ልጆች እንዴት ናችሁ? ትምህርት እንዴት ነው፣ እየጎበዛችሁ ነው አይደል? ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ በቱሉ ዲምቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች “ኆኅተ ሰላም” የተሰኘ ቤተ-መጻሕፍት ምርቃት እና የንባብ ቀን አካሒዶ ነበር፡፡ በዝግጅቱ ላይ ያገኘሁት ህፃን ሱራፌል ፍሬዘር በሚኖርበት አካባቢ ቤተ-መጻሕፍት መከፈቱ ርቆ ሳይሄድ ብዙ መጻሕፍት እንዲያነብ እድል ሊሰጠው እንደሚችል ተናግሯል።
ህፃን ሱራፌል ማንበብ ስለሚወድ በርካታ መጻሕፍትን ያነበበ ሲሆን በትምህርቱም ጎበዝ እንደሆነ ነግሮኛል። ልጆች ሁልጊዜ “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” እላችሁ የለ? ልጆቻቸው በማንበባቸው ሙሉ ሰው እንዲሆኑላቸው ያሰቡ ወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ ቤተ-መጻሕፍት እንዲከፈት የጣሩ ሲሆን ጥረታቸውም ለስኬት መድረሱ እጅግ በጣም አስደስቷቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ- መጻሕፍት ኤጀንሲ በዕለቱም በቱሉ ዲምቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ስር አዲስ ለተመረቀው ኆኅተ ሰላም ቤተ-መጻሕፍት የተለያዩ ይዘት ያላቸው 400 (አራት መቶ) መጻሕፍት በስጦታ ባበረከተበት ወቅት የአብያተ ቤተ-መጻሕፍት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ተፈራ እንደተናገሩት ከኤጀንሲው በስጦታ የተለገሱት መጻሕፍት ለዚህ የጋራ መኖሪያ ቤት ከነዋሪው አንጻር በቂ ያለመሆናቸውንና እንደ እርሾ እንደሆኑም ተናግረው በጋራ መኖሪያ ቤቱ የሚኖሩ ነዋሪዎች እያንዳንዱ አባወራ ከቤቱ አንዳንድ መጽሐፍ ቢያመጣ 20ሺ አባወራ ቢኖር ለዚህ ቤተ-መጻሕፍት 20 ሺህ አዲስ መጻሕፍት ያለው የተሟላ ቤተ-መጻሕፍት ይሆናል ብለዋል። ቤተ-መጻሕፍቱም የተሟላ እንዲሆን ሰዎች አንብበው የጨረሱትን መጻሕፍት በሙሉ ለሌሎች ማጋራት የሚገባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
ቤተ-መጻሕፍት ተማሪዎችም መጻሕፍት ፍለጋ ርቀው በመጓዝ ለእንግልት ከሚዳረጉ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ የሚፈልጉትን መርጃ መጻሕፍት በቅርበት እንዲያገኙና ለጠቅላላ እውቀት የሚረዱ መጻሕፍት እንዲያነቡ በማድረግ ኢትዮጵያን የሚረከብ ዜጋን ለመፍጠር ወላጆችም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዝግጅቱም የሕጻናት መጻሕፍቶች አውደ ርዕይ፣ በወጣቶች የሰርከስ ትርኢት፣ በኮሜድያን አስረስ በቀለ የተዘጋጀ አስተማሪ አጭር ጭውውት ለሕጻናቱ ሲቀርብ በአቶ ለገሠ ኩሳ የልጆች አስተዳደግና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ ስላሉ የወላጅ ግንዛቤ አስመልክቶ ለወላጆች ተሞክሮ የማካፈል ተግባር ተከናውኗል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ያገኘነው ኮሜዲያን አስረስ በቀለ ልጆች በአቅማቸው ልክ መጻሕፍት ከተዘጋጁላቸው ማንበብ ይወዳሉ ያለ ሲሆን፣ ስልክና ቴክኖሎጂ ላይ ተጣብቀው ከመዋል ባለፈ መጻሕፍት ማንበባቸው ትእግስት እንዲኖራቸው አእምሯቸው የበሰለና ከሰዎች ጋር ተግባቢ ሊያደርጋቸው የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።
ልጆች ኮሜዲያን አስረስ በቀለ እንዳለው ልጆች ጥሩ አንባቢ ከሆኑ ከሰው ጋር የሚግባቡ፣ ሀሰባቸውን በነፃነት የሚገልፁ ጠንካራ ልጆች ለመሆን ስለሚያስችላቸው ጎበዝ አንባቢ መሆን ይገባችኋል። ልጆቼ የእውቀትን ሚስጢር ለመረዳት አንብቡ እሺ። መልካም የትምህርትና የንባብ ጊዜ።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም