታማነታችንን ከፍ በማድረግ የአገር ውስጥ ፍጆታን በማሟላት በውጭ ገበያውም ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል›› ሲሉ ያብራራሉ።
በቡና ዘርፍ ላይ በርካታ ምርምሮችን ያደረጉት ዶክተር ታደሰ ኡማ በበኩላቸው፤ ‹‹ኢትዮጵያ የቡና መገኛ በመሆን የተለየ ጣዕም ያለው ቡና ማቅረብ ብትችልም፤ በተለይም በምርታማነት ላይ የሰራነው ስራ እምብዛም ባለመሆኑ በዓለም ገበያ ላይ ዋጋን የመወሰን አቅም አጥተናል›› ይላሉ። ‹‹የአለም ገበያን መያዝ የምንችለው በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ ሆነን መገኘት ስንችል ነው፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ዘላቂ አቅራቢ መሆንንም ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምርታማነት ላይ ሰፊ ስራ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል›› ብለዋል።
አቶ ታደሰ ፤ኢትዮጵያ ቡናን ለማምረት የሚያስችል ሰፊ መሬት እንዳላት ጠቅሰው፣ ተጠቃሚ ለምን አልሆነችም? ሲባል ግን ቀድመው ከሚመጡት ምክንያቶቹ አንዱ ቦታዎቹ ተደራሽ አለመሆናቸው፣ ቡናን ለማምረት ሀብት ማስፈለጉና ይህንን ለማግኘት ደግሞ የብድርና ተያያዥ አገልግሎቶች ውስንነት በምርታማነቱ ላይ ጫና በማሳደራቸው ነው ሲሉ ያብራራሉ ።
«ወጣቶች ስራ ይፈልጋሉ፤ አሁን ባለው ሁኔታ በመንግስት መስሪያ ቤት ገብቶ የመስራት እድሉ እየጠበበ ነው፤ የቡናን ኢንቨሰትመንት በማስፋት ግን እነዚህን ወጣቶች ወደ ምርት ብናሰማራቸው ገበያው ስላለ ተጠቃሚ ይሆናሉ » ብለዋል።
ዶክተር ታደሰ እንደሚሉት፣ ቡናን ለማሸጋገር በዘርፉ የሚደረገው ኢንቨስትመንት መጠናከር አለበት፤ ሀብት ሳይወጣበት የሚገኝ ሀብት የለም፡፡ ቡና የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መገኛ ሆኖ ቢቆይም፤ ለዘርፉ እየወጣ ያለው ሀብት ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፡፡
የአቤጋ ማኔጅመንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ የበጋሸት አለማየሁ እንደሚሉት፤ ቡና በአገሪቱ ለሚገኙ ከ25 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረና ባለው ደረጃም ቢሆን ከአገሪቱ የውጭ ንግድ አንድ ሶስተኛውን ይሸፍናል። ሆኖም አገሪቱ ካላት ለቡና ምርት ምቹ መልክዓ ምድርና የቡና መገኛነት አንጻር ይህ ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ይህንን ሁኔታ እንዴት በማሻሻል በምንስ መልኩ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል? በሚለው ላይ ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት የመፍትሔው አንዱ አካል መሆኑን በመጥቀስ ፣ አቤጋ ማኔጅመንት ኃላፊነቱን ወስዶ ፕሮግራሙን ማዘጋጀቱን ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ አቶ የበጋሸት ማብራሪያ፤ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብትሆንም፣ ከእነ ቬትናምና ብራዚል ጋር ስትነጻጸር ምርታማነቱ እጅግ የወረደ ነው፤ በሌላ በኩልም ቡና የሚመረትበት መጠንም ከአመት አመት መሻሻል አያሳይም፡፡ በመሆኑም ችግሮቹ በዚሁ ከቀጠሉ በቡና ምርት ቀጣይነት ላይ መጥፎ ጥላ የሚያሳርፍ ይሆናል፡፡
ችግሮቹ እንዴት ይፈቱ የሚለውንም በውይይቱ ላይ በተቀመጡ አቅጣጫዎች አማካይነት ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ የበጋሸት፣ እንደዚህ ዓይነት መድረኮች ደግሞ የተለያዩ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩባቸው በመሆኑ የመንግስት ፖሊሲ አውጪዎችና አስፈጻሚ አካላት በርካታ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦች እንደሚወስዱም ይናገራሉ።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የአሁኑ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ እንደሚ ሉት፤ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻም ሳትሆን ሰፊ መሬት ከምቹ ስነ ምህዳር ጋር የያዘች ከመሆኗ በላይ ቡና የሚፈልገውን ሰፊ የሰው ሀይል ማሟላት የምትችል አገር ናት። የኢትዮጵያ ቡና የተለየ ጣዕምና በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር በዓለም ቡና ተጠቃሚዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው።
