የአፍሪካን ዕድገት ለማፋጠን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን መፍጠር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- የአፍሪካን ዕድገት ለማፋጠን በመተማመን ላይ የተመሠረተና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በአፍሪካ ኢንቨስትመንት ሴንተር የተዘጋጀው 3ኛው የአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የአፍሪካን ዕድገት ለማፋጠን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ኢንቨስትመንት አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባት ያስችላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ቀደም ሲል ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ በነበሩት ባንክ፣ ቴሌኮም እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስተሮች እንዲሰማሩ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል። ይህም የሀገራትን ትብብር ለማጠናከር እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ከመሳብና መሠረተ ልማት ከማስፋፋት ባለፈ መተማመን እና የጋራ እሴትን ማጎልበት ላይ አበክራ እንደምትሠራ አስታውቀዋል።

አፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የሰው ሀብት እንዳላት ገልጸው፤ ወጣቶችን በማስተማር እና በማበረታታት የአፍሪካ የቀጣይ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የአፍሪካን እድገት አካታች ለማድረግ በአህጉሪቱ ያለውን አቅም መጠቀም እና መተማመንን የሚያጎለብት ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን መፍጠር እንደሚገባ ጨምረው ገልፀዋል።

አፍሪካውያን ትብብራችንን በማጠናከር እና ተቋማዊ አቅማችንን በማጎልበት ኢንቨስትመንትን መሳብ ከቻልን ሁለንተናዊ ዕድገት ማምጣት እንችላለን ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአፍሪካን የንግድ ትስስር ለማጠናከር፣ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ እና የእሴት ሰንሰለት ልማትን የማጎልበት ዓላማ የያዘውን አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስትራቴጅ ማጽደቋን አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል ሊቀመንበር አብዱልናስር ተርኪ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትና ትስስራቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።

አፍሪካ በሰው ሃይል እና በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች አህጉር መሆኗን ገልጸው፤ ይህንን ጥቅም ላይ ለማዋል ኢንቨስትመንት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ጉባዔው አዳዲስ የገበያና የፋይናንስ እድሎችን ለመፍጠር፣ ድንበር ተሻጋሪ ንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ እና በየአካባቢው ያሉ የገበያ እድሎችን ለማስገንዘብና የአፍሪካን ገፅታ አጉልቶ ለማሳየት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በጉባዔው የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዘርፉ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You