ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የስልጣኔና የነጻነት ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በተለይ በነፃነት ተጋድሎ ታሪኳ ከራሷም አልፎ የብዙ አፍሪካውያንና ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት በመሆን ትታወቃለች። ኢትዮጵያ የነካትን የምታቃጥል እቶን እሳት፤ ኢትዮጵያዊነትም ኃይልነት እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል። ኢትጵዮዊነት ነጻነትና ኩራትም ጭምር ነው። ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት፣ አንድነት እና ትግዕስት ነው።
ኢትዮጵያ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በአንድነት በመመከት አንፀባራቂ ታሪክ አላት። ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ፈተናዎች የተሻገረችው በልጆቿ ትግል ነው። ልጆቿ በታሪክ የሚታወቁት አገራቸው ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች ሲጠብቁና ደማቸውን አፍስሰው የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ ነው።
በበርሊን ጉባኤ የአውሮፓ ሀያላን አፍሪካን ለመቀራመት ሲስማሙና ሲከፋፍሉ ነፃነታቸውን ጠብቀው ለመኖር ከቻሉ ሁለት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች። በየዓመቱ በዓለም የታሪክ ድርሳን ወርሃ የካቲት ሲወሳም የጥቁሮች የነፃነት ተጋድሎና ድል ሚዛን ደፍቶ ይታያል። የዚያ ዘመን ጥቁሮች የነፃነት ድል ጉልላት ደግሞ አድዋ ነው። አድዋ የቅኝ ገዥዎች አከርካሪ የተሰበረበትና መላው የዓለም ጥቁር ክብር የተቀዳጀበት ድል ነው።
ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ የውጪ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማንበርከክ ብዙ ሙከራዎች አድርገው ከሽፎባቸዋል። ይህንን ሽንፈት ለማካካስ ሲሉ ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስበው ኢትዮጵያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማንበርከክ ተደራጅተው የመጡበት የአድዋ ጦርነትም በተባበረው የኢትዮጵያውያን ክንድ ዳግም ተንኮታኩቷል።
ራይሞንድ ጆናስ፣Raymond Jonas ‹‹The Battle of Adwa››በሚለው የመጽሐፉ መግቢያ ላይ‹‹የአድዋ ድል በተፈጥሮ ነጮች አሸናፊዎች፣ጥቁሮች ደግሞ ተሸናፊዎች የሚለውን ዓለም አቀፋዊ እምነት በአፍጢሙ የደፋ ክስተት ነው። አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን መላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ያኮራ ታሪካዊ ድል ነው። የጥቁር ህዝቦች ነጻነት እኩልነትና መብት አብሳሪ የተስፋ ጎሕ ነው›› ሲል ጽፏል።
አለምን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያንቀጠቀጠው የአድዋ ድል በኢትዮጵያውያን የጋራ ተጋድሎ የተገኘና ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ፣ የሚያፋቅርና የሚያስተሳስር ድል ነው።ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ያበረከቱት ወደር የለሽ ስጦታ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ህዝቦች ነፃነት የታገለና ያታገለ የለም ማለት ማጋነን አይሆንም። ወራሪውን የጣሊያን ኃይል ታግላ ነፃነቷን በማስመለስ ያስመዘገበችው ድል በአህጉሪቱ ለነፃነት ሲደረግ የነበረውን ትግል በማቀጣጠል በርካታ ሀገሮች ነፃነታቸውን እንዲጎናፀፉ ምክንያት ሆኗል።
የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ለአፍሪካውያንና የጥቁር ዘር ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ግዛትና ከዘረኝነት መውጣት እንደ ችቦ መብራት ነው።በሃይማኖትና በፖለቲካ የጭቆና ቀንበር ውስጥ ወድቀው ፤እንዴት ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት እንደሚችሉ ሲያስቡና ሲያሰላስሉ ለነበሩ በባርነት የተሸበቡ ጥቁሮች የነፃነት መንገድን ያመላከተ ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያንን አህጉራዊ ድርጅት ከማዋለድ ጀምሮ በማሳደግና ወደ ህብረትነት እንዲቀየር በማድረግ ታሪካዊ ድርሻዋን ተወጥታለች።እንደ መስራችና እንደ ድርጅቱ ዋና መቀመጫነቷ በየትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ወቅት በአፍሪካዊ ወንድማማችነትና መንፈስ ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ጭቆናና በደልን፣ግፍና ብዝበዛን በመቃወም አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋለች። ዛሬም እያደረገች ነው።
