ኢትዮጵያውያን በተላላኪው ትህነግ፣ አሜሪካና አንዳንድ ምእራባውያን መንግሥታት በቅንጅት የተከፈተባቸውን የተቀናጀ ጦርነት በድል ለመወጣት በጦር ግንባር እየተፋለሙ ናቸው:: ድሎችም እየተመዘገቡ ናቸው::
የጦር ግንባር ውጊያው ተጠናክሮ በቀጠለበት በዚህ ወቅት አሜሪካ አሸባሪው ትህነግ የሚታወቅበትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመፈብረክና ማሰራጨት ላይ ተጠምዳለች:: አሜሪካ የወረዳ ወርዳ የትህነግን የክፋት ድርጊት ተሞክሮ ብላ ሀሰተኛ መረጃ በመፈብረክና በማሰራጨት ሀገሪቱን የፈረሰች ሀገር ያህል አድርጋ አለምን እያሳሳተች ትገኛለች::
አዎን! ሀሰተኛ መረጃ ትህነግን የተወሰነ ርቀት አስጉዞታል፤ ጥቂት የማይባሉ የአማራ ክልል ከተሞችን እንዲቆጣጠር መልካም አጋጣሚ ፈጥሮለታል:: ይህ የትህነግ የጦርነት መንገድ ኢትዮጵያውያን አሁን ነቅተውበታል:: የትህነግ ሰርጎ ገቦችና ጀሌዎች ለሚነዙት የመጡ መጡ የሽብር ወሬ ቦታ መስጠት ትተዋል:: ህዝቡ ከተማውን፣ ቀዬውን ከሰርጎ ገቦችና ከትህነግ ጀሌዎች እየጠበቀ ይገኛል::
አሜሪካ ግን የአርማ ቅብብል ያህል ይህን እየከሸፈ ያለ የትህነግ መንገድ ቀጥላበታለች:: የትህነግ የበሬ ወለደ ዘመቻ አሁን በአሜሪካና ተባባሪዎቿ እየተፈጸመ ነው:: አይደለም በአዲስ አበባ በዙሪያ ምንም አይነት ስጋት በሌለበት ሁኔታ አዲስ አበባ በትህነግና ሸኔ ታጣቂዎች ተከባለች እያለች የነዘችው ነጭ ውሸት የሚያመለክተውም ይሄንኑ ነው::
ሀሰተኛ መረጃው የአሜሪካና ተባባሪዎቿ ሰሞነኛ ዜማ ሆኗል:: አንዱ ዘፈኑን ያወጣል፤ ሌላው እያጨበጨበ ዘፈኑን እየተቀበለ ድምቀት ይሰጣል:: ትህነግ በጀሌዎቹ መጡ መጡ እያሰኘ ህዝብን እያስበረገገ ከተሞችን በቀላሉ ሲያዝ እንደ ቆየ ሁሉ አሜሪካም የሕወሓትና የሸኔ ጦር አዲስ አበባን ከቧታል ለቃችሁ ውጡ እያለች የውጭ ዜጎችን ማሳሰብ ከጀመረች ሳምንታት ተቆጥረዋል:: አዲስ አበባ መከበብ አይደለም ለመከበብ ባልታሰበችበት ነው
ተከባለች እያለች ያለችው፤ ይሄው ሳምንታት አልፈውም ከባቢ የለም::
አሜሪካን ያህል ሀገር በእዚህ አሳፋሪ ተግባር ውስጥ መገኘት አልነበረባትም፤ ግን ተገኘች:: አሜሪካ አሁን ‹‹በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ›› አይነት የሆነች ሳይመስላት አልቀረም:: አዲስ አበባ ምንም ባልሆነችበት ሁኔታ አለም አቀፉ ማህበረሰብ አዲስ አበባና ኢትዮጵያን የስጋት ቀጣና አድርጎ እንዲመለከት ብትሰራም ሰሚ አላገኘችም:: እሷ እንደምትለው ሳይሆን አዲስ አበባ እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ ሰላም ናት::
አሜሪካ አዲስ አበባ ተከባለች እያለች ነጋ ጠባ መግለጫ ብታወጣም፤ በተከፋይ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኗ በኩል ብታስለፈልፍም እሷ እንደምትለው አዲስ አበባ ምንም የታየባት ለውጥ የለም:: የውጭ ሀገር ዜጎች ( አማሪካውያን ቱሪስቶችን ጨምሮ ) አዲስ አበባ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን እየመሰከሩ ናቸው::
