በዘመናችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች በእጅጉ እየተራቀቁ ይገኛሉ። የሰው ልጅ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴም በዚሁ ዘመናዊነት እየታገዘ አስደናቂ እድገት እያስመዘገበ ነው። በቴክኖሎጂ የምርምር ዘርፍ ለቁጥር የሚታክቱ የፈጠራ ውጤቶች በየጊዜው ይፋ ይሆናሉ። በዚህም አለማችን በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በትራንስፖርቱና መሰል አያሌ ዘርፎች ላይ ህይወት ቀላል እንዲሆንና ፈጣን እድገት እንዲመዘገብ እድል ተፈጥሯል። አሁንም ድረስ የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በሚያስገርም ፍጥነት ይፋ ይሆናሉ።
ለዛሬ ከሰው ልጅ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች ውስጥ ውጤታማና ስኬታማ አበርክቶ ያለውን “የራዳር ቴክኖሎጂ” ልናስተዋውቃችሁ ወደናል። በመሆኑም ራዳር እንዴት ይሰራል? ለምን አገልግሎትስ ይውላል? የሚለውን በጥቂቱ እንነግራችኋለን። በመረጃ ምንጭነት “የሰዋሰው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ድረ ገፅ፣ ብሪታኒካ፣ ኤክስፕሌን ዘስታፍ” በዋናነት ተጠቅመናል።
ራዳር
በርካቶች ራዳር የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙ ከወታደራዊ ተግባራትና ጦርነት ጋር ማያያዛቸው የተለመደ ነው። በርግጥ ራዳር ለወታደራዊ አገልግሎትም የሚውል ቢሆንም ከዚያ ባሻገር በርካታ ስራዎች በማቀላጠፍ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት አኗኗር በመደገፍና በማቅለል ረገድ የሚጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።
ራዳር በሰማይም ይሁን በምድር ላይ ያሉ አውሮፕላኖችን ለመከታተል እንዲሁም በሚያርፉበት ወቅት አደጋ እንዳያጋጥማቸው በማገዝ በኩል ጉልህ ስራን ይሰራል። መርከቦችም የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ናቸው። ፖሊሶችም በበኩላቸው የመኪኖች ፍጥነት ለመቆጣጠር የራዳር ቴክኖሎጂን ይጠቀማሉ። ምን ይሄ ብቻ የጠፈር ምርምር የሚያካሂዱ መንግሥታትና ተቋማት መሬትንና ሌሎች ፕላኔቶችን ለማመላከት እንዲሁም በጠፈር ላይ የሚገኙ ሳተላይቶችን ለመከታተል ራዳርን በስራ ላይ አውለዋል። የአየር ንብረት ባለሙያዎች አውሎ ንፋስ፣ ማዕበል እና ሌሎች የአየር ሁኔታዎችን ለመከታተልና ቅድመ ጥንቃቄዎችን ለመውሰድ ከሚጠቀሟቸው ቴክኖሎጂዎች አንዱ ራዳር መሆኑን ልብ ይሏል። ውድ የሰዋሰው ቤተሰቦች የራዳር ሙያ ብዙ ነው። ታዲያ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ራዳርን የሚጠቀሙት በሶስት ምክንያት ነው፣
ከርቀት ላይ ሆነው አንድን ነገር መኖር አለመኖሩን ለማወቅ