በተለያዩ ወቅቶች በአህጉሪቱ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በመረጋጋት በመተካት፣ የተጎዱትን በማቋቋምና የተቸገሩትን በመርዳት በማብረድ ረገድ ተሳትፎዋ ቀላል አይደለም።ይህ ተሳትፎዋ በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር የተሞካሸ ነው።
ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ዛሬም በሁሉም መስኮች የህብረቱ ውሳኔዎች ተገዥ በመሆን የአፍሪካውያንን ፍላጎት በየዓለም አቀፍ መድረኩ እንዲንፀባረቅ እያደረገች ትገኛለች። ለሰላምና ለነፃነት በምትሰጠው ዋጋ የላቀ መስዕዋትነት እየከፈለችም ጭምር ነው።
በተለያየ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡና በተለያዩ መድረኮች ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር የሚያደርጉ መሪዎች ሲናገሩ እንደሚደመጠውም፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች እናትናት፤ የነጻነታችን ምልክት /Symbol/ ናት።
በእርግጥም ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ነጻነትና መብት፣ለሰብአዊ ክብራቸውና እኩልነታቸው የከፈለችው ዋጋ ፍሬን ማፍራት አልተቸገረም።ይሁንና በአፍሪካ ምድር የቅኝ ግዛት አገዛዝ በይፋ ካበቃ ከ60 ዓመታት በኋላም በአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገሮች አሁን ድረስ ቅኝ ግዛት አልሞተም።
አገራቱ ነፃነትና ሉዓላዊነትን የተቀዳጁበትን ቀን አመት እየጠበቁ ቢያከብሩም ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መላቀቅ የሆነላቸው አይመስልም።ዋጋ የከፈሉለትን ነፃነት መሆን ባለበትና በሚገባው ልክ ሲያስጠብቁ አይታይም።ይህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የውጭ ኃይሎች ፍላጎትና ጫና መጠቀሚያ ብሎም መጫወቻ እያደረጋቸው ይገኛል።
አንዳንድ ምዕራባውያን አገራትም ከትናንት የቅኝ ግዛት ልክፍት መላቀቅ አልሆነላቸውም። በአሁኑ ወቅትም በቅኝ ግዛት በትር አፍሪካ ውስጥ የመቆየታቸው ዕድል ለማመቻቸትና ጊዜያቸውን ለማራዘም በሁሉም አቅጣጫ በተባበረ የሴራ ገመድ ተሳስረው አገራትን ጠልፎ ለመጣል በመውተርተር ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ አገራትም በተለይ ወራሪውና አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀም በይፋ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት በመክፈቱ መንግስት የህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ መጀመሩን ተከትሎ ሙሉ ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ ላይ አድርገዋል።
አለም ኢትዮጵያን በተሳሳተ መንገድ እንዲገነዘብ የማስጨነቅ፣ የመክሰስ፣ የመወንጀል ዘመቻን ተያይዘውታል። ከዚህም አልፎ የኢትዮጵያን ህዝብ የማሸበር ድርጊታቸውን ተያይዘውታል። በአንዳንድ አገራትና በሌሎች መንግሥታት ላይ የለመዱትን የአጎንባሽነት እና የታዛዥነት ስነልቦና ብሎም ተግባር ኢትዮጵያ ምድር ላይ ካልተመለከትን እያሉ ናቸው። የትናንት ታሪክን ረስተው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እጁን እንዲሰጥ ሲሯሯጡ እየታዘብን ነው።
የእነዚህ ምእራባውያን ሃይሎች ሴራ በስግብግብነት ቅኝት የተቃኘ ነው። ይህንን ብርቱ ፍላጎታቸውንም የሚያሳካላቸው በስግብግብነቱ የታወቀውና ለገንዘብ ሲል ወንድሙን ከመግደል የማይመለሰው አሸባሪው ሕወሓት መሆኑን ተገንዝበዋል።