የአዲስ አበባን ተከባለች ሀሰተኛ ወሬ የሰሙት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ‹‹አዲስ አበባ የተከበበችው በጀግኖች ልጆቿ ነው›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋታል:: የአሜሪካን የሀሰት መረጃ ይዞ ከኢትዮጵያ ለመውጣት ብሎ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ያጨናነቃት ተጓዥም የለም::
ሀገሪቱ ግን አሁንም ማሟረቷን ቀጥላበታለች:: ይህ ሟርት ነው የሚባለው፤ ሌላ ስም አይሰጠውም:: አዲስ አበባ ተከባለች ስትል የቆየችበትን የትህነግ አይነት የመጡ መጡ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሽብር ተግባር አሜሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ ፣ በኢትዮጵያ ያሉትም በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ነጋ ጠባ ከማሳሰብ አልፋ፣ ዜጎቿ( ዜጎቼ የምትላቸው ጭምር)ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ እየወተወተች ትገኛለች:: በስልክ እየደወለች እየሳሰበችም ነው::
በእርግጥ ጥቂት እግር እግርዋ ስር የሚሉ የዘፈኗ ታዳሚዎች ይህን ዘፈን እየደጋገሙ እያሉ ናቸው፤አብረው እየተወዛወዙም ይገኛሉ:: አሜሪካ ዘፈኑን ስታወጣ የእርዳታ ድርጅቷ ዩኤስ አይድ እያጨበጨበና እየጨፈረላት
ነው:: ድርጅቱ ሰራተኞቹን ከኢትዮጵያ እንደሚያስወጣ አስታውቋል፤ ድርጅቱ የዘፈኑ ገጣሚ አልያም ዜማ አውጪ እንደመሆኑ ይህን የመንግሥቱን እርምጃ ለመተግበር ቀዳሚ መሆኑ አይደንቅም:: ድርጅቱ በቅድሚያ ግማሽ የሚሆኑትን ሰራተኞቹን እንደሚያስወጣ የተቀሩትን ደግሞ በሂደት አንደሚያስወጣ አስታውቋል:: ይህን እርምጃው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰችው ተውኔት ተዋናይነቱን ፊት ለፊት በመቆም በሚገባ ተውኖታል ያሰኛል::
ወደ አሜሪካ ልመለስ። ዩኤስ ኤይድ ብዙ ነገር አበለሻሽቶ አላማውን አሳክቶ ነው የሚወጣው:: አንዱን አላማቸውን ያሳኩ መስሏቸው ነው መውጣትን የመረጡት ብሎ ማጠቃለል ይቻላል:: አሜሪካ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር ፣ሁሌም እርስ በርስ የምትባላ ኢትዮጵያ እንድትኖር ነውና የምትፈልገው። ይህ እንዲሆን እርስ በርስ በማባላት የሚታወቀውን ትህነግ አሁን ያን ለማድረግ ትንሳኤውን ያረጋገጠና ብዙ መንገድ የሄደም አርጋ ሳትቆጥረው አልቀረችም፤ ከዚህ በኋላ ነገሮችን በራሱ ያደርጋል ብላ አስባም ይሆናል ዋና የአሸባሪውን ድርጅት መደገፊያ መሳሪያዋን ዩኤስ ኤይድን ወደ ማሳሳት የገባችው::
እውነታቸውን ነው ገንዘብና የተለያየ ሀብት እየዘረፈ ስለሆነ አቅሙን አጎልብቷል፤ አሁን ተንቤን የነበረው ትህነግ አይደለም:: ከአማራ ክልል የዘረፈው ሀብት ሲታሰብ ይህን መጠርጠር ስህተት አይሆንም:: እናም የዩኤስ ኤይድ ከኢትዮጵያ መውጣት የመጣበትን አላማ ያሳካ መስሎት የወሰደው እርምጃ እንጂ ሊያስወጣው የሚችል ሌላ ከጸጥታ ጋር የተያያዘ ምክንያት ኖሮ አይደለም:: እነሱ የፈጠሩት የጸጥታ ችግር ወላፈኑ አስፈርቷቸውም ሊሆን ይችላል::
