የንግድ ሰንሰለትን በማሳጠር ገበያን ማረጋጋት

ዜና ሐተታ

ሀገራቸውን የሚወዱ ሰዎች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ለሀገራቸውና ለወገናቸው ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ፤ ለሕዝባቸውም ይቆረቆራሉ፤ የሀገራቸውንና የዜጎቻቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ይታትራሉ፤ ይተጋሉ።

ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ የህንድ ዜጎች አማራጭ ካላጡ በስተቀር ከራሳቸው ሀገር ምርቶች ውጭ የሌላ ሀገር ምርትም አይጠቀሙም። ይሄውም ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለውን የሀገራቸውን ገበያ ለራሳቸው ምርት መገበያያ እንዲሆን አስችሏቸዋል።

በእኛም ሀገር የዚህ አይነት አሠራርን ለመዘርጋት በመንግሥት በኩል በርካታ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ሰው ሠራሽ የሆነ የዋጋ ንረትን ለመፍጠር የሚታትሩ ደላሎች እና ለሕዝቡ ርህራሄ የሌላቸው ሥነምግባር የጎደላቸው ነጋዴዎች እሴት የማይጨምር የንግድ ሰንሰለት በመፍጠር ሕዝብን የመበዝበዝ ተግባር ሲፈጽሙ ይታያል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ይሠራል። ከዚህም ውስጥ አንዱ የቅዳሜና እሁድ ገበያ፣ ኤግዚቢሽን እና ባዛር፣ የእንጀራ እና ዳቦ መጋገሪያዎች እንዲሁም የተለያዩ መዋቅሮችን በመዘርጋት የኢኮኖሚ አሻጥር የሚሠሩ ግለሰቦችን ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ ተጠቃሽ ነው።

ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ ይግዙ የንግድ ሳምንት ለአምስት ቀናት ማካሄዱ ይታወሳል። “የኢትዮጵያ ምርት ለብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ያካሄደው መርሃ ግብር ሲዘጋ እኛም በቦታው ተገኝተን የነጋዴዎችን ሃሳብ ተቀብለናል።

አቶ አሰፋ ሹምባጋ በቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ምርቶች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ናቸው። በኤግዚቢሽኑ ላይም ንግድ ቢሮ ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ ጋብዟቸው እንደተገኙ ይናገራሉ።

በኤግዚቢሽኑ ላይ ይዘዋቸው የቀረቡ ምርቶች ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፋቸው ለቀጣይ ቋሚ ደንበኛ ሊሆኑ የሚችሉ ገዥዎችን መተዋወቃቸውን ይናገራሉ። የምርት እና የሽያጭ ቦታቸው እምብዛም በሰው ዕይታ ውስጥ የሚገባበት ቦታ ላይ ባለመሆኑ እንደዚህ አይነት ኤግዚቢሽኖች በአንፃራዊነት የዋጋ ቅናሽ ያለባቸውን ምርቶች ለሕዝቡ እንዲቀርብ ከማድረግ ባለፈ እንደልባቸው ተሯሩጠው ገዥን ማግኘት ለማይችሉ አካል ጉዳተኞች የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ይናገራሉ።

የንግድ ሰንሰለትን በመቀነስ ሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን በቀጥታ ከአምራቹ እንዲያገኙም ዕድል ይፈጥራል ይላሉ። የኢትዮጵያ ምርት በጥንካሬ ብርቱ እና በዋጋ ከውጭ ከሚመጣው በእጅጉ የቀነሰ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ምርት እንዲገዙም ጥሪ አቅርበዋል።

በወፍራም ድምፁ እና በተጫዋች አንደበቱ ገዥዎችን እያዝናና ሲሸጥ ያገኘነው የአትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴው አቶ ቦጋለ ናደው ምርቶቹን ቀጥታ ከገበሬው እንደሚያመጣ ይናገራል። በምርቶቹ መካከልም የሚገባ ደላላ ባለመኖሩ በምርቶቹ ላይ ከ 15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ እንደሚያደርግ ያብራራል።

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ አምስት የመሸጫ ቦታ እንዳለው የሚገልፀው ነጋዴው፤ በኤግዚቢሽን ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ይገኛል ይላል። ይህም ለነጋዴው የተሻለ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር ከማድረጉም ጎን ለጎን ገዥው የሚፈልገውን ነገር በአንድ ቦታ እንዲሸምት የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጸው።

የገሊላ ባልትና ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ የሆነችው የሺ መኮንን በበኩሏ ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመምጣት በኤግዚቢሽኑ ላይ መገኘቷን ትናገራለች። በኤግዚቢሽኑ በርካታ ሰዎችን የመተዋወቅ እድል እንዳገኘች፤ የሷን አይነት ምርት የሚያመርቱ ሰዎች ያሏቸውን ምርቶች በማየት ልታሻሽል የሚገባትን ነገር እንድታስተውል እንደረዳት ታብራራለች።

ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውንም ስትገልፅ በከተማው ላይ ያልተለመዱ የአቮካዶ ፍሬ ዱቄት፣ የግብጦ ዱቄት እና የወይራ ሻይ ቅጠል ምርቷን በማስተዋወቅ አዳዲስ ደንበኞች በማፍራት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንዳስቻላት ትገልፃለች። የንግድ አሻጥር እንዳይኖር በማድረግም ኤግዝቢሽኑ የጎላ ሚና አለው ትላለች።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የኮሙዩኒከሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሸናፊ ብርሃኑ እንደሚናገሩት፤ የኤግዚቢሽኑ ዓላማ የኢትዮጵያን ምርት በማስተዋወቅ የዋጋ ንረት እንዲቀንስ ከማድረግ ባሻገር አምራቾችን ማበረታታት ነው።

በዚህም ረገድ ኤግዚቢሽኑ የታሰበለትን ራዕይ በማሳካት ረገድ አበረታች ውጤት እንደታየበት ገልጸው፤ 185 ነጋዴዎች፣ ከ5ሺህ በላይ ሸማቾች እና ጎብኚዎች ተገኝተውበታል ነው ያሉት። 20 በመቶ ቅናሽ ያለው በመሆኑ በርካታ ሽያጮች እንደተካሄዱበትና በስፍራውም የተገኙት አምራቾች በመሆናቸው የንግድ ሰንሰለት ያጠረበት ግብይት እንደተካሄደ አስረድተው፤ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You