ከማንም በፊት ኢትዮጵያ የሴት መሪዎችን አፍርታ በሴት መሪዎቿ ተዳድራለች። ከታችኛው የስልጣን መዋቅር ጀምሮ እስከ ላይኛው ድረስ ሴቶቻችን ያሉ ሲሆን፤ ሲሰጡት በነበረው አመራርም አገሪቷን በብዙ የታሪክ እርምጃዎች ወደፊት አራምደዋታል፤ እዚህም አድርሰዋታል።
ዛሬ ለሴቶች መብት እንቆረቆራለን የሚሉት አገራት አገር ሆነው በእግራቸው ሳይቆሙ ኢትዮጵያ ሴት መሪዎች ነበሯት። ይህ ከንግስተ ሳባ ጀምሮ አለም ያወቀው እውነት ነው። ዛሬም ድረስ ይህ ታሪክ እንደቀጠለ ነው።
“ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ነች” ሲባል በአንድ ስርአተ ፆታ አባላት ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም የሆነችው በሁለቱም ስርአተ ፆታ አባላት አማካኝነት ሲሆን፤ በሁለቱም በአለም ስመጥር ነች። በአትሌቲክ ኢትዮጵያ አለች፤ በጦር ሜዳ ጀብድ በኩል ኢትዮጵያ አለች፤ በአመራር በኩል ኢትዮጵያ አለች። በሁሉም በኩል ኢትዮጵያውያን ሴቶችም ወንዶችም አሉ።
እርግጥ ነው በብዙዎቻችን አእምሮ ውስጥ ጀብድ የፈጸሙ (ወይም የሚፈፅሙ) ሴቶች አይታወሱም፤ ወንዶች እንጂ። “ለምን?” ሁሉም ለየራሱ ሊመልሰው የሚገባ ጥያቄ።
የእኛዎቹም አልተዘመረላቸውም እንጂ፣ ባለፈው (ግንቦት 2020) የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ያበቃበት 75ኛ ዓመት ዕለት ሲከበር በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀብድ የፈጸሙ ስምንት ሴቶች እንደተዘከሩት (“ያልተነገረላቸው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀግና ሴቶች” በሚል ርእስ ለንባብ እንደበቃው) ሁሉ እኛም ስንትና ስንት እንስት ጀግኖቻችንን ባስታወስንና ውለታቸውን በከፈልን ነበር። ግና ምን ያደርጋል፤ የሴቶቹ ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ታሪክ ተረስቷል። ያልተመዘገበው እንዳለ ሆኖ የተመዘገበውም ካልተመዘገበው በላይ ተረስቷል።
ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጀግንነታቸው በጦር ሜዳ ብቻም አይደለም፤ በአትሌቲከስ ወይም በፖለቲካው መስክ ብቻም አይደለም፤ ባደገው አለም አሉ የተባሉ ሴቶቻችን ሁሉ በማስከንዳት አለምን ጉድ ያሰኙ ሴቶች ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያዊትዋ ፍሬወይኒ መብርሃቱ (የ«CNN» ጀግኖች 2019 ሽልማት አሸናፊዋ)ን መጥቀስ ይበቃል።
ልክ እንደ ስምንቱ (ቻይናዊቷ ቼንግ ቤንሁ፣ የህንድ ልዕልት እና የብሪታኒያ ሰላይ ነበረችው ኖራ ኢናያት ካሃን ፣ አልሞ ተኳሿ ሩሲያዊቷ ሊዩድሚል ፓቨሊቼንኮ ባሪክ (በአንድ ጊዜ 360 ጠላትን ዘርራለች)፣ ኒው ዚላንድ ተወልዳ አውስትራሊያ ያደገችውና በ”ነጯ አይጥ” ቅፅል ስሟ የምትታወቀው ናንሲ ዌክ፣ ትውልዷ በአፍሪካዊቷ ኮንጎ ሪፐብሊክ ሆኖ በልጅነቷ ወደ ፈረንሳይ ያቀናችው ጄን ቫያል፣ ትውልደ ኦስትሪያዋና መልከ መልካሟ ሄዲይ ላማር፣ በጎራዴና በመርዝ ጠላትን ድባቅ የመታችው የበርማዋ የማይ ዪ፣ ኢንዶኔዢያዊቷና በ”ሴቷ አንበሳ” ቅፅል ስሟ የምትታወቀው ራሱና ሰይድ፣ ስምንተኛዋ ተዘነጋችኝ ) ሁሉ፤
ወግጅልኝ ዜማ ወግጅልኝ ቅኔ
ወንዶች በዋሉበት መዋሌ ነው እኔ።