በሌላ በኩል የአገሪቱ ስነ ምህዳር የተለያየ ጣዕምና ባህርይ ያላቸውን ቡናዎች ለማምረት የሚያስችል ቢሆንም፤ በዘርፉ ምን ያህል ነው የተራመድነው የሚለው ሲታይ ግን 5ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር ለቡና ተስማሚ የሆነ መሬት በሌላ ሰብል ተሸፍኖ ነው የሚገኘው። ከዚህ ውስጥ አንግዲህ ቡና እየለማበት ያለው አንድ ሚሊዮን ሄክታሩ ብቻ ነው። ከዚህም ውስጥ እንደገና ለምርት የደረሰው 725 ሺ ኩንታል አካባቢ ነው። ይህ ደግሞ እጅግ አነስተኛ መጠን ነው።
በዚህ ስሌት መሰረትም አሁን ያለው የምርታማነት መጠን በአማካይ 6 ኩንታል በሄክታር ነው፤ ይህም በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ ሌሎች አገራት አሁን በሄክታር ከ 10 እስከ 25 ኩንታል እያመረቱ ነው፤ ይህም የኢትዮጵያ ምርታማነት ብዙ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ያመላክታል።
አቶ ሳኒ፣ ‹‹ቡናን የምናመርተው ለዓለም ገበያ ቢሆንም ምን ያህሉን ነው በትክክል ወደውጭ ገበያ የምንልከው ቢባል ከምርቱ ከ 40 እስከ 45 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ገበያ እያቀረብን አይደለም። ይህ ማለት ደግሞ እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል ማለት እንደሆነም ያብራራሉ። ይህ ደግሞ ከቡና አምራች አገሮች ሁሉ ለየት የሚያደርገውን ድክመታችን ነው›› ይላሉ።
አገሪቱ የቡና መገኛና ምቹ ስነ ምህዳር ያላት ብትሆንም፤ ከላይ በተጠቀሱትና እና በሌሎች ምክንያቶች ግን እስከ አሁን ድረስ ወደ ውጭ ከምንልከው ቡና አንድ ቢሊየን ዶላር እንኳን ማግኘት አልቻልንም፤ በሌላ በኩልም የሚገኘው አነስተኛ ገቢ ደግሞ አምራቹ ዘንድ ምን ያህል ይደርሳል ቢባል ከሌሎቹ አገሮች በጣም ዝቅተኛ ነው። ይህ ደግሞ የቡና ምርታማነት እንዳያድግ ፣ጥራቱ እንዳይሻሻል፣ የውጭ ንግዱም በሚፈለገው ልክ አንዳይሆን አድርጎታል።
‹‹እኛ ወደ ውጭ ልከን ከምናገኘው ገቢ ወደ አርሶ አደሩ የምናደርሰው 60 በመቶውን ብቻ ነው›› የሚሉት አቶ ሳኒ፣ እነ ቬትናም 94 በመቶ፣ ኮሊምቢያ 86 በመቶውን ያደርሳሉ፤ እኛም ምርታማነታችን እንዲያድግና ተወዳዳሪነታችን በተሻለ ደረጃ ላይ አንዲገኝ የምንፈልግ ከሆነ በዚህ ልክ ማዳረስ ይገባናልም›› ይላሉ ።
ለነዚህ ክፍተቶች ወይም ችግሮች መንስኤው የመንግስት ፖሊሲና የትኩረት አቅጣጫ ማነስና በዘርፉ የሚደረገው ኢንቨስትመንትም ውስን መሆኑን ይጠቀሳሉ ።
በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶችም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰሩት ስራ፣ ለምርምር የሚያወጡት ወጪና ዘርፉን ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት አናሳ መሆን ሌላው ችግር መሆኑን አቶ ሳኒ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹የግብይት ስራውን ለማዘመንም የሚሰራው ስራ አነስተኛ መሆኑ የቡናችንን የተለየ ባህርይ በዓለም ገበያ ላይ አስተዋውቀን ከመሸጥ ይልቅ የዓለም ገበያ ለቡናችን የሰጠንን ዋጋ ተቀብለን የምንሸጥ እንድንሆን አድርጎናል›› በማለት ያስረዳሉ።
‹‹ከዚህ አንጻርም የአገር ውስጥ ገበያው ለቡና ዕድል ሆኖ ነው የቆየው›› የሚሉት አቶ ሳኒ፣ ‹‹በአገራችን ቡና የሚሸጥበት ዋጋ ወደ ውጭ ከሚላክበት ይበልጣል፤ የቡና አቅርቦቱ ደግሞ የአገር ውስጥን ፍላጎት ሸፍኖ የውጭውንም ለመሸፈን የማያስችል መሆኑን ያሳያል፤ ወደፊት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እንደ እቅድና አቅጣጫ የአገር ውስጥ ገበያውን እንደ ስጋት ከመቁጠር ይልቅ ምርታማነትን በማሻሻል፣ በቡና የሚሸፈነውን መሬት በማስፋት፣ አቅርቦታችንን በማሳደግ፣ የአገር ውስጥ ገበያውን በመሸፈንና የውጭ ገበያ መጠናችንን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል›› ብለዋል።
የቡና ምርታማነትን ማሳደግ ለማንም የማይተው የቤት ስራ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከመድረኩ ያገኙትንም ግብዓት በመጠቀም ስራቸውን መጀመር አንዳለባቸው እሙን ነው። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ናት የሚለው አባባል ከአባባልነት ማለፍ የማይችል ይሆናል።
እፀገነት አክሊሉ