የሌሎች ሀገሮች ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን የአሜሪካን ያህል በሀሰተኛ መረጃው የተሸበሩ አይመስለኝም:: መሬት ላይ ያለው እውነታም አሜሪካ እንዲወሰድ ወደ አሳሰበችው እርምጃ የሚያስወስድ አይደለም:: አሜሪካ ማሳሰቢያውን ከለቀቀች ሳምንታት አልፈዋል፤ ተላላኪዎቿም ያሉት በሩቁ ነው::
ዜጎቿም ሆኑ ዜጎቼ የምትላቸው መግለጫውን ከቁብም አልቆጥር ቢሏት ሰሞኑን ደግሞ ዙሩን ማክረር ያስችላል ያለችውን ዘመቻ ጀምራለች:: ምንም የተለየ የጸጥታ ችግር ያላዩት ዜጎቿ / የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ጭምር/ አርፈው ቢቀመጡም ኤምባሲው በየአድራሻቸው ስልክ እየደወለ በአስቸኳይ ለቃችሁ ውጡ የሚል መልእክት እያስተላለፈ እረፍት እየነሳቸው ነው:: ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ ከሌላቸውም ብድር እንደሚሰጣቸው እየገለጸ ነው:: ይሄ የጸጥታ ችግር አለ ሲሉ የቆዩበትን የሀሰት መረጃ የመፈብረክና የማሰራጨት ስራ ዙር ከማክረር ውጪ ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል::
አዎን አሜሪካ ዙር ማክረር ውስጥ ገብታለች:: ይህን ማሳሰቢያዋን ተከትሎ በአየር ማረፊያ መጨናነቅ እንዲፈጠር በማድረግ ዘፈኗን ለማድመቅ እየሞከረች ነው:: ያኔ ደግሞ ወኪሎቿ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን በማሰማራት አየር መንገድ በመሄድ አሜሪካውያን በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ችግር ውስጥ ወድቀዋል ተብሎ ይለፈፋል:: የአሜረካን ዘፈን ለማድመቅ ይሰራል:: ከዚያ ደግሞ ዜጎቼን ራሴ ለማውጣት እገባለሁ ትል ይሆናል::አትልም ተብሎ አይታሰብም፤ ምክንያቱም አሜሪካ ናት፤ ይህ ደግሞ ሌላው የሀገር ሉአላዊነትን መዳፈር ይሆናል::
አሜሪካ በሌለ ችግር አቧራ መቀስቀስ ውስጥ የገባችው ከአህያ የዋለችው ጊደር ምን ተምራ ትመጣለች እንደሚባለው ነው፤ አሜሪካኖች ክፉ ለመስራት የማይመለሱ ቢሆኑም፣ ከሀሰተኛ መረጃ ቆማሪው ትህነግ መዋላቸው ሀሰተኛ መረጃ ፈጣሪና አሰራጭ አላደረጋቸውም ተብሎ አይወሰድም::
ይህ አካሄድ ምንም ይሁን ምን እኔ ስዘፍን አጅቡኝ አጨብጭቡልኝ፣ ከበሮ ደልቁልኝ እንደ ማለት ይቆጠራል፣ ከእኔ ተከትላችሁ በሉ ብሎ ነገር የትህነግ መንገድ ብቻ አልሆነም፤ አሜሪካም የወረዳ ወርዳ ቀጥላበታለች:: ወይም የመንገዱ ባለቤት ማናቸው እንደሆኑ ማን እንደ ኮረጀ አሁንም የምንገምተው ቢኖርም፣ ወደፊት የምናውቀው ቢሆንም አዋጭ መንገድ ግን አይደለም፤ የሚያዋጣው የሰላም መንገድ ፣የእውነት መንገድ ነው::
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ኅዳር 15/2014