በማለት ወደ ጦር ሜዳ የገሰገሱ፤ ገስግሰውም ጠላትን መድረሻ ያሳጡ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም። በመሆኑም ከታሪክ ባለፈም እንደ ላይኛዎቹ ስምንቱ ሁሉ ሁሌም ሊታወሱና ሊዘከሩ ይገባል።
የአድዋው ጦርነት እነ እቴጌ ጣይቱን አፈራ። አፍርቶም የክፍለ ዘመኑን ምርጥ ሴት ጀግና ለአለም አበረከተ። በወቅቱ ጉዳዩን በፊት ለፊት ሽፋናቸው ካስተናገዱት የህትመት ሚዲያዎች መገንዘብ እንደተቻለው ጣይቱ ፍፁም ተወዳዳሪ የሌላቸው፤ አለምን ጉድ ያሰኙ ጀግና ናቸው።
በገጠሙን ጦርነቶች ሁሉ በጦር ሜዳ የሴቶች ሚና በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፤ አይደለምም። አዲስ አድማስ ጋዜጣ በአንድ ወቅት በርእሰ አንቀፁ እንዳስነበበው ዘመናዊ ጠመንጃ ከመምጣቱ በፊት ሴቶች፣ ከሰልና ጨው ወቅጠው፣ ባሩድ (ዳሄራ የሚባል) ያሰናዱ ነበር። በዚህም ምክንያት እናቶች፡-
ሴቶች ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሄራ፣
ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ።
በማለት ከመልእክቱ ባለፈ ለታሪክ ይሆን ዘንድ በዚህች መንታ ግጥም (ይሄን ግጥም ሴቶች የዘፈኑት፣ ንጉስ ምኒልክ ራስ አዳል ጋ ጦርነት ሊያደርጉ ሲሰናዱ መሆኑን ፀሀፊው ጠቅሰዋል።) ቋጥረው አኑረዋል። (በዚህ በተያያዝነው “ሕግ የማስከበር” እና “የህልውና ዘመቻ”ም የሴቶች/እናቶች ሁለ-ገብ ተሳትፎን የተመለከቱ ግጥሞች ወደ ፊት በብዛት እንደሚኖረን አንጠራጠርምና ለአሁኑ የድሮዎቹን ይዘን እንቀጥል።)
በቀድሞው ዘመን፣ በዚያ አለም አይኑ ባልተገለጠበት ክፉ ዘመን ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ያልተሰማሩበት የሙያ ዘርፍና ያላስመዘገበቡት ገድል የለም ማለት እስኪቻል ድረስ ዘልቀው ሄደዋል። በግብርና፣ በባህል አልባሳቱ ስራና በሌሎቹም ሁሉ ገስግሰው ውጤታማ ሆነዋል። በተለይ በአዋላጅነት ሚናቸው አንዳንድ የዛሬ አዋላጅ የጤና ባለሙያዎችን ባስከነዳ መልኩ ብዙ ሰርተዋል፤ አሁንም ገጠሪቱ ኢትዮጵያን ቀጥ አድርገው የያዟት እነሱ እንጂ ሌላ አይደለም። (“የመጀመሪያው የጦር መሳሪያ ፋብሪካ የእናቶቻችን ሙቀጫ የተመረተበት ሲሆን፤ የመጀመሪያው የጦር መሳሪያም የእናቶቻችን ሙቀጫ” መሆኑን ያስነበብከን ጸሐፊ – እናመሰግናለን።)
በድሮ ጊዜ፣ ምንም አይነት ዘመናዊ ወታደራዊ ትጥቅና ስንቅ በሌለበት ጊዜ፤ ወታደር እንደ ቅርብ ጊዜው ኮቸሮውን በላስቲኩ፣ ውሃውን በኮዳ ይዞ መዝመት በማይችልበት በዚያ ዘመን የእናቶችንና የሙቀጫን ውለታ ለማስታወስ በዛን ጊዜ መኖርን አይፈልግም። አይደለም ያኔ፣ ዛሬም ቢሆን የጦርነትና ስንቅን ጉዳይ ከእናቶችና ሙቀጫ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በተለይ ያ ዘመን፣ ምንም አይነት ዘመናዊነትን ባልተላበሰበት ዘመን ሴቶች ማጀታቸውን ወደ ጦር ሜዳ ይዘውት ነበር የሚዘምቱት ቢባል አንዱም ጋር ማጋነን ሊሆን አይችልም።
“ብዙ ጊዜ ስለ ጦር ሜዳ ስናስብ ቶሎ የሚመጣልን ፉከራ፣ ሽለላ፣ ሁልጊዜ የሚያባርር አርበኛ፣ ሁልጊዜ የሚወድቅ ጠላት፤ የመድፍ ተኩስ፣ የባሩድ ሽታ ወዘተ ነው።በጦር ሜዳ እንጀራ ሲጋገር፣ ወጥ ሲሰራ፣ ጠጅ ሲጣል ማሰብ ለአእምሮ የተለመደ አይደለም።ግና ከባሩድ ጭስ በማይተናነስ መጠን የማእድ ቤት ጭስ ታሪክ ሰርቷል፡፡” የሚለውን የጋዜጣውን ርእሰ አንቀፅ እዚህ ላይ ሳይጠቅሱ ማለፍ ይከብዳል።
ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረስላሴን በመጥቀስ ‹‹እንዲህም እየሆነ፣ አጤ ምኒልክ ባዳራሹ እቴጌ ጣይቱ በልፍኝ ባለሟሎችዎን ወይዛዝሩን ይዘው ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል፣ ይዘምታሉ። ከዘመቻ ላይ ጠጁ ማሩ አለመጉደሉ፣ ስለምንድነው ያልህ እንደሆነ ይህንን ታሪክ መመልከት ነው። በስድስት ድንኩዋን እንጀራው ሲጋገር ሲያድር፣ በአራት ደንኳን ወጡ ሲሠራ ሲያድር፣ ጠጁ በቀንድ በኮዳ ደግሞ ሶስት መቶ ስድስት መቶ የሚሆን ገንቦኛ ሲጓዝ ግብሩ ይጎድል ይመስልሀል?›› በማለት ያሰፈረውም ለጥቅስ የሚበቃ ነውና የኢትዮጵያ ሴቶችን ከኢትዮጵያ የአንድነትና ሉአላዊነት፤ ጀግንነትና አይበገሬነት . . . ወዘተ ታሪክ ነጥሎ ማየት ከቶ እንዴትስ ይቻላል?
ዛሬም እየሆነ ያለው ይሄው ነውና ኢትዮጵያ ተደፈረች ባተባለበት ጊዜ ሁሉ፤ ሉአላዊነቷ በተነካበት ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ነበሩ፤ አሉላትም። ለዚህም ደግሞ ይህንኑ አሁን ተገደን የገባንበትን ጦርነት ተከትሎ ዜናው “የአማራ ክልል ሴት አደረጃጀቶች በተያዘው በጀት ዓመት እስከ ጥቅምት 21 ድረስ ከ560 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የስንቅ ዝግጅት ማቅረባቸውን፤ ከጥቅምት ጀምሮ ደግሞ 34 ሺህ 400 ኩንታል ደረቅ ስንቅ ማዘጋጀታቸውን” ማወጁ ብቻ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው። (ሁሉም ክልሎች የሴቶችን አስተዋፅኦና የህልውና ዘመቻው ተሳትፏቸውን በዚህ መልኩ ሰንደው ሲያቀርቡት የምናገኘውን የተሟላ መረጃም በዚሁ ልክ ማሰቡ ጠቃሚ ነው።)
“በኔ ግምት፣ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረስላሴን ያክል ለሴቶችና አስተያየቶቻቸው ቦታ የሰጠ ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊ ያለ አይመስለኝም” የሚለው ከላይ የጠቀስነው ርእሰ አንቀፅ ፀሀፊ አሁንም ከእኚሁ እውቅ ሰው ስራ የሚከተለውን ይላል፤
ባብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ያዳራሽና ያደባባይ ታሪክ ነው።የእልፍኝ (ጓዳ) ታሪክ ከቁጥር አይገባም። ገብረ ስላሴ ግን፣ ጦር ሜዳ ዘምተው፣ መድፉን፣ ነፍጡን እንደሚቆጥሩ ሁሉ እልፍኝ ገብተው ምጣዱን እንጀራውን ቆጥረውልናል። አንዳንዴ በማጀቱና በጦር ሜዳው መካከል ያለውን ድንበር በዘይቤ ያፈርሱታል። ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያ አርበኞችን የስነ ልቦና ዝግጅት ሲገልጹ፤ ‹‹የሠራዊቱ ልብ እንደ ምጣድ ግሞ ነበር›› ይላሉ። የሰራዊቱን ወኔ ለመግለጽ የተመረጠው የጋለ ብረት አይደለም። እሳተ ገሞራ አይደለም።ወንድ ያስተውለዋል ተብሎ የማይታሰበው ‹‹የጋለ ምጣድ ነው›› (ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ፤ ገጽ 241)