በአብዛኛው ራዳር ከርቀት ላይ የሚገኙ በበረራ ላይ ያሉ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን መኖር አለመኖራቸውን የማወቅ ብቃት ቢኖረውም ከምድር በታች የተቀበሩ የማይንቀሳቀሱ ነገሮችንም ማወቅ ይችላል። በነገራችን ላይ ራዳር እንዲሁም አውሮፕላን መኖር አለመኖሩን ብቻ አይደለም የሚያውቀው የአውሮፕላኑም አይነት ጭምር እንጂ።
የአንድን ቁስ ፍጥነት ለማወቅ
እንዴት ነው መኪናዎን እየነዱ ሲያልፉ ትራፊክ ፖሊሶች አስፓልቱ ጠርዝ ላይ ቆመው አንዳች ትንሽዬ መሳሪያ ይዘው ወደ መኪናዎ ደቅነው ሲመለከቱዎት ታዝበው ይሆናል፣ እርስዎ በምን ያክል ፍጥነት እየነዱ እንደሆነ ራዳርን በመጠቀም እየተመለከቱ ነው። ታዲያ እርስዎ ከፍጥነት ገደቡ በላይ እየነዱ ከሆነ ራዳሩ ለፖሊሶቹ ስለሚጠቁማቸው በቁጥጥር ስር መዋልዎ አይቀርምና የፍጥነት ወሰኑን ጠብቀው ያሽከርክሩ።
አንዳች ነገርን በካርታ ላይ ለማመላከት
መንኮራኩሮችና እና ምድርን የሚዞሩ ሳተላይቶች የፕላኔቶችን እና የጨረቃን ገጽታ ዝርዝር የአቀማመጥ ካርታቸውን ለመፍጠር ሰው ሰራሽ አፐርቸር ራዳር የሚባል ነገር ይጠቀማሉ።
ውድ የሰዋስው ቤተሰቦች በሚያስገርም ሁኔታ እነዚህ ሶስት ጉልህ ነገሮችን በሙሉ በራዳር አማካኝነት ለማሳካት ሁለት ሀሳቦችን ብቻ ነው እምንጠቀመው። የድምጽ መስተጋባት (በተለምዶ የገደል ማሚቶ) እና የዶፕለር ለውጥን ብቻ። እስኪ ራዳር እንዴት እንደሚሰራ ከማየታችን በፊት በመጀመሪያ እነዚህን ሁለት ሀሳቦች ለየብቻ እንረዳቸው።
የድምጽ መስተጋባት
የድምጽ መስተጋባት ማለት በየቀኑ የምንሰማው ድምጽ አንዳች ነገር ላይ ነጥሮ ሲመለስ ደግሞ ደጋግሞ የራሳችንን ድምጽ መልሶ የሚያሰማን ክስተት ነው። መቼም በአንድ ዋሻ ነገር ውስጥ ሆነው ሲጮሁ ከደቂቃዎች በኋላ የራስዎ ድምጽ ተመልሶ ሲመጣ ታዝበው ይሆናል። ይህ በተለምዶ የገደል ማሚቶ አልያም የድምጽ መስተጋባት የሚፈጠረው የእርስዎ የድምጽ ሞገድ በዋሻው ስር ከሚገኝ ውሃ አልያም አንዳች አካል ላይ ነጥሮ ሲመለስ ነው። ታዲያ በእርስዎ ድምጽ እና በገደል ማሚቶው ድምጽ መከሰት መካከል ያለው ደቂቃ የሚወሰነው ድምጽዎ ነጥሮ እንደሚመለስበት አካል ርቀት መሆኑን ልብ ይሏል።
የዶፕለር ለውጥስ ምንድን ነው?
በነገራችን ላይ ይህንም ጉዳይ በየቀኑ ህይወትዎ ሳይታዘቡት አይቀርም። ቀለል አድርጎ ለማስረዳት ያክል፣ የዶፕለር ለውጥ ማለት አንድ የሚንቀሳቀስ ነገር ድምጽ ሲፈጠር ወይም አንጸባርቆ ሲመለስ ያለውን ክስተት ይወክላል። ይህን በምሳሌ እንመልከተው፣
አንዲት መኪና በእርስዎ አቅጣጫ በሰዓት 60 ኪ.ሜ እየከነፈች ጡሩምባዋም እየጮኸ ነው እንበል። ይሄኔ የጡሩምባው ደምጽ ደመቅ ብሎ ይሰማዎታል ነገር ግን መኪናዋ አልፋ ስትሄድ የጡሩምባው ድምጽ እየቀነሰ ይሄዳል። እዚህ ላይ “ታዲያ እስከአሁን ድረስ ሁለቱንም ደምፆች እያወጣ ያለው ያው ተመሳሳይ ጡሩንባ ሆኖ ሳለ እንዴት የድምፅ ለውጥ መጣ?” ብለው ከጠየቁን::
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014