አሸባሪው ቡድን ለአገርና ለህዝብ ግድ እንደሌለው ለገንዘብ ሲል የማይፈፅመው ሴጣናዊ ድርጊት እንደሌለ በእጅጉ በመረዳታቸውና በአልጠግብ ባይነት አብሯቸው የኢትዮጵን ሀብት ሲዘርፍና በውጭ ባንኮች ሲያከማች በማየታቸው ወደ ፈለጉት አቅጣጫ የሚያደርስ ፈረሳቸው አድርገውታል።
ኢትዮጵያውያን በአንፃሩ የነጻነት መንፈስ በፈጠረው ወኔ የአባቶቻቸው ልጆች መሆናቸውን በአግባቡ በማስመስከር ላይ ተጠምደዋል። ኢትዮጵያ ታሸንፍ ዘንድ ፣በህዝባዊ አደራ የሞትና የሽረት ተግዳሎ እያደረጉም ይገኛል።በወጉ ተደራጅተው፣ነቅተውና ታጥቀው በወያኔና በግብራበሮቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰዱም ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ መንግሥት በሁሉም መንገድ ሉዓላዊነት የሚያስከብርና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ እንደማይሰጥና የትኛውንም የእጅ ጥምዘዛ እንደማይቀበል በተግባር ማሳየቱም የቅኝ ግዛት እሳቤ የተቆራኛቸው ምእራባውያን አገራት እና መገናኛ ብዙሃን ከማስገረምም በላይ አስደንግጧቸዋል።ይህም ከመቼውም ጊዜ በተለየና በተቀነባበረ መልኩ እንዲፍጨረጨሩ እያደረጋቸው ይገኛል።
ስመጥር የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ምሁራንና ግለሰቦች እንደሚስማሙበትም፣ ምእራባውያኑ በዚህ መጠን ኢትዮጵያ ላይ መረባረባቸው ያለምክንያት አይደለም።ለዚህ ደግሞ ከሁሉ የገዘፉ አብይት ምክንያቶችን ማንሳትን ይቻላል።
ቀዳሚው ደግሞ ወያኔን ከመቃብር ማስነሳትና ታዛዥ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ማስቀመጥ ነው።ሌላኛው ደግሞ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ አባዱላ ገመዳ ከቀናት በፊት እንደገለፁት፣ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ጠንክራ ከወጣች አፍሪካም ትጠነክራለች ከሚል ስጋት የመነጨ ነው›።
ምንም እንኳን የምእራባውያኑ ሴራ እያደር በመጠን እየጨመረና መልኩን እየቀያየረ ቢጧጧፍም ኢትዮጵያ በአንጻሩ ዛሬም እንደ ትላንቱ ከራሷ ባሻገር በፀረ ቅኝ አገዛዝ፣ በፀረ ባርነትና በፀረ ዘረኝነት ተጋድሎ በአጠቃላይም በየትኛውም አውድ ለአፍሪካ ተምሳሌት መሆኗን እያስመሰከረች ትገኛለች።
የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን የነፃነት፣ በራስ መተማመን፣ለራስ ክብር መስጠት፣ራስን መቻል እንዲሁም የዉጭ ጭቆናን መቋቋም፣አቋምና አቅም አስተምሮትም በመላው አለም በሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችና የኢትዮጵያን ወዳጆ ተከታይ እያፈራ ይገኛል።
ይህ የነጻነት መንፈስና መነቃቃትም አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ቀንበር አላቆ ልጆችዋ በነጻነትና በእድገት ጎዳና እንዲገስግሱ የሚያደርግ መሆኑን የተረዱ በርካታ አፍሪካውያንንም እያስከተለ ነው። የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ታሪክ ጠንቅቀው የሚረዱና ለነፃነት ክብርና ቦታ የሚሰጡ ግለሰቦችም የምእራባውያኑን ጫና በመቃወም ድምጻቸውን እያሰሙ ናቸው።
በፓን አፍሪካኒስት ስሜት ግንባር ቀደም የ# NO MORE ሃሽታግ ዘመቻን በመቀላቀል፣ጠንካራ መልእክቶችን ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ በማስተላለፍ የምእራባውያን የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት የአፍሪካ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝቡና ለነፃነት የሚታገሉ አገራት ቁጥርም ከእለት አለት እየጨመረ መጥቷል።
በርካታ የአፍሪካ ዝነኛ ማህበረሰብ አንቂዎችም ፍልሚያውን ተቀላቅለዋል። ከእነዚህ መካከል ‹‹Futurical›› በሚል መለያ ስሙ የሚታውቀው ኡጋንዳዊው ዝነኛ አክቲቪስት አንዱ ነው። አክቲቪስቱ ከቀናት በፊት ለተከታዮቹ ያጋራው መልእክትም‹‹ሁኔታው አሁን ላይገባንና ልንደነቅ እንችላለን፣ነገር ግን ኢትዮጵያውያን አፍሪካን ጦርነት እየተዋጉልን ነው የሚል ነበር።
አሜሪካ ወደ አፍሪካ የመግቢያ በር በኢትዮጵያ በኩል እንደሆነ ጠንቅቃ እንደምታውቅና ኢትዮጵያን ዝም ማሰኘት ከተቻለ ሌላውን ከዋሽንግተን በሚሰነዘር አንድ ቃል እንደሚንበረከክ የገለፀው ዝነኛው አክቲቪስት፣ ‹‹ስለዚህ እኛ ማድረግ የምንችለው ቢያንስ ኢትዮጵያን መደገፍ ነው›› ሲልም የትብብር ጥያቄ መልእክቱን አጋርቷል።
ስመ ጥር የፓን አፍሪካ አቀንቃኞችም የነፃነት ትግሉን በይፋ ተቀላቅለውታል።የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው ማፖንጋ ጆሽዋ በዚህ ረገድ ቀዳሚ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ምልክት ስለመሆና አፅእኖት የሰጠው ጆሽዋ፣‹‹የአፍሪካ የነፃነት እናት የሆነችው ኢትዮጵያ በበረከተባት ጫና ብትዳከም አፍሪካ ያለጥርጥር ወደ ዳግም ቅኝ ግዛት ትገባለች ሲልም ነው››የገለፀው።
‹‹በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው የጣልቃ ገብነት ችግር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ችግር በመሆኑ አፍሪካዊያን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል››ያለው ምሁሩ፣አፍሪካዊያን ለነፃቸው መከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ሳያስገነዝብ አላለፈም።
በእርግጥ የዚህ ዘመን ተረኛ ፋሺስት ለመሆን የሚዳዳቸውና የፍላጎት ጫፍ የደረሱ አገራት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ተነስተዋል።ይሁንና እንደ ትናንቱ ሁሉ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን የአባታቸውን አደራ እንደማይበሉ እያስመሰከሩ ናቸውም ብሏል።
ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው በአንድነትና በወኔ በመነሳት በኢትዮጵያ ጉዳይ እንደማይደርደሩ እያስመሰከሩ ናቸው። አፍሪካዊቷ የቴሌቪዥን ሾው አዘጋጅ ዶክተር ሙምቢ ሲራካ እንዳሉትም፣በአፍሪካ ምድር ድሮም ክብሯን ሳታስደፍር የኖረችው ኢትዮጵያ ዛሬም ዳግም ነጮችን ድል እንደምታደርግ ጥርጥር የለውም።
ይሁንናን የኢትዮጵያ የነፃነት ትግል ከራስ አልፎ ለአህጉር ብሎም ለአለም የሚተርፍ እንደመሆኑ ከዚህም በላይ ተከታይና ብሎም ደግፊ ማፍራት የግድ እንደሚለው እሙን ነው። በተለይ አፍሪካውያን የነፃነት መርከብን መሳፈር የግድ እንደሚላቸውም ይታመናል።
በኢትዮጵያ የአንጎላ አምባሳደር ፍራንሲስ ጆዜ ዳ ክሩዝ ፣አፍሪካውያን የአገራቸውን ነፃነትና ሉዓላዊነት በየዓመቱ ቀን እየጠበቁ የሚያከብሩት ብቻ ሳይሆን ሁሌም የሚጠብቁትና ዘብ የሚቆሙለት ሊሆን እንደሚገባ ማሳሰባቸውም ለዚሁ ይመስላል።
በእርግጥ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በአሁኑ ወቅት የምእራባውያኑን ተጽእኖ ከመቃወምና ለባርነት አሻፈረኝ ከማለት ባሻገር ‹ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ወቅታዊ ችግር ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት በራሷ አቅም መፍታት ትችላለች የሚለውን ሃሳብም በሚያስደንቅ መልኩ እየተጋሩት ይገኛሉ።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኬንያ ለገቡት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንና ልዑካን ቡድናቸው‹‹ኢትዮጵያ ወቅታዊ የውስጥ ችግሯን ያለ ምንም ውጭ ጣልቃ ገብነት በራሷ መፍታት እንደምትችል መናገራቸውም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከቀናት በፊት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫም ይህንኑ አረጋግጠዋል። “አፍሪካዊያን ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ወቅታዊ ችግር በራሷ አቅም መፍታት ትችላለች የሚለውን ሃሳብ እየተጋሩት ነው፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካም እየሆነ መጥቷል” ነው ያሉት።
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ መላ አፍሪካውያንና የጥቁር ህዝብ እንዲሁም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ ሁሉ ለአገራቸው ሉአላአዊነት፣ ነጻነትና ክብር እንዲሁም ሁለንተናዊ እድገት በጋራ መቆምና መረባረብ የሚገባቸው ትክክለኛ ሰአት አሁን ነው። ኢትዮጵያ ግን ዳግማዊ የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት እየሆነች ትገኛለች።
ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው ማፖንጋ ጆሽዋ
ዶክተር ሙምቢ ሴራኪ
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014