የሆነው ሆኖ፣ ሴቶቹ ‹‹ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል›› ያን ያህል ጊዜ፣ (ከጥቅምት እስከ የካቲት) ያን የሚያክል መንገድ (ከእንጦጦ እስከ አድዋ) ሰራዊቱን መመገብ መቻል ከባድ መስዋእትነት ነው። ለዚህ መስዋእትነት ክብር ባንሰጥ የእናቶቻችን አጽም ወስፌ ሆኖ ይወጋናል” እንደ ተባለው ሁሉ፤ አሁንም ይህ ጽሑፍ ሽብርተኛው ቡድን በተሰማራበት አገር የማፍረስ ተግባርና ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንም “አታፈርስም” በሚል ሳይወድ በግድ የገባበትን አገርና ሕዝብን የማዳን ተገባር፤ እንዲሁም፣ አጠቃላይ ልጆቿም “እኛ እያለን ልጆቿ እኛ እያለን …” ዜማን በማዜም ወደ ግንባር እየተመሙ ባሉበት በዚህ ፈታኝ ወቅት በግንባር የተሰለፉትን ጨምሮ፤ ከኋላ ደጀን ሆነው ስንቁን በማዘጋጀት፣ በማደራጀት፣ በመላክ …. እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ያሉ እናቶችን አለማወደስ፤ ውለታቸውን ለታሪክ አለማስቀመጥ በታሪክ ያስጠይቃልና ስናመሰግናቸው እጅ በመንሳት ነው። አንድ ጉልህ ታሪክ እንጨምርና እናብቃ።
የአገራችን ሴቶች የጦር ሜዳ ውሎም ይሁን የኋላ ደጀን በመሆን ሲያከናውኑ የነበሩት ተግባር በታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራን ይዞ የሚገኝ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል፤
“የብልህ ሴቶች መላ ታሪክ ቀይሯል።ዝነኛው ምሳሌ እቴጌ ጣይቱ በመቀሌ ጦርነት ያቀረቡት የጦር ስልት ነው። እቴጌ ከተለመደው የወንዶች ደካማ ጎን ከሆነውና ወገንን ለዘግናኝ እልቂት ከሚዳርገው እሳት-ራታዊ የውግያ ልማድ ወጣ ብለው በማሰብ በጣልያኖች አይበገሬ ምሽግ አቅራቢያ ያለው ኩሬ በቁጥጥር ስር እንዲውል አዘዙ። መቀሌ ላይ ጣልያኖች የተደፈሩት እንደ ንግስተ ሳባ በውሃ ጥም ምክንያት ነው ማለት ይቻላል፡፡” የሚለውና ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ የሚነገረው የጣይቱ ከዘመኑ የቀደመ የጦር ሜዳ ጀብድ ነው። ለጊዜው አይድረስ እንጂ ይህ ጦርነት ካለቀ፣ ከድል በኋላ የምንሰማው የብዙ ሴቶቻችን ጀብድ ይኖራልና “ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ነች” ሲባል ዝም ተብሎ አይደለም። (ጥቅምት 17 1904 ዓ.ም የተወለዱትንና ብዙም ያልተዘመረላቸው የአርበኛ ከበደች ሥዩምን ታሪክና፤ በወቅቱ “ዮሀንስ” እየተባለ የሚጠራውን ሱሪ በመልበስ ጦራቸውን በመምራት የፈፀሙትን ገድልም ከዚሁ ጋር አያይዞ ማንሳት ይቻላል።)
ሁሌም ቢሆን፣ ዘመን የራሱን ጀግና ይፈጥራልና ይህ ተገደን የገባንበት ጦርነትም የራሱን ጀግኖች ይዞ ብቅ ማለቱ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ከወንዶቹ መሳ ለመሳ ሴቶችም እንዳሉ ሁሉ ከሁለቱም ስርአተ ፆታ አባላት በርካታ ንጥር ጀግኖች እንደሚወጡ ከወዲሁ መረዳት ይቻላልና ጊዜው ሲደርስ የምንለውን እንላለን። ከዛ ሁሉ በፊት ግን በግንባር ለተሰለፈው ሰራዊታችን ስንቅ በማዘጋጀትና በመላክ ላይ ያሉትን እናቶች ማመስገን ይገባልና፤ አሁንም እንላለን – እናመሰግናለን!
አካባቢዎን ይጠብቁ!!!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014