
አዲስ አበባ፡– በአዲሱ አዋጅ የምርጫ ተወዳዳሪ እጩዎች የፋይዳ መታወቂያ መያዝ እንዳለባቸው ግዴታ ሆኖም ተቀምጧል ሲል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
የፖለቲካ ፖርቲ ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ በተመለከተ በ26 የአዋጅ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን አስመልክቶ፤ በትናንትናው እለት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ በማብራሪያቸው፤ በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ውስብስብ የሆነውን የምርጫ ሂደት በቴክኖሎጂ በማገዝ ግልፅ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ምርጫ ማካሄድ እንዲያስችል እጩዎች የፋይዳ መታወቂያ መያዝ እንዳለባቸው ግዴታ ሆኖም ተቀምጧል ብለዋል።
አዋጁ ከመሻሻሉ በፊት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን የተናገሩት ሰብሳቢዋ፤ ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ካለው ጊዜ አንጻር ውስን አንቀጾች ላይ ብቻ ማሻሻያ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
በሀገሪቱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻል ሴቶችና አካል ጉዳተኞችም በምርጫ ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ማሻሻያ ከተደረገባቸው የአዋጅ ድንጋጌዎች ውስጥም የምርጫ አስፈፃሚዎችና ቅሬታ ሰሚዎች ብዛት፣ የመራጭነትና የእጩነት እድሜ በተመለከተ፣ ከሴቶችና አካል ጉዳተኞች የድጋፍ ፊርማ ቁጥር ጋር በተያያዘ የተሻሻሉ ድንጋጌዎች መኖራቸውን አብራርተዋል።
የእጩ ተወዳዳሪዎች የድጋፍ ፊርማ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተከልክሎ የነበረው በአዋጅ ቁጥር 1235/2013 መሆኑን ተናግረው፤ አሁን በተሻሻለው አዋጅ የድጋፍ ፊርማ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በአዋጁም የሴቶችንና አካልጉዳተኞችን ለበለጠ ተሳታፊ ለማድረግ የድጋፍ ፊርማ ዝቅ የተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
በምርጫ ጣቢያ የሚመደቡ አስፈጻሚዎች ቁጥር የተገደበ መሆኑ በአስፈጻሚዎች ላይ ጫና መፍጠሩን አስታውሰው፤ ቦርዱ በምርጫ ጣቢያዎች የሚኖረውን የመራጭ ቁጥርና ሁኔታ በማገናዘብ እንደ አስፈላጊነቱ የሚመድብበት ሁኔታ በተሻሻለው አዋጅ መካተቱን ጠቁመዋል።
በተሻሻለው አዋጅ መሠረት አንድ ሰው ለመምረጥና በእጩነት ለመቅረብ እድሜው 18 ዓመት የተመራጮች ከ21 ጀምሮ እንዲሞላው የሚገደደው በድምጽ መስጫ ወቅት ነውም ብለዋል፡፡
ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንባቸው የደነገጉትን ከአባላት የሚሰበሰብ መዋጮ አስመልክቶም፤ 20 በመቶ ከሚሆኑት አባሎቻቸው የደነገጉትን የገንዘብ መጠን መሰብሰብ እንደሚገባቸው በአዋጁ እንደተደነገገ አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ለፓርቲ መዋጮ ከሰራተኞ ው የሚቆረጥ ገንዘብ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
አንድ ፓርቲ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ በቀድሞ አዋጅ ከአምስት ክልሎች አባላት ሊኖረው ይገባል የሚለው መስፈርት በተሻሻለው አዋጅ ወደ ሰባት ክልሎች ከፍ ተደርጓል። ይኸውም የሆነበት ምክንያት የክልሎች ቁጥር ከፍ በማለቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገራዊ ፓርቲው መሠረት ካደረገበት ክልል 40 በመቶ አባላትን ማሰባሰብ ይኖርበታል፡፡ ከሌሎች ስድስት ክልሎች ደግሞ 60 በመቶ አባላት ሊኖሩት እንደሚገባም አዋጁ የሚያስገድድ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በእዚህ ማሻሻያ ውስብስብ የሆነውን የምርጫ ሂደት በቴክኖሎጂ በማገዝ ግልፅ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ምርጫ ማካሄድ እንዲያስችል እጩዎች የፋይዳ መታወቂያ መያዝ እንዳለባቸው ግዴታ ሆኖም ተቀምጧል ብለዋል።
በአጠቃላይ በተሻሻለው አዋጅ ወደ 26 አንቀጾች ማሻሻያ እንደተደረገባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ማሻሻያው ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማነት የራሱን ድርሻ እንደሚጫወት ተጠቅሷል፡፡
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በነበሩ ክፍተቶች ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ እና ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመነሳት የአዋጅ ማሻሻያ መደረጉን ገልፀው፤ ማሻሻያውም ከሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ አስታውቀዋል፡፡
በመክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም